Print this page
Monday, 23 December 2013 10:21

“እኔ ዝንጀሮ ሆኜ ዝንጀሮ አልወድም…”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ስለነገርየው በማጥናት መተንተን አንድ ነገር ነው፡፡ “አናሊሲስ” ይባላል፡፡
የተጠናውን እና የተተነተነውን ነገር ወስዶ በሌላ የተጠና እና የተተነተነ ነገር ላይ መደመር ደግሞ ለላ ነገር ነው፡፡ መደመሩን “ሴንቴሲስ” ይሉታል፡፡
ለምሳሌ 1 + 1 = 2 “አንድ” ቁጥር ምንን እንዳሚወክል አናውቅም፡፡ “አንድ ሰው” ማለት ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ መንግስት---- አንድ ብርጭቆ አሊያም አንድ የሃሳብ ዘውግ ሊሆን ይችላል፡፡ ለአንድ ነገር መወከያ መጠን ገላጭ ነገር መሆኑን ብቻ ነው የምናውቀው፡፡ ምንነቱን እስካላወቅን ድረስ ከሌላ ምንነቱ ባልተተነተነ ነገር ላይ ወስደን ልንደምረው፣ ልንቀንሰው፣ ልናባዛው ወይንም ልናካፍለው እንችላለን፡፡
ነገር ግን የተተነተነ ሃሳብን ወስደን በሌላ በተተነተነ ሃሳብ ላይ የመደመሩን ፍቃድ ማነው የሰጠን? የሚለው ነው ጥያቄዬ፡፡ ወንድ ሲደመር ሴት…”ወንድ ሴት” ይፈጠራል ልንል አንችልም። የማይደመሩ ነገሮችን ከመደመር ብዙ የፅንሰ ሃሳብ መንጋደዶች ተፈጥረዋል፡፡ ለመደመር ብቁ የሚያደርጋቸው ነገር “ሎጂክ” ብቻ ሳይሆን “ምክንያታዊነትም” አንዱ  መመዘኛ መሆን አለበት፡፡
እኔም አንድን ነገር ልውሰድና…በመጠኑ በመተንተን ከሌላ ማንነቶች ጋር ለመስፋት ልሞክር፡፡ ሙከራዬ ልክ ሆኖም ይሁን ስህተት ስፌቱን የምትለብሱት እናንተ ብያኔ ትሰጣላችሁ፡፡ ለመተንተን የመረጥኩት ነገር በጣም ቀላል መሆን አለበት፡፡ ለሁላችንም ቅርብ እንዲሆን፡፡ በቀላሉ የሚገኝ…ተፈጥሮአዊ ነገር፡፡ ሁላችንንም ከተወለድን ጀምሮ ስለታደልነው እግሮቻችን ሊሆን ይችላል። ግን በተፈጥሮ ለሁላችንም የተሰጠን ነገር ከሆነ ደግሞ በተወሰኑ ሰዎች ላይ ሳይሆን ጥናት መስራት የሚያስፈልገው በብዙሐኖቹ ላይ ነው፡፡ ያ ደግሞ በጣም ብዙ ጊዜ፣ ብዙ መረጃ ያስፈልገዋል፡፡ በእኔ አስተውሎት ብቻ ሊከናወን የሚችል አይሆንም፡፡
እንደ ኪንታሮት በሽታ የመሰለ ነገርንም አይደለም መመርመር የፈለግሁት፡፡ ጤነኝነትም በሽታም ከመሰለ ነገር ቢሆን እመርጣለሁ፡፡ ምክንያቴ ወደኋላ የሚገለጽ ይሆናል፡፡
ብዙ ሩቅ መሄድ አያሻኝም ምሳሌዬን አግኝቼዋለሁ፡፡ በወንዶች እራስ ላይ የሚገኝ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን በሁሉም ወንዶች ላይ ግን አይደለም። በአንዳንዶች እንደ ውበት፣ በሌሎች ደግሞ መልክ አጥፊ ተደርጐ ይቆጠራል፡፡ ከቁርንድድ ፀጉር ባለቤቶቹ ይልቅ ለስለስ ያለ ፀጉር ባላቸው የሰው ዝርያዎች ላይ ይኼ ክስተት ይበዛል፡፡ አንዳንዶች “የምሁርነት” ምልክት ነው ይሉታል፡፡ ከሽበት ማብቀል ባልተናነሰ ነገርዬው በማህበረሰቡ ውስጥ ያስከብራል፡፡ ተቀማጭን አሽቆጥቁጦ ከወንበር ያስነሳል፡፡ የነገርየው ባለቤቶች ቆብ በነገርየው ላይ መድፋት ያዘወትራሉ፡፡ ማዕዘናም የራስ ቅል ባላቸው ላይ በብዛት አይታይም፡፡ ወይንም በማዕዘናም ራሶች ላይ ከመውጣቱ በፊት የራስ ቅላቸውን ቅርጽ ወደ እንቁላል ክብነት ይቀይረዋል፡፡
እስካሁን ግልፅ ካልሆነላችሁ ምናልባት የነገርየው ባለቤት ስለሆናችሁ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገርየው “በራ” ተብሎ ይጠራል፡፡ “ራሰ በራ” ደግሞ የነገርየው ባለቤት ነው፡፡ የሚገርመው ግን ስለ እዚህ ነገር ያገኘሁት ትንተና ከሁለት መስመሮች የረዘመ አይደለም፡፡ በተለይ ነገርየው በጤና እክል ወይንም በአደጋ ምክንያት የመጣ ካልሆነ፡፡ በዘር የሚወረስ ምክንያቱ ግልጽ ያልሆነ የፀጉር መብቀል መቆም ነው፡፡ ልክ ሽበት ማለት የፀጉር ቀለም የሚያመርቱት የቆዳ ስር ፒግመንቶች ቀለሙን ማምረት ሲያቆሙ የሚከሰት የዕድሜ ቁልቁለት ላይ በተፈጥሮ ሂደት የሚያጋጥም ጉዳይ እንደሆነው፡፡
ይህ የተፈጥሮ ገጽታ በሽታ አለመሆኑን ካረጋገጥን በኋላ፣ ወደ ተጨማሪ አስተውሎቶቻችን እንሻገር፡፡ በተወሰኑ የወንድ ዘር ግንድን ተከትሎ የሚመጣ መሆኑን እያወቅንም…በተፈጥሮ ረገድ ሳይሆን እስካሁን ባስተዋልኩት አንፃር ድምሮቼን ለመስራት ልሞክር፡፡ ጽሑፌ ላይ ስነሳ የማይደመሩ ነገሮችን ከመደመር ነው የፅንሰ ሃሳብ መንጋደድ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ አጉል እምነት እና አምልኮ የሚከሰቱት ብያለሁ፡፡
ምን ማለቴ እንደሆነ የበለጠ ልግለጽ፡፡ ለምሳሌ በአንድ የገጠር መንደር (ማህበረሰብ) ውስጥ የሚመለክ ዛፍ አለ እንበል፡፡ ዛፉ ትልቅ፣ ግንዶቹን ወደ ሰማይ፣ ስሮቹን ወደ አፈር ስር ሰድዶ ያጠነከረ አድባር ሊሆን ይችላል፤ በስፍራው ለሚኖሩ አምላኪዎቹ፡፡
እንግዲህ እዚህ ላይ ሁለት ነገሮች አሉ…አንድ ዛፍ አለ፡፡ ሁለት በነዋሪዎቹ አእምሮ ወይንም ነፍስ ውስጥ የፈጣሪ እውቀት እና ፍላጐት…ዛፉን የፍላጐታቸው መወከያ ወይንም የእውቀታቸው መጠቅለያ ተጠቅልሎ የሚገኝበት ቦታ ሲያደርጉት ተራው ዛፍ ወደ አድባርነት ደረጃ ከፍ ይላል። ሁለት የማይደመሩ ነገሮችን ደምረዋል የሚሉ የሎጂክ እና ምክንያታዊነት አምላኪዎች ቢኖሩም። እነሱም ከመደመር ነው እውቀታቸውን ያገኙት፡፡ እነሱም ሃሳባቸውን ከቁሳዊ እቃ ጋር ለማስተሳሰር የሚጠቀሙበት መንገድ አላቸው፡፡ የተፈጥሮን ሚስጢር ማወቂያ መንገድ ብለው ነው ይኸንን ምክንያታዊነታቸውን የሚጠሩት፡፡ ቅልብጭ ባለ ስያሜው ግን “ሳይንስ” ነው፡፡
ሳይንስ ለመባል አንድ ነገር መጀመሪያ በአስተውሎት ሊጤን ይገባል፡፡ ከማስተዋል እና ማጤኑ በኋላ…ስለነገርየው ያስተዋለው ሰው “መላ ምት” ይሰጥበታል፡፡ ከመላምቱ በኋላ ሦስተኛው እና ወሳኙ ደረጃ ይመጣል፡፡ መላ ምቱን ወደ ተጨባጭ የማይለዋወጥ እውነታ ለመቀላቀል በቤተሙከራ ተፈትኖ እውነትነቱ እና እምነትነቱ ይረጋገጣል፡፡
እኔ በመላጣ ላይ ለመምታት የሞከርኩት መላ…በመላምትነቱ ብቻ ነው የሚቀረው፡፡ ወደ ቤተሙከራ ወስዶ ለማረጋገጥ ከዚህ የበለጠ ሙያ እና አቅም ይጠይቃል፡፡ እኔ የሌለኝ ነገር ነው፡፡ መላ ምቶች ለሳይንስ ከሚቀርቡት ይልቅ ለጥበብ የቀረበ ዝምድና አላቸው፡፡ ስለ ራሰ በራ የምለውን ከጥበብ በበለጠ እርግጠኝነት ኮስተር ብሎ መቀበል ሞኝነት ነው፡፡   
 መላምቴን የትም ቦታ መጀመር እችላለሁ። ራሰ በራዎች በአብዛኛው መሪዎች ናቸው ልል እችላለሁ፡፡ ራሰ በራ ጠቅላይ ሚኒስትር እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ የመሪነት መድረክ ላይ ዋና ተጫዋች እንደነበረ ትዝ ይለኛል?..ሌላ ማን አለ?!...አፄ ምኒልክ ራሰ በራ አልነበሩም ለማለት ብችልም….ራሳቸው ሳይሸፈን ግልጽ ፎቶአቸውን ግን አይቼ አላውቅም፡፡ የአፄ ሃይለስላሴ ፀጉር ገባ ያለ ቢሆንም እስከመጨረሻው ደረጃ አልተመለጠም፡፡
ለመሆኑ የሀገር መሪ ሆኖ የተመለጠ ሰው ካለም ሀገሩን የመራው በጭንቅላቱ ነው ወይንስ በክንዱ…ሌኒን ራሰ በራ ነበረ፡፡ ብዙ ያነብብ እና ይጽፍ የነበረ ሰው ነው፡፡ ብዙ የሚያነብና እና ብዙ የሚጽፍ መሪ ነው የሚመለጠው ማለት ነው?
መሪ ስል በጥቅሉ ነው ወይንስ በተናጠል? ለምሳሌ ቬክስፒርም በዘመኑ የስነ ጽሑፍ ዘርፉ መሪ ነበር፡፡ ራሰ በራ ነው፡፡ ግን አንዱ የአእምሮዬ ጓዳ ደግሞ አንድ የታወቀ አሉባልታ ሹክ አለብኝ፡፡ የሼክስፒርን ቅኔዎች እና ቴአትሮች የደረሰው Sir frincis ነው የሚል አሉባልታ፡፡ ሼክስፒር ተመልጦ የሚያሳይ ፖርትሬት በብዙ አጋጣሚ አይቻለሁ፡፡ ራሰ በራው ሼክስፒር ሆኖ ግን በጥበቡ ግዛት መሪ ያደረገውን ሥራዎቹን የሰራለት ባለ ሙሉ ፀጉሩ “ሰር ፍራንሲስ ቤከን” ከሆነ ---- መመመለጥ መሪ ያደርጋል የሚለውን መላ ምቴን ቅዠት ያደርገዋል፡፡
በሼክስፒር ላይ የሚወራው አሉባልታ ወደ አንድ ጥርጣሬ መራኝ፡፡ ራሰ በራ ሌባ ሊሆን ይችላል ማለት ነው? ነገር ግን በህይወት ዘመኔ  ራስ በራ የሆነ አጭበርባሪ አይቼ አላውቅም፡፡ ታክሲ ለመያዝ ስጋፋ ከጐኔ ያለው ሰው ራሰ በራ ከሆነ ለኪሴ የማደርገውን ጥንቃቄ እቀንሳለሁ፡፡ ይህ የሚያሳየው ነገር አለ፡፡ ራሰ በራ ከተሞክሮ እድሜ ልኬን እንዳየሁት የተከበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ የረከሰ የኪስ አውላቂ ስራ አይሰሩም፡፡ ለአቅመ ራሰ በራነት ከደረሰው ይልቅ ድፍን ፀጉር ያለውን እና ወጣት የሆነውን ነው ኪሴ እንዳይገባ የምጠነቀቀው፡፡
እኔ ራሴ ፀጉረ ድፍን እና ወጣት ሆኜ ሳለሁ --- እኔን መሰል ወጣት መጠራጠሬ ምን የሚሉት ለ”መላ ምት” የማያመች ነገር ነው? “እኔ ወጣት ሆኜ ወጣቶች አልወድም/ሰይጣን ይመስሉኛል--- የዳቢሎስ ወንድም” የሚለው ይገልፀኝ ይሆን?
ለማንኛውም ራሰ በራ ኪስ አውላቂ ሊሆን አይችልም፡፡ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ከሚመሩት ሰዎች ምን ያህሉ ራሰ በራ ናቸው። የተከበሩበትን ያህል ፀጉራቸው ገባ ያለ ይሆን? ፕሮፌሰር መስፍን ራሰ በራ ባለመሆናቸው ምክንያት ይሆን ብዙውን ጊዜ ፊታቸው ላይ የቁጣ ቅላፄ የሚነበበው?
ይሄንኑ የራስ በራ መላምቴን እያሰላስልኩ ጫማዬን የጠረገልኝ በፒያሳ የሚገኝ ሊስትሮ ራሰ በራ ነው፡፡ መነጽርም አድርጓል፡፡ ጫማዬን ጠርጐ፣ ክሬም ቀብቶ ያስከፈለኝ 8 ብር ነው፡፡ ነገር ግን የቀባልኝም ክሬም፣ ለመቀባት የወሰደበት ጊዜም ዘለቅ ያለ ነው፡፡ በጥራት ነው ስራውን የሰራው፡፡ በሊስትሮ ሙያ ላይ ለእኔ መሪ ነው፡፡ ገና ስራውን ከመጀመሩ በፊት እንኳን በደንብ አድርጐ ጫማዬን እንደሚያክምልኝ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ እንደጠበቅሁት ሆነ፡፡
ቅድም የፈጠርኩት መላምቴ ትክክል ሳይሆን አልቀረም መሰለኝ፡፡ ለምሳሌ ህመም ታምሜ አንድ ክሊኒክ ብሄድ እና ከጠረጴዛው ጀርባ ተቀምጦ ስለ ህመሜ ባህሪ የሚጠይቀኝ የህክምና ዶክተር ራሰ በራ ቢሆን … እርግጠኛ ነኝ ግማሽ ህመሜ ለቀቅ እንደሚያደርገኝ፡፡ ከወጣት እና መላጣ ካልሆነው ዶክተር የበለጠ ራሰ በራው እና ምራቁን ዋጥ ያደረገው ባለሞያ መፍትሄ እንደሚሰጠኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡
ሌላው በእይታ ካደረግሁት ጥናት የተገነዘብኩት ነገር … መለጥ ያሉ ሰዎች ወፈር ለማለትም የቀረቡ ናቸው፡፡ ወፈር ለማለት እና ቦርጭ ለማውጣት ቅርብ ናቸው፡፡
ደራሲዎችን በአይነ ህሊናዬ ደርድሬ … ይሄ በተለምዶ የሚደፉትን ቆብ በምኞት እጄ እየገለጥኩ አናታቸውን መረመርኳቸው፡፡ የሚገርመው (በተለይ በሐገራችን ላይ ያሉት) “ራስ ሙሉ” ናቸው፡፡ ከባህር ማዶ ያሉትም ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ትያትር ፀሐፊዎች እና ገጣሚዎች ግን በተገላቢጦሽ ፀጉራቸው የገባ ብዙ አገኘሁ፡፡ የህዝቡን ሀላፊነት በራሳቸው ላይ ተሸክመው በመወጣት በኩል ትልቅ ሚና የተሸከሙት ደራሲዎች ናቸው ገጣሚዎች እና ትያትር ፀሐፊዎች …፡፡
እስካሁን በራሰ በራዎች መሪነት፣ አስተዋይነት፣ ምሑርነት ላይ ማረጋገጫ ለመስጠት ስባዝን ቆይቼ አሁን እጄን ልሰጥ አልችልም! … ከደራሲ ይበልጥ ገጣሚዎች ለህዝብ ሀላፊነት ይቀርባሉ ማለት ነው-እንደኔ መላምት፡፡
ማረጋገጫዬ አስተውሎቴ ብቻ ነው፡፡ ራሰ በራ የሆኑ የአእምሮ በሽተኞችም ብዙ አይቻለሁ። ከተራው የአእምሮ በሽተኛ ላቅ ያሉ ቢሆኑ ነው የሚል መላምት አለኝ፡፡ ራሰ በራ የሆነን በሽተኛ ፀጉረ ጨብራራ ከሆነው እኩልማ ልመዝነው አልችልም፡፡ በትምህርት ብዛት ካበደው ጋር በትምህርት እጦት ምክንያት ያበደውን እኩል ቦታ ላስቀምጠውም ህሊናዬ አይፈቅድም፡፡
በዝግመተ ለውጥ እይታም ራሰ-በራነትን ልመለከተው እችላለሁ፡፡ እነ ሉሲ እና አርዲ (በስዕል ባሳዩን መሰረት) ሰውነታቸው በፀጉር የተሸፈነ ዝንጀሮ ነው የሚመስሉት፡፡ ራሰ በራ በእነሱ የጦጣ ዘመን ላይ ያለ አይመስለኝም፡፡ በዝንጀሮዎች ዘንድ ራሰ በራ የሆነ አይታችሁ ታውቃላችሁ? … እኔ አላውቅም፡፡ በሰዎች ዘንድ ግን ሰውነቱ በፀጉር የተሸፈነ ብዙ አለ፡፡ ባይሆን ዝንጀሮዎች ሲመለጡ ደረታቸው አካባቢ ነው፡፡ ጭላዳ ዝንጀሮ ደረቱ ላይ አይደለ ራሰ-በራው ያለው፡፡
ስለዚህ ፀጉሩ ገባ ገባ ካለው ይልቅ ያላለው ወደ ዝንጀሮኛ ይቀርባል እንደኔ መላምት፡፡ ግን እኔም ፀጉራቸው ገባ ካላሉት መሀል የምመደብ ነኝ። እኔ ራሴ ወደ ዝንጀሮዎቹ ጐራ ሆኜ ነው እንዴ መሰሎቼን የምነቅፈው? “… እኔ ዝንጀሮ ሆኜ ዝንጀሮ አልወድም/ሰይጣን ይመስለኛል የዳቢሎስ ወንድም”
እዚህ ላይ ላብቃ፡፡ የማይደመሩ ነገሮችን ከመደመር ምን አይነት መላ ምቶች እንደሚገኙ ለማሳየት ጥሩ ምሳሌ ይመስለኛል፡፡    

Read 3523 times
Administrator

Latest from Administrator