Saturday, 14 December 2013 12:56

“የሼፎች ውፍረት ከምግብ ጋር መያያዙ ስህተት ነው”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(5 votes)

ሒልተን ማሰልጠኛ ስላለው ሠራተኞቹ በእንግዳ አያያዝ ተወዳዳሪ የላቸውም
ሰውነቴ የሚንቀሳቀስ አይመስልም፤ ግን በጣም ቀልጣፋ ነኝ
በሆቴል መስተንግዶና ደንበኞች አያያዙ በጣም ብዙ ይቀረናል

በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ለ25 ዓመታት ሰርቷል፡፡ አሁን በምግብ ዝግጅት ክፍል በሼፍነት እየሰራ ቢገኝም የጀመረው ግን በእቃ አጣቢነት እንደሆነ ይናገራል፡፡ ሰውነቱ ወፍራም ቢሆንም ማናቸውንም ስራዎች ከማከናወን እንዳላገደው የገለፀው የምግብ ዝግጅት ባለሙያው ታደሰ አራጋው፤ ውፍረትና ሼፍነት ምንም የሚያገናኛቸው ነገር እንደሌለ ያስረዳል -የራሱን ተመክሮ በመጥቀስ፡፡ በአገራችን ሆቴሎች በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፉ ቢሆንም የመስተንግዶ ችግር እንዳለና ሥልጠና ላይ አተኩሮ መስራት እንደሚያሻ ይናገራል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከሼፍ ታደሰ ጋር ያደረገችው ቃለምልልስ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ትውልድህና እድገትህ የት ነው?
ትውልድና እድገቴ አዲስ አበባ ራስ ደስታ ሆስፒታል አካባቢ ነው፡፡
ስንት የልደት ሻማዎች አብርተህ አጠፋህ?
ዞሮ ዞሮ እድሜህ ስንት ነው ለማለት ነው አይደለም? በ1956 ነው የተወለድኩት፤ ሀምሳ አመቴ ነው፡፡
ሆቴል ከመግባትህ በፊት ስራህ ምን ነበር?
አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ኢትዮጵያ ትቅደም ት/ቤት ካጠናቀቅኩ በኋላ “ኦአይሲ” በሚባል ድርጅት በግንበኝነት ትምህርት ስልጠና ላይ ቆይቼ፣ ባሌ ክ/ሀገር መስሎ የሚባል ቦታ በስራ ላይ ከቆየሁ በኋላ፣ አዲስ አበባ ተመልሼ ነው የሆቴል ስራ የጀመርኩት፡፡
እንዴት ነው ወደ ሆቴል ስራ ልትገባ የቻልከው?
ባሌ ውስጥ ስኖር እናቴ ርቄያት ስለምኖር ትጨነቅ ነበር፡፡ በመሀል ልጠይቃት መጣሁ፡፡ በአጋጣሚ ሂልተን የሚሰራ ሰው አየኝ፡፡ እዚያ ሆነህ እናትህን ከምታስጨንቃት ሆቴል ውስጥ ሥራ ብሎ አስገባኝ፡፡
በመጀመሪያ በምን ስራ ላይ ነው የተሰማራኸው?
በመጀመሪያ እቃ አጠባ ነው የገባሁት - “ስቲዋርዲንግ” ይባላል፡፡ ብረት ድስት ማጠብ አለ … ምን የማይታጠብ ነገር አለ፡፡ በወቅቱ ውሀው እና የሚታጠብበት ኬሚካል እጄን እየቆራረጠው በጣም እማረር ነበር፡፡ እናቴ ግን እጄን ባዝሊን እየቀባችና እያባበለች ስራው ላይ እንድቆይና ርቄ ክፍለ ሀገር እንዳልሄድ ታደርግ ነበር፡፡ ስራ ያስገባኝም ሰው እንድበረታ ያደርገኝ ስለነበረ፣ ታግዬ አሁን የደረስኩበት ደረጃ ደርሻለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሂልተን ያስገባኝን አዳነን አመሰግነዋለሁ፤ አሁን ያለው አሜሪካ ነው፡፡
በሂልተን ሆቴል ውስጥ ስንት አመት ሰራህ?
የ25 ዓመት የሆቴል ስራ ልምድ አለኝ፡፡
እንዴት ነው ወደ ምግብ ዝግጅት ሙያ የገባኸው?
እዚያ ቦታ ስትሰሪ ስልጠናው አለ፣ በማየት የምታዳብሪው አለ፡፡ እናም ከእቃ አጣቢነት ወጥቼ ዌይተር ሆኜ መስራት ጀመርኩ፡፡ አሁን ሱፐርቫይዘር ነኝ፡፡ በካፕቴይን ማዕረግ ላይ ነው ያለሁት፡፡ ታዲያ ካፕቴይን ስልሽ የሆቴሉን ነው፤ የአውሮፕላኑን እንዳይመስልሽ (ሳ…ቅ)
እስኪ ስለ ሼፍነትህ እና ስለ ሰውነት አቋምህ እናውራ፡፡ ውፍረትህ ከሼፍነትህ ጋር ይያያዛል?
ሼፍነት የተማርኩት እዛው ሆቴል ውስጥ ነው። ሆቴል ውስጥ መስራት ብዙ ነገር ያስተምራል፡፡ ዩኒቨርስቲ የማታገኚውን በርካታ ነገር ትማሪበታለሽ። እኔም ሼፍነትን የተማርኩት በማየትና በራሴ ጥረት ነው፡፡
ከሰውነት አቋም ጋር በተያያዘ ያነሳሁት ጥያቄ ነበር፡፡ ውፍረትህ ሼፍነትህን ተከትሎ የመጣ ይሆን? አብዛኞቹ ሼፎች በጣም ወፍራሞች ስለሆኑ ከምግብ መቅመስ ጋር የሚያያይዙት ወገኖች አሉ፡፡ አንተስ ምን ትላለህ?
ይሄ እንኳን እውነት ለመናገር የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ እንዲያውም ሼፎች ብዙ ጊዜ ምግብ አይበሉም፡፡ አንደኛ የሚሰሩት ምግብ ሽታ ይዘጋቸዋል፡፡ ሁለተኛ ስራው አድካሚ እንደመሆኑ በጣም ቢዚ ይሆናሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ሼፎችን ካስተዋልሽ ደረቅ ነገሮችን ሲበሉ ነው የምታያቸው፡፡ እንጀራ በጨው፣ ደረቅ ዳቦ ምናምን ነው የሚቀማምሱት። እንደሚባለው አስሩን ምግብ በመቅመስ አይደለም ውፍረቱ የሚመጣው፡፡
ያንተ ውፍረት መንስኤ ምን ይመስልሀል? ለመሆኑ ስንት ኪሎ ትመዝናለህ?
ወደ 98 ኪሎ ግራም ነኝ፡፡ ሰውነቴን ስታይው የሚንቀሳቀስ አይመስልም ግን በጣም ቀልጣፋ ነኝ። በተለይ ፊልድ ስወጣ ሰዎች እምነት የላቸውም። የምንቀሳቀስ አይመስላቸውም፡፡ እስከ አፋር እና መሰል ቦታዎች ከቱሪስቶች ጋር በመዘዋወር ምግብ አዘጋጃለሁ፡፡ ፈረንጆቹ በጣም ነው የሚገርማቸው። ኦሞ፣ ዳሽን እና የመሳሰሉት ቦታዎች ሁሉ ሄጄ ሰርቻለሁ፡፡ የእግር ጉዞውም ሆነ ማንኛውም ነገር አያቅተኝም፡፡ እኔ መወፈር የጀመርኩት ከ30 አመት በፊት ነው፡፡ እስከ 20 ዓመት እድሜዬ ቀጭን ነበርኩኝ፡፡ ይህ ማለት የሆቴል ስራ ከመጀመሬ ከአምስት አመት በፊት ማለት ነው፡፡ ሆቴልም ስራ ጀምሬ ቶሎ ሼፍ  አልሆንኩም፡፡ በአጠቃላይ ውፍረቴ ከሼፍነቴ ጋር ጨርሶ አይገናኝም፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች ሲያዩኝ ግን ይጨንቃቸዋል፡፡
98 ኪሎ ያልከውን ግን… ተጭበርብሯል ባይ ነኝ…
እውነቱ ይሄው ነው፤ ሄደን አስመዝኝኝና እውነቱን እወቂ፡፡ ስታይ ግን 200 ኪሎ ነው የምመስለው ግን 98 ኪሎ ነኝ፤ መቶ ለመሙላት እየጣርኩ ነው (ሳቅ…)
ቀደም ሲል እንደገለፅከው በሆቴል ውስጥ ብዙ ትምህርትና ገጠመኞች አሉ፡፡ ከገጠመኞችህ ብታካፍለን… በተለይ ከውፍረትህ ጋር በተያያዘ …  
በርካታ ገጠመኞች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ጊዜ ምን ገጠመኝ መሰለሽ? ከአንድ ቱር ኦፕሬተር ጋር ወደ አፋር ዳሎል ዲፕሬሽን ለመሄድ ስንነጋገር፣ “እሱን ይዤ አልሄድም ይሞትብኛል” ብሎ ታቃወመ፡፡ እኔ እንደምችልና ውፍረቴን አይቶ ሊገድበኝ እንደማይገባ ተሟገትኩ፡፡ እሱም “አፋር በጣም ሙቀት ስላለው ይሞትብኛል አልፈልግም” አለ፡፡ እኔ እንደውም ብርድና ቅዝቃዜ ሲሆን ነው የማይስማማኝ፡፡ እግሬን ያመኛል፤ ያው ይህን ሁሉ ክብደት ስለሚሸከምም ሊሆን ይችላል፡፡ ከብዙ ክርክር በኋላ ሊወስደኝ ተስማማንና ሄድኩኝ፡፡ እዛ ከሄድን በኋላ በክርክሩ ተፀፅቷል፡፡ በጣም በጥሩ ሁኔታ ቱሪስቶቹን ሳገለግል ቆይቼ፣ ምንም ችግር ሳይፈጠር ለመመለስ ቻልን፡፡ እንዲህ አይነት በርካታ ገጠመኞች አሉ፡፡
ሌላ የጤንነት እክል አለብህ ወይስ ጤነነትህ የተሟላ ነው?
አያመኝም፡፡ ምንም ችግር የለብኝም ግን እንዳልኩሽ እግሬን አልፎ አልፎ ያመኛል፡፡ በተረፈ ጤነኛ ነኝ፤ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡
አንዳንዴ በራስህ ውፍረት ላይ እንደምትቀልድ ሰምቻለሁ…  
አዎ እቀልዳለሁ፡፡ በራሴ መቀለድ ደስ ይለኛል፡፡ አንዳንዴ ስልክ ደውዬ ማን ልበል ሲሉኝ፤ “ዙሪያው ነኝ” እያልኩ አስቃቸዋለሁ፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ሰዎች ሲያዩኝ በጣም ይደነግጣሉ፡፡ ክብደቴም ብቻ ሳይሆን የቁመቴ ማጠርም ጭምር የሚያስደነግጣቸው አሉ። እና ድንጋጤያቸውን ሳይ፣ ዘና እንዲሉ አንዳንድ ቀልዶችን በራሴ ላይ ጣል አደርጋለሁ፡፡
በልክህ የተዘጋጁ ልብሶች ታገኛለህ?
አላገኝም፤ አሰፍቼ ነው የምለብሰው፡፡  
ስንት ሜትር ይበቃሀል?
እሱ እንኳን ያው ነው፡፡  
ያው ነው ስትል ከሌላው ሰው እኩል ነው ለማለት ነው?
አዎ፡፡ ከሌላው ሰው ጋር እኩል ነው፤ ኮትም አንድ ተኩል፣ ሱሪም አንድ ሜትር ተኩል ነው የሚበቃኝ፡፡
ይሄማ እንዴት ሊሆን ይችላል?   
እሱን እንዴት እንደሆነ ባላውቅም ከሌላው ጋር እኩል ነው የምለብሰው፡፡ ሬዲ ሜድ (የተዘጋጀ ልብስ) አልፎ አልፎ ሸሚዝ ብቻ አገኛለሁ፤ ግን የውጭ እቃ አድናቂ ስላልሆንኩ የአገሬን ልብሶች እያሰፋሁ እለብሳለሁ፡፡ አሁን ያደረግሁት ኮፍያ ራሱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ኮፍያ ነው፤ ምርቱን ስለምወደው ነው ኮፍያውንም ያደረግሁት፡፡ በአጠቃላይ ልብሶቼና ጫማዎቼ የአገር ውስጥ ምርቶች ናቸው፤ ሁሉም ሰው የአገሩን ምርት ቢጠቀም ደስ ይለኛል፡፡  
አሁን ባለህ የሰውነት አቋም ትጨነቃለህ?
በፍፁም አልጨነቅም፤ ደስተኛ ነኝ። ምክንያቱም ምንም ከማድረግ አያግደኝም፡፡ እዝናናለሁ፤ እጫወታለሁ፤ እደንስበታለሁ፡፡ ብታይኝ ይገርምሻል፤ በጣም ጐበዝ ዳንሰኛ ነኝ፡፡
ብዙ ጊዜ ወዳጅ ዘመዶችህን ከእኔ ጋር ገበያ አትውጡ ትላለህ ይባላል፡፡ ለምንድነው?  
እውነት ነው፤ እኔ ገበያ ስሄድ 10 ብር የነበረው እቃ 20 ብር ይሆናል፡፡ በእጥፍ ይጨምሩብኛል፤ ውፍረቴን ሲያዩ፣ ወርቃማውን ባለ ጉልላት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እመስላቸዋለሁ መሰለኝ…
ባለ ትዳር ነህ?
በአንድ ወቅት ባለ ትዳር ነበርኩኝ፤ አሁን ሚስቴን ፈትቼያለሁ
ከሰውነት አቋምህ ጋር በተያያዘ ነው ትዳርህን የፈታኸው?
በፍፁም! በተለያዩ አለመግባባቶች ነው የተፋታነው፡፡ ከውፍረቴ ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡
ልጆች ወልዳችኋል?
አልወለድንም
እስኪ ወደሼፍነት ሙያ እንመለስ፡፡ የአገራችንን ሼፎች ከሌላው አለም ሼፎች ጋር አወዳድር ብትባልስ?
አሁን አሁን የአገራችን ሼፎች በጣም በጣም ጐበዝ እየሆኑ ነው፣ በጣም አሪፍ አሪፍ ሼፎች አሉ፡፡ ይገርምሻል፤ ከውጭ ከሚመጡት ሁሉ ይበልጣሉ። እንደውም ከውጭ የሚመጡት የአገራችንን ያህል ችሎታ አላቸው ብዬ አላምንም፡፡ ያለ ችሎታ ሁሉ የሚመጡ አሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ታዝቤያለሁ፡፡ ነጭ ስለሆኑ ብቻ ይችላሉ ተብለው ይመጣሉ፡፡ እዚህ ግን በጣም ጐበዝ ጐበዝ ሼፎችን ታገኛለሽ፡፡
በሆቴል ኢንዱስትሪው ስላለው የመስተንግዶና የእንግዳ አቀባበል ሙያ ምን ትላለህ?
ኢትዮጵያ ውስጥ የመስተንግዶ ሙያ ዳብሯል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በተለይ ከአዲስ አበባ ራቅ እያልሽ በሄድሽ ቁጥር በጣም ችግር አለ፡፡ ሩቅ ሳንሄድ እዚህ ቁጭ ብለን እየተወያየን ባለንበት ካፌ ውስጥ ሻይ ከቀረበ በኋላ ስኳር የመጣው በስንት ልመናና ጩኸት ነው፤ እንደዚህ አይነት ስህተቶች አሉ፡፡ ይሄ የአስተናጋጆች ጥፋት አይደለም፡፡ የአሰሪዎቹ ነው፣ ስልጠና እንዲያገኙ አላደረጓቸውም፣ የደንበኛ አያያዝ ላይ ግንዛቤ የላቸውም፤ ስለዚህ ችግር አለ፡፡
ይህን ችግር ለመቅረፍ በየቦታው እየተዘዋወርክ ስልጠና እንደምትሰጥ አውቃለሁ፡፡ እኔም በአንድ ወቅት ያቤሎ ውስጥ ለሆቴል አስተናጋጆች ስልጠና ስትሰጥ አግኝቼሀለሁ …  
ትክክል! በተለያዩ ቦታዎች ከቱሪስቶች ጋር በሼፍነት እንደምሄደው ሁሉ ሰራተኞችን እንዳሰለጥንላቸው የተለያዩ ሆቴሎች ይጠሩኛል። ግን ይህን ስልጠና ለሰራተኞች እንድሰጥላቸው የሚጠሩኝ ጥቂቶች ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ሆቴል ይከፍታሉ፤ የዕለት ገቢ መሰብሰብ እንጂ ደንበኛዬን እንዴት ልያዝ፣ ምን ያስፈልገዋል፣ ለአስተናጋጆቹ ምን አይነት ስልጠና ይሰጣቸው የሚለው አንገብጋቢ ጉዳይ ትዝ አይላቸውም፡፡ አንድ ተስተናጋጅ ለምሳሌ አራት ቢራ ለመጠጣት አስቦ፣ የአስተናጋጆቹን ሁኔታ በማየት አንድ ብቻ ጠጥቶ ይወጣል፡፡ አራት ሊጠጣ የመጣን ሰው በአያያዙ ማርኮት፤ ስምንት እንዲጠጣ ነው ማድረግ ያለበት፡፡ ያለበለዚያ ኪሳራ እንጂ ትርፍ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡
በዋናነት የአስተናጋጆች ችግር የባህሪ ነው ወይስ…
እኔ እንደምታዘበው በርካታ ችግሮች አሉ። ለምሳሌ የንፅህና ጉዳይ አለ፤ የፀጉር አያያዛቸው፣ የደንብ ልብስ አለባበሳቸው … በዚያው መጠን የባህሪና ስነ-ምግባር ችግሮችም አሉ፡፡ በተለይ አንዳንድ ትልቅ መስለው የሚታዩ ሆቴሎች ወደ ውስጥ ስትገቢ “ውስጡን ለቄስ” እንደሚባለው ናቸው፡፡ በደንቡ መሰረት የአንድ ሆቴል እይታ የሚጀምረው ገና ከጥበቃ ሰራተኛው ነው፡፡ ያማረ የደንብ ልብስ፣ የተስተካከለ አቋምና መሰል ነገሮችን አሟልቶ ስታይው ወደ ውስጥ ለመግባት ይጋብዛል። ከበር ይጀምራል ሁሉም ነገር፡፡ የጥበቃ ሰራተኛ ስለመስተንግዶ ስልጠና ማግኘት አለበት፡፡ ገና ለገና ዘበኛ ነው ተብሎ የመስተንግዶ ስልጠና ካላገኘ በር ላይ ያለው አቀባበል ደንበኛውን ወደ ኋላ ሊመልሰው አሊያም ተመልሶ እንዳይመጣ ሊያደርገው ይችላል። ይሄ ሁሉ ትኩረት ካላገኘ ቢዝነሱ ውሀ በላው ማለት ነው፡፡ ብዙ ዘበኞች እንግዳ ይገላምጣሉ፣ ፍተሻ ላይ ስርዓት የላቸውም፤ ይሄ ሁሉ ችግር አለ፡፡
አሁን አሁን ብዙ ባለሀብቶች ወደ ሆቴል ቢዝነስ እየገቡ ነው፡፡ ይህን እንዴት ታየዋለህ?
ትክክል ነው፤ አሁን ሆቴሎች እንደ አሸን እየፈሉ ነው፡፡ ነገር ግን የአገሪቱም እድገት በዚያው ልክ እየፈጠነ ስለሆነ ሆቴሎች አስፈላጊ ናቸው፡፡ እንደውም ዘርፉ ገና አልተሰራበትም ባይ ነኝ፡፡ ነገር ግን ሆቴል ሲከፈት ከሆቴሉ ጋር አብረው መታየት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ቢዝነሱን ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ከቢዝነስ ጋር በተያያዘ የሰማሁትንና ያሳቀኝን ቁም ነገር ያዘለ ቀልድ ልንገርሽ፡፡ ለስራ ወደ አንዱ ክልል የወጡ ሰዎች ያጋጠማቸው ነው። ሰውየው የሚያምር ፔኒሲዮን ሰርተዋል፡፡ እዚያ የሚያርፉ ሰዎች ጠዋት ቁርስ ሲፈልጉ ራቅ ወዳለ ቦታ (ከተማ) መሄድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ታዲያ ይህን የተመለከተ ተስተናጋጅ ባለቤቱን “አባቴ ጥሩ የእንግዳ ማረፊያ ሰርተዋል፣ ምቹ አልጋ አለ፣ ነገር ግን እንግዳ ጠዋት እርቦት ነው የሚነሳው፡፡ ግቢው ሰፊ ነው፤ እዚህ ትንሽ ቤት ሰርተው ቁርስ ቢያቀርቡ ምን ይመስልዎታል?” ይላቸዋል፡፡ ጋቢያቸውን ደርበው ግቢ ውስጥ የሚንጐማለሉት የእንግዳ ማረፊያው ባለቤት ምን ቢሉ ጥሩ ነው? “ደሞ ያጋደምኩት አንሶኝ ከርሱን ልሙላው?” ብለው አረፉት፡፡ ይሄ ቀልድ ሊመስል ይችላል፤ ግን ቢዝነስ አለማወቅ ነው። ሰው አንድ ስራ ሲሰራ ወይም ሊሰራ ሲነሳ አብሮ ሊሰራቸው የሚገባውን ነገሮች ማወቅ አለበት፡፡
አሁን ክብደትህን ለመቀነስ አላሰብክም?
እንደውም ለመጨመር ጥረት እያደረግሁ ነው፡፡  
ምግብህን ራስህ ነህ የምታዘጋጀው?
በአብዛኛው ራሴ አዘጋጅቼ ነው የምመገበው፡፡ አልፎ አልፎ ሌሎች የሚያዘጋጁትንም እመገባለሁ፡፡
ምን አይነት ምግብ ታዘወትራለህ?
እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ነው የምመገበው። የተለየ አመጋገብ የለኝም፤ ብቻ ጥሩ ተደርጐ መሰራት አለበት፡፡
ብዙ ጊዜ ሼፎች የሚስቶቻቸው የምግብ አሰራር አይጥማቸውም … በሚስቶቻቸው ላይ ጫና ይፈጥራሉ የሚባለው እውነት ነው?
ጫና መፍጠር አይደለም፤ እሷም ጥሩ ምግብ አብሳይ እንድትሆን ታሳያታለሽ፡፡ ይህን እንዲህ አድርጊው፣ ይህን ጨምሪበት ብለሽ ትመክሪያለሽ፤ ታስተምሪያለሽ እንጂ ጫናውን ምን አመጣው፡፡ እኔ አሁን ብዙ ሰው በሚያዘጋጀው ምግብ ደስተኛ አይደለሁም፡፡ ከመጠን በላይ ዘይት፣ ጨው፣ ቅመም… ይጨምራሉ፡፡ ይህ ለጤና ከፍተኛ ችግር ነው፡፡ የንፅህናው ጉዳይም እንደዛው ትንሽ ያስጨንቀኛል፡፡
የንፅህናው ጉድለት ጉዳይ ስትል?
ሩቅ ሳንሄድ የቀድሞ እናቶችን የበርበሬ አዘገጃጀት እንውሰድ፡፡ በርበሬ በፈረሱላ ተገዝቶ እንደመጣ ዛላውን ያጥባሉ፣ ይቀነጥሳሉ፣ በቅመም ይደልዛሉ፡፡ ሲፈጭ ጣዕሙ የሚጠገብ አይደለም፡፡ አሁን ያየሽ እንደሆነ ገና ከገበያ እንደመጣ በፀሀይ ይደርቃል፤ ከነዛላው ወፍጮ ቤት ይገባል፤ አልታጠበ በደንብ አልፀዳ፡፡ እናቶች ደልዘው ቀምመው በሚያስፈጩት በርበሬ እንጀራ ስትበይበት አያቃጥልም፤ ይጣፍጣል እንጂ፡፡ የአሁኑ በርበሬ እንኳን እንጀራ በደረቁ ልትበይበት ወጥ ውስጥ ገብቶ እንኳን እንዴት እንደሚፋጅ አስቢው፡፡ ይህ ሁሉ ደስ አይለኝም። እናም በአብዛኛው ንፅህናው ያስጨንቀኛል፡፡ ሆቴሎች ብዙ አልጠቀምም፤ ቤቴ ራሴ አዘጋጃለሁ፡፡
ሒልተን በጣም አንጋፋና ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ነው፡፡ አለም አቀፍ እንግዶች የሚያርፉበት ነው፡፡ አንተ እነማንን አግኝተህ ታውቃለህ?
እውነት ለመናገር ብዙ መሪዎችን አግኝቻለሁ። ከታቦ ኢምቤኪ ጋር ተግባብቼ አዋርቼአቸዋለሁ፡፡ ሌሎች በቴሌቪዥን ብቻ የሚያዩዋቸውን እኛ እዛ ስለምንሰራ ብቻ በቀላሉ አግኝተን እናዋራቸዋለን። እነሱም በቀላሉ ጓደኛ ያደርጉሻል፡፡ እና እከሌ እከሌ ለማለት ያዳግተኛል፡፡ ሂልተን ለሰራተኞቹ የራሱ የስልጠና ማዕከል ስላለው፣ ሰራተኞቹ በእንግዳ አያያዝ ተወዳዳሪ የላቸውም፡፡ ስለዚህ ሆቴሉ ከአመት አመት እንግዳ ቀንሶቦት አያውቅም፡፡ ብዙ አለም አቀፍ እንግዶች ይመጣሉ፡፡ ሆቴላችን ለስልጠና ከፍተኛ በጀት መድቦ የሰራተኞቹን አቅም ይገነባል፡፡
ላለፉት 25 አመታት ማለትም የእድሜህን ግማሽ በሆቴል ስራ ላይ አሳልፈሀል፡፡ ስልጠናም ትሰጣለህ፡ የራስህን ሆቴል ወይም ማሰልጠኛ ማዕከል ለመክፈት አልሞከርክም?
ብዙ ጥረቶች አድርጌ ነበር፡፡ በተለይ የስልጠና ማዕከል ለመክፈት ሀዋሳ ፕሮፖዛል አስገብቼም ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙ እንቅፋቶች ገጠሙኝና ሳልከፍት ቀረሁ፡፡
አሁን ግን አንድ በመጠናቀቅ ላይ ያለ ነገር አለኝ፡፡ በተለይ ከአዲስ አበባ ውጭ ስትሄጂ የአስተናጋጆቹ የትምህርት ደረጃ አነስተኛ ነው። መስተንግዶ ተምረዋል ቢባል እንኳን ደረጃውን የጠበቀ ሳይሆን የለብ ለብ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን አስተናጋጆች የሚያግዝ ስለ መስተንግዶ አጠቃላይ መረጃ የሚሰጥ መፅሀፍ ፅፌ ጨርሻለሁ፡፡ አሁን ለህትመቱ ስፖንሰሮችን እያፈላለግሁ ነው፡፡ መፅሀፉ ለአንባቢ ሲደርስ የዚህን አገር የመስተንግዶ ደረጃ እንደሚያሳድገው እምነት አለኝ፡፡ ምክንያቱም መስተንግዶ ላይ በጣም በጣም ይቀረናል፡፡

Read 3890 times