Monday, 23 December 2013 09:33

የአማራ ክልሉ “ዱላ ቅብብሎሽ” ግራ አጋባኝ እኮ!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(17 votes)

“የመተካካት ሂደት የዱላ ቅብብሎሽ ነው”
አቶ አያሌው ጐበዜ “ዱላውን” ለማነው ያቀበሉት?

እናንተ … የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ነኝ የሚለው “CPJ” እና የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ነኝ ባዩ “ሂዩማን ራይትስዎች” ከላያችን ላይ አንወርድም አሉን አይደል? (ከኢህአዴግና ከኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበራት ላይ ማለቴ እኮ ነው!) እኔማ ባለፈው የአፍሪካ ሚዲያ ፎረም ሲካሄድ… ሦስቱ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበራት፤ በጋራ የሰጡትን “ዱላቀረሽ” መግለጫ መስማታቸው ስለማይቀር አርፈው ይቀመጣሉ ብዬ ነበር፡፡ ችግሩ ግን “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ…” የሚለውን ተረት አያውቁትም!፡፡ አያችሁ … የመብት ተሟጋቾች እኮ ችኮ ናቸው፤ ነገር ከያዙ አይለቁም፡፡ መቼም መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉት ሶስቱ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበራት “የታሰረ አንድም ጋዜጠኛ የለም” ማለታቸውን የመብት ተሟጋቾቹ መስማታቸው አይቀርም፡፡ ግን ምን ያደርጋል? ሰሞኑን CPJ ባወጣው ሪፖርት፤ ጋዜጠኞችን በማሰር ኢትዮጵያን ከ10 የዓለም አገራት በሁለተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧል (ገፅታ ለማበላሸት እኮ ነው!)
ድሮም ኒዮሊበራሊስቶች ለጦቢያ ተኝተው አያውቁም! እኔ ግን ሳስበው… እንዲህ ካሉት “ጃይንት” ዓለምአቀፍ ተቋማት ጋር ከመጋፈጥ ይልቅ “ፒስ” ማውረድ ነው ተመራጩ፡፡  (“አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው ታላቅ ችሎታ ነው” አለ መሐሙድ!)
ይኸውላችሁ…ኢህአዴግን ልማት ወጥሮ ይዞት ነው እንጂ CPJ ን ማሳመን አያቅተውም ነበር፡፡ ትዝ ይላችኋል …እነ IMF እና እና ዎርልድ ባንክ በባለሁለት ዲጂቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ከመንግስት ጋር ሲወዛገቡ! ኢህአዴግ ነፍሴ ምን አደረገ? 10 ዓመት ቢፈጅበትም አሳመናቸው! አሁን የኢህአዴግን ዕድገት እኮ  አምነዋል፡፡ ከጋዜጠኞች ተሟጋቾቹም ሆነ ከሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ጋር ያለውንም ውዝግብ፤ ኢህአዴግ በውይይት ቢሞከረው ይሻላል ባይ ነኝ፡፡
እኔ የምለው…በመብራት፣ በውሃና በስልክ አገልግሎቶች አዲስ የተቆረቆርን አገር መሰልን አይደል? (ደቡብ ሱዳን እኮ ተሻለች!) ሰሞኑን በኢቴቪ የሰማሁት የውሃ ችግር ግን “የባሰ አለና አገርህን አትልቀቅ” የሚያሰኝ ነው፡፡ “ሰሜናዊቷ ኮከብ” እየተባለች በምትሞካሸው መቀሌ ከተማ 3 ወር ሙሉ ውሃ አልነበረም ተባለ፡፡ (አሁንስ የታለ?) የከተማዋ ነዋሪዎች ለኢቴቪ ቅሬታቸውን ሲናገሩ፤ በውሃ እጦት ክፉኛ መሰቃየታቸውን ገልፀዋል፡፡ (ግን እንደኛ ሳይማረሩ!) እኔማ… የመቀሌ ውሃና ፍሳሽ መ/ቤት፤ ተዘግቶ ነው ብዬ ተወራርጄ ነበር፡፡ አስበሉኝ!  ወዲያው የመ/ቤቱ ሃላፊ በኢቴቪ ከች አሉ (አለማፈራቸው!) እናም “የውሃ እጥረቱ የተከሰተው ከከተማዋ ዕድገት ጋር ተያይዞ ነው” ብለው በቀላሉ ተገላገሉት (ይሄማ የተበላ ዕቁብ ነው!)
“ስኳር ለምን ጠፋ?”
“ገበሬው ስኳር መጠቀም ስለጀመረ!”
“መብራት ለምን ይቆራረጣል?”  
“የኢንዱስትሪ ዘርፉ ስላደገ!” እነዚህ ሁሉ ሰበቦች አሁን ፋሽናቸው አልፏል፡፡ (ሃላፊው አልሰሙማ!)
እንዴ… እነ መብራት ሃይልና የውሃና ፍሳሽ መ/ቤት ከተማውና ኢንዱስትሪው ሲያድግ የማንን ጐፈሬ እያበጠሩ ነበር? (አብረው አያድጉም እንዴ?) ወይስ የአገሪቱን ዕድገት እየተነበየ፣ ዕቅድ የሚያወጣ አዲስ መ/ቤት ማቋቋም ሊያስፈልግ ነው? (አሁንም እቅጯን ይናገሩ!)
እኔ ግን አንድ ሃሳብ አለኝ…ሦስቱ ትላልቅ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት (ውሃና ፍሳሽ፣ መብራት ሃይል፣ ኢትዮ - ቴሌኮም) የኢኮኖሚ ዕድገቱና የከተሞች መስፋፋት ከአቅማቸው በላይ ስለሆነባቸው፣ ትንሽ የዕድገቱ ግስጋሴ በረድ…ቀዝቀዝ … ቢልላቸው ጥሩ ነው (ሌላው ለጥጦ ያቅዳል እነሱ …) ይሄ እንግዲህ በቀና ልቦና ሲተነተን ነው፡፡ ግን ደግሞ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳሉት፤ የSabotage (አሻጥር) ነገር ሊኖርበትም ይችላል፡፡ ምናልባትም የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኞች ሰርገው ገብተው ይሆናል፡፡ (መረጃ ውድ በሆነበት አገር ሃሜትና ጥርጣሬ ቢነግስ አይገርምም!)
እኔ የምለው ግን…አፄ ምኒልክ ድንገት ቀና ብለው ይሄን ሁሉ “ምስቅልቅል” ቢመለከቱ “የት አገር ነው የነቃሁት” ብለው ግር የሚላቸው አይመስላችሁም? ከአንድ ክ/ዘመን በኋላ ጦቢያን እንደ አውሮፓ ሆና አገኛታለሁ ሲሉ፣ ከጥንቱም ብሳ ሦስት ወር ውሃ የሚጠፋባት አጃኢብ አገር ሆናላቸዋለች (እንዴት እንደሚያፍሩብን!)
በነገራችሁ ላይ…ካዛንቺስ አካባቢ ባለገመዱ ስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ከተቋረጠ ድፍን ወር ሞላው፡፡ ምኒልክ ቢኖሩ … “ማርያምን አልምርህም!” ይሉን ነበር፡፡ እናላችሁ…ኢትዮ ቴሌኮም በተደጋጋሚ ደውለን (በሞባይላችን ማለቴ ነው!) ስንጠይቅ የተሰጠን ምላሽ ምን መሰላችሁ? “አገልግሎቱ የተቋረጠው ከመንገድ ሥራው ጋር በተያያዘ ስለሆነ ትንሽ ታገሱ” የሚል ነው (ኧረ ተመስገን ነው! መዘለፍም አለ እኮ!) እኔ የምለው ግን… “ትንሽ ታገሱ” ሲባል ምን ማለት ነው? 1 ወር? (ወርማ ሊያልፈን ነው!) 2 ወር? 1 ዓመት? 5 ዓመት? (አልነገሩንማ!) ለጊዜው ግን እኛም የመንገድ ሥራ ማለት “ልማት” እንደሆነ ስለምናውቅ፣ የመንግስት ልማት ከሚስተጓጐል የእኛ ልማት አፈር ድሜ ይብላ ብለን ልንታገስ ተስማማን (ምርጫ የለንማ!) ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ? የዛሬ ዓመት ገደማ የኢትዮ-ቴሌኮም ከፍተኛ ሃላፊ፤ ከኔትዎርክ ችግር ጋር ተያይዞ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ የመንገዱን መቆፋፈር እንደምክንያት ሊያቀርቡ አሰቡና፣ የፓርቲያቸውን ግምገማ ፈሩ መሰለኝ፣ እንዲህ በብልሃት ተናገሩ:- “ከተማዋ ምስቅልቅል ላይ ናት…ግን የዕድገት ምስቅልቅል ነው!” (ከማንኛውም ምስቅልቅል ያውጣን!)
እኔ የምለው ግን … ይሄ ለሁሉ ነገር እንደ ፍቱን መድሃኒት የሚታዘዘው የ1ለ5 አደረጃጀት (በቤት ስሙ “ጥርነፋ!”) በቴሌ፣ በውሃና ፍሳሽ፣ እንዲሁም በመብራት ሃይል አልተሞከረም እንዴ? (1ለ5 ያልገባበት የለም ብዬ እኮ ነው!) በቅርቡ እንደውም ይሄ አደረጃጀት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መግባቱን የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩና የመድረክ ፓርቲ አመራር አባል የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና ተናግረዋል (የአካዳሚ ነፃነት ውሃ በላው እንዴ?) ግን እኮ እዚህ እንደውም ዘግይቷል፡፡ በየክልሉ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች፣ የ1ለ5 አደረጃጀት ሥራ ላይ ተተግብሮ አመርቲ ውጤት እንዳመጣ፣ በኢቴቪ መስኮት ብቅ የሚሉ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እየመሰከሩ ነው (ካድሬ ናቸው እንዳትሉኝ!) ዝም ብዬ ሳስበው (መረጃ የለማ!) 1ለ5 ለተማሪዎች እንኳን ሳይበጅ አይቀርም (ለፖለቲካ ቅስቀሳ ሳይሆን ለጥናት!) ችግር የሚመጣው አንድ ፕሮፌሰር ከአምስት ዶክተር ጋር ይጠርነፍ ሲባል ነው (እዚህ አገር ፍሬን የለማ!) እናም በዚያው ከቀጠለ… አንድ ከፍተኛ ባለሃብት ከአምስት መካከለኛ ባለሃብቶች ጋር ይጠርነፍ መባሉ አይቀርም (ቀይ መስመር ማለፍ ተለምዶ የለ!)
ይሄን ፖለቲካዊ ወግ እየከተብኩ ሳለ፤ “ኢቴቪ ወዳጄ” … አንድ ሰበር ዜና ሹክ አለኝ፡፡ ለስምንት ዓመት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በመሆን ያገለገሉት አቶ አያሌው ጐበዜ ባቀረቡት “የመተካካት ጥያቄ” መሰረት፣ አስቸኳይ ጉባኤ ተጠርቶ ሥልጣናቸውን ለምክትላቸው አስረከቡ አለኝ-ኢቴቪ! አይገርምም ፍጥነትና ቅልጥፍናቸው! የህዝብ አንገብጋቢ ጉዳዮችም አስቸኳይ ጉባኤ እየተጠራ እንዲህ አስቸኳይ እልባት ቢሰጣቸው አልኩ-በሃሳቤ፡፡ 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ደግሞ ኢቴቪ ሌላ መረጃ አቀበለኝ፡፡ “የቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሙሉ አምባሳደርነት ሹመት ተሰጣቸው” የሚል፡፡ ሌላ ፍጥነት! ሌላ ቅልጥፍና! አትሉም (ከሮቦት ብቻ የሚጠበቅ!) “የመተካካት ሂደት የዱላ ቅብብሎሽ ነው” ያሉት አቶ አያሌው ጐበዜ፤ “ዱላውን ለሚቀጥሉት ወጣት አመራሮች አስረክቤአለሁ” ብለዋል፡፡
እኔን ያልገባኝ ምን መሰላችሁ? የዱላ ቅብብሉ ዓይነት! (ወደ ጐን  የዱላ ቅብብሎሽ አለ እንዴ?) ሌላም ያልገባኝ ነገር አለ፡፡ ወጣቱ ትውልድ ወይም New blood የሚባለው የትኛው ነው? አቶ አያሌው ጐበዜን የተኩት (የቀድሞው ምክትላቸውን ማለቴ ነው!) የአዲሱ ትውልድ አባል ናቸው እንዴ? (“ለሚቀጥሉት ወጣት አመራሮች አስረክቤአለሁ” ስለተባለ እኮ ነው!) በነገራችሁ ላይ ኢህአዴግ New blood የሚለው በስንት የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉትን እንደሆነ ግልፅልፅ አድርጐ ቢነግረን ከ“ብዥታ” እንወጣለን፡፡ ወይም ደግሞ የዱላ ቅብብሎሽ ወደ ጐንም ይቻላል ብሎ እቅጩን ይንገረን፡፡ ያኔ አፋችንን ዘግተን እንቀመጣለን (እኔ New blood እንዳልሆንኩ ይታወቅልኝ!)
በመጨረሻ … አንድ ጥያቄ አለኝ፡ አቶ አያሌው ጐበዜ ስልጣናቸውን የለቀቁበትን ምክንያት በፌስ ቡክ ላይ ይፃፉልን!! (“ኢህአዴግ ፌስቡክ መጠቀም ያበረታታል” ሲባል ሰምቼ እኮ ነው!!)

Read 6120 times