Saturday, 28 December 2013 10:29

ለረዥም ጊዜ ሳይቋጭ የዘለቀው ውዝግብ!

Written by 
Rate this item
(4 votes)

“ጋዜጠኞች ታስረዋል አልታሰሩም?”

      ከአዘጋጁ- ባለፈው ሳምንት በኒውዮርክ የሚገኘው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (CPJ) ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርቱ ጋዜጠኞችን በማሰርና በማሰቃየት ኤርትራን በቀዳሚነት በማስቀመጥ ኢትዮጵያንና ግብፅን በሁለተኛነትና በሦስተኛነት ደረጃ ላይ አስቀምጧቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ “ከጋዜጠኝነት ሙያው ጋር በተያያዘ ያሰርኩት አንድም ጋዜጠኛ የለም፤ በእስር ላይ ያሉት በሽብርተኝነት ተፈርዶባቸው የታሰሩ ናቸው” ቢልም ሲፒጄ ግን በሽብር ሽፋን ለእስር የተዳረጉ ጋዜጠኞች እንደሆኑ በሪፖርቱ ገልጿል፡፡ በአገሪቱ ያለውን የፕሬስ ነፃነት ሁኔታ አጥብቆ የሚተቸው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጄ፤ ከመንግስት በደረሰባቸው ማስፈራሪያና ወከባ በርካታ ጋዜጠኞች ለስደት እንደተዳረጉ ሲገልፅ ቆይቷል፡፡ ድርጅቱ ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገውን ሪፖርት አስመልክቶ የመንግስት ባለሥልጣን፣ የጋዜጠኞች ማህበር አመራሮችና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ በማነጋገር የሰጡትን አስተያየት እንደሚከተለው አጠናቅረን አቅርበነዋል፡፡

“ሲፒጄ ፖለቲካዊ አጀንዳ ያለው ነው”

(አቶ ሽመልስ ከማል፤ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ) በመጀመሪያ ሲፒጄ የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት እንዲያድግና እንዲስፋፋ አይፈልግም፡፡ ፖለቲካዊ አጀንዳ ያለው፣ መንግስት በኃይል ለመለወጥ ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጋር የሚንቀሳቀስ፣ በጋዜጠኝነት ታፔላ ድጋፍ የሚሰጥ ድርጅት ነው። ሥራው ከጋዜጠኝነት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፤ ከእርሱ ጋር ከሚጠቃቀሱት አንዱ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ነው፡፡ አምነስቲ ሲፒጄን፣ ሲፒጄ አምነስቲን --- እርስ በእርስ እየተጠቃቀሱ፣ አንዳቸው ያንዳቸውን የፈጠራ ውሸት እየያዙ፣ የአገራችንን ስም ሊያበላሹ የሚጮሁ፣ ስነምግባር የሌላቸው ተቋማት ናቸው፡፡ እናውቃለን… የፖለቲካ አጀንዳ እንዳላቸው። ሁለተኛ በኢትዮጵያ የትኛው ጋዜጠኛ ነው የታሰረው? እንግዲህ እናንተም የምትኖሩባት አገር ናት፤ እናንተ መቼ ታሰራችሁ? የማታውቁት ከማርስ የመጣ የታሰረ ጋዜጠኛ አለ እንዴ ? ከቁጥሩ ብዛት ኢትዮጵያን ከአለም ሁለተኛ ሊያስብላት የሚችል---? እንዲህ ነው--- እነ ዳንኤል በቀለ እየፈተፈቱ ሲሰጧችሁ የምትቀበሉት!! የሂውማን ራይትስዎች የአፍሪካ ዴስክ ሃላፊ ዳንኤል በቀለ፣ የቅንጅት መሪ ነበረ፡፡ በ97 በሰብአዊ መብት ድርጅት ስም መንግስት ለመገልበጥ ሲሰራ ተፈርዶበት በምህረት የወጣ ነው፡፡ ይሄ ግለሰብ መንግስት ለመገልበጥ አንዴ የጋዜጠኛ ማህበር አቋቁሙ እያለ ቅስቀሳ ያደርጋል፡፡ በየትም በየትም ብሎ ይህንን መንግስት በብረትድስት ከትቶ በምድጃው ላይ መጣድ ነው የሚፈልገው፡፡ ገለልተኛነት በሌላቸውና ችግር ላይ በወደቁ ግለሰቦች የሚፃፉ አስተያየቶችን በመፃፍ የእነሱ መሳሪያ አትሁኑ፡፡ ኢትዮጵያ በጋዜጠኝነት ያሰረችው አንድም ጋዜጠኛ የለም፤ ካለ ይምጣና “እኔ በጋዜጠኝነት ስራዬ ምክንያት ታስሬአለሁ” ይበል፡፡ ግን በጋዜጠኝነት ምክንያት የታሰረ የለም።

ቆይ የሚታመነው ማነው? የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ነው ወይስ ሲፒጄ? የኢትዮጵያ ፍርድቤት ርዕዮት አለሙ ላይ ፅፋ ነው የፈረድኩባት አላለም፡፡ በፃፈው ተፈርዶበት የታሰረ አለ ከተባለ ዶክመንቶችን ማገላበጥ ያስፈልጋል፡፡ ማንም ደግሞ አልታሰረም። ይህ አልሆነም፡፡ ከምላሴ ላይ ፀጉር ይነቀላል፡፡ ሲፒጄ ስላጨበጨበ፣ ዳንኤል ስለጮኸ እና ብሩን ስለበተነ፣ የግንቦት ሰባት መፅሄቶች ስለጮሁ እውነቱ ተገልብጦ ይቀርባል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያላችሁ ጋዜጠኞች ታያላችሁ፣ ትሰማላችሁ፣ ታገናዝባላችሁ፣ እስኪ በፃፈው ፅሁፍ ታሰርኩ የሚል ካለ አምጡ፡፡ የሲፒጄ ቃል የሙሴ ቃል አይደለም፤ ለምን እንደ ጣኦት ታመልኩታላችሁ? በጣም እምናዝነው---- እዚህ አገር ያሉ በሳል ጋዜጦች ላይ እንዲህ አይነት ነገሮች መፃፋቸው ነው፤ የዚህ ዘመቻ ሰለባዎች መሆናቸው ያሳዝነናል፡፡ ይሄ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ነው፤ “መንግስት ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህልፈት በኋላ አቋሙን ይቀይራል” ብለው ትንሽ ፋታ እንስጠው በማለት ለትንሽ ጊዜ ያቆሙት ነገር እንጂ ከዚህ በፊትም ሲያወሩት የነበረ ነው፡፡ ሲፒጄ እድሜውን ሁሉ መግለጫ ሲያወጣ፣እኛም መልስ ስንሰጥበት ነው የኖርነው፡፡ አዲስ አይደለም፡፡ ሲፒጄ መቼ ነው ስለኢትዮጵያ መልካም ነገር ተናግሮ የሚያውቀው? በፕሬስ ህጉ ላይ ሳይቀር “ኑ ና እንነጋገር” ብለናቸው ሽሽት ነው የመረጡት፡፡

ስለዚህ ሲፒጄ በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ላይ የተሰነዘረ ስድብ ነው፡፡ እንዲህ የሚያደርገው ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኝነት የለም ብሎ ስለሚያምን ነው፡፡ እግራቸው ሸብረክ ሲል ወንበር የሚያቀርቡላቸው በጋዜጠኝነት ስም የሚነግዱ አሉ፡፡ እነሱን ስለለመደ ሌሎቹን እንደ ባለሙያ አይቆጥርም፤ ስለዚህ ኒውዮርክ ውስጥ ቁጭ ብሎ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰቃየትና በማሰር ከአለም ሁለተኛ ነች ይላል - እናንተ አፍንጫው ስር ቁጭ ብላችሁ፡፡ ፈረንጅ የተናገረው ሁሉ ለምንድነው እንዳለ የሚወሰደው? ሁሌም አምኖ መቀበል ነው እንጂ ጉዳዩን ለማጣራት ሲሞከር አይታይም፡፡ “ሲፒጄ የወሮበሎች ቡድን ነው” (የኢብጋህ ፕሬዚዳንት፤አቶ አንተነህ አብርሃም) ሲፒጄ ኢትዮጵያን በተመለከተ ባወጣው ሪፖርት ላይ የማህበርዎም ሆነ የእርሶ አቋም ምንድነው? ሲፒጄ ያወጣው የተዛባ መረጃ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአለም በምንም ሁለተኛ አይደለችም፡፡ የሀገራችንን ስም ለማጥፋት ስለሚፈልግ ነው፤ ምክንያቱም ድርጅቱ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ከፍተኛ የሆነ የጥቅም ችግር ያለበት ነው፡፡ የሦስት እስረኛ ጋዜጠኞችን ቁጥር ከፍ አድርጐ ማውራት ምንም አይጠቅምም፡፡ እነሱም የታሰሩት በአሸባሪነት ተጠርጥረው ነው እንጂ በጋዜጠኝነታቸው በፃፉት ፅሁፍ አይደለም፡፡ ሲፒጄ እውነተኛ ከሆነ ቱርክ ስለታሰሩት 64 ጋዜጠኞች ለምን አያወራም፡፡ ግን በማያገባው ነው የሚገባው፡፡ ሲፒጄ፤ በእስር ላይ ያሉት ጋዜጠኞች በአሸባሪነት ነው የታሰሩት የሚለውን እንደማይቀበል ይገልፃል። እርስዎ በታሰሩት ጋዜጠኞች ዙርያ አቋምዎ ምንድነው? የታሰሩ ጋዜጠኞች አሉ፤ ግን የታሰሩት በፃፉት ፅሁፍ አይደለም፡፡

ማህበራችሁ ለየትኞቹ ጋዜጠኞች መብት ነው የቆመው? እስካሁን የታሰሩ ጋዜጠኞችን ለማስፈታት ጥረት አድርጓል? እኛ የምንቆመው ከሙያ ጋር በተያያዘ ለታሰረ ጋዜጠኛ ነው፡፡ በፃፈው ፅሁፍ የተነሳ የሚታሰር ጋዜጠኛን ወዲያው እናስፈታለን፡፡ የማህበራችሁ አባላት የየትኛው ሚዲያ ጋዜጠኞች ናቸው ? ምን ያህል አባላትስ አላችሁ? የግልም የመንግስትም ጋዜጠኞች አባሎቻችን ናቸው፡፡ በአጠቃላይ 600 አባላት አሉን፡፡ ከአገር ውጪ የምስራቅ አፍሪካ ጋዜጠኞች ምክትል ፕሬዚዳንት ነን፡፡ እኛ በማውገዝ አናምንም፤ በውይይት እንጂ፡፡ በአሁኑ ሰአት የጋዜጠኞች እስር ቆሟል፤ ይህም የሆነው በኛ ጥረት ነው፡፡ የ“ኢትዮ ምህዳር” ጋዜጠኞች ከጥቂት ወራት በፊት ተከሰው አዋሳ በሄዱ ጊዜ አንደኛው ባልደረባቸው ላይ ከፍተኛ አደጋ ደርሶበታል፡፡ እነዚሁ ጋዜጠኞች ለገጣፎ ለሁለትና ለሶስት ቀናትም ታስረው ነበር፡፡ ነገር ግን የትኛውም የጋዜጠኞች ማህበር እንዳልጎበኛቸው ነግረውናል…ማህበራችሁ ለየትኞቹ ጋዜጠኞች መብት ነው የሚቆመው? መታሰራቸውንም መከሰሳቸውንም በጋዜጣቸው ላይ ሲፅፉ ነው የምንሰማው እንጂ ለኛ መጥቶ የነገረን የለም፡፡ አደጋ ደረሰበት ስላልሽው ልጅም ጓደኞቹ ወይም ቤተሰብ ከጠየቀን እንረዳለን፣ ካልጠየቀን ግን በስሙ እርዳታ አንለምንም፡፡ ማንም ጋዜጠኛ ታስሮ ወደ የትም ክልል እንዳይወሰድ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ተነጋግረን መተማመን ላይ ደርሰናል፡፡ የጋዜጠኞች ማህበር እንደመሆናችሁ ከሲፒጄ ጋር ለመወያየት የሞከራችሁበት አጋጣሚ አለ? ሲፒጄ የወሮበሎች ቡድን ነው፤ የተወሰኑ ወሮበሎች ተሰብስበው ያቋቋሙት ነው፤ ጋዜጠኞችን እንወክላለን ብለው ገንዘብ ለመሰብሰብ የተቀመጡ ናቸው፡፡ ውብሸትን ለማስፈታት እንኳን እንቅፋት ሆነውብናል፡፡ ውብሸትን ለማስፈታት ሞክራችሁ ነበር ? አዎ! ይቅርታ ጠይቅ ብለነው ጠይቋል፤ በሱ ስም ግን ሲፔጂ መግለጫ እያወጣ ስራችንን አስተጓጉሎብናል፡፡ ሲፒጄ መግለጫ የሚያወጣው ለኢትዮጵያ ጋዜጠኞች አስቦ አይደለም፤ ኢትዮጵያን ለማጥቃት ነው፡፡

ብዙ በደል የሚደርስባቸውን የሌላ አገር ጋዜጠኞች ትቶ፣ ስለማያገባው ያወራል እንጂ እኛ በመወያየት ስራችንን እየሰራን ነው፡፡ የጋዜጠኞች መታሰርን አስቁመናል፤ ይህ የሆነው በኛ ጥረት ነው፡፡ “መንግስት ጋዜጠኞችን እንደሚያስር እስር ቤት ሄዶ ማየት ይቻላል” (ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ የመድረክ አመራር አባል) ለመሆኑ እዚህ አገር የጋዜጠኞች ማህበር አለ እንዴ? መንግስት ጋዜጠኞችን እንደሚያስርና እንደሚያንገላታ ለማወቅ እስር ቤት ሄዶ ማየት ይቻላል፡፡ ጋዜጠኞቹ ራሣቸው ታስረው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ስለነበር፣ አይኔን የበሬ ግንባር ያድርገው ካልተባለ በስተቀር ነገሩ አከራካሪ አይደለም። መንግስት እንደተለመደው የታሠረ ፖለቲከኛም ጋዜጠኛም የለም የሚለው ቀልድ ካልሆነ በቀር እነ እስክንድር፣ ውብሸትና ርዕዮትን የመሣሠሉት ታስረው እኮ ነው ያሉት፡፡ እነዚህ ሠዎች እኮ ሽጉጥ ሲሠርቁ አልታሠሩም፡፡ መንግስት፤ ጋዜጠኞቹ የታሠሩት በፃፉት አይደለም በማለት የሚናገረው ነገር መራር ቀልድ ነው፤ ዝም ብሎ “የሌባ አይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ” አይነት ነገር ነው እንጂ ሠዎቹ ጋዜጠኞች መሆናቸውና የነፃ ጋዜጣ ባለቤትና አዘጋጅም እንደነበሩ በሚገባ ይታወቃል፡፡ ከ97 ዓ.ም በኋላ እኮ መንግስት በግልፅ ጋዜጠኞች ላይ ጫና እያሣረፈባቸው ነው፡፡ ነፃ ጋዜጦች የሚኖሩት የፖለቲካ ምህዳሩ ሲሠፋ ነው፤ የፖለቲካ ምህዳሩ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የተዳፈነ ነው፡፡

“ሲፒጄ ሪፖርቱን ሲያወጣ የራሱ የሆነ ተልዕኮ አለው” (የኢነጋማ ሊቀመንበር፤ አቶ ወንደወሰን መኮንን) ባለፈው ሳምንት ሲፒጄ ባወጣው ሪፖርት፤ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር ከአስር ሃገራት መካከል ሁለተኛ እንደሆነች ገልጿል፡፡ የጋዜጠኞችን እስር በተመለከተ የማህበራችሁ አቋም ምንድነው? ጋዜጠኞች ይታሰሩ የሚል አቋም መቼም ቢሆን ሊኖረን አይችልም፡፡ የታሰሩ ጋዜጠኞች ካሉ ጉዳያቸው ታይቶ መንግስት መፍታት አለበት የሚል አቋም ነው ያለን፡፡ ሲፒጄ ግን ይሄንን ሪፖርት ሲያወጣ የራሱ የሆነ ተልዕኮ አለው፡፡ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር ሁለተኛ ናት ብሏል፡፡ ይሄ ከዚህ በፊትም ሆኖ የማያውቅ ግነት ነው፡፡ የታሰረ የለም። ለአፍሪካ ሚዲያ ፎረም ጉባኤ ወደ አዲስ አበባ በመጡ ጊዜ እንደ አዲስ ነው ዘመቻ የተከፈተው፡፡ በአጭሩ ግን የኢትዮጵያ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶት … ሁኔታውን አጢኖ የታሰሩ ጋዜጠኞችን ቢፈታ በጣም ደስተኞች ነን፡፡ ማህበርዎ ኢነጋማ ስንት አባላት አሉት? ለጋዜጠኞች መብት መከበር ያደረጋችሁት እንቅስቃሴስ ምን ይመስላል ? እኛ ከዚህ በፊትም ትግል ስናደርግ ነው የኖርነው፣ አሁንም እያደረግን ነው ያለነው፡፡ አባላት አሁን አሉ ከሚባሉትም በላይ በዚህ ሂደት ውስጥ የሚታወቅና የተለየ ስፍራ አለን ብለን ነው የምናምነው፡፡ እንደ በፊቱ የመንግስትና የግል ጋዜጠኛ የሚባል ነገር የለም፤ ያንን አንኮታኩተን ጥለነዋል፡፡ ሙያው አንድ ነው፤ ይሄንን ልዩነት የፈጠሩት እርስ በርስ ሲያባሉ የነበሩና የተለየ የፖለቲካ ተልኮ ያላቸው ሃይሎች ናቸው፡፡ እነሱ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከጨዋታ ውጪ ሆነዋል፡፡ ከጀርባቸው የተለየ ተልዕኮ ያላቸው ናቸው፡፡ ጋዜጠኛውን እርስ በርስ ሲያባሉ ቆይተዋል፤ አሁንም እያባሉት ይገኛሉ። ይሄንን እኔ አልቀበለውም፤ ጋዜጠኞች ሙያውን ከፖለቲካ ነፃ ሆነው መስራት አለባቸው፡፡ ጋዜጠኛው ተቀራርቦ በራሱ ጉዳይ መምከር አለበት፡፡ ጋዜጠኞች በነፃነት መስራት፣ ሃሳባቸውን መግለፅ፣ በተጨባጭ ማስረጃዎች ላይ ተመርኩዘው መተቸት አለባቸው። የሕዝብ ጥያቄ በሚመልሱበት ሰዓት በአግባቡ የመከላከል፣ የመከራከር፣ ድምፃቸውን የማሰማት መብት አላቸው፡፡

በእኛ በኩል በመንግስት፣ በግልና በኮሙዩኒኬሽን ቦታ ላይ ያሉ የሚዲያ አባላቶችን ይዘን፤ ከተወሰኑ ወራት በኋላ ጠቅላላ ጉባዔ እናደርጋለን፤ ለውጦችም ይኖራሉ፡፡ እኛ የፖለቲካ መጠቀሚያ አይደለንም፣ የትኛውንም የፖለቲካ አቋም አናስተጋባም፤ የመንግስትንም ሆነ የተቃዋሚውን። በነፃነት ሃሳባችንን በመግለፃችን ነው ውርጅብኝ ሲወርድብን የኖረው፡፡ ይሄንን ደግሞ እናውቀዋለን፡፡ ማህበራችሁ ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶ ለመብቱ የተከራከራችሁለት ጋዜጠኛ አለ? ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ላልሽው ---- እንናገረው ብንል መፅሃፍ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ተሰሚነት የነበረው በአገር ውስጥም ሆነ በአለማቀፍ ደረጃ ኢነጋማ ነው፤ እሱ አከራካሪ አይደለም፡፡ ነገር ግን የቀድሞው አመራሮች በሚዲያው ውስጥ በነበረው የእርስ በርስ ትግል አዳክመው፣ ገለውት ነው የሄዱት። ዛሬም በአሜሪካና በአውሮፓ ሆነው “ኢነጋማ አለ” እያሉ መግለጫ እያወጡ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ከሙያው ጋር በተያያዘ የታሰረ ጋዜጠኛ የለም። የታሰሩት በሌላ ጉዳይ ነው፤ ቢሆንም መፈታት አለባቸው ብለን እናምናለን፤ ነገር ግን መግለጫ አናወጣም፡፡ መግለጫ መስጠትም አይቻልም። ጋዜጠኛው ከሌላ አካል ከመጠበቅ ይልቅ በአንድ ላይ ሆኖ ለመብቱ መቆም አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ የሚያስፈልገው ተቀራርቦ በመነጋገር ችግሮችን መፍታት ብቻ ነው፡፡ በተለያየ ጎራ ሆኖ መተቻቸቱ ፋይዳ የለውም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሶስት “ነፃና ገለልተኛ ነን” የሚሉ የጋዜጠኞች ማህበራት አሉ፡፡ በቅርቡ ደግሞ አዲስ የጋዜጠኛ ማህበር ለማቋቋም እንቅስቃሴ የጀመሩ ወገኖች አሉ፡፡ አዲሱን ማህበር በተመለከተ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው? ሊቋቋሙ ይችላሉ መብታቸው ነው፡፡ ነገር ግን እነማ ናቸው የሚያቋቁሙት፣ እንዴት ነው የሚቋቋሙት፣ ከጀርባ እነማን አሉ ---- ይሄን ጠንቅቀን እናውቀዋለን፡፡ ትልቅ ጉዳይ አይደለም፤ ኖረንበታል፡፡ ለእኛ አዲስ ነገር አይደለም፡፡

Read 4134 times