Saturday, 14 December 2013 13:08

የኢትዮጵያ ደራስያን ማኀበር ለነባሩ ሥራ አስፈጻሚ አሸኛኘት አደረገ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አዲሱ የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ነባሩን የሥራ አስፈፃሚ አባላት ባለፈው ሐሙስ በወይን ኢትዮጵያ የባህል ምግብ አዳራሽ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ሸኘ፡፡
አንጋፋና ወጣት ደራስያን እንዲሁም የልዩ ልዩ ሙያ ማህበራት መሪዎች በተገኙበት  የተሰናባቹ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ገጠመኞቻቸውን እያቀረቡ ታዳሚውን ከማዝናናታቸውም በላይ ለስምንት ዓመታት ማህበሩን ሲመሩ፣ የነበራቸው የእርስ በርስ መናበብ ሐላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ብርታት እንደሰጣቸው ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ማህበሩን በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንደገለጹት፤ የግል ሥራቸውንና ማህበራዊ ጉዳዮቻቸውን በመተው ለማህበሩ ዕድገት ሲጥሩ ለነበሩት የቀድሞ መሪዎች ክብርና ሞገስ ሊቸራቸው ይገባል፣ አዲሱ አመራርም አርአያነታቸውን ተከትሎ በትጋትና በፍቅር በመሥራት ማህበሩን ወደተሻለ የዕድገት ደረጃ ከፍ ለማድረግ ይጥራል ብለዋል፡፡
ክቡር አቶ ሙሉጌታ ሰኢድ የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በበኩላቸው፤ ለተሰናባቾቹ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ማህበሩ ያዘጋጀላቸውን የዋንጫና የአድናቆት ምስክር ወረቀት ከሰጡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፣ ሌሎች የሙያ ማህበራት መሪዎችም ከኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ሊማሩ ይገባል፤ ሚኒስቴር መ/ቤታችንም ከኪነ ጥበብ ማህበራት ጋር ለመሥራት ከመቸውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል ማህበሩን በፕሬዚዳንትነት ይመሩ የነበሩት አቶ ጌታቸው በለጠ ከመስከረም 25 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ ከሃላፊነታቸው ወርደው በዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ ፕሬዚዳንትነት የሚመራ አዲስ ሥራ አስፈፃሚ መሰየሙ ይታወሳል፡፡

Read 1433 times