Monday, 23 December 2013 09:29

አቶ መለስ ከሞቱ ወዲህ

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(36 votes)

“ኢህአዴግ፣ በህልውና ስጋት ስልጣኑን የማደላደል ጣጣ ውስጥ ገብቷል”
ጠ/ሚ ኃይለማርያም ቅን ናቸው፣ ነገር ግን ቅንነት ብቻውን በቂ ሊሆን አይችልም
ካለፈው ትውልድ ብንሻልም በሽታ አጋብቶብናል፤ አዲሱ ትውልድ ነው ተስፋዬ
በኢትዮጵያ የአረብ አገራት አይነት ቀውስ ከተፈጠረ ማብቂያ አይኖረውም”

ከኢዴፓ መስራችና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ልደቱ አያሌው ጋር የተደረገውን ቃለምልልስ ማጠቃለያ በዚህ ሁለተኛ ክፍል እናቀርባለን። የኢትዮጵያ ዋና ዋና ፈተናዎችን ከአረብ አገራት ቀውስ ጋር በማያያዝ፣ እንዲሁም ከአቶ መለስ ዜናዊ ህልፈት ወዲህ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ ይተነትናሉ። በቅድሚያ ግን በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዙሪያ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣሉ፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሁለት በሦስት ጥምረት ውስጥ የመሰባሰብ እድል አላቸው? ቀጣዩ ምርጫ አንድ አመት ብቻ ነው የቀረው…
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ አንድነት ቢኖር ጥሩ ነበር፡፡ ችግሩ ግን በተቃዋሚ ጐራ ውስጥ የመቻቻል አዝማሚያ የለም፡፡ አንዳንዱ ታቃዋሚ ከሱ የተለየ አመለካከት የምታራምድ ከሆነ አሉባልታ ያስወራል፤ ጥላቻ ያራምዳል፡፡ ይሄ የሚያሳየው ከእኔ አመለካከትና መስመር ውጭ ማራመድ አይቻልም የሚል ስሜታዊ የፅንፍ አስተሳሰብ መያዙን ነው፡፡
በእንደዚህ አይነት አስተሳሰብ ደግሞ፣ መቻቻልን መፍጠር አይቻልም፡፡ በዚህ ረገድ በ2007 ዓ.ም ምርጫም ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል ብዬ አላስብም፡፡
ኢዴፓን በሚመለከት ፓርቲያችን ብቻውን ተዓምር ይፈጥራል የሚል እምነት የለኝም - የፓርላማና የክልል ምርጫ ላይ፡፡ ከፍተኛ ውጤት ሊያመጣ ይችላል ብዬ የማምነው የ‹‹ሶስተኛ አማራጭ››ነት ሚናውን በማጉላት ነው፡፡ ምክንያታዊ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ምትክ የሌለው ምርጫ መሆኑን፤ እንዲሁም ገዢው ፓርቲና አብዛኛው የተቃዋሚ ጐራ እስካሁን የተጓዝንበት መንገድ እንደማይበጀን በማሳየት ረገድ ኢዴፓ ትልቅ ውጤት ያመጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ በአግባቡ ከተጠቀምንበት፣ ሃሳባችንን ህብረተሰቡ ጋ ካደረስን፣ አጀንዳችንን በግልጽ ማስረዳት ከቻልን፣ የማይናቅ ውጤት እናመጣለን ብዬ አስባለሁ፡፡ የተወሰኑ መቀመጫዎችን ማሸነፍም እንችላለን፡፡
በእርግጥ የተወሰኑ ወንበሮችን ማግኘት በአገር አቀፍ ደረጃ ያን ያህል ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ብዬ አላምንም፡፡ ነገር ግን ዋናው ነገር አመለካከትን ማስተካከል ነው፡፡ ያኔ ዘላቂ ለውጥ ይመጣል፡፡ አብዛኛው ተቃዋሚና ገዢው ፓርቲ አሁን የያዙትን የሁለት ፅንፍ አመለካከት ይዘው እስከቀጠሉ ድረስ ግን፤ ኢዴፓ ውጤት ሊያመጣ የሚችለው በተራዘመ ጊዜ ይሆናል ማለት ነው፡፡
በህብረተሰቡ ውስጥ የኢዴፓን አመለካከት ለማስፋፋት ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ ብቻችንን ይሄን ውጤት በአጭር ጊዜ እናመጣለን የሚል አጉል ተስፋ የለኝም፡፡ አሁን አብዛኞቹ ተቃዋሚዎች ኢዴፓ የያዘውን አመለካከትና አቀራረብ ቢቀበሉት ግን፤ ውጤቱ በጣም ፈጣን ይሆናል፡፡
እና ተቃዋሚዎች መሰባሰብ ቢችሉ ውጤት ሊያመጡ ይችላሉ?
መሰባሰብ የሚያስፈልገው፤ ሰላሳ፤ አርባ ፓርቲ ብሎ ለመቁጠር አይደለም፡፡ የሚፈጠረው ስብስብ፣ ከቀድሞዎቹ ስህተቶች በደንብ የተማረ መሆን አለበት፡፡ ያለፉትን ስህተች ላለመድገም የተዘጋጀ መሆን አለበት፡፡ ዝም ብሎ መሰባሰብ ጥቅም የለውም፡፡
“የእስካሁኖቹ ስብስቦች ለምንድን ነው ውጤታማ ያልሆኑት? ህዝቡ የጣለባቸውን ተስፋ እውን ማድረግ ያልቻሉት ለምንድነው?” በእነዚህ ጥያቄዎች ዙሪያ ከታሪክ መማር መቻል አለብን። አሁን ግን ለመማር ብዙም ጥረት አናይም፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የቀድሞው ቅንጅት ምንም ስህተት ሰርቷል ብለው አያምኑም፡፡ ትክክል ነበር ብለው ያምናሉ፡፡ ካለፈው ስህተት መማር አልቻሉም፡፡
የኢህአዴግ አባል፣ በጭፍን ድጋፍ ሁሉንም ስህተት በተቃዋሚዎች ላይ እንደሚያላክክ ሁሉ፣ እነዚህ ተቃዋሚዎችም በጭፍንነት ሁሉንም ስህተት በኢህአዴግ ላይ ወይም በሌላ አካል ላይ ይለጥፋሉ፡፡
በዚህ መልኩ ለውጥ ሊመጣ አይችልም፡፡ ያለምንም ጥርጥር የተቃዋሚዎች ህብረት አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን፣ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ሲባል እንጂ፣ ህብረት መፍጠር በራሱ ግብ አይደለም። ጥሩ ለውጥ ማምጣት ከፈለግን የቀድሞዎቹ ህብረቶች ለምን ውጤታማ እንዳልሆኑ ቁጭ ብለን ከምር መወያየትና መገምገም አለብን፡፡ ስህተቶችን ቁልጭ አድርገን አውጥተን እነዚህን ስህተቶች፣ “አንደግማቸውም፤ ተምረንባቸዋል” ብለን ልናስተካክላቸው ይገባል፡፡
“መድሎት” በተሰኘው መጽሐፍዎ ላይ፣ የአቶ መለስ አለመኖር የስልጣን ሽኩቻን ያመጣል ብለው ነበር፡፡ አሁንስ የእርሳቸው በህይወት አለመኖር፣ ምን አንደምታዎች ይኖሩታል? ገዢው ፓርቲ ውስጥ ክፍፍል አለ እየተባለ ይወራል፡፡ የርስዎ ስጋት እውን ይሆናል ይላሉ?
በ“መድሎት” ውስጥ በገለጽኩት ሃሳብ ዙሪያ፣ አሁን እሳቸው ከሞቱ በኋላስ ትክክል ነው ወይንስ አይደለም ብዬ ነገሮችን ለማየት ሞክሬያለሁ፡፡ ግምገማዬ ትክክል እንደሆነ ነው የሚሰማኝ፡፡ ያኔ ያነሳሁት ጭብጥ፤ ኢህአዴግ በስልጣን ላይ መቆየቱ ካልቀረ አቶ መለስ በስልጣን ላይ ቢቆዩ ይሻላል ወይስ አይሻልም የሚል ነው፡፡  
የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታው የተሻለ አቅጣጫ ሊይዝ የሚችልበትን መስመር ለማየት አቶ መለስ ከሌሎቹ የኢህአዴግ አመራሮች የተሻለ እድል ነበራቸው፤ ፍላጐቱም ነበራቸው ብዬ አምናለሁ፡፡
ኢህአዴግ በስልጣን ላይ መቀጠሉ እስካልቀረ ድረስ፣ አቶ መለስ ቢኖሩ ይሻል ነበር ብዬ አምናለሁ። ያኔም ብየዋለሁ፡፡
ለምን ቢባል፤ አቶ መለስ እሳቸውን የሚተኩና ጐልተው የሚታዩ ሰዎችን ፈጥረዋል ወይ? እዚህ ላይ ድክመት ነበረባቸው ብዬ አምናለሁ። እንደማንኛውም አምባገነን መሪ፤ በራሳቸው ስር ከፍተኛ ስልጣን አሰባስበው ነበር፡፡ እሳቸው ብቻ ነበሩ የሚደመጡበት፡፡ ከመደመጥም አልፈው የሚመለኩበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ያ ሁኔታ አሁን የራሱ የሆነ ጉዳት አስከትሏል ብዬ አምናለሁ፡፡
የመልካም አስተዳደር እጦትንና ሙስናን በመዋጋት ደረጃ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገዢው ፓርቲ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ መተካካቱ ችግር አላስከተለም ማለት ነው?
እኔ ይሄን ከምንም አልቆጥረውም፡፡ አቶ መለስ በህይወት ከነበሩበት ጊዜ የተለየ ነገር የለም። እሳቸው በነበሩበት ጊዜ አቶ ታምራት በሙስና ታስረው ነበር፡፡ ተመሳሳይ ዘመቻዎችም ታይተዋል። ሙስና የሚገታው በዚህ ዓይነት ዘመቻ አይደለም፡፡ በመሠረታዊ የአስተሳሰብና የአሠራር ለውጥ እንጂ፣ በሰሞነኛ ግርግርና ዘመቻ የሚፈታ ችግር አይደለም። ግርግር በሳቸውም ጊዜ አይተናል፤ አሁንም እያየን ነው፡፡
ይልቅስ፤ አሁን የተፈጠረ አዲስ ነገር ሌላ ነው። ከአቶ መለስ ሞት በኋላ፤ የፓርቲው የስልጣን እንብርት  የት እንደሆነ በግልጽ ወጥቶ አልታየም። አልለየለትም፡፡ ህዝቡ፤ እኛ ተቃዋሚዎች፤ የኢህአዴግ አባላትም ጭምር እቅጩን የሚያውቅ የለም፡፡ ኢህአዴግ እንደ አዲስ ድርጅት ስልጣንን እንደገና የማደላደልና ዘላቂ የማድረግ ሂደት (ፓወር ኮንሰልዴሽን) ውስጥ ነው የገባው፡፡
ኢህአዴግ እንደ አዲስ ስልጣኑን የማደላደል ጣጣ ውስጥ መግባቱ የዲሞክራሲ ሂደቱን በጣም ይጐዳዋል፡፡  አቶ መለስ ባይሞቱ ኖሮ፣ የሚቀጥለው ምርጫ የተሻለ ለውጥ ይታይበት ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን ግን ኢህአዴግ እንደዛ አይነት ለውጥ ለማስተናገድ የሚችልበት ሁኔታ ውስጥ አይደለም፡፡ በድርጅቱ ውስጥ የስልጣንና የሃይል ድልድሉ አልጠራም፡፡
አቶ መለስ በኢህአዴግ ውስጥ፣ ሃያልና ገናና የሆኑት ባለፉት አስር ዓመታት ነው፡፡ ከዛ በፊት ገናና አልነበሩም፡፡ እንደ አቶ መለስ በሁሉም የኢህአዴግ አመራርና አባላት ዘንድ ተደማጭነት ያለው ገናና ሰው እስኪፈጠር ብዙ ዓመታት ይወስዳል፡፡ እስከዚያው ኢህአዴግ ተደላድያለሁ ብሎ ስለማይተማመን የህልውና ጉዳይ የበለጠ ያሳስበዋል፡፡ ልፈረከስ እችላለሁ ብሎ ይሰጋል። ተቃዋሚዎች ቀዳዳ ተጠቅመው ያዳክሙኛል ያፈራርሱኛል ብሎ ይፈራል፡፡ ስጋቱና ፍርሃቱም፣ የበለጠ በሩን እንዲያጠብና እንዲዘጋ ይገፋፋዋል፡፡
ይህንን ነው እያየሁ ያለሁት፡፡ ከዛ አንፃር ነው፤ አቶ መለስ ቢኖሩ ይሻል ነበር የምለው፡፡ በመሪነት ሚናቸው አምባገነን ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን አቶ መለስ ዞሮ ዞሮ ያን ያህል ዓመት ገዝተውናል። የኋላ ኋላ ለታሪካቸውም ሲሉ፣ የመንግስት መሪ በመሆን ከተማሯቸው የተለያዩ ጉዳዮች በመነሳት፣ ከሌሎች የኢህአዴግ አመራሮች በተሻለ መልኩ፣ በጐ ለውጥ የማምጣት እድል ነበራቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ እነዚያን እድሎች የመጠቀም አንዳንድ ምልክቶችም እያየን ነበር፡፡ በ97 ምርጫ፤ በሩን ሰፋ የማድረግ ሁኔታ ያየነውም  ከዛ ጋር የተያያዘ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢህአዴግ እንደ ድርጅት አምባገነን ነው፤ አቶ መለስም አምባገነን መሪ ነበሩ፤  ግን ከኢህአዴግ አመራር አባላት ውስጥ ማወዳደር ካስፈለገ፣ አቶ መለስ የተሻሉ ዲሞክራት ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ እሳቸው ከስልጣን ከመውረዳቸው በፊት ለተወሰኑ አመታት በስልጣን ቢቆዩ ለአገሪቱ በዲሞክራሲ ሂደቱ የተሻለ ነገር ሊያመጡ ይችላሉ የሚል ግምት ነበረኝ፡፡ አሁን እሳቸው በህይወት የሉም፡፡ ኢህአዴግ በህልውና ስጋት ስልጣኑን የማደላደል ጣጣ ውስጥ ገብቷል፡፡ በቀጣዩ አመት ምርጫ የተሻለ ነገር ይዞ ሊመጣ ይችላል የሚል ተስፋ እንዳይኖረኝ ያደረገኝ ይኼ ነው፡፡
ከኢትዮጵያ ዋና ዋና ፈተናዎችና ትልልቅ ስጋቶች ሶስቱን ይጥቀሱ ቢባሉ የትኞቹን ያስቀድማሉ?
አንደኛው ፈተና፣ የዲሞክራሲ ሂደት አለመኖር ነው፡፡ ዲሞክራሲ ታፍኖ በቀጠለ ቁጥር፣ አገሪቱ አደጋ ማስተናገዷ የማይቀር ነው፡፡ ዲሞክራሲን እስከወዲያኛው አፍኖ መኖር አይቻልም፡፡
የዲሞክራሲ ጥያቄዎች እንዳልተመለሱና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በአግባቡ እንዳልተከበሩ ህብረተሰቡ እሮሮ እያቀረበ ነው፡፡ ይሄ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ ሁልጊዜ የህዝብን ጥያቄ ወይም የተቃዋሚን እንቅስቃሴ በሃይል እያፈኑ መኖር አይቻልም፡፡ እመቃውና አፈናው ያለ ምንም መሻሻል ከቀጠለ፣ ኢትዮጵያን ወደ መጥፎ አደጋ ሊያስገባት ይችላል፡፡ አንዱ ስጋቴ ይህ ነው፡፡
ሁለተኛው ከሙስና ጋር የተያያዘው ስጋት ነው፡፡ በስርዓቱ ውስጥ እጅና ጓንት ሆኖ አላግባብ የሚጠቀምና የኢኮኖሚ የበላይነትን የሚቆናጠጥ ማህበረሰብ እየተፈጠረ ነው፡፡ ብዙ ጦም አዳሪ ባለበት አገር፤ አንዳንድ ሰዎች ከመንግስት ጋር ባላቸው ግንኙነት፣ የአውሮፓና የአሜሪካ ዓይነት ኑሮ ሲፈጥሩ ህብረተሰቡ እየታዘበ ነው፡፡ ይሄ የፖለቲካውን ብሶት የበለጠ ተቀጣጣይ ያደርገዋል፡፡ በተለይ  እንደ ኢትዮጵያ ብዙ ብሔረሰብ ባለባትና የፖለቲካ ቅራኔ በከረረባት አገር፣ እጅግ አስጊ ነው፡፡ መፍትሔ ካልተበጀለት በቀር፣ ለአገሪቱ ትልቅ አደጋ እንደሆነ አምናለሁ፡፡
ሶስተኛው ስጋት፣ ኢኮኖሚያችን ውስጥ ያለው ችግር ነው፡፡ የኢኮኖሚ ጥያቄ፣ የድህነት ጥያቄ ብቻ አይደለም፡፡ የሰላም ጥያቄ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ጥያቄ የዲሞክራሲ ጥያቄ ነው፡፡ የኢኮኖሚ እድገት የህልውና ጥያቄ ነው፡፡ ይህች አገር ከሞላ ጐደል  የእርሻ አገር ናት፡፡ ከተማ ከገባን ደግሞ የሱቅና የቢሮ አገር ናት፡፡ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች አገር አይደለችም፤ መሆንም አልቻለችም፡፡ መዋቅራዊ ሽግግር ካልመጣ በቀር፤ የእስካሁን አመጣጧ ከፍተኛ አደጋ ላይ ያደርሳታል፡፡ ለምን ቢባል፤ በመዋቅራዊ ሽግግር ኢንዱስትሪ ካልተስፋፋ፣ ድህነት እጅግ ይባባሳል፣ የሰው ኑሮ ይበልጥኑ ይናጋል፡፡ ያለጥርጥርም፤ የፖለቲካ አለመረጋጋትን ያስከትላል፡፡
የዲሞክራሲ ሂደት አለመኖር፣ ከሙስና ጋር የተያያዘ የሃብት ሽሚያ አበጋዞች መፈጠር እና ከእርሻ በላይ የሚሄድ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር አለመኖር ናቸው ሶስቱ ትልልቅ የአገሪቱ ፈተናዎች። አስቸኳይ እርምጃ ካልተወሰደ የዚህች አገር ሁኔታ አስቸጋሪ ነው፡፡
አካባቢያዊ ጉዳዮችን ላንሳ፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በአረብ አገራት የተፈጠረውን እንቅስቃሴ እንዴት ያዩታል? የግብፅና የሶርያ ወደ አልተጠበቀ አቅጣጫ ማምራት እንዴት ይመለከቱታል?
አሁን የጠቀስኳቸው ሶስቱ የአገራችን ችግሮች ካልተፈቱ፤ ኢትዮጵያም እንደዛ አይነት ቀውስ የምታስተናገድበት አደጋ ይኖራል፡፡ በግብጽ፣ በሶሪያ፣ በሊቢያ ያየነው አይነት ቀውስ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢፈጠር፤ ውጤቱ ከእነሱም የከፋ አውዳሚ ሊሆን ይችላል፡፡ በአገራችን ውስጥ የሚታዩ ችግሮች፣ ብዙ አቀጣጣይ ነገሮችን ያቀፉ ናቸው፡፡ ስሜታዊ ሃይሎች በቀላሉ የሚያግለበልቧቸው የብሔረሰብ ጉዳዮች፣ እንዲሁም ፅንፍ ድረስ የተወጠሩ ጭፍን የፖለቲካ አስተሳሰቦች በበረከቱባት አገር ውስጥ ቀውስ ተጨምሮበት ምን ያህል ውድመት እንደሚፈጠር ለማሰብ ይከብዳል፡፡
ግብፅ ውስጥ፣ ጐዳና የወጣው ጦር ሰራዊትና ጐዳና የመጣው ወጣት፣ በሰላምታ ሲጨባበጥ አይተናል፡፡ ቀውሱን ሙሉ ለሙሉ ለማስወገድ ባይችልም፤ ያረግበዋል፡፡ በኛ አገር ግን እንደዚያ አይነት ማርገቢያ ነገር የሚፈጠር አይመስለኝም፡፡ ቀውሱ ውስጥ ከገባን ማብቂያና መመለሻ የምናገኝ አይመስለኝም፡፡ መፍራትና መጠንቀቅ ያለብን፣ ይህቺ አገር ወደዛ ዓይነት ቀውስ እንዳትገባ ነው። አንዳንድ ሰዎች እንደዛ ዓይነት እንቅስቃሴ እንደሚናፍቁ አውቃለሁ፡፡ ግን ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ነው፡፡ ለማንኛችንም አይጠቅምም፡፡
አገራችንን እንወዳታለን ካልን፤ አገራችን ችግሯ ተፈቶ ወደተሻለ ውጤት እንድትሄድ ከፈለግን፤ የዚያ ዓይነት ቀውስና አብዮት እዚህ አገር ላይ መከሰት የለበትም፡፡ ስላልፈለግን አይመጣም ማለት አይደለም፡፡ ቀውስ እንዳይከሰት መመኘት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ የአገራችንን ዋና ዋና ችግሮች ለመፍታት መጣደፍ አለብን፡፡ የዲሞክራሲ ሂደትን ማነቃቃት፤ በሙስና የሃብት ቅርምት መኳንንትን መግታት፣ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግርን ማፋጠን ያስፈልጋል፡፡
በሌላ በኩል፤ ከዓባይ ጋር በተያያዘ፤ ከሱዳንና ግብጽ ጋር ያለው የፖለቲካ ግንኙነት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ሠላም ምን ትርጉም ይኖረዋል?
ከቅርብ ጊዜ አንፃር ካየነው፤ ኢትዮጵያ የምትሠራው ግድብ፣ ሱዳንንና ግብጽን ይጠቅማቸዋል እንጂ አይጐዳቸውም፡፡ በዚህ ረገድ፣ መንግስት የሚያራምደው አቋም እውነት ነው ብዬ እቀበላለሁ፡፡ ግድቡ እንደማይጐዳቸው እነሱም አያጡትም፡፡ ግብፅ እና ሱዳን ከኢትዮጵያ በሚሄድ የአፈር ደለል ግድቦቻቸው እየሞላ በጣም እየተቸገሩ ነው፡፡ ይሄ ችግር ይቃለልላቸዋል - ኢትዮጵያ በምትሰራው ግድብ፡፡ በክረምት ወራት በጐርፍ ይጐዳሉ፤ በበጋ ወራት ደግሞ የውሃ እጥረት ይገጥማቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የምትሰራው ግድብ፣ የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት እንጂ ለመስኖ አይደለም፡፡ ውሃው የኤሌክትሪክ ተርባይኖችን እያሽከረከረ ወደ ሱዳንና ግብጽ አመቱን ሙሉ ሳያቋርጥ ይሄዳል፡፡ ከክረምቱ ጐርፍና ከበጋው የውሃ እጥረት እፎይ ይላሉ፡፡
ውሃው በትነት እንዳይባክን በማድረግም የኢትዮጵያ ግድብ ትልቅ ጥቅም ያስገኝላቸዋል፡፡ በዚያ ላይ ሱዳንና ግብጽ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ችግር አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚመነጨው የኤሌክትሪክ ሃይል የመጠቀም እድል ይኖራቸዋል። በአጭሩ ከኢትዮጵያ ግድብ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያገኙ አይጠፋቸውም፡፡ ስለዚህ ግድቡ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን እነሱንም ይጠቅማል በሚለው አቋም የዲፕሎማሲ ጥረትን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡
ነገር ግን ስጋታቸውንም በጥልቀት ማጤን ይገባል፡፡ የእነሱ ዋነኛ ስጋት፤ ኢትዮጵያ ወደፊት በኢኮኖሚ ካደገችና እንዲህ  ትልቅ ፕሮጀክቶችን መስራት ከጀመረች ወዴት ያደርሰናል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በኢንዱስትሪ ካደገች፣ ሌሎችንም ወንዞች የመገደብና ውሃውን የመጠቀም አቅሟ ከጨመረ ምን ይፈጠራል የሚል ነው ስጋታቸው፡፡
ስለዚህ በአንድ በኩል በውሃው የመጠቀም መብታችንን እንዲቀበሉ የምንፈልገውን ያህል የእነሱንም መብት እንደምንቀበልና ጉዳት የማድረስ ሃሳብ ፈጽሞ እንደማይኖረን በቅንነት ለማስረዳት መጣር አለብን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፤ መጠርጠርና መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ እንዳናድግ አንዳንድ የተንኮል ስራዎችን አይሰሩም ብሎ መሞኘት አይቻልም፡፡ ተንኮል  ሊሠሩ እንደሚችሉ በታሪክ እናውቃለን፡፡
ዲፕሎማሲያችንን ጤናማ ማድረግ ያስፈልጋል። የነሱንም በቅንነት ለማስተናገድ መሞከር ይገባል። ነገር ግን የዲፕሎማሲ ግንኙነት፣ ላይ ላዩ እንደሚታየው ሙሉ በሙሉ ጤናማ ነው ማለት አይደለም፡፡ ይህቺ አገር እንዳታድግ፤ ዘላቂ ሠላም አንዳይኖራት ግብጽ ብዙ ነገር ስትሰራ ኑራለች፡፡ አሁን ከግብጽ በኩል ከዚህ የተሻለ አስተሳሰብ አለ ብዬ አላምንም፡፡ ስለዚህ ነገሮችን በጥርጣሬ ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ግን ደግሞ ሁልጊዜ ነገሮችን በጥርጣሬ እያየን ግንኙነቱን ይበልጥ እንዲሻክር እድል መፍጠር የለብንም፡፡ በእኛ በኩል በጐ አመለካከት መያዝና ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለእነሱም መብት እውቅና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ፣ የዲፕሎማሲውን ሚዛን ጠብቆ መጫወት ያስፈልጋል፡፡
የአባይ ውሃን መጠቀምና ግድብ መገንባቱን በተመለከተ ደስተኛ ነኝ፤ እደግፋለሁ፡፡ ግን ግድቡ የኢህአዴግ ፕሮጀክት ወይም የአቶ መለስ ራዕይ ብቻ አይደለም፤ የሚሊዮኖች ራዕይ ነው። እንደ አንድ ዜጋ የሳቸውም ራዕይ ነው፡፡ ግን የትውልዶችም ራዕይ ነው፡፡ የእኔም እና የአንቺም ራዕይ ነው፤ የአባቶቻችንና የእናቶቻችን ራዕይ ነው፡፡ ይሄን የትውልዶች ራዕይ ከአንዱ ፓርቲ ወይም ከሌላኛው ድርጅት ጋር ሳናገናኝ ሁላችንም መደገፍ መቻል አለብን፡፡
በእኔ እና በእርስዎ ትውልድ ምን ዓይነት ኢትዮጵያን አያለሁ ብለው ይገምታ?
የእኔ እና የአንቺ ትውልድ መሃል ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ወይ ከቀድሞዎቹ አልሆንም፡፡ ወይ ከመጪዎቹ አልሆንም፡፡ አስቸጋሪ ነው፡፡ ባለፉት ትውልዶች ዙሪያ የነበረ ድክመት በተወሰነ ደረጃ ተጋብቶብናል፡፡ ነገር ግን ከእነሱ የተሻለ በጐ ነገር አለን ብዬ አምናለሁ፡፡ መሃል ላይ ነን፤  ነገር ግን ለመጪው ጥሩ ዘመን የሚመጥን ደረጃ ላይ አልደረስንም፡፡
ለዚች አገር የበለጠ በጐ ነገር የምጠብቀው፤ ከእኔ እና ከአንቺ ትውልድ ሳይሆን፤ ከእኛ በታች ካለው ትውልድ ነው፡፡ በዩኒቨርስቲ፣ በኮሌጅ፣ በሃይስኩል ደረጃ ያለው ትውልድ ነው፤ የዚህችን አገር እጣ ፈንታ በዘላቂነት የሚለውጠው፡፡
ቀደም ሲል በፊውዳል ስርዓት፣ ከዚያ ቀጥሎም የግራ ፖለቲካውና የደርግ አገዛዝ የተፈራረቀባቸው ትውልዶችን አይተናል፡፡ ለዘመናት የዘለቀው ነባር ባህልና አስተሳሰብ ሁሉ የራሱ ችግር አለበት፡፡ ውጥንቅጥ  ውስጥ እንድንገባ ያደረጉንም እነዚህ ነገሮች ናቸው፡፡ በተለይ የግራ ፖለቲካ (ማርክሲዝም ሌኒኒዝም) ኢትዮጵያ ውስጥ መስፋፋቱና በደርግ አማካኝነት ለአስራ ሰባት ዓመት መንሰራፋቱ ብዙ የትውልድ አባላትን በክሏል፡፡ ከዚያ በሽታ ዛሬም አልተላቀቀንም፡፡ ከመቻቻልና ከመደማመጥ የተራራቅነው ያለምክንያት አይደለም፡፡ የተበላሸ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ስለኖርን ነው፡፡ ያ በሽታ በተወሰነ ደረጃ በእኔ እና በአንቺ ትውልድም ይታያል - ከቀድሞው ትውልድ ብንሻልም፡፡
ከኛ በታች ያለው  ትውልድ ግን ከበሽታ ነፃ የመሆን ዕድል አለው፡፡ ከመተላለቅና ከመጠላለፍ ይልቅ ነገሮችን በቀጥታ ለማየት የተዘጋጀ፣ ከቂም በቀል የፀዳ፤ ኮተት ያልተጫነበት ትውልድ እየመጣ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡  የእኛ ትውልድ ከቀድሞው ትውልድ የተጋባብን የበሽታ ቅሪት ወደ አዲሱ ትውልድ እንዳይሻገር በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦ ይኖረናል ብዬ አስባለሁ፡፡ የኛ ትውልድ ሚና ይሄ ይመስለኛል፡፡ በውርስ የመጡ በጐ ያልሆኑ ነገሮች ይሄኛው ትውልድ ላይ መቆም አለባቸው፡፡
በጐ ያልሆኑት ነገሮች ስህተት መሆናቸውን በጉልህ አውጥተን በማስተማርና ጥሩ ጥሩ ነገሮችን በማውረስ አቅጣጫውን ማሳየት ይጠበቅብናል ብዬ አስባለሁ፡፡
የጠ/ሚ አቶ ሃይለማርያምና የአዲሱ አስተዳደር አዝማሚያና ብቃት ላይ ምን ይላሉ?
አዲሱን ጠ/ሚኒስትር በግል አውቃቸዋለሁ። ፓርላማ በነበርኩበት ጊዜ እሳቸውን የማግኘትና የማናገር ብዙ እድሎች ነበሩን፡፡ በጣም በጐና ቅን ሰው እንደሆኑ በእርግጠኝነት አውቃለሁ፡፡ ቅንነት ብቻውን በቂ አይደለም ግን በጐ ሰው መሆናቸው፣ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሃላፊነታቸው ላይ የሚኖረው ቦታና አገራዊ ፋይዳውን ስናይ የራሴ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ ኢህአዴግ ስልጣኑን የማደላደል ጣጣ ውስጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አቶ ሃይለማርያም የተሻለ ነገር ለማምጣት ምን ያህል እድል አላቸው የሚለው ነገር ግልጽ አይደለም፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ፣ ለውጥ ለማምጣት ምን ያህል ፍላጐት አላቸው? ፍላጐትስ ካላቸው ምን ያህል አቅም አላቸው? አንድ መሪ በአንድ ድርጅት ወይም መዋቅር ውስጥ በአንድ ጊዜ ተደማጭነት የማግኘት እድል የለውም፡፡ ጊዜና ሂደት ይጠይቃል።
አቶ ኃይለማርያም ያንን ጊዜና ሂደት ቢያገኙ፤ የለውጥ ሃዋርያ ሆነው የተሻለ ነገር ይፈጥራሉ ወይ የሚለው ወደፊት የሚታይ ነው፡፡ እድሉን ሳያገኙ ስልጣናቸውን ሊለቁ ይችላሉ ወይም እድሉን አግኝተው የተሻለ ሁኔታ ሊፈጥሩ ይችሉ ይሆናል። ወይም እድሉን ላይጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ ለጊዜው በርግጠኝነት መናገር የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ትንሽ ጊዜ መጠበቅና ማየት ይሻላል፡፡  

Read 7170 times