Saturday, 14 December 2013 13:09

በጅግጅጋ ከተማ የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ያቋቋመው የ33 ዓመት ወጣት

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(13 votes)

“ሥራ ህይወት ያለው ነገር ነው፤ ካላከበርከው ያዝናል፤ ይታዘብሃል”
የፌዴሬሽን ም/ቤት በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ዋና ከተማ በጅግጅጋ በተከበረው 8ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል ላይ እንድንገኝ ባደረገልን ግብዣ መሠረት ባለፈው ሳምንት በደማቅ ሁኔታ የተጠናቀቀው በዓል ተሳታፊ ነበኩር፡፡ እግረ መንገዴን ዋና ከተማዋን ስቃኝ ለሥራ፣ ከፍተኛ ክብርና፣ የተለየ አመለካከት ያለው ወጣት ኢንቨስተር አገኘሁ፡፡
“እኛ አልተረዳነውም እንጂ፣ ሥራ ሕይወት ያለው ነገር ነው፡፡ ሥራን ንቀን እንዳልባሌ ነገር ስንቆጥረው ይታዘበናል፣ ይከፋል፣ ያዝናል፡፡ “የዘራኸውን ነው የምታጭደው” እንደሚባለው ሁሉ፣ ምላሹም መጥፎና የከፋ ይሆናል፡፡ ስናከብረው ደግሞ ይስቃል፣ ይደሰታል፣ … ሥራውን ያከበረ ሰው ካሰበው ይደርሳል፤ እኔ ሥራዬ  ጓደኛዬ ነው” ይላል ወጣቱ ኢንቨስተር አሚር ሙክታር አብዱራህማን፡፡
በጅግጅጋ ከተማ ተወልዶ ያደገው አሚር፤ የ33 ዓመት ወጣት ሲሆን እስከ 12ኛ ክፍል ተምሯል፡፡ ትምህርት ላይ ጐበዝ እንደነበር የሚናገረው አሚር፤ ጉርምስና ሲጀምረው ለትምህርት ብቻ የነበረውን ሐሳቡን ብዙ ነገሮች ይጋሩት ጀመር፡፡ ከትምህርት ቤት እየጠፋ (እየፎረፈ) መቅረት ሲያበዛ ውጤቱም እንደዚያው ማሽቆልቆል ጀመረ፡፡ ከዚያስ ምን አደረገ? ራሱ ያጫውተናል፡፡
ትምህርት እንደማይሆነኝ ሳውቅ፣ እዚያው ላይ ሙጭጭ ማለት አልፈለኩም፤ ፈጣን እርምጃ ወሰድኩና ኮምፒዩተር መማር ጀመርኩ። ትምህርቱን አብረውኝ፣ እንደሚማሩት ልጆች ሳይሆን ጧት ወጥቼ እስከ ምሽት 4፡00 ድረስ ኮምፒዩተር ላይ ስለምቆይ፣ ጥሩ እውቀት ቀሰምኩ። ምሳዬን የምበላው በ10 ሰዓት ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ የኮምፒዩተር ቤቱ ባለቤት እንድረዳው በ500 ብር ቀጠረኝ፡፡ እኔም፣ በተፈጠረልኝ የሥራ ዕድል ደስ ብሎኝ መሥራት ቀጠልኩ፡፡ እዚያ፣ አንድ ዓመት ተኩል ያህል እንደሠራሁ፣ ከባለቤቱ ጋር ስላልተስማማን ለቅቄ ወጣሁና የራሴን ቢዝነስ ጀመርኩ፡፡
በወቅቱ የነበረኝ ገንዘብ 10ሺህ ብር ነበር፡፡ በዚያ ገንዘብ “አልአሚር ስቱዲዮ” የተባለ ሙዚቃ ቤት ከፍቼ መሥራት ጀመርኩ፡፡ በመቀጠል ደግሞ ከመንግሥት ሲኒማ ቤት ተከራይቼ “አልአሚር” የተባለ ፊልም ቤት ከፈትኩ፡፡ እነዚህ ሥራዎች መነሻ ሆኑኝ፡፡ ይህ የሆነው በ1994 ዓ.ም አካባቢ ነበር። ሙዚቃ ቤቱን ከፍቼ እያለሁ ጥሩ የኮምፒዩተር እውቀት ስለነበረኝ፣ በየክፍለ ሀገሩ እየተዘዋወርኩ ኮምፒዩተር እጠግን ነበር፡፡ ይህ ሥራ ስለጠቀመኝ፣ ለተለያዩ ቢሮዎችና መ/ቤቶች ኮምፒዩተርና መለዋወጫቸውን እንዲሁም የተለያዩ የቢሮ ቁሳቁስ ማቅረብ ያዝኩ፡፡ በዚህ ዓይነት ገንዘብ መምጣት ጀመረ፡፡
ይኼኔ “ኢንፎቴክ ኮምፒዩተር ሴንተር” የተባለ የኮምፒዩተር ማስተማሪያ ት/ቤት ከፈትኩ። ጅግጅጋ ውስጥ ከከፍተኛ ባለሥልጣን እስከ ዝቅተኛው የከተማዋ ነዋሪ ድረስ አብዛኛው ሕዝብ እኛ ጋ የተማረ ነው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ስሠራ ቆይቼ የሚበቃኝን ያህል ከሠራሁ በኋላ በዚሁ ሥራ መቀጠል የለብኝም ብዬ ሙዚቃና ፊልም ቤቱን ዘጋሁ፡፡
ሙዚቃ ቤቱን እንኳ መዝጋት ሳይሆን አራት ወይም አምስት ዓመት ከሠራሁበት በኋለ አብሮኝ ይሠራ የነበረው ልጅ ራሱን እንዲችልበት አስተላለፍኩለት፡፡ ለአምስት ዓመት ያህል ኮምፒዩተር ቤቱን እያስተማርንበትና ለተለያዩ መ/ቤቶችና ድርጅቶች የተለያዩ የኮምፒዩተር ዕቃዎች ሳቀርብ ከቆየሁ በኋላ ከአሁን በኋላ፣ ከፍ ያለ ነገር መሥራት አለብኝ ብዬ ስለወሰንኩ ኮምፒዩተር ቤቱን ዘጋሁ፣ዕቃ ማቅረቡንም ተውኩ፡፡
እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስኩት በቀላሉ አይደለም። አንደኛ የክልሉ መ/ቤቶች ጥቂት ናቸው፡፡ ያላቸው ቋሚ ዕቃዎችም ቶሎ ቶሎ ስለማይበላሹ፣ በየጊዜው የመግዛት ዕድሉም አነስተኛ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የከተማዋን ብዙ ሕዝብ ስላስተማርን ለመማር የሚመጣው ሰው ቁጥር ትንሽ ስለሆነ፣ እነዚህን ሥራዎች አቁሜ ቀጣይነት ወዳለው ቢዝነስ መግባት አለብኝ በማለት ወስኜ ነው፡፡
ለመዝጋት መወሰን ብቻ ሳይሆን በቀጣይ መሰራት ያለበትን ነገር መለየትም ቀላል አልነበረም። “እዚህ አካባቢ፣ ወደ ገንዘብ ሊቀየር የሚችል ምን ዕድል (ፖቴንሻል) አለ?” በማለት ለሁለት ዓመት የከተማዋን የወተት ፍላጐትና አቅርቦት በጥልቀት አጠናሁ፡፡ የጥናቱም ውጤት በልማዳዊ መንገድ የታለበ፣ ንፅህናው ያልተጠበቀ ወተት ከየአቅጣጫው ወደ ከተማዋ እንደሚገባ፣ ይህ ወተት በዘመናዊ መንገድ ፓስቸራይዝድ ተደርጐና ታሽጐ ቢቀርብ ከከተማዋ ሕዝብ ፍላጐት የሚተርፍ፣ … መሆኑን አመለከተ፡፡ በዚሁ መሠረት ዘመናዊ የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለማቋቋም ወሰንኩ። ሌላው ክፍተት ደግሞ በከተማዋ ዲጂታል ፎቶግራፍ ማተሚያ መሳሪያ አልነበረም፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሙላት በልጆቼ ስም “3 ኤስ” የተባለ ዲጂታል ስቱዲዮ ቤት ከ3 ዓመት በፊት አቋቋምን። ማተሚያው ዋጋውን የመለሰው በሰባት ወር ሲሆን፣ አሁንም በጥሩ ሁኔታ ገቢ እያስገባ ነው። ሥራ በጣም እወዳለሁ። አንድ ሥራ ላይ ተወስኖ መቀመጥ አልወድም፡፡ ስለዚህ ሥራ ጓደኛዬ ነው፡፡
ይህን የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የተከልክበትን ቦታ የክልሉ መንግስት ነው የሰጠህ?
ጠይቄ ነበር፡፡ የክልሉ መንግሥት ምላሽ ዘገየብኝ፡፡ ቢዝነስ ፈጣን ውሳኔ ስለሚፈልግ 3ሺህ ካ.ሜ ቦታ ከግለሰብ ገዝቼ ወደ ሥራ ገባሁ። ከጀርባ ያለውን ቦታ ለመግዛት እየተነጋገርኩ ነው፤ መንግሥትም ለማስፋፊያ የሚሆን ቦታ እሰጣችኋለሁ ብሎ ቃል ገብቶልናል፡፡
ይህን ፋብሪካ ለማቋቋም ምን ያህል ካፒታል ወጥቷል?
እስካሁን ድረስ በአጠቃላይ 15 ሚሊዮን ብር ያህል ፈጅቷል፡፡ በፍጥነት ሥራ ካልጀመረ ደግሞ ይጨምራል፡፡
ለስንት ዜጐች የሥራ ዕድል ፈጥሯል?
እስካሁን 48 ሠራተኞች አሉን፡፡ ይህ ቁጥር በቅርቡ 58 ይደርሳል፡፡ በዕቅዳችን ግን 72 ሠራተኞች ይኖሩናል፡፡
ይህ ፋብሪካ ምን ይሠራል?  ፋይዳውስ ምን ያህል ነው?   
የዚህ ፋብሪካ መቋቋም ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡ ወተት፣ ከገጠር እያመጡ የሚሸጡ ሴቶች መንገድ ላይ አይተህ ይሆናል፡፡ እነዚህ ሴቶች የመኪና አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ ፀሐዩ፣ አቧራው፣ …አለ፡፡ ወተቱ ደግሞ ሳይሸጥ ቀርቶ ሲመለስ ይበላሻል፡፡ ይህ ፋብሪካ ሥራ ሲጀምር፣ ቋሚ ገበያ ይፈጠርላቸዋል ማለት ነው፡፡ ምን ለማድረግ አቅደናል መሰለህ? አርብቶ አደሮቹ ወተት ለመሸጥ ከተማ አይመጡም። እዚያው በአካባቢያቸው ወተት የሚያስረክቡበት ጣቢያ ወይም ማዕከል እናቋቁማለን፡፡ እዚያ ሆነን ወተቱን እንገዛቸዋለን ወይም ያስረክባሉ፡፡
አርብቶ አደሩ፣ ወተቱን ከሸጠ በኋላ ገንዘቡን ቋጥሮ ወደ ቤቱ አይመለስም፤ ከተማ ሄዶ የሚያስፈልገውን ስኳር፣ ዱቄት፣ ሸቀጣ ሸቀጥ ይገዛበታል፡፡ እኛ አሁን ለማድረግ ያቀደነው ከተማ ሄደው የሚገዙትን ዕቃ፣ በአካባቢያቸው ሱቅ ከፍተን፣ ከተማ መሄድ ሳያስፈልጋቸው ወተቱን አስረክበው፣ እዚያው ከሱቁ የሚፈልጉትን ዕቃ ገዝተው እንዲመለሱ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ከመኪና አደጋ፣ ከፀሐይና ከአቧራ፣ … ይድናሉ፡፡ እኛ ፍሪጅ ያላቸው መኪኖች ስላሉን ከየማዕከላቱ ወተቱን ሰብስበን ወደ ፋብሪካው አምጥተን ፕሮሰስ አድርገንና አሽገን እንሸጣለን፣ ኤክስፖርት እናደርጋለን፡፡
ወዴት ነው ኤክስፖርት የምታደርጉት?
ጅቡቲ፣ ሀርጌሳ፣ … አቅም ካላቸው ተቀባዮች ጋር ተስማምተን ጨርሰናል፡፡ አዲስ አበባ ሩዋንዳ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ላሉ ሶማሌዎችም የግመል ወተት እናቀርባለን፡፡ ድሬዳዋ እናከፋፍላለን፡፡ ሥራውን በአጭር ጊዜ ለማስፋት አቅደናል፡፡
መቼ ነው ሥራ የምትጀምሩት?
በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንጀምራለን፡፡ ለዚህ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል እናደርሳለን ብለን ነበር፡፡ ነገር ግን አንዳንድ የማሸጊያ ቁሳቁሶች ስለልደረሱልን ነው የዘገየው፡፡
ያጋጠሙህ ችግሮች አሉ? እንዴትስ ፈታሃቸው?
በሥራ ዓለም ብዙ ችግሮች ያጋጥሙሃል። ችግሮችን የምታስብ ከሆነ እዚያው አካባቢ ነው የምትሽከረከረው፡፡ ከችግሮቹ ወዲያ ማዶ ያለውን ስኬት ካየህ፣ ያጋጠመህ ችግር ቀላል ሊሆን ይችላል። ችግሮችን አግዝፈን ካየህ፣ አንዳንዱ እስከነጭራሹ አስሮ ሊያስቀርህ ይችላል፡፡ እኔ እምፈልገው ነገር ላይ ላይ ለመድረስ እንጂ ችግር ላይ አላተኩርም፡፡
በአንድ ወቅት ያጋጠመኝን ችግር እንዴት እንደተወጣሁት ላጫውትህ፡፡ ለተለያዩ መ/ቤቶች የተለያዩ የቢሮ ዕቃዎች እናቀርብ ነበር፡፡ ለአንድ መ/ቤት ዕቃ አቅርበን ከ500 እስከ 600ሺህ ብር የሚደርስ ኪሳራ አጋጠመን፡፡ ገንዘብ፣ ነገ ሠርተህ ታገኛለህ፤ ስምና ክብርህ ከጠፋ ግን ለመመለስ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ያቀረብነው ዕቃ በመበላሸቱ፣ መ/ቤቱ እንዳጭበረበርነው ነበር የቆጠረው። ስሜንና ክብሬን ለመጠበቅ እነዚያን ሰዎች ለማሳመን፣ ከእነሱጋር እንደገና መሥራት ነበረብኝ። እስከ መታሰር የሚያደርስ ነገር ነበር፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ከድርጅቱ ገንዘብ ተቀብለን ከውጪ ድርጅት የተፈለገውን ዕቃ አቀረብን። ዕቃው ሲታይ፣ ላኪው ድርጅት ይወቅ አይወቅ ባላረጋገጥም፣ ዕቃው የቴክኒክ ችግር ነበረበት፡፡ ድርጅቱን የላካችሁልን ዕቃ የተበላሸ ነው ብንል “እኛ የላክነው ደህና ነው፤ እስኪ ላኩትና እንየው” አሉ። ቅሬታውን ካቀረበው መ/ቤት ዕቃውን ተረክበን እንዳንመልስ ተጠቅሞበታል፤ ገንዘብ ከፍሎ ቢያዝም ዕቃው ችግር ስለነበረበት ሊገለገልበት አልቻለምና እንዳጭበረበርነው ነበር የቆጠረን፡፡ ስለዚህ ስምና ክብራችንን ለመጠበቅ ከስረንም ቢሆን ጥሩ ዕቃ አስመጥተን አስረከብናቸው፤ ስማችንን አደስን፡፡
ያንን ያደረኩበት ምክንያት መንገድ ላይ የሚያይህ ሁሉ “አጭበርባሪው ነው፤ ታስሮ ነበር…” እያለ ሲጠቋቆምብህ ጥሩ አይደለም፤ በጣም ያማል። ገንዘቡን ከስሬ ትክክለኛ ሰው መሆኔን አስመስክሬ፣ ከዚያ በኋላ ብዙ ሥራ አብረን ሠራን፡፡
ለእናቱ ብቸኛ የሆነው አሚር፣ የ2ኛ ደረጃ ተማሪ እያለ የተዋወቃትን ልጅ ነው ያገባው፡፡ ከጋብቻ በፊት የ7 ዓመት ትውውቅ ሲኖራቸው፣ ትዳር ከመሠረቱ 10 ዓመት አልፏቸዋል፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸው 10ኛ ልደቷን ያከበረችው ከ15 ቀን በፊት ሲሆን፣ ሁለቱ ወንዶች የ7 እና የ4 ዓመት ሕፃናት ናቸው፡፡
አሚር ለመሥራት ያሰበውን ነገር ሁሉ ለባለቤቱ ያማክራታል፡፡ ሚስቴ ለእኔ ሁሉ ነገሬ ናት፤ እንማከራለን፡፡ እምወደውንና የምጠላውን ነገሮች እነግራታለሁ፡፡ አንድ ሰው የቱንም ያህል አዋቂና ብልህ ቢሆን፣ የሆነ ጉድለት አያጣም፡፡ የእኔንም ጉድለት ባለቤቴ ታይልኛለች፣ ታግዘኛለች። እያንዳንዱን ነገር ከማድረጌ በፊት እነግራታለሁ፣ እንወያያለን፡፡ ብልህና አስተዋይ ስለሆነች እኔ ያልታየኝን ታሳየኛለች፡፡
በትዳር ዓለም 25 ወይም 50 ዓመት የኖሩ ሰዎች “አንድም ቀን ተጋጭተን አናውቅም” የሚሉት ከእውነት የራቀ ስለሆነ እኔ አልቀበለውም፡፡ ባልና ሚስት የሆነ ሰው ብዙ ጊዜ ይጋጫል፡፡ እኔና ባለቤቴ ተጋጭተን ማንም ሰው ሳያውቅ ሳምንትና 15 ቀን ልንዘጋጋ እንችላለን፡፡ የምንታረቀውም ራሳችን ነን-ሰው ገብቶብን አያውቅም፡፡ ከባለቤቴ ጋር ትንሽ ስንጋጭ እረበሻለሁ፣ ሥራ መሥራት ሁሉ ያቅተኛል።
ከባለቤቴ ጋር ያለኝ አግባብ ይህን ያህል ነው። እሷም ታውቀዋለች፡፡ ጥፋቱ የእሷ ከሆነ ደውላ ይቅርታ ትጠይቀኛለች፡፡ የእኔ ከሆነ ደግሞ ረጋ ብላ ታስረዳኛለች፡፡ በዚህ አይነት ነው ተግባብተን እየኖርን ያለነው፡፡
አንድ የቢዝነስ ሰው ለሥራው ታማኝ መሆን አለበት፡፡ ሥራ’ኮ ሕይወት ያለው ነገር ነው፡፡ ሥራ ካላከበሩት ይታዘባል፣ያዝናል፡፡ ካከበሩት ደግሞ ይስቀል ይደሰታል፡፡ አንድ ሰው ውጤታማ መሆን እፈልጋለሁ ካለ ለሥራው ታማኝ መሆን አለበት። ለሥራህ ታማኝ ከሆንክ ችግር ቢያጋጥምህም ሥራውን አትተውም፡፡ ያንን ችግር አብረኸው ታሳልፋለህ፡፡ የሥራ ትንሽ ስለሌለው፣ በትክክልና በታማኝነት ማገልገል አለብህ፡፡ አንድ ሥራ ስታከናውን ብዙ መስዋዕትነት መክፈል ሊኖርብህ ይችላል፡፡ ከጓደኛ መለየት፣ ከቤተሰብ መራቅ፣ … አለ፡፡ ያን ሁሉ መስዋዕትነት ከከፈልክ ሥራው ዋጋህን ይከፍልሃል፡፡ ሥራን ከናቅኸው መልሶ ይንቅሃል፡፡ ይህንን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡  
የወደፊት እቅድህ ምንድነው?
ጅግጅጋ ብዙ ጊዜ የምትታወቀው በአሉታዊ ነገሮች ነው፡፡ ወደፊት ይህንን አመለካከት የሚቀይር፣ ወጣቱን፣ አዛውንቱን፣ ሕፃናቱን፣…ሁሉንም ያማከለ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት መዝናኛዎች በብዙ መንገድ የተሻለ (በገንዘብ ሳይሆን በሚሰጠው አገልግሎት) መዝናኛ ማቋቋም እፈልጋለሁ፡፡ በዱባይ፣ በኬንያ፣ ያሉ መዝናኛዎችን አይቻለሁ፡፡ በሁሉም አገሮች ያሉትን መዝናኛዎች ጉድለት አይቸባቸዋለሁ፡፡ “ይኼ ይኼ ቢኖረው ጥሩ ነበር” እላለሁ፡፡ የክልሉ መንግሥት አላስረከበንም እንጂ 20ሺህ ካ.ሜ ቦታ ፈቅዶልናል፡፡ መሬቱን እንደተረከብን፣ በዚህ ዓመት በሌሎች አገሮችና በኢትዮጵያ ያሉ መዝናኛዎች ያላቸውንና “ይጐድሏቸዋል” ብዬ ያየኋቸውን አገልግሎቶች ያሟላ እጅግ ዘመናዊ መዝናኛ ግንባታ ለመጀመር ጥናትና ዲዛይኑ ተጠናቋል፡፡ አሁን የምንጠብቀው መሬቱን እስኪያስረክቡን ነው፡፡ ከአሁን በኋላ ትናንሽ ሥራዎች ሞክሬ ያየኋቸው ስለሆነ ወደዚያ አልመለስም፡፡ መንግሥት ትኩረት በሰጣቸው አምራች ኢንዱስትሪዎች መሳተፍ ነው ትኩረቴ፡፡ ጊዜው እስኪደርስ ይቆዩ እንጂ ሁለትና ሦስት ጥናታቸው የተጠናቀቀ ትላልቅ ፕሮጀክቶችም አሉ፡፡
“በዚህ አጋጣሚ እኔ እንድለወጥና ሰው እንድሆን የረዱኝን ሰዎች ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ከእግዜር ቀጥሎ የመጀመርያዋ ተመስጋኝ ባለቤቴ ናት፡፡ ከእሷ ቀጥሎ አቶ አካሉ ቢረዳን በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ እኔ መኪና ያላቸው ብዙ ጓደኞች አሉኝ፡፡ ይህ የወተት ማቀነባበሪያ ፕሮጀክት ከተጀመረ አንድ ዓመት ሆኖታል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ነው መጥተው ያዩት፡፡ አቶ አካሉ ግን መኪና የለውም፤ ፋብሪካው እየተሠራ ያለው ከከተማው ርቆ ዳር ላይ ነው፡፡ ታዲያ ፀሐይ እየለበለው በትራንስፖርት መጥቶ ብዙ ጊዜ አበረታቶኛል፤ ምክር ለግሶኛል፡፡ “ለካስ የዚህ ዓይነት ቅን ሰውም አለ! ከእንግዲህ ሰው አንድ ነገር ሲሰራ እኔም እንደአካሉ አደርጋለሁ፤ ለሰው ቅን እሆናለሁ” በማለት ሐሳቤን እንድለውጥና ሰብዕናዬን እንድቀርጽ ስላደረገኝ አመሰግነዋለሁ፤ አከብረዋለሁ፡፡” በማለት ለአቶ አካሉ ቢረዳ ያለውን አድናቆት ገልጿል፡፡

Read 3524 times