Print this page
Saturday, 07 December 2013 13:05

“ወይ ወስኑ፤ ወይ መንኑ!...”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(11 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

እኔ የምለው…ጥያቄ አለን፣ የቦሌ መንገድ ሲሠራ “ሶሪ ፎር ዘ ኢንኮንቪኒየንስ…” ምናምን የሚል ይቅርታ ቢጤ ነገር አንድ፣ ሁለት ቦታ ተቀምጦ ነበር…ታዲያ ምንሊክ አደባባይ አካባቢ ያልተደረገልን…በዚችም የመደብ ልዩነት አለ ማለት ነው? (ዘንድሮ እኮ ነገርዬው … ከእግር እስከ ራስ እየገረመመ ‘የብቃት ማረጋገጫ’ የሚሰጠንና የሚከለክልን በዝቶብናል፡፡ ያውም በር ላይ ካለው… አለ አይደል… ሥራው ጥበቃ ብቻ ከሆነው የጥበቃ ሠራተኛ ጀምሮ!) ገና ለገና ‘ቦልሼቪክ አብዮት’ ‘ዘ ሎንግ ማርች’ ምናምን አልቆለታል ተብሎ ነው እንዴ…ካለው ‘ጫማ ስር መውደቅ፣’ ከሌለው ከ‘ጫማ ስር ለመርገጥ’ መሞከር የበዛው! ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ነገረ ሥራችን ሁሉ…አለ አይደል…‘ትለብሰው የላት ትከናነበው አማራት’ እየሆነብን ተቸግረናል፡፡ የምር…የተያዘው በስርአት አልሠራ ብሏል በሌለ አሻንጉሊት… “እንቁልልጭ!” አይነት ነገር ስንባል አስቸጋሪ ነው፡፡ እናላችሁ…ብዙ አገልግሎቶች፣ ወደፊት መሄዱን ተዉት…ባሉበት መቆየት እንኳን እያቃታቸው ይኸው ‘በመነጫነጭ በዓለም ቀዳሚዋ አገር’ ምናምን ሊያሰኘን ነው! ታዲያላችሁ…ዘንድሮ እዚህ አገር እጅግ በጣም አስቸጋሪ እየሆኑ ከመጡት ነገሮች አንዱ ምን መሰላችሁ…በሞባይል ስልክ መነጋገር ነው፡፡ አሁን እኮ “…ሊያገኟቸው አይችሉም…” “መስመሮች ሁሉ ተይዘዋል…” ምናምን ብቻ ሳይሆን እያወራን በየመሀሉ የሚቋረጥብን ነገር ‘እያሳበደን’ ነው፡፡

እና “እንቁልልጩ” በልክ ሆኖብን ቢያንስ እያወራን አታቋርጡንማ! ስሙኝማ…ዘንድሮ ብዙ ስፍራ ነገሮችን ለማስፈጸም ውሳኔ ሰጪ እያጣን ተቸግረናል፡፡ እናላችሁ… እንደሚባለው ውሳኔ ላይ ፊርማቸውን ለማኖር የሚደፍሩ ‘የሚመለከታቸው’ ሰዎች ቁጥር እያነሰ ነው ተብሏል፡፡ (“የተገልጋዮችን ደብዳቤዎች በጊዜ ሳትፈርምላቸው ቀርተህ አጉላልተሀቸዋል…” ተብሎ… አለ አይደል… ዘጋቢ ፊልም ባይሠራበት እንኳን በአደባባይ የተገሰጸ ሰው ብዙ አላየንማ! እናማ… በየመሥሪያ ቤቱ ውሳኔ አሰጣጥ ነገር ያሳስባል፡፡ ውሳኔ ለሚገባው ውሳኔ ከመስጠት ይልቅ… “ምን እንደሚመጣ ይታወቃል፣ ልጄ ቅዝምዝምን ዝቅ ብሎ ማሳለፍ ነው…” እየተባለ ማድፈጥ ሥራዎችን እየጎተተ ነው፡፡ ስሙኝማ…የውሳኔ መስጠትን ነገር ካነሳን አይቀር…በእግር ኳስ ዳኞች አንጀታችሁ የቆሰለ ሁሉ ይቺን ስሙኝማ…አንድ እግር ኳስ ተጫዋች ከዚህ ዓለም ይሰናበትና ገሃነም ይወርዳል፡፡ ገሃነም በር ላይም ዲያብሎስ ይቀበለዋል፡፡ ዲያብሎስ፡— ባለፈው ሕይወትህ ምን ስትሠራ ነበር? ተጫዋች፡— እግር ኳስ ተጫዋች ነበርኩ፡፡ ዲያብሎስ፡— ጥሩ፣ እንግዲያው ሰኞ አንድ ጨዋታ ይኖርሀል፡፡ ማክሰኞ ሁለት፣ ረቡዕ አንድ፣ ሐሙስ ሁለት፣ ዓርብ አንድ፣ ቅዳሜና እሁድ ሁለት ግጥሚያዎች ይኖሩሀል፡፡ ተጫዋች፡— በጣም ደስ ይላል፡፡ ምድር ላይም እንዲህ እንደ ልቤ ለመጫወት ዕድል ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ዲያብሎስ ይመጣና “ጌታው፤ ስህተት ተሠርቷል፡፡

መግባት የነበረብህ መንግሥተ ሰማያት ነበር፣” ይለዋል፡፡ ከዛም ተጫዋቹ ወደ መንግሥተ ሰማያት ይሄድና ቅዱስ ዼጥሮስን በር ላይ ያገኘዋል፡፡ ቅዱስ ዼጥሮስ፡— ባለፈው ሕይወትህ ምን ስትሠራ ነበር? ተጫዋች፡— እግር ኳስ ተጫዋች ነበርኩ፡፡ ዲያብሎስ፡— እንግዲያው የመጀመሪያ ጨዋታህን ከስድስት ወራት በኋላ ታደርጋለህ፡፡ ተጫዋች፡— ስድስት ወር! ገሃነም ሳለሁ በየቀኑ አንድ ጨዋታ ነበረኝ፣ አንዳንድ ቀን እንደውም በቀን ሁለት ጨዋታዎች ነበሩኝ፡፡ እዚህ ችግሩ ምንድነው፣ በቂ ተጨዋቾች የሉም እንዴ? ቅዱስ ዼጥሮስ፡— ተጨዋቾች እንኳን ብዙ አሉን፣ ችግሩ ዳኞቹ በሙሉ ገሃነም መሆናቸው ነው፡፡ ይሄ የምር ቂ…ቂ…ቂ… ያሰኛል፡፡ ለካስ “ዳኛ በድሎን ነው…” ምናምን የሚባለው ነገር…አለ አይደል…ዳኞቹ “ገሀነም መግባቴ ካልቀረ…” እያሉ ነው ፍጹም ቅጣት ምት የሚከለክሉን! ከኳስ ሳንወጣ…ይቺን ቀልድ አንብቡልኝማ…አንድ ምሽት ሜሲ የሆነ ፓርቲ ላይ አንዲት ቆንጅዬ ልጅ ያገኛኝና ይግባባታል፡፡ ከዛማ… በቃ፣ ‘እነሆ በረከት’ ሊባባሉ ይስማማሉ፡፡ እሷዬዋ ሜሲን ቤቷ ይዛው ትሄድና “ጋደም ብለህ እየተዘገጃጀህ ጠብቀኝ” ብላ መታጠቢያ ቤት ትገባለች፡፡ ትንሽ ቆይታ ስትመለስ ከሜሲ ጎን ዣቪና ኢኒዬሰታ መለመላቸውን ተኝተው ታይና ትደነግጣለች፡፡ ፊቷን ኩስትርትር አድርጋም “ምንድው ይሄ፣ ምን እየተካሄደ ነው?” ትላለች፡፡

ሜሲ ምን ቢል ጥሩ ነው… “ያለ ሁለቱ እርዳታ ብቻዬን ጎል ማግባት አልችልማ!” ‘እዛ’ጋም’ “ጎል!” ይባላል እንዴ!” ቂ…ቂ…ቂ… ልክ ነዋ፣ ጎል የሚባልም ካለ እኮ ኦፍ ሳይድ ምናምን የሚሏቸውም ህጎች ይሠራሉ፤ አሁን ካልጠፋ ህግ ኦፍ ሳይድን ምሳሌ የምታደርገው ምን ለማለት ነው…ለምትሉ ወዳጆቼ… “ኖ ኮሜንት!” ልጄ፤ ዘንድሮ…‘ኖ ኮሜንት’ን የመሰለች የብረት አጥር የለችም፡፡ እናላችሁ…ውሳኔ ሰጪዎች ሁሉ ‘ገሃነም ገብተው’ ካልሆነ በስተቀር… ‘እንቁልልጩ’ ይቅርብንና ውሳኔ ለሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ውሳኔዎች ይሰጡንማ! ስሙኝማ…ነገሬ ካላችሁ “ከእንዲህ ዓመት በኋላ እንዲህ እናደርጋለን…” “በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲህ አይነት ለውጦች እናመጣለን” ማለት አሪፍ ማምለጫ የሆነ ይመስላል፡ አሀ…“ለውጥ እናመጣለን…” ምናምን ማለት ‘ልማታዊ’ ነዋ! ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ… ስለ አምስትና አሥር ዓመት ዕቅድ ቅብጥርስዮ ሲያወሩ “ምነው እስከዛሬ ያለችዋን ሚጢጢዋን ሥራ ማሳካት አቃታችሁ!” ብሎ የሚጠይቅ መጥፋቱ! እና የምለው…እዚህ አገር ‘ቦተሊካዊ’ ስርአታችን…ለእኛ ለሰፊዎቹ ህዝቦች በሚገባን መልኩ ይገለጽልንማ! ምክንያቱም በየጊዜው የሚለዋወጡት ነገሮች…በአራድኛው ‘ጦጣ’ እያደረጉን ነው፡፡ “ይሄ መመሪያ የካፒታሊስት ምናምን ይመስላል…” ብለን ሳንጨርስ ሌላ መመሪያ ይተካል፡፡ “ይሄኛው ደግሞ ከኮሚኒስት ማኒፌስቶ ቃለ በቃል የተወሰደ ይመስላል…” እንላለን፡፡ ስሙኝማ…እግረ መንገዴን፣ ይቺን አሪፍ ነገር እዩዋትማ…የተለያዩ ፖለቲካዊ ስርአቶች ገለጻ ነገር ነች፡፡ ሶሻሊዝም፡— ሁለት ላሞች አሉህ፡፡ መንግሥት አንዱን ይወስድብህና ለሌላ ሰው ይሰጠዋል፡፡ ኮሚኒዝም፡— ሁለት ላሞች አሉህ፡፡ መንግሥት ሁለቱንም ይወስድብህና ወተቱን ይሰጥሀል፡፡ ፋሺዝም፡— ሁለት ላሞች አሉህ፡፡ መንግሥት ሁለቱንም ይወስድብህና ወተቱን ይሸጥልሀል፡፡ ወታደራዊ ጁንታ፡— ሁለት ላሞች አሉህ፡፡ መንግሥት ሁለቱንም ይወስድብህና አንተን ደግሞ ይረሽንሀል፡፡ ቢሮክራሲ፡— ሁለት ላሞች አሉህ፡፡ መንግሥት ሁለቱንም ይወስድብህና በስህተት አንዷን ገድሎ ወተቱን ፍሳሽ ማስወገጃ ውስጥ ይደፋዋል፡፡

ካፒታሊዝም፡— ሁለት ላሞች አሉህ፡፡ አንዱን ትሸጥና ኮርማ ትገዛለህ፡፡ ያልተበረዘ ዲሞክራሲ፡— ሁለት ላሞች አሉህ። ወተቱ ለማን መድረስ እንዳለበት ጎረቤቶችህ ይወስናሉ፡፡ የውክልና ዲሞከራሲ፡— ሁለት ላሞች አሉህ፡፡ ወተቱ ለማን መድረስ እንዳለበት የሚወስነውን ሰው ጎረቤቶችህ ይመርጡልሀል፡፡ የአሜሪካ ዲሞክራሲ፡— መንግሥት ለእሱ ድምጽ ከሰጠህ ሁለት ላሞች ሊሰጥህ ቃል ይገባልሀል፡፡ ከምርጫው በኋላ መንግሥት በሠራው ሸፍጥ ምክንያት ከስልጣን ይወገዳል፡፡ መገናኛ ብዙኃኑ ጉዳዩን የ“ካውጌት” ቅሌት ብለው ይሰይሙታል፡፡ ሥርዓተ አልበኝነት፡— ሁለት ላሞች አሉህ፡፡ ወይ ወተቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ትሸጣለህ፣ አለበለዛ ጎረቤቶችህ ይገድሉህና ላሞቹን ይወስዳሉ፡፡ እናማ…ስታስቡት ከአብዛኞቹ ነገሮች ጥቂት፣ ጥቂት ያለን አይመስላችሁም! ለሁሉም መጀመሪያ ግን የ‘ሁለቱ ላሞች’ ጉዳይ ነው፡፡ ሁለት ላሞች ለሌሉት ገለጻው አይሠራማ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… ስሙኝማ…ዛሬ መቼም ተረት በተረት ሆነናል…አሁንም ስለ እግር ኳስ ዳኞች ስሙኝማ፡፡ ዓለም ካለቀች ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በመንግሥተ ሰማያትና በገሃነም መካከል የድንበር ጭቅጭቅ ይነሳል፡፡ የመንግሥተ ሰማያት ተወካዩ መልአክ ለጉዳዩ በቶሎ መፍትሄ ለመፈለግ ዲያብሎስን ለድርድር ይጋብዘዋል፡፡ ዲያብሎስም ጉዳዩን ለመፍታት በመንግሥተ ሰማያትና በገሃነም መካከል የእግር ኳስ ግጥሚያ እንዲካሄድ ሀሳብ ያቀርባል፡፡ መልአኩም ፍትሀዊ በመሆኑ ለዲያብሎስ እንዲህ ይለዋል፡ “ሙቀቱ ጭንቅሌህን አዛብቶታል መሰለኝ። ጨዋታው የአንድ ወገን ብቻ ነው የሚሆነው፣ ምርጦቹ ተጫዋቾች በሙሉ መንግሥተ ሰማያት እንደሆኑ ታውቃለህ፡፡” ዲያብሎስ ሳቅ ብሎ ምን ቢል ጥሩ ነው… “ልክ ነህ፣ ግን ዳኞቹ በሙሉ እኛ ዘንድ ናቸው፡፡

” ስሙኝማ…ዲያብሎስን ልንጠይቀው የምንፈልገው ነገር አለ…እባክህ ውሳኔ ሰጪዎች ሁሉ አንተ ዘንድ ሊመጡ ‘ዌይቲንግ ሊስት’ ላይ ካሉ ሰርዝልንማ! አሀ…እዛ መሄዳችን ካልቀረ ለምን ብለን ነው ደግ ሥራ የምንሠራው እያሉ መከራችንን እያበሉን ነው፤ ወይም ለባሰባቸው እዛው ገሀነም ውስጥ…አለ አይደል…‘ጨለማ ቤት’ ነገር አዘጋጅልንማ! አሀ… እሱን እንኳን ፈርተው ጉዳያችንን ሊፈጽሙልን ይቻላሉዋ! እናላችሁ…ብዙ ነገር እየተበላሸ ያለው ‘አስፈራሚ’ “አቤት” ሲል ‘ፈራሚ’’ አልሰማሁም እያለ ነው፤ ስሙኝማ…ዘንድሮ ያለምንም ‘ደጅ መጥናት’ የሚፈረም ነገር… የተጫዋቾች የዝውውር ሰነድ ብቻ ይመስላል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… እናላችሁ…ሰዉ ሲከፋው አንድዬን “ወይ ውረድ፣ ወይ ፍረድ!” እንደሚለው ሁሉ…አለ አይደል… ጉዳዩን የሚፈጽሙለት ‘ከባድ ሚዛኖች’ እያጣ…አለ አይደል… “ወይ ወስኑ፣ ወይ መንኑ!” ማለት ደረጃ እንዳይደርስ ልብ ያለው ልብ ይበልማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4148 times