Saturday, 07 December 2013 11:53

የመንግሥት በተስፋ የተሞላ ቃል ተስፋ አስቆራጭ እንዳይሆን!

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

“ከእንግዲህስ ተስፋዬ ምንድን ነው?” ከሣውዲ ተመላሽ ወጣት

“ወደ ሀገሬ ተጠርዤ ከመጣሁ ጀምሮ ታናናሽ ወንድም እና እህቶቼን ቀና ብሎ ማየት አቅቶኛል፤ እናቴም አንዴ ከሚጥላት ሲያሻው ከሚያቃናት ህመሟ ጋር እየታገለች በተቻላት አቅም እኔ እንዳልከፋባት የምታደርገውን ስታጣ፣ የምትይዝ የምትጨብጠው ሲጠፋት ሳይ ቤቱን ለቀህ ብረር ብረር ይለኛል፡፡ ወንድምና እህቶቼ ቅስማቸው ተሰብሮ፣ ተስፋቸው ጠውልጐ ያየሁ እየመሰለኝ እረበሻለሁ፡፡ ይኸው የሀገሬን ምድር ከረገጥኩና ቤተሰቦቼን ከተቀላቀልኩባት ከዛች ምሽት ጀምሮ እላዬ ለይምሰል ፈክቶ ውስጤ ግን ጠቁሮ እየተብሰለሰልኩ አለሁ፤ ያለፉትን ሃያ ቀናት በሌቱ እንቅልፍ ቀርቶ በቀኑም ያቃዠኛል፡፡ የሚታየኝ ሁሉ ተስፋቢስነት ነው፡፡ ልብሴን እንኳ ሳልይዝ ባዶ እጄን ነው የመጣሁት፡፡ ቀደም ሲል በባንክ ያስቀመጥኳት ገንዘብ ደግሞ የእኔንም ሆነ እንደ አባት በልጅነቴ የማሳደጉን እዳ ልወጣ ቃል ገብቼ የተቀበልኳቸው ወንድምና እህቶቼን ጉሮሮ ለመድፈን ከሁለት ወራት በላይ አቅም የላትም፡፡

እዚህ ከመጣሁ በኋላም ምንም ተስፋ የሚሰጥ ነገር ማየት አልቻልኩም፡፡ አትጠራጠረኝ የውጭ ጉዞ በድጋሚ ሲከፈት ህጋዊ መንገዱን ተከትዬ ተዋርጄ ወደመጣሁባት ሀገር አሊያም ወደሌላ ሃገር መሄዴ አይቀርም” ይህን ያለኝ ከ20 ቀናት በፊት ከሣውዲ አረቢያ “ህገወጥ ስደተኛ” ተብሎ በፖሊሶች ከተደበደበ በኋላ የተመለሰው የ24 አመቱ ያሬድ ግርማ ነው። ገና በልጅነቱ ወላጅ አባቱ በኤችአይቪ ኤድስ ማለፋቸውን ተከትሎ፣ የቤተሰብ ሃላፊነትን እንደተረከበ የሚናገረው ያሬድ፤ ከ4 አመት በፊት ወደ ሣውዲ አረቢያ ያመራው ከኤችአይቪ ጋር እየታገሉ ልጆቻቸውን ለማሳደግ በጉሊት ችርቻሮ የቤተሰቡን ጉሮሮ ለመድፈን የተሣናቸውን እናቱን ድካም ለማቅለል ነበር። በትምህርቱ ጐበዝ ቢሆንም የአባቱ የአደራ ቃል እረፍት ሲነሣው፤ የኑሮ ውድነት የቤተሰቡን ህልውና እየተፈታተነ መሆኑን ሲገነዘብ ከ9ኛ ክፍል ለማቋረጥ ተገደደ፡፡ ወላጅ አባቱ በመጨረሻዋ ደቂቃ ደጋግመው “የእናትህንና የታናሽ ወንድምና እህቶችህን ጉዳይ አደራ” ብለውት ነበር፡፡ እናም የአባቱን አደራ ለመፈፀም ለራሱ ቃል ገባ፡፡ መጀመርያ የታክሲ ረዳት ሆነ፤ ገቢው ግን ከቤተሰቡ ፍላጐት ጋር ሊመጣጠን አልቻለም፡፡

ጋራዥ ተቀጥሮ መስራት ጀመረ፤ እሱም ተስፋ ያለው አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ አንድ እድል ይዞለት መጣ፡፡ ሲጨንቀው የቤተሰቡን ገመና ለጋራዡ ባለቤት ወንድም ዝርግፍ አድርጐ ችግሩን ሁሉ አዋይቶት ነበርና፣ ሣውዲ አረቢያ የተሻለ ሠርተህ ገንዘብ ታገኛለህና ልላክህ አለው፡፡ በሃሣቡ ተስማማ። የያሬድ ቤተሰብም የመጣውን እድል በደስታና በፀጋ ተቀበለው፡፡ ከዚያም በሰውየው ስፖንሰርነት፣ ለደላላዎች 15ሺህ ብር ገደማ ተከፍሎ ጅቡቲ ድረስ ረዳት መስሎ በጭነት መኪና ከተጓዘ በኋላ፣ በቀይ ባህር አድርጐ የመንን በማቋረጥ ከአንድ ወር በኋላ ሣውዲ ገባ፡፡ “እንደ እድል ሆኖ በመንገድ ላይ ብዙም እንግልት አልደረሰብኝም” የሚለው ያሬድ፤ ወዲያው እዚያ ሀገር ባሉ ተቀባይ ደላላዎች አማካኝነት የፍየል ጠባቂነት ስራ እንዳገኘ ይናገራል፡፡ ደሞዙም 400 ሪያል ነበር፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከፍየል ጠባቂነቱ ጐን ለጐን ከአንድ ባንግላዲሺያዊ ጋር በፈጠረው ወዳጅነት፣ በትርፍ ጊዜው ለአንድ የሃብታም ቤት የጥበቃ ስራ መስራት ጀመረ፡፡ በዚህም የስራ እድል ተጨማሪ 300 ሪያል ማግኘት ቻለ፡፡ ወንድምና እህቶቹንም ጥሩ ትምህርት ቤት ለማስተማር ብሎም እናቱን ለመርዳት በቂ እንደነበር ያሬድ ያስታውሳል። “ያለፉትን አራት አመታት በዚህ መልኩ ቤተሠቤን ለችግር ሣልዳርግ የአባቴን ቃል መፈፀም በመቻሌ ደስታዬ ወደር አልነበረውም፤ የወደፊቱ ተስፋዬም ብሩህ ሆኖ ይታየኝ ነበር” ይላል - ያሬድ፡፡ የሣውዲ መንግስት ከ7 ወራት በፊት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በግዛቱ የሚኖሩ ህገወጥ ያላቸውን ስደተኞች በቶሎ ወደ ህጋዊነት መስመር እንዲገቡ ማሣሠቢያ መስጠቱን ያሬድ ያስታውሣል። በወቅቱ የሃገሪቱ መንግስት እንዲህ ይጨክናል ብሎ ያሠበ አልነበረም፡፡ ሊጨክን እንደሚችል ፍንጭ የታየው በድጋሚ ለማስታወስ ማሣሠቢያ አዘል አዋጅ ሲያውጅ ነበር፡፡ “በ3 ወራት ውስጥ አጠናቅቁ” ይላል ማሣሠቢያው፡፡ እሡና መሠሎቹ በዚህኛው ማሣሠቢያ በመጠኑም ቢሆን መረበሻቸው አልቀረም፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ኤምባሲ በማምራት “ኢትዮጵያዊነታችን ተረጋግጦ ፓስፖርት ይሠጠን” ሲሉ ከአንድም ሁለቴ ተመላልሠው እንደጠየቁ የሚናገረው ያሬድ፤ ኤምባሲው “ዜግነትን የማረጋገጥና ፓስፖርት የመስጠት ጉዳይ የደህንነት ጉዳይ ስለሆነ የማጣራት ስራው የወራት እድሜ ሊወስድ ይችላል” እንዳላቸው ያስታውሳል። ከተስፋ አስቆራጩ የኤምባሲው ምላሽ በኋላም የሚመጣውን በፀጋ ለመቀበል ወስነው ጥቅምት ሃያ አራትን መጠባበቅ ጀመሩ፡፡ የተፈራው አልቀረም፤ የሃገሪቱ መንግስት ሰአታት እንኳ ሣያባክን እርምጃውን መውሠድ ጀመረ፡፡ ያሬድም በጥበቃ ስራው ላይ እንዳለ ተይዞ ከመጀመሪያው የእርምጃው ሠለባዎች አንዱ ሆነና ከሺዎች ወገኖቹ ጋር ወደ ሃገሩ ተመለሠ፡፡ “ቦሌ ስንደርስ ከመልካም አቀባበል ጋር ብስኩት፣ የታሸገ ውሃ እና የመቋቋሚያ ተብሎ 900 ብር በነፍስ ወከፍ ተሰጥቶናል” የሚለው ከስደት ተመላሹ ያሬድ፤ በተደረገልን ገለፃም የስራ እድሉ ሠፊ መሆኑ ተነግሮናል ይላል፡፡ “እዚህ ሃገራችሁ ስራ ፈጥራችሁ ኑሩ፤ መንግስትም ድጋፍ ያደርግላችኋል ተብለን ነበር፤ ከቀናት ቆይታ በኋላ ግን የሠፈር ጓደኞቼ ያሉበትን የኑሮ ሁኔታ እና ቤተሠቤን በቅጡ ሳጤን የነበረኝ ተስፋ ጠውልጐ ልቤ ከቁስሉ ሣያገግም ተመልሶ ስደት ናፋቂ ሆኗል” ሲል በተስፋ መቁረጥ ስሜት ተናግሯል።

“ይኸው ከመጣሁ ወር ልደፍን ነው፤ እስካሁን ብዙ ነገር ያስለመድኳቸውን ቤተሠቦቼን ምን ሠርቼ፣ ምን የገቢ ምንጭ ፈጥሬ ማኖር እንዳለብኝ እንኳ ማወቅ ቸግሮኛል የሚለው ያሬድ፤ ቤተሠቦቼ የነበራቸው ተስፋ ሲጠወልግ፣ የሞቀው ኑሮአቸው መልሶ ሲቀዘቅዝ ማየት አልፈልግም ይላል። የዚህ ወጣት የህይወት ተሞክሮ መቼም የሁሉንም ከስደት ተመላሾች ይወክላል ባይባልም ከእጅ ወደ አፍ በሚኖርባት፣ በርካቶች ስራ አጥ በሆኑባት ሃገራችን ግን የአብዛኛው ተመላሽ ተመክሮ ተመሣሣይ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይገድም። ባለፉት ቀናት መንግስት ከ90ሺህ በላይ ዜጐችን ወደ ሃገር ቤት መመለሡ ታውቋል። ገና የሚመለሡም አሉ፡፡ እነዚህ ዜጐች እዚያ ሃገር ሠርተው በሚያገኙት ገቢ ስንት ማቲያቸውን እንደሚያስተዳድሩ፣ ስንት የተራበ ጉሮሮ ይደፍኑ እንደነበር ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ “ህይወቴ ተቀየረ፣ ኑሮዬ ተሻሻለ፣ አዲስ ብርሃን እየበራልኝ ነው” ሲሉ መልሶ የጨለመባቸውን፣ ለመሄጃ የተበደሩትን እንኳ ሣይመልሡ ከድጡ ወደ ማጡ መግባታቸውን እያሰቡ የሚቆዝሙ ቁጥራቸው ቀላል እንደማይሆን ለመገመት ጥልቅ ተመራማሪነትን አይሻም፡፡ በአንድ አለማቀፍ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ በከፍተኛ የኢኮኖሚ ኤክስፐርትነት የሚሠሩት አቶ ይስማው በላይ፤ የስደት ተመላሾቹ ጉዳይ መንግስት በተገቢው ትኩረት ካልያዘው የሚፈጥረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ቀላል አይደለም ይላሉ፡፡ እነዚህ ወደ 100ሺ የሚጠጉ ከስደት ተመላሽ ወገኖች፣ በስራቸው የሚያስተዳድሩት ቤተሠብ በርካታ ነው።

የተመላሾቹ በኢኮኖሚ መጐሣቆል በቀጥታ ተጐጂ የሚያደርገው ቤተሠባቸውን ነው፤ ከዚያም ሲያልፍ ሃገርን ይጐዳል የሚሉት አቶ ይስማው፤ በተለይ በመንግስት ላይ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደሚያስከትል ያስረዳሉ - በአንድ ወቅት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከሃገሪቱ የውጪ ንግድም በላይ የውጭ ምንዛሬ ማስገባታቸውን በማስታወስ። የኢኮኖሚ ባለሙያው፤ በመንግስት በኩል የተለያዩ የስራ ፈጠራ ፖሊሲዎችን እስከ መፈተሽ የሚደርስ እርምጃ ሊወሠድ ይገባል ይላሉ፡፡ በቂ እና ቋሚ የስራ እድል መፍጠር፣ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ በሚፈቅደው ልክ የክፍያ ማሻሻያዎች የመሣሠሉትን አማራጮች መፈተሽ የግድ ነው፡፡ የግል ባለሃብቶች ከጥቃቅን የንግድ ተቋማት ወጥተው በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጐች የስራ እድል መፍጠር የሚችሉ ፋብሪካዎችንና የኢንዱስትሪ ተቋማትን መገንባት እንዲችሉ በመንግስት በኩል ሊበረታቱ ይገባል። መንግስት በጀመራቸው ግዙፍ የመሠረተ ልማት ግንባታ ላይ ተሣታፊ እየሆኑ ያሉ ዜጐች፣ የቀን ክፍያም በቀጣይ ሊታሠብ የሚገባው ነው የሚሉት ባለሙያው፤ አሁን ያለው የ35 እና የ40 ብር የቀን ክፍያ ከኑሮ ውድነቱ አንፃር እንኳን የቤት ኪራይና አልባሣትን የመሣሠሉ ወጪዎችን ሊሸፍን ቀርቶ የእለት ጉርስን እንኳ ማሟላት አይችልም ይላሉ፤ በቀን 40 ብር ከምሣና ከቁርስ ወጪ የማያልፍ መሆኑን በማስታወስ፡፡ ታዲያ ኑሮው ከእለት ገቢው ካልተስማማ ስደትን ያላየው ለማየት ቢጓጓ፣ ገፈቱን የቀመሠው እንዲህ መልሶ ልቡ ሲቆም እንዴት እንኮንነው? መንግስት በይፋ የስደት በሩን ለጊዜው ዘግቻለሁ ብሎ ባወጀ ማግስት እንኳን እግር ጥሎት ሜክሲኮ አካባቢ ወደሚገኘው የሱዳን ኤምባሲ ያመራ የስደት አላሚዎችን ረጅም ሠልፍ ማየቱ አይቀርም። መንግስት ለጊዜው በሩን ቢዘጋም በሱዳን በኩል ህጋዊ በሚመስል መልኩ የተከፈተ መስኮት አለ፤ ይህ ቀደም ብሎ የነበረ መስኮት ቢሆንም መንግስት በሩን ሲዘጋ ደግሞ የበለጠ ስራ በዝቶበታል፡፡ ወጣት እንስቶቻችን ወደ ቤሩት፣ ዱባይ፣ ባህሬን የመሣሠሉ ሃገራት ለመሄድ “የሁለት ወር የሱዳን የሽርሽር ጊዜ ቆይታ” የሚል ቪዛ ይሠጣቸዋል፡፡ ከዚያም የሞላላቸው በአውሮፕላን ጐንደር ድረስ ሄደው፣ በመተማ አድርገው፣ ወደ ካርቱም በደላሎች አቀባባይነት በመኪና ይገሠግሣሉ።

ካርቱም ላይ የሚቀበሏቸው ደላላዎች ደግሞ ወደ አረብ ሃገራቱ አሣፍረው ይልኳቸዋል፡፡ አብዛኞቹ በአዲስ አበባ ያሉ ይህን ስራ የሚሠሩት ደላሎች ሱዳናውያን እንደሆኑ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ ባለፈው ሳምንት በስደት ዙሪያ ሃሣባቸውን ያካፈሉት የፖለቲካል ሣይንስ ምሁሩ እና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ዶ/ር መራራ ጉዲና፤ ሃገሪቷ የስደት ሃገር የሆነችው መንግስት የስራ እድል ባለመፍጠሩ ነው ብለዋል፡፡ አደገ የሚባለው ኢኮኖሚም የኑሮ ውድነትን ከማባባስ ውጪ በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ ያመጣው የኢኮኖሚ ለውጥ አለመኖሩን ዶ/ር መረራ ገልፀዋል፡፡ የስደቱ መንስኤ በሃገራችን በቂ የስራ እድል አለመፈጠሩ ነው የሚሉት የባንክ ባለሙያውና የቀድሞው የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሠሙ በበኩላቸው፣ ዜጐቹ በመንግስት እርዳታ መመለሣቸው በበጐ ጐኑ የሚታይ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሃገሪቱ ምቹ የስራ እድል ባልተፈጠረበት ሁኔታ ችግሩ መከሰቱ የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት በቀላሉ የሚታይ አይደለም ይላሉ። እነዚህ ሠዎች ሲሠደዱ ሃብት ንብረታቸውን ሸጠው፣ ከዘመድ ወዳጅ ገንዘብ ተበድረው ሊሆን እንደሚችል የጠቆሙት አቶ ሙሼ፤ ያለ ጥሪት መመለሣቸውን ተከትሎ እዳዬን መልስ አትመልስ በሚል ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል ይላሉ። አቶ ሙሼ እንደሚሉት፤ እዚህ የሚገጥማቸውን ኑሮ ለማሸነፍም ወደ አልተገባ የስራ ባህሪ ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ የመፈጠር እድሉም ሠፊ ነው፡፡ ማህበራዊ ቀውሡ፣ የኢኮኖሚ ጥያቄን ለመመለስ የሚፈጠር ትንቅንቅ እንዲሁም የደረሠባቸው ስነ ልቦናዊ ቀውስ ከመንግስት ጋር እስከ መጋጨት የሚያደርስ ችግር ሊፈጠር ይችላል። “እነዚህን ሠዎች መልሶ ማቋቋም ቀላል አይደለም” የሚሉት አቶ ሙሼ፤ መንግስት አሁን ቀላል አስመስሎ እያቀረበው ቢሆንም የሠጣቸው የትራንስፖርት አበል እንኳ በአግባቡ ሃገራቸው የሚያደርሣቸው አይደለም ይላሉ፡፡

ከዚህ ባለፈም መንግስት ይሄን ያህል ሠው ቀርቶ 1ሺህ እና 2ሺህ የማይሞሉ ተፈናቃዮችን እንኳ የማቋቋም ብቃቱም ልምዱም የለውም በማለት አቶ ሙሼ ስጋታቸውን ይገልፃሉ፡፡ “በጦርነት እና በተፈጥሮ ጉዳት ካልሆነ በስተቀር በዚህ መልኩ የተፈናቀሉ ሠዎች ስለመኖራቸው በታሪክ አላስታውስም” የሚሉት አቶ ሙሼ” ለተፈናቃዮቹ የስደተኞች ጠባቂ ድርጅቶች የሚያደርጉት እገዛ ከጊዜያዊነት ያለፈ አይደለም ይላሉ። ጊዜያዊ ድጋፍና ማቋቋም የተለያዩ ነገሮች ስለሆኑ መንግስት የማቋቋሙን ስራ በፕሮጀክት መልክ ቀርፆ፣ ገንዘብ መድቦ በጥልቀት በማሠብ ሊሠራ ይገባል ብለዋል። መንግሥት ከስራ ፈጠራ ጋር በተያያዘ ጉድለት እንዳለበት በይፋ ያመነ ይመስላል፡፡ በቅርቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፤ “እውነቱን እንነጋገር ከተባለ መንግስት ስራ መፍጠር መቻል አለበት” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ እንዴት? መቼ? የሚሉት ግን አፋጣኝ ምላሽ የሚሹ አንገብጋቢ የወቅቱ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ከንግግርና ከፕሮፓጋንዳ በላይ የሆኑ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች የግድ ይላሉ - ያውም በብልህነትና በአርቆ አስተዋይነት የተሞሉ!!

Read 2591 times