Monday, 23 December 2013 09:25

“ባህላዊ” ዘፈንና ውዝዋዜ - የሚያስከብር ኩረጃ

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(12 votes)

ሺ ጊዜ የሰማናቸው ተመሳሳይ “ጥንታዊ ዜማዎችን” እና እልፍ ጊዜ ያየናቸው ተመሳሳይ “ልማዳዊ ውዝዋዜዎችን” በቴሌቪዥን እየተጋትን የት እንደምንደርስ እንጃ። ያንገሸግሻል - አዳዲስ ፈጠራዎችን መስማትና ማየት ለሚፈልግ ሰው።
“ባህላዊ”፣ “አገራዊ”፣ “ብሄረሰባዊ” .... እያልን የተለያየ ስም ልንሰጣቸው እንችላለን። ግን፣ ስያሜ ስለተቀየረላቸው ብቻ፣ አዲስ ፈጠራ አይሆኑም። ያው ጥንታዊና ልማዳዊ ናቸው።
ተራው ሰው፣ ነሸጥ ሲያደርገው ለጨዋታና ለመግባቢያ፣ በየአጋጣሚውም ሰርግና ልደት ለመሳሰሉ ድግሶች ማድመቂያ፣ ጥንታዊዎቹን ዜማዎች ቢያንጎራጉር፣ ልማዳዊዎቹን ውዝዋዜዎች ቢጨፍር ተገቢ ነው። ሙያው አይደለማ። ሙያው ያልሆነ ሰው ደግሞ፣ ከጥንት የወረሰውን ዜማ ከማንጎራጎርና በልማድ የተረከበውን ውዝዋዜ ከመድገም ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም።
ለ“ኪነጥበብ ባለሙያ” ወይም ለ“አርቲስት” ግን፣ አይመጥናቸውም። እንደተራ ሰው ጥንታዊውን ዜማና ልማዳዊውን ውዝዋዜ እየኮረጁ መኖር፣ ከኪነጥበብ ሰው አይጠበቅም። የድሮ ፈጠራዎችን መኮረጅ፣ መደበኛ የዘወትር ስራቸው መሆን የለበትም። ሙያውን አሳንሶ ክብሩን እንደማሳጣት ነው የሚቆጠረው። ደግሞስ፣ የኪነጥበብ ሰዎች አዲስ ዜማና ውዝዋዜ ካልፈጠሩ፣ ማን ሊፈጥር ይችላል? አብዛኞቹኮ የኩረጃ ውድድር ውስጥ የገቡ ነው የሚመስሉት።
ለማጅ ድምፃዊያን፣ የሌላ ሰው ዜማ እየዘፈኑ ቢወዳደሩ አይገርምም። ጀማሪ የidol ተወዳዳሪዎች፣ በየተራ እየመጡ ቴዎድሮስ ታደሰ የተጫወታቸውን ዜማዎች እያንጎራጎሩ ይወዳደሩ የለ? ግን እድሜ ልክ እየኮረጁ ለመቀጠል አይደለም። ቀደምት የፈጠራ ሥራዎችን ከማድነቅ ተነስተው፣ ከዚያም ላይ ተምረውና ልምድ ቀስመው፣ ወደፊት የራሳቸው ጥበብ መፍጠር ይችሉ እንደሆነ ለማየት ነው የሚወዳደሩት። አርቲስት የመሆን ተስፋ እንዳላቸውና እንደሌላቸው ለማወቅ ነው፣ የሌላ ሰው ዜማ በመዝፈን የሚወዳደሩት። ገና አርቲስት ስላልሆኑ፣ አዲስ ፈጠራ ማቅረብ አይችሉማ።
ታዲያ፣ በምን ሂሳብ ነው፣ ጥንታዊ ዜማዎችንና ልማዳዊ ውዝዋዜዎችን እየኮረጁ ማቅረብ፣ የአንጋፋና የታዋቂ አርቲስቶች መደበኛ ስራ የሚሆነው? በኢቲቪ የሚቀርቡ አዳዲስ የሙዚቃ ክሊፖችኮ፣ በአብዛኛው የጥንታዊ ዜማና የልማዳዊ ውዝዋዜ ኩረጃዎች ናቸው። ቅድም እንዳልኩት፣ “ባህላዊ” ዜማ፣ “አገራዊ” ዘፈን፣ “የብሄር ብሄረሰብ” ጭፈራ... የሚሉ ስያሜዎች ሊያጣሉን አይገባም። ዋናው ቁምነገር፣ የጥንት አርቲስቶች ፈጠራ እንጂ፣ የዛሬ አርቲስቶች ፈጠራ አለመሆናቸው ነው።
በእርግጥ፣ አንዳንዴ ከጥንታዊው ዜማ በመነሳት፣ አዳዲስ ፈጠራዎችን የሚያቀርቡ አርቲስቶች መኖራቸው አይካድም። ሙሉቀን፣ አስቴር አወቀ፣ ጌታቸው ካሳ፣ ስለሺ ደምሴ እና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል። ግን፣ ኢቲቪ “የባህል ዘፈን” ብሎ የሚያቀርብልን፣ የእነዚህ ድምፃዊያን ስራዎችን አይደለም።
“የባህል ዘፈን” የሚል “ክብር” በአብዛኛው ከጥንት ተኮርጆ የተሰራ መሆን አለበት። ኩረጃ ሲያስከብር ይታያችሁ። የጥንቱ ዜማ ብዙም አይቀየርም። ለነገሩ የዘፈኑ ግጥምም ከድሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ መሆን አለበት። አለባበስና አጨፋፈርም እንዲሁ፣ በልማድ የተወረሰ መሆን ይኖርበታል። ጨዋታው ያለው ምን ላይ ነው? እንዲያው ለስሙ ሌጣ ኩረጃ እንዳይሆኑ፣ ላይ ላዩን መቀባባት፣ እዚህና እዚያ መከርከም፣ ከጫፍና ጫፍ ማበጠር ብቻ ነው። ከሳር ጎጆ ሳንላቀቅ፣ አንዴ ከሳሩ አናት ላይ የእንስራ ገል በማስቀመጥ፣ ሌላ ጊዜ የጎጆዋን ድንክዬ በር ወደ ደቡብ አቅጣጫ በማዞር፣ ወይም በዙሪያዋ ቅል በማንጠልጠል፣ “አዲስ የቤት አሰራር ፈጠራ አመጣሁ” ብሎ እንደመኩራት ቁጠሩት። እንዲህ እያልን፣ የእንስራ ስባሪውን የምናስቀምጥበትና ቅሉን የምናንጠለጥልበት ቦታ ማለቁ ይቀራል?  እስከ መቼ ያዛልቃል?
የጥንታዊዎቹ ዜማዎችና የልማዳዊ ውዝዋዜዎች ላይ የሚቀባው፣ የሚከረከመውና የሚበጠረው ነገርስ ተንጠፍጥፎ አያልቅም? ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያለቀ የመጣ ቢመስልም፣ ልንለቃቸው ፈቃደኛ አይደለንም። ብዙ አርቲስቶች፣ በድሮው ላይ አንዳች የምትቀባ ነገር ለማግኘት መከራቸውን ያያሉ። ለአዲስ ፈጠራ ከመነሳሳት ይልቅ፣ ነባሩን አንጠፍጥፎና አሟጥጦ ለመጠቀም መሻማት ይሉሃል ይሄ ነው።
የአማርኛ፣ የትግርኛ፣ የኦሮሚኛ፣ የጉራጊኛና መሰል ጥንታዊ ዜማዎችና ልማዳዊ ውዝዋዜዎች ላይ፣ ከጎንና ጎን እየቆረጡ በመቀጠል፣ ከራስጌና ከግርጌ እየቀባቡ፣ እያፈጠኑና እያረገቡ፣ እያጯጯሁና እያርገበገቡ... ያቀረቡልንን የኩረጃ ስራ ለበርካታ አመታት አድምጠናል፤ ተመልክተናል። ኩረጃው ከመብዛቱና ከመደጋገሙ የተነሳ፣ ከእንግዲህ በእነዚህ ዜማዎችና ውዝዋዜዎች ዙሪያ፣ በቀላሉ ቀባብቶ የመኮረጅ እድል እየተሟጠጠ መጥቷል። ለዚህም ይመስላል፤ የባለፉት አምስት አመታት የደቡብ ክልል ጥንታዊ ዜማዎችና ልማዳዊ ውዝዋዜዎች ላይ ሰፊ ዘመቻ የተካሄደው። በእርግጥም፣ ለተወሰነ ጊዜ ትኩረትን የሚስቡ የኩረጃ ፈጠራዎችን ለማየት ችለናል። አሁን እንደምታዘበው ከሆነ ግን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ድግግሞሽ እየበረከተ፣ ስራዎቹ ለዛ እያጡ፣ ለቅምሻ ያህል እንኳ የፈጠራ ምልክት እየራቀቸው ነው። ቢሆንም፤ ኩረጃው መቀጠሉ አይቀርም - እንጠፍጥፎና አሟጥጦ ለመጠቀም!

በአረንጓዴ ቁምጣ ምትክ ሃምራዊ ቁምጣ
ትዝ ይላችሁ እንደሆነ፣ ከጥቂት አመታት በፊት በሚቀርቡ የአማርኛ “ባህላዊ” ጨዋታዎች ላይ፣ የወንድ ተወዛዋዦች ልብስ በአብዛኛው የሸማ ወይም የአቡጀዲ ልብስ ነበር - ጥብቆ፣ ተነፋነፍ፣ እጀ ጠበባ ወዘተ...። አሁን ያ በሌላ ተቀይሯል። በቲሸርትና በሱሪ፣ በሸሚዝና በቁምጣ... አንዳንዴም በጂንስ ሆኗል። ከዚህም ጋር ነው፣ የገጠር ሰዎችን ውዝዋዜ ቀርፆ የማሳየት ፈሊጥ ብቅ ያለው። ውዝዋዜው ሳይቀየር፣ አለባበስና የተወዛዋዦቹ ማንነት ስለተለወጠ ብቻ፣ እንደ አዲስ ፈጠራ ነበር የታዩት። ከጀማሪዎቹ መካከልም “ባላገሩ” በሚል ስያሜ የቀረቡ ክሊፖች በምሳሌነት የሚጠቀሱ ይመስለኛል። በእርግጥም፤ ያኔ ስናያቸው የነበሩ የሸማ አለባበሶች፣ ገጠር ውስጥ ተረት ሆነው የቀሩት ገና ድሮ ነው። የ“ባላገሩ” ክሊፖች፣ የገጠር አለባበስ እንደተቀየረ የገባቸው ይመስላል። የገጠር ነዋሪዎች ጭፈራ ማካተቱም፣ ነገሩን በደንብ እንድናየውና ጥያቄ እንድናነሳ እድል ይሰጣል። ለምን በሉ።
የገጠር ጎረምሳና ኮረዳ አሳምረው የሚወዛወዙ ከሆነ፣ የነሱን ኮርጆ የሚወዛወዝ ከተሜ ለምን “አርቲስት” ወይም “የኪነጥበብ ባለሙያ” የሚል ማዕረግ ይሰጠዋል? በእርግጥ የገጠሮቹ ወጣቶችም፣ ከአባት ከእናት ኮርጀው ነው። ነገር ግን፣ የገጠሮቹ ወጣቶች በሙያ ገበሬዎች ናቸው። አርቲስት ነን አይሉም። ታዲያ፣ ጥንታዊውን ውዝዋዜ ከወላጆቻቸው የኮረጁ የገጠር ወጣቶች፣ “ተወዛዋዥ አርቲስት ወይም የዳንስ ባለሙያ” ካልሆኑ፣ ውዝዋዜያቸውም እንደ ፈጠራ የማይታይ ከሆነ፣ እንዴት ነው የኩረጃ ኩረጃ እንደ ፈጠራ ስራ የሚቀርብልን - ለዚያውም በውዝዋዜ አርቲስቶች፣ በፕሮፌሽናሎች።
እውነት ለመናገር፣ የገጠር ገበሬ ውዝዋዜና የከተሜ አርቲስት ውዝዋዜ “በአቀራረብ” ይለያል። አርቲስቶች ያመጡት ለውጥ ምን መሰላችሁ? አንደኛውና ደምቆ የሚታየው ልዩነት፣ የልብስ ቀለም ነው። ከገጠር ወጣቶች በተለየ ሁኔታ፣ ፕሮፌሽናል ተወዛዋዦች አለባበስ የተዘበራረቀ አይደለም። እንደዩኒፎርም ነው ልብስ አሰፍተው የሚለብሱት - “ባህላዊ ልብስ” መሆኑ ነው።
እንዲያም ሆኖ “ባህላዊ” ወይም “ልማዳዊ” የሚባሉ የልብስ አይነቶችን በሙሉ አይተን የጨረስን ይመስለኛል። “አዲስ ፈጠራ” የምናይ ከሆነ ከልብስ የቀለም ለውጥ አያልፍም። አረንጓዴ የነበረው የተወዛዋዦች ቁምጣ፣ በሌላ ዘፈን በሃምራዊ ቀለም የደመቀ ቁምጣ ሆኖ ይመጣል። በዛጎል ጥለት የተሸፈነ ጉርድ ሸሚዝ ውልቆ፣ በረድፍና በመስመር የልብስ ቁልፎችን የተዥጎረጎረ ጉርድ ሸሚዝ ይለበሳል። በባለ ቢጫ ሸንተረሩ ሰማያዊ ቲሸርት ምትክ፣ ቀይ ሸንተረሮች የተጋደሙበት አረንጓዴ ቲሸርት ተተክቷል። በ“ባህላዊ” የዘፈን ክሊፖች ላይ የምናየው “አዳዲስ ፈጠራ”፣ ከጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችና ከልብስ ሰፊዎች የቀለም ግዢ ብዙም አይለይም።
በአጠቃላይ፣ “ባህላዊውን እስክስታ”፣ “አገራዊውን ውዝዋዜ” ወይም “የየብሄረሰቡን ጭፈራ”…  በአብዛኛው ከየአይነቱ እልፍ ጊዜ በተደጋጋሚ ብናይም፤ “ይብቃችሁ” የሚል አላገኘንም። ያንኑ ተመሳሳይ እስክስታ በሌሎች ተወዛዋዦች፣ ተመሳሳይ ውዝዋዜ ከሌላ ዘፋኝ ጋር፣ ተመሳሳይ ጭፈራ በሌላ ጊዜ እየተደጋገመ መምጣቱ አላቆመም። “ተመሳሳይ ቢሆንም አዳዲስ ነገሮችን ይዘው የሚመጡም ይታያሉ” የሚል ሰው ካለ አልተሳሳተም።
እጃቸውን ወገባቸው ላይ አሳርፈው፣ ወይም ዱላ ጨብጠው፣ አልያም የመቀነት ጫፍ ይዘው ሲወዛወዙ የነበሩ ባለሙያዎች፣ በሌላ ዘፈን እጃቸውን የቁምጣ ኪሳቸው ውስጥ አስገብተው ያንኑን ተመሳሳይ ውዝዋዜ ይደግሙታል። አልፎ አልፎ፣ ጉልበት ጨምረውበት ሲወዛወዙ አቅርቦ የሚያሳይ ቀረፃም ይመጣል። ጉልበት እየጨመሩ፣ ውዝዋዜውን ወደ መንገጫገጭና መንፈራገጥ እያመዘነ መሄዱ፣ “ጥሩ ፈጠራ ነው” ያስብለዋል ብዬ ግን አላምንም። ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሴት ተወዛዋዦች ይልቅ ወንድ ተወዛዋዦች እየበረከቱ የመጡትም በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
አሁን አሁንማ፣ እጅ ኪስ ውስጥ አስገብቶ ወይም በጉልበት እየተወራጩ መወዛወዝን የመሳሰሉ “ፈጠራዎችም”ቀስ በቀስ እየተሟጠጡ ሳይሆኑ አይቀርም። የተወዛዋዦቹን ቁጥር ማብዛትና ማሳነስምኮ ራሱን የቻለ አዲስ ፈጠራ ነው ካላልን በቀር ማለቴ ነው። ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ሁለት የተለመዱ የውዝዋዜ አይነቶችን አቀላቅሎ ማቅረብስ አዲስ ፈጠራ ነው? መሞከር አይከፋም። ግን፣ በአንዳች ዘዴ ሁለቱን ልማዳዊ ውዝዋዜዎች አዋህዶ ወይም አቀናብሮ፣ አንዳች አዲስ ትዕይንት ካልፈጠረ በቀር፣ ሺ ጊዜ በየተራ ያየናቸውን ጥንታዊ ውዝዋዜዎች ማዶ ለማዶ አስቀምጦ ቢያፈራርቅብን ምን ዋጋ አለው? እሺ ዋጋ ይኑረው። ለ1001ኛ ጊዜ ውዝዋዜዎቹን ማየት፣ የራሱ የሆነ ዋጋ ይኖረዋል እንበል። ነገር ግን አዲስ ፈጠራ ነው ተብሎ፣ እውቅና የሚጠየቅበት ሊሆን ይችላል?     
ከእለት ተእለት ብቻ ሳይሆን፣ ከአመት አመት የጥንት ዜማዎችን መስማት፣ ልማዳዊውን ጭፈራ የሚያስነኩ ተወዛዋዦችን ማየት አይሰለችም? ከአመት አመት የማይቀየር ነገር ማየት፣ ከማሰልቸትም አልፎ የመታፈን ስሜትንም ሊፈጥር ይችላል። አገሪቱ፣ አንዳች የጊዜ ስንጥቅጥ ውስጥ ተቀርቅራ፣ በህልም ሩጫ ውስጥ ያለመፈናፈኛ፣ እንደ ነባሩ ጭፈራ ባለችበት ቦታ  እየረገጠችና እየተንፈራገጠች የምትባክን አትመስልም? ለዚያውም፣ በተመሳሳይ አለባበስ (አብዛኛውን ጊዜ ወደ ጎን ተሰልፈው)፣ ለዚያውም በተመሳሳይ ቦታ (አብዛኛውን ጊዜ ገጠር ውስጥ አረም በወረረው ቦታና ከሳር ጎጆ አጠገብ) ነው ዘፈኖቹና ውዝዋዜዎቹ የሚቀርቡት። እንዲያው ስታስቡት፣ በዛሬው ዘመን የገጠር ኑሮን ማሞካሸትና የሳር ጎጆን ማሞገስ ምን ያደርግልናል?

የሳር ጎጆንና ሽሮን የመናፈቅ ወግ
የገጠር ወጣቶችኮ፣ ኑሮ እያማረራቸው ነው ወደ ከተማ የሚጎርፉት። ወደ ገጠር የሚፈልስ የከተማ ወጣትስ አለ? የለም። ታዲያ ለምንድነው ከተሜ ኢትዮጵያውያን ገጠርን የሚያሞካሹት? ገጠር ሄደው መኖር አይፈልጉም። ወደ ገጠር ከሄዱም፣ የሙዚቃ ክሊፕ ቀርፀው ለመመለስ ነው።
ገጠሬው በዚህም ብሎ በዚያ፣ ከብትና ሰው ተፋፍጎ የሚያድርባትን የሳር ጎጆ፣ በባለ መስኮት ክፍሎች ለመቀየር፣ የሳር ጣራውን በቆርቆሮ ለመቀየር ደፋ ቀና ይላል።
ወገኞቹ ከተሜዎችስ? ከተማ ውስጥ የሳር ጎጆ አስመስለው ለመስራት ይሞክራሉ። ወይም ደግሞ፣ የሳር ጎጆ አጠገብ በአረም የተወረረ ቦታ ላይ ይዛወዛሉ። “እንደ ሽሮ የምወደው ምግብ የለም” ብሎ ከሚናገር ወገኛ ዳያስፖራ ምንም ልዩነት የለውም።
የድሮ ዘፋኞች፣ የህንፃ ጣሪያ ላይ፣ ቪላና ሳሎን ቤት  ወይም መናፈሻ ውስጥ ብቻ ነው ክሊፕ የሚሰሩት እየተባሉ ሲተቹ ትዝ ይለኛል። እና አሁን፣ የሳር ጎጆ አጠገብ መወዘወዝና በአረም የተወረረውን ማሳ እየረገጡ መጨፈር ይሻላል? ብዙ ክሊፖች ላይ የምናየው ይሄው ነው። አለበለዚያ ደግሞ፣ አስፋልት መሃል ላይ ሲወዛወዙና ሲዘፍኑ። አስፋልት መሃል፤ ከመኪና ጋር እየተጋፉ! በየቀኑ ስለመኪና አደጋ የሚለፈልፉት እነ ሳጅን፣ አደጋውን ለመቀነስ አለመቻላቸውና ድካማቸው ከንቱ መሆኑ ምኑ ይገርማል?

ማንነትና ፈጠራ የነጠፈበት ኋላቀር ባህል
በዚህ ጉዳይ ላይ ሌላ ወገኛ መከራከሪያ መቅረቡ አይቀርም። “የባህል ዘፈኖቻችን” እና “የብሄረሰብ ጭፈራዎቻችን”፣ “ቋንቋዎቻችን”... የማንነታችን መገለጫ ናቸው፤ ከእነሱ ውጭ ማንነትና ህልውና የለንም... ብሎ የሚከራከር ሰው አይጠፋም። ወገኛ በሉት። የገጠርወጣቶች ህይወታቸውን ለማሻሻል ወደ ውጭ አገራት የሚሰደዱት፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የከተማ ወጣቶች ዲቪ የሚሞሉት ለምን ይመስላችኋል? አማርኛ ወይም ትግርኛ፣ ኦሮሚኛ ወይም ጉራጊኛ፣ ሱማሊኛ ወይም ሲዳምኛ፣ አፋርኛ ወይም ወላይትኛ ፈለጋ ነው አሜሪካ ለመሄድ መቶ ሺ ብር የሚከፍሉት? ጥንታዊ ዜማና ልማዳዊ ጭፈራ ለማግኘትና በባህርና በበረሃ ወደ አረብ አገራት የሚሰደዱት? የኑሮ መተዳደሪያ ለማግኘትና በዚህም፣ ህልውናቸውን ለመጠበቅና ማንነታቸውን ለመገንባት ነው።
ለነገሩ፣ ጥንታዊ ዜማና ልማዳዊ ውዝዋዜ ላይ ሙጭጭ ብሎ ኩረጃን እንደጣኦት ማምለክ፣ አገርንና ባህልን ማክበር ሳይሆን፣ መናቅ ነው። አዲስ ፈጠራ የማያፈልቅ አገርና ባህል ምኑ ይከበራል?
መቼም እነዚያ ጥንታዊ ዜማዎችና ውዝዋዜዎች ከእነ ሉሲ ጋር አብረው የተፈጠሩ አይደሉም። ከምድር የበቀሉ ወይም ከሰማይ የወረዱም አይደሉም። የሆኑ ምርጥ የፈጠራ ሰዎች፣ የሆኑ ኢትዮጵያውን ድንቅ ጥበበኞች ናቸው ዜማዎቹንና ውዝዋዜዎቹን የፈጠሯቸው።
ከነሱ በፊትም ዜማና ውዝዋዜ እንደነበረ አያጠራጥርም። ግን የድሮውን በመኮረጅ እዚያው እየረገጡ እድሜያቸውን የሚጨርሱ አይነት ደካማ ሰዎች አልነበሩም ማለት ነው። አዳዲስ ፈጠራዎችን የሚያፈልቅ የተከበረ አገርና ባህል ነበራቸው ማለት ነው። ያንን ክቡር ባህልና አገር መጠበቅ የሚፈልግ ሰው፣ የድሮዎቹን ፈጠራዎች እያደነቁ እንደነሱ በተራው አዳዲስ የጥበብ ፈጠራዎችን ያመነጫል። ቢያንስ ቢያንስ ደግሞ የሚያመነጩ ፈጣሪዎችን ያበረታታል። ካልሆነም የፈጠራ ስራዎችን ለማየት ይመኛል።  
እንዴት መሰላችሁ? ሰውን ከዋሻ ኑሮ ያላቀቀ የሳር ጎጆ፣ በአፈታሪክ ብቻ ከመምታታት ሊገላግል የሚችል የብራና ላይ ፅሁፍ፣ አፈር ላይ ከመንከባለል የሚያድን ባለሶስት እግር በርጩማ... እነዚህ ሁሉ የጥንት ዘመን ምርጥና ድንቅ ፈጠራዎች ናቸው። ጎጆ፣ ብራና ወይም በርጩማ ላይ ሙጭጭ ብለን ከቀረን፣ ጥንታዊዎቹን የፈጠራ ሰዎችና ባህላቸውን እንደማዋረድ ነው የሚቆጠረው። እንደነሱ አዳዲስ ፈጠራዎችን የሚያፈልቅ ባህልና አገር የለንም ማለት ነው።
የጥንት አባቶቻችን ባህል፣ አዳዲስ ፈጠራዎችን የሚያፈልቅ የስልጣኔ ባህል ሲሆን፣ የኛ ባህል ግን ከኩረጃ ባሻገር መመልከት የተሳነውና ፈጠራ የነጠፈበት ኋላቀር ባህል ሆኗል።   
ነገሩ ሌላ ተጨማሪ ገፅታም አለው። በዜማና በውዝዋዜ ጥበብ ላይ ለፈጠራ መሟጠጥ ትልቁ መንስኤ፣ የኋላቀርነት ባህል ቢሆንም፣ ኢቲቪም ትልቅ ድርሻ አለው። አንድም “አገራዊና ልማታዊ” አልያም “ባህላዊና ብሄረሰባዊ” የሙዚቃ ክሊፖችን ነው በብዛት የሚያስተናግደው። አማራጭ ያጣ አርቲስት ሁሉ፣ ኢቲቪን ለማስደሰት “ጥንታዊ ዜማ”ና “ልማዳዊ ውዝዋዜ” ላይ ቢረባረብ አይገርምም። 

Read 4754 times