Saturday, 07 December 2013 12:20

በሴካፋ አዳዲስ ዋልያዎች ብቅ ብለዋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

በኬንያ በሚካሄደው 37ኛው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና በአዳዲስ ዋልያዎች የተጠናከረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባሳየው አቋም ተደነቀ፡፡ በሴካፋው ከደመቁ አዳዲሶቹ ዋልያዎች መካከል ሳላዲን በርጌቾ ፤ቶክ ጀምስ ፤ማንአዬ ፋንቱ ፤ ፋሲካ አስፋውና ምንተስኖት አዳነ ይጠቀሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድቡ የመጀመርያ ጨዋታ ከኬንያ ጋር 0ለ0 አቻ ከተለያየ በኋላ የዛሬ ሳምንት ዛንዚባር 3ለ1 የረታ ሲሆን ባለፈው ማክሰኞ ደግሞ በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ደቡብ ሱዳንን 2ለ0 በማሸነፍ በ7 ነጥብ እና በአራት የግብ ክፍያ ወደ ሩብ ፍፃሜው ገብቷል፡፡ በዚሁ ምድብ ኬንያም ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ ነጥብ እና የግብ ክፍያ በመያዝ ለሩብ ፍፃሜ መድረሷን አረጋግጣለች፡፡ ከሶስቱ ምድቦች ወደ ሩብ ፍፃሜ በማለፍ ኡጋንዳ እና ሱዳን ከምድብ 3 የመጀመርያዎቹ ሲሆኑ ከምድብ 2 ደግሞ ዛምቢያ እና ታንዛኒያ በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ አልፈዋል፡፡ በጥሩ ሁለተኛነት ሩብ ፍፃሜ የገቡት ደግሞ ከምድብ 2 ብሩንዲ እንዲሁም ከምድብ 3 ሩዋንዳ ናቸው፡፡ ሻምፒዮናው በሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ሲቀጥል ዛሬ ኡጋንዳ ከታንዛኒያ እንዲሁም ኬንያ ከሩዋንዳ ሲገናኙ፤ ነገ ደግሞ ዛምቢያ ከብሩንዲ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከሱዳን ይጫወታሉ፡፡ በምድብ ጨዋታዎች የሴካፋ ሻምፒዮናው በከፍተኛ የተመልካች ድርቅ መመታቱን ያማረረው የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ ነው፡፡ አስቀድሞ በያዘው በጀት ላይ ተጨማሪ ወጭዎች በማውጣት መጨናነቁን ገልጿል፡፡ በኬንያ ብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች እና በኬንያ በሚኖሩ የኡጋንዳ፤ የደቡብ ሱዳን እና የኢትዮጵያ ስደተኞች ቡድኖቻቸውን ለመደገፍ ስታድዬሞችን ከመግባታቸው በቀር የታንዛኒያ፤ የደቡብ ሱዳን፤ የሱዳን፤ የሩዋንዳ እና የዛንዚባር ጨዋታዎች ላይ ስታድዬሞች ባዶ ነበሩ፡፡ የሴካፋ ምክር ቤት እና የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ ከሩብ ፍፃሜ በኋላ ስታድዬሞች በተመልካች መድመቃቸውን ተስፋ አድርገዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የኡጋንዳ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት ሚቾ ከቻን በፊት የሴካፋን ዋንጫ ማንሳት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስን ያሰለጥኑ የነበሩት ሰርቢያዊው ሰርዶቪች ሚሉቲን በብሄራዊ ቡድን ደረጃ መስራት ከጀመሩ በኋላ ሩዋንዳ ለ1 የውድድር ዘመን መርተው ከዚያም በኋላ ላለፉት ሁለት ዓመት በኡጋንዳ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ሚቾ “ዘክሬንስ” የተባለውን የኡጋንዳ ብሄራዊ ቡድን በደቡብ አፍሪካ ለሚሰተናገደው ሶስተኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ አብቅተውታል፡፡ በሴካፋ ለ13 ጊዜያት ሻምፒዮን በመሆን የዞኑን ከፍተኛ ውጤታማነት ያሳየችው ኡጋንዳ እንደኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ እና በዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች እስከ መጨረሻው ምዕራፍ መድረስ እንደሚገባት የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃናት መክረዋል፡፡ የኢትዮጵያን ቢ ቡድን፤ ዛንዚባር፤ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳንን ማሸነፍ በቂ አይደለም ብለዋል፡፡ በሴካፋው ሻምፒዮና ሙሉ ቡድኑን ባያሳትፍም በዝውውር ገበያ የተጨዋቾች የዋጋ ተመን ከፍተኛ ዋጋ ያለው የኬንያ ብሄራዊ ቡድን ሲሆን በ15.3 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመኑ ነው። ተጋባዡ የዛምቢያ ቡድን በ2012 የአፍሪካ ሻምፒዮን የሆኑትን የቡድን አባላት ባይዝም በ12 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመን ሁለተኛ ደረጃ ሲኖረው፤ ዩጋንዳ በ3.1 ሚሊዮን ዩሮ፤ ሱዳን በ2.93 ሚሊዮን ዩሮ፤ ኢትዮጵያ በ800ሺ ዩሮ፤፤ ታንዛኒያ በ500ሺ ዩሮ፤ ሩዋንዳ በ475ሺ ዩሮ እንዲሁም ደቡብ ሱዳን በ150ሺ ዩሮ የዋጋ ተመናቸው እስከ 8 ያለውን ደረጃ ሲያገኙ፤ ሶማሊያ፤ ኤርትራ፤ በሩንዲና ዛንዚባር ዋጋ ተመን የላቸውም፡፡ በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ በሴካፋ ዞን ግንባር ቀደም የሆነችው ኡጋንዳ በዓለም 85ኛ በአፍሪካ 20 ደረጃ ላይ ያለችው ኡጋንዳ ናት፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም 95 በአፍሪካ 25፤ ኬንያ በዓለም 118 በአፍሪካ 32፤ብሩንዲ በዓለም 121 በአፍሪካ 34፤ ሩዋንዳ በዓለም 129 በአፍሪካ 37፤ ታንዛኒያ በዓለም 129 በአፍሪካ 38፤ ሱዳን በዓለም 136 በአፍሪካ 39፤ ኤርትራ በዓለም 195 በአፍሪካ 50፤ ሶማሊያ በዓለም 201 በአፍሪካ 52 እንዲሁም ደቡብ ሱዳን በዓለም 204 በአፍሪካ 54 ሆነው በተከታታይ ደረጃ ይቀመጣሉ፡፡

Read 4470 times