Saturday, 14 December 2013 13:31

የኢትዮጵያ ፓርቲዎች፣ የሚያጣላ ነገር ሳያጡ በማንዴላ ይጣላሉ

Written by  ዮሐንስ ሰ
Rate this item
(6 votes)

              ኔልሰን ማንዴላን ካደነቅን አይቀር፣ አርቆ አስተዋይነታቸውንና የሰከነ አስተሳሰባቸውን እንዲሁም ለራሳቸውና በአጠቃላይ ለሰው ልጅ  ያላቸውን አክብሮት በመገንዘብ መሆን አለበት፡፡ አልያ አድናቆታችን ትርጉም የለሽ የወገኛ ትዕይንት ይሆናል፡፡
ከ25 ዓመት በፊት የነበረው የደቡብ አፍሪካ ሁኔታ፣ በቀለሙና በመጠኑ ይለያይ እንደሆነ እንጂ በመሠረታዊ ባህሪው በአብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ከሚታየው ውስብስብ የኋላቀርነት ችግርና መከራ የተለየ አይደለም፡፡ ካልተሳሳተው ይልቅ የተሳሳተው፣ ጥፋት ካልፈፀመው ይልቅ ጥፋት የፈፀመው የሚበዛበት አገር ውስጥ ምን ማድረግ ይቻላል? የኋላቀርነት ጣጣና መዘዝ እንዲህ ውስብስብ ነው፡፡ በየተራ አሳዳጅና ተሳዳጅ፣ በፈረቃ አሳሪና ታሳሪ፣ ካልሆነም በግርግር መተራመስና በዘፈቀደ መተላለቅ የሚዘወተርበት የአገር ባህልና የፖለቲካ ቀውስ ማቆሚያው የት ነው?
አንዱ ዘረኛ ተነስቶ፣ ሰዎችን በቋንቋ ወይም በዘር ሀረግ እየፈረጀ ግፍ ይፈጽማል፡፡ ግፍ የደረሰበት ሰውዬ ደግሞ፤ ግፍ የፈፀመበትን ሰው ለይቶ አፀፋ መመለስ አይሆንለትም፡፡ “የእገሌ ወገን” በድሎኛል በሚል የጅምላ ፍረጃ፣ በጭፍን ስሜት ጦር ይወዘውዛል፡፡ ወዝውዞም አይቀርም፡፡ አጠገቡ ያልደረሰ ሌላ ሰው ላይ ጥቃት ይሰነዝራል፡፡ አዙሪቱ ይቀጥላል፡፡ በአንድ በኩል አምባገነንነት፣ በሌላ በኩል አሸባሪነት፣ እርስበርስ አንዱ ሌላውን እያጦዘ፤ አብዛኛውንም ህዝብ ወደጥላቻ ማጥ እየገፉና እየጐተተ አገሬው በሙሉ እንዲጨማለቅ ያደርጋል፡፡ አብዛኛው ሰው ግፈኛና ተገፊ ይሆናል፡፡ የአንዱ ሰው ጥቃትና ጉዳት ከሌላው ሰው የባሰና የከፋ፣ የበዛና የመረረ መሆኑ ባይቀርም፤ ለጥፋት እጁን ያልሰነዘረ ሰው ማግኘት እስኪያስቸግር ድረስ፣ ከዳር እስከ ዳር አገር ይታመሳል፡፡ መያዣ መጨበጫ ለሌለው ለእንዲህ አይነቱ ቀውስ እንዴት ተደርጐ ፈውስ ይገኝለታል?
የኔልሰን ማንዴላ ትልቅነት ገዝፎ የሚታየው፤ እዚህ ላይ ይመስለኛል፡፡ ዘላቂው መፍትሔ፣ የእያንዳንዱ ዜጋ መብት እንዲከበር ማድረግ መሆኑን አውቀዋል፡፡ በቆዳ ቀለምና በተወላጅነት ወይም በቋንቋና በቀዬ፣ ሰዎችን በጅምላ የመፈረጅ ዘረኝነት ተወግዶ፣ እያንዳንዱ ሰው በግል ድርጊቱና በባህርይው የሚመዘንበት ስልጡን አስተሳሰብን ጨብጠዋል ማንዴላ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡
እያንዳንዱ ዜጋ የራሱን ህይወት በነፃነት የመምራት መብቱ የሚከበርበት ፍትሃዊ የፖለቲካ ስርዓት መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገብቷቸዋል፡፡ በአጭሩ ስልጡን አስተሳሰብ የሰፈነበት ማህበረሰብና የህግ የበላይነት የተከበረበት አገር መፍጠር ነው ዘላቂው መፍትሔ፡፡ በእርግጥ ቀላል አይደለም፤ የረዥም ጊዜ ጥረትን የሚሻ ፈታኝ ስራ ነው፡፡ ፈተናው ግን ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ለአመታት ሲከመር ለቆየው የኋላቀርነት ጣጣ አንዳች እልባት ካልተዘየደለት ወደፊት የመራመድ ዕድል አይኖርም፡፡
ስልጡን አስተሳሰብ ባላያቸውና ዘረኝነት በነገሰባቸው በርካታ አመታት፤ የህግ የበላይነት ባለተፈጠረባቸው የአምባገነንነትና የሽብር ዘመናት፤ በየመስኩ የተፈፀሙ ግፎችንና የተፈለፈሉ የጥላቻ ስሜቶችን ምን ብናደርጋቸው ይሻላል?
አበበ ከበደን ደበደበ፡፡ ከበደ ደግሞ በቂም በቀል፣ የአበበ ጐረቤት የሆነውን ደረጀን ፈነከተ፡፡ ደረጀ በአፀፋው የከበደ ሰፈር ጋ ሄዶ፣ የከበደን ሳይሆን የደበበን ቤት አቃጠለ፡፡ በቃ፣ አብዛኛው  ሰው ተነካክቷል፡፡ አገሬውን ሁሉ መክሰስና ማሰር አይቻልም፡፡ በፈረቃ፣ ከአንደኛው መንደር የተወሰኑ ሰዎች ተቧድነውና አጋጣሚ ጠብቀው፣ በጭፍን ስሜት የሁለተኛውን መንደር ሰዎች እየወነጀሉ ቢያሳድዱ መፍትሔ አይሆንም፡፡ ከሁለተኛው መንደር የተወሰኑ ሰዎች ስልጣን ሲይዙ ደግሞ በተራቸው በሌላኛው መንደር ላይ ይዘምታሉ፡፡ ይሄ ግን፣ ከተለመደው የጥንቱ ቀውስ የተለየ አይደለም፣ እናም የሚለወጥ ነገር አይኖርም፡፡
“ከዚያ ይልቅ፤ በዚያ ክፉ ዘመን እጅግ የከፋ ወንጀል የፈፀሙትን ሰዎች ብቻ በመደበኛው የህግ ስርዓት በመቅጣት፤ ሌሎቻችን  ይብዛም ይነስ በዳይ እና ተበዳይ ስለሆንን፤ ጥፋታችንንና ጉዳታችንን ተገንዝበን፤ ይቅርታ ተጠያይቀን፤ ከቀውስ አዙሪት እንውጣ፤ ያለፈው የኋላቀርነት ምዕራፍ ይዘጋ፡፡ መጪውን ዘመን በስልጡን አስተሳሰብ እንክፈተው፡፡ የየራሳችንን ህይወት ሳናስነካ በነፃነት ለመምራት፣ የያንዳንዱን ሰው መብትም ሳንነካ ለማክበር ቃል እንግባ፡፡ ለቃላችን ዋስትና የሚሆን፣ የህግ የበላይነትና የሰፈነበት የመብት ማስከበሪያ ስርዓት እንፍጠር…” ይሄ ነው የኔልሰን ማንዴላ መንገድ፡፡
ላለፈው ዘመን ስህተቶችና ጥፋቶች መቋጫ የሚያበጅ፤ የወቅቱን ችግሮች የሚያቃልል፤ የወደፊቱን ጐዳና የሚጠርግ መፍትሔ ማቅረብ… እውነትም የማንዴላ የሰከነ አስተሳሰብን፣ አርቆ አስተዋይነትንና ሰው የመሆን ክብርን ይመሰክራል፡፡ “በእስካሁኑ ኋላቀር አስተሳሰብና ባህል፣ ብዙዎቻችን ተሳስተን አጥፍተናል፡፡ ዛሬ ለትናንቱ የጭፍን ጥላቻና የመጠፋፋት መርዝ ማርከሻ እንፍጠር፡፡ ከእንግዲህ እንዳንሳሳትና እንዳናጠፋ ለወደፊት የሚያዛልቅ ሁነኛ መላ እንዘይድ” …እንዲህ አይነቱ የመሪነት ብቃት በክብር ቢደነቅ፣ ይገባዋል፡፡ የዛሬን ተግባርና የነገን አላማ፤ ፍቅርንና ህግን፤ ይቅርታንና መብትን ያዋሃደ፤ የህዳሴና የአገራዊ መግባት መፍትሔን ነው ማንዴላ የፈጠሩት - ብልሃተኛና ጥበበኛ መፍትሔ፡፡
ለነገሩ ስለ ማንዴላ ብዙ ሃተታ ማቅረብ ላያስፈልግ ይችላል፡፡ አብዛኛው ሰው፤ የአገራችን ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች ጭምር፤ ለኔልሰን ማንዴላ ባላቸው አድናቆት ይስማማሉ፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው? የማንዴላን አርአያነት የሚያደንቁ ፖለቲከኞችም ሆኑ ፓርቲዎች፤ አድናቆታቸውን የሚገልፁት ያንኑ የሚያደንቁትን ነገር በሚያፈርስ መንገድ ነው፡፡ የአገራችን ፓርቲዎች፣ ኔልሰን ማንዴላን በማክበር አድናቆታቸውን የሚገልፁት፤ “በኋላቀር አስተሳሰብና ባህል ሳቢያ፤ ብዙዎቻችን ተሳስተን አጥፍተናል” በሚል ስክነትና አስተዋይነት አይደለም፡፡ እርስ በርስ በስሜታዊነት መወነጃጀላቸውን አያቆሙማ፡፡ ከኋላቀርነት አዙሪትም አይወጡም፡፡  ወደፊት እንዳይሳሳቱና እንዳያጠፋ ቃል በመግባት “የእያንዳንዳችንን መብት የሚያስከብር የነፃነት ስርዓት እንገንባ” በሚል ራዕይ ሳይሆን፤ የመጠፋፋት አባዜን በሚያነሳሳ ንግግር ነው የማንዴላን የመታሰቢያ በዓል የሚያከብሩት፡፡
የአገራችን ፓርቲዎች፤ “አይ እኛ እንዲህ አይደለንም” የሚሉ ከሆነ፤ ሁሉም ፓርቲዎች፣ ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች በሙሉ፣ እንስማማበታለን በሚሉት የማንዴላ አድናቆት ዙሪያ በመሰባሰብና በጋራ የመታሰቢያ በዓል በማክበር ሊያሳዩን ይችሉ ነበር፡፡
 


Read 1516 times