Saturday, 14 December 2013 13:03

ረቂቅ

Written by  ዋሲሁን አባይ (አዋበ)
Rate this item
(13 votes)

ተጨረማምተው የወደቁት ወረቀቶች ለከራማ የተበተኑ ፈንድሻ መስለዋል፡፡
ጅምር ጽሑፍ…፡፡
የተሰበረ እርሳስ…፡፡
በረባው ባልረባው ነገር የተጣበበ ጠረጴዛ…፡፡
ያለቀበት የሶፍት ካርቶን…፡፡
ሶስት ቀን ያስቆጠረ ያልታጠበ የቡና ስኒ…፡፡
ያልተከደነ ፔርሙዝ…፡፡
የምጥን ሽሮ ቀለም ያለው ግድግዳ ላይ አራት አመት ያለፈው ካላንደር “ኧረ የአስታዋሽ ያለህ” የሚል ይመስል ተንጠልጥሏል፡፡
እነዚህ … እነዛ … የታሰቡት … ያልታሰቡት … ሁሉም እንደ ሐሳቡ ተዘበራርቀው ተቀምጠዋል፡፡
ሐሳብ ሲያላምጥ የቆረጠመው እርሳስ የመፋቂያ ጫፍ ሊመስል ትንሽ ነው የቀረው፡፡ ኤርምያስ የአስር አመት ፍቅረኛውን ፋይል ሳይዘጋ ከእህቷ ጋር የጀመረው አዲስ ምዕራፍ ውጤት ምን እንደሚሆን ለማወቅ ጓጉቷል … ረቂቅ እማታውቀው ነገር ቢኖር … ያላወቀችው ብቻ ነው፡፡
የወትሮው ደንደና ልቡን ከተሰደደበት መልሶታል፣ በከፊል የራሱን ታሪክ እየመሠለው ቢቸገርም መጨረሻውን ለማግኘት የጀመረው ጉልበት ሆኖታል፡፡ አጠገቡ ያሉትን ሐሳብ የሚበታትኑ ምስቅልቅል ነገሮች በሙሉ ተነስቶ አፀዳ፡፡ ጥግ ከቲቪው ጀርባ … የተሸረፈው ማጨሻ ጢም ብሎ ከተሞላው ፍም ላይ እጣን በተን አደረገ… ከርቤ እና ወገርት ቀላቅሎ ማጨስ ያስደስተዋል። ቅዳሜና እሁድ ብቻ ነው በተለየችው ማጨሻው ነጭ እጣን የሚያጨሰው፡፡ ያኔ ስስ ካናቴራ በረጅም ሙታንታ፣ በሰፊ ሸበጥ፣ ለስላሳ ሙዚቃ ከፍቶ ሙሉ ቀን በረጅም መፋቂያ ጥርሱን እየሟጨ … በእጣኑ ሽታ ከሠማይ ቤት እረፍት አድርጎ ይመጣል፡፡
ከአልጋው ትይዩ ያለውን አስራ አራት ኢንች ቲቪ ተመለከተው … የተሸከመውን አቧሯ አይቶ ራሱን ነቀነቀ፡፡ የቲቪው ማስቀመጫ ወደ ኋላ ዘንበል ስላለ፣ ውኃልኩ እንዲቃና በውጭ ሀገር አፍ በተፃፈ መጽሐፍ ነበር ያስደገፈው፡፡ “ፐርፌክት ዴዝ” የሚለውን መፅሃፍ አንገቱን ዘመም አድርጐ ተመለከተ፡፡ ቆይቷል ካነበበው… ሴት ናት ፀሐፊዋ … በእጣ ፈንታ ላይ ያተኮረ መጽሐፍ ነው… አልሆንለት ያለ ደራሲ ሲዳክር በጉልህ ያሳያል … ቢሆንም የመጽሐፉ እጣ ፈንታ በራሱ ያሳዝናል… የቲቪ ድጋፍ፡፡
ወደ ቦታው ተመለሠ… ግራ እጁን ወደ ቴፑ ሰዶ ከፈተ … የሙሉ ቀን መለሠ ሥርቅርቅ ድምፅ አጀበው … “ቁመትሽ ሎጋ ነው የኔ አለም…”
ካቆመበት ለመቀጠል እርሳስና ወረቀቱን ጠመደ፤ የእጣኑ ጢስ ሲትጐለጐል ራቁቷን ጀርባዋን ሠጥታ፣ ለወንድ ራሷን የሸለመች ልጃገረድ ይመስላል… ሽቅብ የጢሱ ቅርፅ አጓጓኑ፡፡
“በዚህ ቅዝቃዜ … ለዚያውም ማንም በሌለበት ብቻችንን እዚህ መሆኑን ወደኸው ነው?”
“ተመልከተው እስቲ ሰማዩን … ከእግዚአብሔር የበለጠ ሰዓሊ አለ ብለህ ታስባለህ?”
“አዎ!”
“ማን?”
“አንቺ”
“ሒድ ሞዛዛ… የምሬን ነው እግዚአብሔር ኮፒ የማይደረግ ሰዓሊ ነው፡፡”
እጇን ሳበው … ጣቶቿ ከርዝመታቸው በተጨማሪ የጥፍሮቿ ውበት የሰጠ ነው፡፡”
ጥፍሮቿ ላይ የተጋደመው ሠማያዊ ቀለም የሆነ ያልታወቀ ነገር አመላካች ነው፡፡ አግድም ጥቁር ጥቁር መስመር አለበት፡፡ ኤርምያስ የረቂቅን አይበሉባ ገለበጠውና የውስጥ እጇን ሳማት…
“እንደዚህ አትሣመኝ አላልኩህም?”
“ብለሽኛል” መልሶ ሳማት፡፡
“እና ለምን ውስጤን ይበልጥ ትረብሸዋለህ?”
“መሣም የት ሃገር ነው የረብሻ ምልክት የሆነው…?”
“ሌባ መሆኔ ቀረ፡፡”
“እኔን ነው የሠረቅሽው… ምን ችግር አለው?”
“ውስጥ እጄን እና አንገቴ ስር ስትስመኝ የሆነ የማላውቀው መንፈስ መላው ሰውነቴ ላይ ሲርመሠመሥ ይታወቀኛል …”
“እህትሽም እንዲህ ትለኝ ነበር…” አንገቷን አቀረቀረች፡፡ ሌባነቷ ውስጧን ሲሟገታት፣ ሲተናነቃት ታቀረቅራለች… “ምነው የኔ ቆንጆ … አጠፋሁ?”
“ታናሽ እህቴ ስላንተ ባወራችኝ ቁጥር እየወደድኩህ … እየተራብኩህ መጣሁ…”
“ይኸው አገኘሽኝ እኮ”
“በስርቆት የተገኘ ማንኛውም ነገር አንገት ይሠብራል” አሁንም ውስጥ እጇን ሳማት
“ተው! እንደ ኤሌክትሪክ ይነዝረኛል እያልኩህ?”
“ከከንፈሬ ግድብ የሚመነጨው ስድስት ሺ ቮልት እኮ ነው” ሳቀላት፡፡
“ሒድ ሞዛዛ … ባዶ ሜዳ ላይ እንዲህ መለኮስ ያስወነጅላል…”
“በየት ሃገር ወንጀለኛ መቅጫ ህግ?”
“የእኛ ሃገሩ ነዋ!”
“የኛን ሃገር ተይው!”
“ለምን?”
“አሰርዘን ሌላ ማፃፍ እንችላለን!”
“ስማ አንዲትን ልጃገረድ ሳትፈቅድና ሳታስበው ልቧን አሸፍቶ ለጦርነት መቆስቆስ ሐጥያት ነው ይላል ህጉ!”
“የምድር ህግ ስለ ሐጢያት ቦታ የለውም”
“ሞዛዛ አትሟዘዝብኝ… የኔን ሐሳብ ማናናቅህ ነው…?” አሁንም ደግሞ ውስጥ እጇን ሳማት፡፡ በምላሱ በስሱ ዳበሳት… ለመከልከል ግን ጉልበቱ አልነበራትም፡፡
“እዚህ ሆቴል አልጋ ይዣለሁ…” ቀስ ብሎ ተመለከታት … ዝምታዋ እንደ ጨረቃዋ ውብ ነው … እንደጠራው ሰማይ ቅኔ ነው …ፀጥ ያለ ባህር ሲዘፍን ይመስላል… ከዋክብቶቹ ፊቷ ላይ የፈጠነቁት ብርሃን ጥይምናዋ ላይ እንደወርቅ መርገፍ ተነስንሰዋል፡፡
“አልሠማሽኝም?”
“እ…?” ፈገግ አለች… በጠረጴዛው ሥር እግሮቿን ጭኖቹ ላይ አድርጋ ነበር፡፡ እጇን መለሠላትና … ሁለቱንም እጆቹን ከጠረጴዛው ሥር ሠደዳቸው…
“የኔ ቆንጆ… አንድ አይነት ላባ ያለን ሰዎች ነን፤ ምናለበት አብረን ብንበር…?”
“የት?”
“ከልብሽ ሰፈር… ከፍቅርሽ ዋሻ … ከሠላምሽ ደጀ ሠላም…?” ሷቋ መጣ… ህሊናዋ ውስጥ ሥርቆሽ ለምን እንደሚጣፍጥ …አብዝቶ የተወራን ጥሩ ፍቅር ለምን ሰርቆ የራስ ለማድረግ እንደምንማስን አሠበች … እጆቹ እግሮቿን እየዳበሠ፣ እሳቱን ይበልጥ ለማቀጣጠል እያራገቡ ናቸው፤ በለስላሳ መዳሰስ፡፡
ከወንበሩ ጠጋ አለ፤ ወደ እሷ … ከወንበሯ ጠጋ አለች፤ ወደ እሱ … እጆቹ ግን እዛው እሣት እያቀጣጠሉ ነው፡፡ ሥር የሠደደው የጭኗ ሙቀት መላ ሠውነቷን በንዳድ ናጣት … በእነዛ በሚያማምሩ ጣቶቿ የጠረጴዛውን ጨርቅ ጭምድድ አድርጋ ያዘች… ከምትገልፀው በላይ ውስጧ ሲርመሠመሥ ተሠማት… ሰማዩ ዝቅ ብሎ የተገለጠውን የፍቅር መሶብ ለመክደን ተቃርቧል፡፡
የእጣኑ ሽታ ከሩቅ ደብር ተሠዶ እንደሚመጣ ጣዕሙ እየቀነሠ ነው፡፡ ደረጄ … ለአፍታም ካቀረቀረበት ቀና አላለም፡፡ በሁለቱ ፍቅር የቀና ይመሥል ሠውነቱ ግሏል፡፡
ረቂቅ … የጠጣችው ሁለት ብርጭቆ ወይን ከሥር ከሚቆሠቆሠው ፍም ጋር ተዳምሮ አግሏታል… ጭኖቿን ጭምቅ ስታደርግ አብራ እጆቹንም ከጭኖቿ ጋር አጣበቀችው … “አራግበው” ይመስላል ሁኔታዋ፤ አይኑ አይኗ ላይ የተፃፈውን “ፈጠን በል የምን መፍዘዝ ነው…” የሚል ጽሑፍ እያነበበ ነው፡፡
ሥራ አልፈቱም እጆቹ፡፡ ሁለቱም ወንበራቸውን ስበው ተጠጋግተዋል… ያስተዋለ ግን አልነበረም፣ ቀኝ እጁን ከፍም ዳርቻ አንሥቶ አቀፋት … አንገቷን ከፍም የተበጀ እጅ ሲያሞቃት ተሠማት…፡፡
ደረጄ … ጭኑ ስር ሙቀት ሲፈስበት ታወቀው… ተቁነጠነጠ… እነሱን ለማረቅ እርሱ መቀዝቀዝ እንዳለበት ዘነጋ … እርሳሱን ጠበቅ አድርጐ ያዘ፡፡
ረቂቅ … በትከሻው አልፎ የመጣውን ፍም የለበሠ ሥጋ ሳመችው… ግራ እጇን ከጠረጴዛው ሥር ወርውራ እጅ ለእጅ ተቆራኙ… ሁለቱም የቀራቸውን ቀይ ወይን እኩል ተጐንጭተው ተነሱ…፡፡ ጃኬቱን አለበሳት…፡፡ የሁለቱም የልብ ትርታ ሲዳምኛ ይደልቃሉ፡፡
ደረጄ … አሁንም ተገርሞና በሙቀቱ ተወብቆ የመጻፊያ እርሳሱን ጠበቅ አደረገ፤ የእጣኑ ሽታ ሙሉ በሙሉ ርቋል፣ የማጨሻው ፍም አምዷል፡፡ ረቂቅ … የእሱን እጅ ጥብቅ አድርጋ ይዛ እየተከተለችው ነው… እየተቻኮለ የተከራየውን በር ከፈተ… ረቂቅ … ወደ ኋላ ቀረት አለች… ዞሮ አያት… መሬት መሬት ተመለከተች… አይበሉባዋን ሳማት … እጇን ከእጁ አላቀቀች፡፡
ደረጄ … ጠበቅ አድርጐ ሲፅፍ እርሳሱ ተሠበረ… “ቲሽ!” አለ ተበሳጭቶ፤ የተሠበረውን በንዴት ግድግዳው ላይ አላተመው… ማጨሻው አጠገብ ኩርምት ብሎ ተቀመጠ፤ እርሳሱ፡፡

Read 4130 times