Saturday, 14 December 2013 12:32

ለቡጊ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በግሬ ጣራ መርገጥ
ሙዚቃ ሲጋልብ መውጣት መውረድ መፍረጥ
ዓይኔን ማገላበጥ
መርበትበት መንቀጥቀጥ
መላጋት መንገድገድ እንደሰከረ ሰው
የናፈቀኝ ይህ ነው፡፡
ተነስቼ ልዝለል
ቡጊ ቡጊ ልበል…
ቡጊ ቡጊ ቡጊ
    ከበሮ ሲያጋፍት ሙዚቃ ሲያናፋ
ልብሴን ጥዬ ልጥፋ
ልራቆት አብጄ
ልብረር ካለም ሄጄ
ሙዚቃ በጥላው ይምጣ ይሸፍነኝ
ሁሉንም ያስረሳኝ፡፡
እንደ እሳት ቦግ ቦግ
መውለብለብ መንተግተግ
መቃጠል መሞት ነው
ይህ ነው፣ ዳንሴ ይህ ነው፡፡
ልቤን ይነሳኛል
ዛር ይሰፍርብኛል
ልወርውር እጆቼን
    ሙዚቃን እንደ ኳስ ልለጋው በግሮቼ
ልዝለል ተነስቼ፤
ቡጊ ቡጊ ልበል
መሬት ልንከባለል
ልዝለል ጮቤ ልምታ
ያቃዠኝ አንዳፍታ፤
ቡጊ ቡጊ ቡጊ
ገብረክርስቶስ ደስታ

Read 2939 times