Saturday, 14 December 2013 11:07

14 ህፃናት ከመኪና ቃጠሎ ተረፉ

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(12 votes)

14 ህፃናት ተማሪዎችን አሳፍሮ ከጎተራ ወደ ካቴድራል ትምህርት ቤት ይጓዝ በነበረ ኩምቢ ቮልስ መኪና ላይ ባልታወቀ ምክንያት በተነሳ እሳት ሙሉ በሙሉ የወደመ ሲሆን በህፃናቱ ላይ ምንም አይነት አደጋ አለመድረሱ ታውቋል፡፡ ጎተራ ማሳለጫ ላይ ከመኪናው የፊት አካል የተነሳውን እሳት የተመለከተው ሹፌሩ፤ ልጆቹን ፈጥኖ ከመኪናው በማውጣቱ በህይወት ላይ አደጋ አለመድረሱን የጠቆመው ፖሊስ፤ መኪናው በምን ምክንያት ለእሳት ቃጠሎ እንደተዳረገ የቂርቆስ ፖሊስ መምሪያ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አመልክቷል፡፡ እሳቱ በምን እንደተነሳ የተጠየቀው ሹፌሩ፤ እሱም ምክንያቱን እንደማያውቅ ተናግሯል፡፡ ስለ አደጋው ያነጋገርናቸው የእሳትና ድንገተኛ አደጋ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ንጋቱ ማሞ በበኩላቸው፤ መኪናው 8 ሰው ብቻ መጫን ያለበት ቢሆንም 14 ህፃናት አሳፍሮ እንደነበር ገልፀዋል፡፡ እሳቱን ለማጥፋት ከ25 ሺህ ሊትር በላይ ፈሳሽ እንደፈጀና መኪናው በቃጠሎው ከጥቅም ውጭ እንደሆነ አቶ ንጋቱ ገልፀዋል፡፡

Read 3042 times