Saturday, 07 December 2013 12:40

“ሦስተኛው ዓይን” እውነትና ውበት የተሞላ መድበል!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

ስግብግብነትን ጠንቁሎ ያወጣው ይመሥላል፡፡ ስግብግብነት ነገን የሚያይ ዓይን የለውም፡፡ ዛሬን ብቻ እያየ፣ ነገን የሚገድል ነቀርሣ ነው፡፡ ፀሐይን በሻማ ያሸጣል፡፡ ንፍሮ ለመቀቀል አጥር ያስፈርሳል፡፡ እንደ መጽሐፍ ቅዱሱ ኤሣው ብኩርናን የሚያህል ታላቅ ክብር በምሥር ወጥ ይሸጣል፡፡ ዘመኑን ሁሉ በሆዱ አጭቆ ትውልድ ይገድላል! … ዮናስ በትንንሽ ነገሮች የተጠመደ ገጣሚ አይደለም፤ አይኖቹ ትልልቅ ክፍተቶችን አይተዋል፡፡ ሮበርት ሂሊየር ስለ ግጥም እንደ ግጥም በሚጣፍጡ ሙዚቃዊ ቃላት የሚጽፉ ምርጥ የግጥም ባለሙያ ናቸው - ለኔ፡፡ ገለፃቸው፣ አተያያቸው፣ ኩርኮራቸው ሁሉ ይጣፍጠኛል፡፡ ታዲያ እሣቸው ግጥምን ገና በጽንሱ ነው የሚሥሉት፡፡ በአእምሮ ውስጥ ክንፍ አውጥቶ ሲዋኝ! የባህር መዋዠቅ፣ የልብ ትርታ፣ የሁለንታው አለም (ዩኒቨርስ) ዳንስ እንቅስቃሴን የገጣሚ ጆሮ ይሰማል፡፡ ያንኑ እንደገደል ማሚቱ ያስተጋባል። እናም በዓለም ውጥንቅጥ ግራ አጋቢነት የተምታታው የሰው ልጅ ሕይወት፣ ጥሞና አግኝቶ ከሚውለበለብበት ረገብ እንዲል ግጥም ጆሮውን ትጠቅሰዋለች፤ የሚል ሃሳብ አላቸው፡፡ በርሳቸው አባባል ግጥም ለጆሮ እንጂ ለዓይን አይደለም፡፡ ምናልባትም አንድ ፀሐፊ እንደሚሉት፤ ጆሮ ቀለም ያጣጥማል ሣይሆን አይቀርም፤ የልባቸው ድምጽ፡፡ ሴኔት ይሁን ሌሪክ፣ ኤፒክ ይሁን ባላድ ሁሉም ግን የነፍስን ነገር የማውጠንጠን አቅም አላቸው - እንደየስሜታችን፣ እንደልባችን ቁሥልና ሕመም፤ ዜማና ምት! ስለግጥም ማንበብም አንዳንዴ ግጥም የማንበብን ያህል ባይጥም ኖሮ የት እንገባ ነበር? ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ ፈረንጆቹ ብቻ ሣይሆኑ አቶ ብርሃኑ ገበየሁም ስለግጥም የፃፈበትን ቋንቋ በጣም አደንቅለታለሁ፡፡ (ለምን የፈረንጁን መጽሐፍ ሃሳብ ያለ ፈቃድ ወሰደ የሚለው ቅር ቢለኝም) ታዲያ በእጄ የያዝኳትን መጽሐፍ አንብቤ እያጣጣምኩ ሳለ፣ የዮናስ አብረሃም “ሦስት ዓይን” የግጥም መጽሐፍ እጄ ገብታ አገላብጬ አየኋትና የራሴን ገዛሁ፡፡ ዮናስ አብረሃም ብዙዎቻችን በማንረሳው የሬዲዮ ፋና “ልብ ለልብ” የደብዳቤዎች ፕሮግራም ላይ ከእማዋይሽ ዘውዱ ጋር ሲተርክ ነበር የማውቀው፡፡ ሁለቱም የማይረሣ ትዝታ አላቸው፡፡ “ትንንሽ ፀሐዮች” በሚባል ድራማውም የብዙዎችን ቀልብ መማረክ ችሏል፡፡ ስለዚህ ልቤን ካስደነገጡት፣ ስሜቴን ብቻ ሳይሆን ሕሊናዬን ካከኩልኝ ግጥሞች ጥቂቱን ለማየት ፈለግሁ፡፡ ከገጽ 77 ጀምሬ እንደ አረብኛ ጽሑፍ ወደፊት እመጣለሁ፡፡ “የአስከሬን አበባ” የሚለው ርዕስ ብዙ ጊዜ የተለመደውን የሞተ ሰው ማድነቅ ጉዳይ የሚያነሳ መስሎኝ ነበር፤ ግን አይደለም፡፡ የዘመናችንን ዋነኛ ሕመም፣ አሠቃቂ ግፍ የሚተርክ ነው፡፡ እውነት ለመናገር ብዙ ሺህ ጊዜ በዝርው ቢፃፍም እንደ አዲስ “እህ” ብዬ እንድሰማው አድርጐኛል፡፡ እንዲህ ይነበባል:- ስለኔ ስትጮህ… ቁስሌን ስታክልኝ ካንተ ጋር ለማበር ጽዋ እንጠጣ ብትል… ባዶ ቅሌን ይዤ ገባሁኝ ባንተ በር፡፡ ስለኔነው ብዬ ከፊት ተሰለፍኩኝ - ባቆምከው ማህበር በገዛ ፈቃዴ… ጉልበቴ ተልጦ ወገቤ እስኪሰበር በአፍህ ብትዳብሰኝ ምታነሳኝ መስሎኝ ወንበር ሆኜ ነበር፡፡ ጀርባዬ ላይ በቅለህ ገርጥቼ ከወዛህ ዛሬ እንኳን አስታውስኝ፤ በጌጠኛው ሆቴል… ሆድህን እያሻሸህ ሆዴን አታስብሰኝ፤ ላፕቶፕ ዘርግተህ ስለኔ ያፈሰስከው የአዞ እንባህ ጠበሰኝ ቁልቁል አድርገኸኝ ከሆንክ አሜከላ ግፍ እስኪያፈነዳህ በችግሬ ነግድ ስሜን ሸጠህ ብላ!! በግጥሙ ተራኪው ገፀ ባህሪ፤ አንድ ባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት በስሙ የነገደበትን ያወራል፡፡ እርሱም ተሟጋች አገኘሁ፤ አዛኝ መጣልኝ ብሎ አብሮት ይሰለፋል፤ ከወደቀበት የሚያነሳው መስሎት፣ ራሱን ወንበር ለማድረግ አልሰሰተም ነበር፡፡ ግና ወንበሩን አላስታወሰውም፡፡ እንጀራ መጋገሪያ ያደረገውን ምጣድ ከልቡ ሠርዞታል፡፡ ተራኪው ገርጥቷል፣ የግብረ ሰናይ ልብስ ያጠለቀው ዋሾ ወዝቷል፡፡ ይሄኔ ዘወር ብሎ በጌጠኛ ሆቴል ውስጥ ላፕቶፑን ዘርግቶ ስለርሱ ያፈሰሰውን እንባ ይታዘብና ጦር ይመዛል ስንል “ግፍ ያፈነዳልሃል” ብሎ መጪውን ቀን ይጠብቃል፡፡ እኔ ግን ግፍ እስኪያፈነዳው ባይጠበቅ ሕግ ቢያፈነዳው ብዬ እመኛለሁ… ቁልቁል አድርገኸኝ ከሆንክ አሜከላ ግፍ እስኪያፈነዳህ በችግሬ ነግድ ስሜን ሸጠህ ብላ!! የሚለው ሃሳብና ስንኞች ከነዜማና ምታቸው ቆንጆ ናቸው፡፡ ሃሳቡ ግን ትንሽ ያቁነጠንጣል፤ ቀጠሮ ባያገኝ ያስመኛል፡፡ ብቻ ገጣሚው ጥሩ ነገር ቃኝቷል፡፡ ያሳረረን ነገር ኮርኩሮታል፡፡ “ሞኝ የዕለቱን” የሚለውም ግጥም ቁምነገሩም ምቱም ጣዕም አለው፡፡ ዳሩን ዘንግተነው መሀል ስንሻማ ፀሐይዋን አጥፍተን ስንሮጥ ለሻማ፤ ጃንጥላ ተማምነን ዋርካውን ገንድሰን ንፍሮ ለመቀቀል አጥሩን አፈራርሰን በግለኝነት ጦስ… ችግሮች ስር ሰደው - አንድ ላይ ካበሩ አጥር በሌለበት እንዳይጠፋን በሩ፡፡ ጥቂት ስንኞች ትልቅና ግዙፍ ሀሣብ ይዘዋል። ንፅፅሮቹም ከፍ ባለ አቅም ተቀምጠዋል። ሥዕላቸውም ደማቅ፣ ለዛቸው ጣፋጭ ነው። ምናልባትም የዘመናችን ጉድፎች ከምንላቸው -ስግብግብነትን ጠንቁሎ ያወጣው ይመሥላል፡፡ ስግብግብነት ነገን የሚያይ ዓይን የለውም፡፡ ዛሬን ብቻ እያየ፣ ነገን የሚገድል ነቀርሣ ነው፡፡ ፀሐይን በሻማ ያሸጣል፡፡ ንፍሮ ለመቀቀል አጥር ያስፈርሳል። እንደ መጽሐፍ ቅዱሱ መሣው ብኩርናን የሚያህል ታላቅ ክብር በምሥር ወጥ ይሸጣል፡፡ ዘመኑን ሁሉ በሆዱ አጭቆ ትውልድ ይገድላል! … ዮናስ በትንንሽ ነገሮች የተጠመደ ገጣሚ አይደለም፤ አይኖቹ ትልልቅ ክፍተቶችን አይተዋል፡፡ ቀጣዩ ግጥም “የዛሬን-ዛሬ ልንገርህ” የሚል ርዕስ አለው፡፡ ይሁን እንጂ ርዕሱ ምነው “ወረት” የሚል በሆነ ብያለሁ፡፡ የስሜት መለዋወጥ ነው ወረት፡፡ አሁን ያየነው ፍም መልሶ አመድ ሲሆን! … ሣይቆይ የሚጠወልግ ቅጠል አይነት! እንዲህ ይላል ግጥሙ:- ፍቅራችን ከእቶን ቢግልም ለነገ ዋስትና የለንም ምናልባት አድሮ አይኖርም፡፡ አንደበታችን ቢስማማ በአንድ ዋንጫ ብንጠጣ እርግጠኞች አይደለንም ነገ ምን እንደሚመጣ፡፡ የነገ ነገ ስላለ የዛሬን ዛሬ ውሰደው አሁን “መልአክ” ነህ ያልኩህን “ሠይጣን ነህ” ብዬ ሳልክደው፡፡ ተራኪው ራሱን ጠርጥሯል፤ ራሱን ፈርቷል፤ “ማን ያውቃል!” እያለ ነው፡፡ ስለዚህ ቡራኬህን ውሰድልኝ ነው የሚለው፡፡ ግጥም የማይረግጠው አበባ፣ የማያደማው እሾህ የለም፡፡ ከሕይወት ቁና ላይ ጣፋጭና መራራውን ይነካል፡፡ ትናንትን ሣይዘነጋ ዛሬን ይተርካል፤ ነገንም ይተነብያል፡፡ እውነተኛ የግጥም አንባቢ ደግሞ የዘመኑን ግጥም ብቻ የሙጢኝ ማለት የለበትም፤ እንደሂሊየር እምነት፡፡ የትናንትን ግጥሞች ሃይልና ውበት ወይም እውነትና ውበት፣ የዘመኑንም እንዲሁ ማጣጣም ግዱ ነው፡፡ ምናልባትም ግጥም እንደዝርው ፅሁፎች በየዘመኑ ጣዕሙን የሚጥል ሣይሆን፣ የዘመንን አድማስ የሚሻገር መሆን አለበት ይላሉ -የግጥም ባለሙያዎች፡፡ የዮናስ ግጥሞችም ላይ ከወደ ጭራቸው የሚጐትቷቸው ድክመቶች መኖራቸውን አንክድም! ብዙ የዘርፉ ጠበብት እንደሚስማሙበት፤ የግጥም ቋንቋ አዘወትራዊው ፈንጠር ያለ፣ ከፍታ ያለው ማማ ቢሆን ደግ ነው፡፡ እናም “ሦስተኛው ዓይን” ፓ! የሚያሠኝ ገለፃ፤ የዘይቤዎች ዳንስና ፍካት አልታየበትም፡፡ ምቱና ዜማው ደስ ይላል፡፡ እውነት ለመናገር የገጣሚው አይኖች ትኩረትና ውበትም የበለጠ ነው፡፡ ግን የተሻለ ሊፅፍ ይችላል፡፡ ወደ ሃሣብ ስንሄድ፣ ሀሣቦቹ ባብዛኛው የተመረጡ ቢሆኑም ክሊሼ የሆኑ ለዓመታት የተወራባቸው ሣይቀሩ መፅሐፍ ውስጥ ተካትተዋል። እነዚህ ደግሞ የመፅሀፉን ክብር በአፍጢሙ እንዳይደፉት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ቀዳሚ ምሣሌ የሚሆነን “የግድግዳው ሰዓት” የሚለው ነው። እናንብበው:- የግድግዳው ሰዓት … ከቆመ ቆይቷል፤ ምናልባት ጌጥ እንጂ … ጊዜ ማብሰር ትቷል አይተነው ባናምነው … “እውነት የለjትም ዋሽቷል” ያለው ማነው? ጨልሞ እስኪነጋ ነግቶ እስኪጨልም ሁለቴ ልክ ነው፡፡ ገጣሚው ይህንን ተብሎ ተብሎ የቸከ ሀሣብ ባይደግመው ይመረጥ ነበር፡፡ “አዝማሪው” የሚለው ግጥም ደግሞ፣ የዜማ ልፍስፍስነትና ስብራት ይታይበታል፡፡ ሙዚቃው ሞቷል፡፡ ደግሶ ሲጠራ… መብዛቱ ሲገርመኝ - አጓጉል አመስጋኝ የመሸታው ልክፍት … ኪነጥበብ መንደር “ዳር ዳር” ሲል አሰጋኝ፡፡ ግጥሙ ለአይን መምታቱ ብቻ የታየ ይመሥላል። ግና ደካማ ነው፡፡ “የሰይጣን ደግነት” የሚለው ግጥም ከ “የአስከሬን አበባ” ጋር መዝጊያው ይመሣሠላል፡፡ ተደጋጋሚ ሀሣብ ባይነሳ ይመረጣል። ይሁንና የዮናስ “ሦስተኛው ዓይን” እውነትና ውበት የተሞላ፣ አይን የሚስብ፣ ልብ የሚሰጠው መድበል ነው፡፡ አንድ ገጣሚ ግጥሞቹ ሁሉ ጥሩ እንዲሆኑ አይጠበቅም … የቱም ታላቅ ገጣሚ ዝርክርክ ግጥም ሾልኮ ይገባበታል፡፡ ብዙ ጊዜ ምርጫው ላይ ገለልተኛ አርታኢ ከጐን ሆኖ ቢያግዝ ጥሩ ነው፡፡ የዮናስ ቀጣይ የሳቁና የመጠቁ እንደሚሆኑ ብሩህ ተስፋ አለኝ፡፡

Read 2970 times