Saturday, 30 November 2013 12:04

አዝናኝ ወግ ከዳንኤል ጋጋኖ ጋር

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(11 votes)

በራሱ ላይ መቀለድ የሚችለው አርቲስት
ዳንኤል ታደሰ ይባላል፡፡ ብዙዎች “ጋጋኖ” በሚል ቅፅል ስም ይጠሩታል። በተለያዩ ቴአትሮችና ፊልሞች ላይ በመተወን

የሚታወቅ ሲሆን በተለይም “ሳምራዊ” በተሰኘ ፊልም ላይ በመተወን ይበልጥ ዝነኝነትን አትርፏል፡፡ ለየት ያለ የሰውነት

አቋም ያለው ዳኒ ጋጋኖ፤ ራሱን በመተረብና ሰዎችን በማሳቅ ይታወቃል፡፡ “አንዳንዴ ራሴን ስስለው ባለ ቆቡን ምስማር

የምመስል ይመስለኛል” ከሚለው አርቲስት ዳንኤል ጋጋኖ ጋር የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ቀጣዩን አዝናኝ

ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡

ራስህን አስተዋውቀን?
ዳንኤል ታደሰ በላይነህ እባላለሁ፡፡ አዲስ አበባ ጋንዲ ሆስፒታል ተወልጄ፣ አዲሱ ገበያና ደጃች ውቤ ነው ያደግሁት፡፡
የአባትህ ስም ጋጋኖ ይመስለኝ ነበር፤ ቅጽል ስምህ ነው እንዴ? ዳኒ ጋጋኖ ስትባል  እሰማለሁ..
ድሮ ፑሽኪን የሚታይ “ዶክተር ጋጋኖ” የተሰኘ አንድ ቴአትር ሰርቼ ስለነበር፣ በዛው ጋጋኖ ተብዬ ቀረሁ፡፡ ብዙ ሰው ዳኒ

ጋጋኖ ይለኛል፡፡
መቼ ነው ቴአትሩን የሰራኸው?
ጊዜው ትንሽ ቆየት ብሏል፡፡ ትርጉሙ የጋሽ አያልነህ ሙላት ነው፤ የኒኮላይ ጐጐልን ድርሰት ተርጉሞ በቴአትር መልክ

አቅርቦት ነበር፡፡ እዛ ላይ ዶ/ር ጋጋኖን ሆኜ ተጫውቻለሁ፡፡
ትምህርትህን የት ነው የተማርከው?
ቤተልሄም፣ ራስ አበበ፣ ዘርፈሽዋል እና መነን ት/ቤቶች ተምሬያለሁ፡፡  
የአዲስ አበባን ት/ቤቶች አዳርሰሃቸዋላ?
ት/ቤቶቹን ብቻ ሳይሆን ያደግኩትም ብዙ ሰፈር ነው፡፡ ከላይ አዲሱ ገበያንና ደጃች ውቤን ጠቀስኩልሽ እንጂ ብዙ ሰፈር

ነው ያደግኩት፡፡  
ወደ ጥበብ የገባህበት አጋጣሚ ምን ይመስላል?  
ወደሙያው የገባሁት እንደቀልድ ነው፡፡ ት/ቤት ውስጥ አንዳንድ ተሳትፎዎች ነበሩኝ፤ እነሱም ቢሆኑ እንደ ቀልድ

የሰራኋቸው ነበሩ፡፡ ግን እያደር እያመረርኩ መጣሁ፡፡ ከዚያ በኋላ እነ ቴዎድሮስ ለገሰ የነበሩበት “ዩኒቲ” የተሰኘ የቴአትር

ክበብ ተከፍቶ ነበረ፡፡ “የልብ እሳት” ቡድኖችን ተቀላቀልኩኝ፡፡ የቀልድ የነበረው ጅማሬ ይህን ቡድን ስቀላቀል ወደ

እውነት ተቀየረ፡፡
“ዶ/ር ጋጋኖ” … የመጀመሪያ ስራህ ነበር?
አይደለም፤ ከዚያ በፊት ሌሎች ቴአትሮችን ሰርቻለሁ፡፡ የመጀመሪያ ስራዬ “የልብ እሳት” ቴአትር ነው፡፡ ቀጥሎ “ዋናው

ተቆጣጣሪ” የተሰኘ ቴአትር የሰራሁ ሲሆን በየክልሉ እየተዘዋወርን እናሳይ ነበር፡፡ እኔም የተለያዩ ገፀ ባህሪያትን

እየቀያየርኩ አዘጋጁ ባስገባኝ ቦታ ሰርቼአለሁ፡፡ የተፈሪ አለሙ ትርጉም የሆነው “አሉ” ቴአትር “የቀለጠው መንደር”

ከዶክተር ጋጋኖ በፊት የሰራኋቸው ናቸው፡፡ ሌላው “የአራዳ ትዝታ” በሚል ከአንጋፋ አርቲስቶች ጋር ትዊስት ዳንስ

ሰርቻለሁ፡፡ ማስተር ሳውንድ ሙዚቃ ቤት ነው ቪሲዲውን ያሳተመው፡፡ በዚህ ስራ ላይ ችሮታው ከልካይ፣ በላይነሽ

አመዴ (ኩንዬ)፣ ሙናዬ መንበሩ፣ ፍሬ ህይወት ባህሩ፣ ፋንቱ ማንዶዬና ሌሎች አንጋፋ አርቲስቶች አሉበት፡፡ ምን

አለፋሽ … እኔ ብቻ ነኝ ወጣት ሌሎቹ አንጋፋዎች ናቸው፡፡ የሚገርም ስራ ነው፡፡
ዳንስ ስትል መድረክ ላይ ነው?
በፊት “የቀለጠው መንደር” ላይ ስሰራ፣ ዳንስ መለማመድ እንደምፈልግ ተናግሬ፣ ሀገር ፍቅር ቴአትር ውስጥ

ተለማመድኩ፡፡ አንድ ጊዜ እንደውም ለአዲስ አመት ሀገር ፍቅር  ቴአትር ቤት ዳንስ አቅርቤያለሁ፡፡
ለዳንስ ሰውነትህን በደንብ ማዘዝ ትችላለህ?
በምንም መልኩ አያስቸግረኝም፤ በደንብ አዘዋለሁ፡፡ በቃ ሰውነቴን ላስቲክ በይው፡፡
ብዙ ሰዎች እንደሚሉት፤ እኔም እንዳስተዋልኩት ከሰውነት አቋምህ ጋር በተያያዘ በራስህ ላይ መቀለድ ታበዛለህ፡፡

“ቀልድና ጽዳት ከራስ ሲጀምር ጥሩ ነው” ብለህ ነው?
በእኔ እምነት በሰው ከመቀለድ በራስ መቀለድ ቀላልም ጥሩም ነው፡፡ የእኔ ሰውነት ደግሞ ራሴ ከቀለድኩበት ለቀልድ

የተመቸ ነው፡፡
እንዴት ማለት?
አንዳንድ ሰዎች ለማንጓጠጥ ብለው ወይም በስድብ ፎርማት የሚናገሩትን አርቲስቲክ ማድረግ ጥሩ ነው፡፡ ይህን ሳደርግ

ሰዎችም ዘና ይላሉ፤ እኔም እዝናናለሁ፡፡
እስቲ በራስህ ላይ ከቀለድካቸው ጥቂቱን አጫውተኝ…
“ከኋላ ለሚያዩኝ ባለቆቡን ምስማር ልመስል እችላለሁ፣ ከመሃል ለምታዩኝ ደግሞ ዣንጥላ እመስላችሁ ይሆናል፡፡ ከፊት

ለፊቴ ያላችሁ ያላለቀ ኮንዶሚኒየም ስለምመስል ያለሁበትን ሳይት ለማወቅ እየተነጋገራችሁ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡” ስል

ሰዎች በሳቅ ይሞታሉ፡፡
“ባለቆቡን ምስማር እመስላለሁ” ስትል ከምን ተነስተህ ነው? ወይስ ሰዎች ትመስላለህ ብለውህ ያውቃሉ?
አንዳንዴ ራስሽም እኮ ትፈጥሪያለሽ፡፡ ፀጉሬን ፈትቼ ስለቀው ጅፍ ይላል እና ከሩቅ ሲያዩኝ ባለቆቡን ምስማር

እንደምመስል ለራሴ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ራሴን ስስለው እንደዛ ይሰማኛል፡፡
አንተ ከምትለው ውጭ ጓደኞችህ ተርበውህ ያውቃሉ? ማለቴ ለየት ያለ ነገር …
ይገርምሻል፤ እነሱ እንደውም አይተርቡኝም፡፡ እኔ ራሴን ስተርብ ግን በጣም ይዝናናሉ ይስቃሉ፡፡
ከሁለት ወይም ከሶስት አመት በፊት ጅማ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ አንድ ፕሮግራም ላይ ተገናኝተናል እናም ስታንድ አፕ

ኮሜዲ አቅርበህ ሰዎችን ስታስቅ ነበር፡፡ እስቲ ስለዛ መድረክ ትንሽ አጫውተኝ?
እንዳልሽው ሁለት ወይም ሶስት አመት ይሆነዋል፡፡ የጅማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ኤችአይቪ ኤድስ ላይ የምትሰራ

አምባሳደር ሞዴል ለመምረጥ ባዘጋጁት ፕሮግራም ላይ “ሶል ኤጀንት” የተባለ ድርጅት ነው የወሰደን፡፡ እንደውም

በመድረክ ላይ ደፍሬ ቀልድ  ሳቀርብ የመጀመሪያዬ ይመስለኛል፡፡ ከአለባበሴ ጀምሮ ለየት ብዬ ለመቅረብ ሞክሬያለሁ።

ቅድም እንዳልኩሽ ነው ቀልዱ፡፡ “ከኋላ ላላችሁ ባለ ቆቡን ምስማር ልመስል እችላለሁ፤ ከመሀል ላላችሁ ጃንጥላ፤ ከፊት

ለፊቴ ላሉት ያላለቀ ኮንዶሚኒየም ቤት እየመሰልኳቸው ይነጋገራሉ፡፡ ከሁለም የገረመኝ ከመድረክ ጀርባ አብረውኝ

የሚሰሩት ልጆች የሚያወሩት ነው፡፡ ግማሾቹ ዝናብ የመታው አውራ ዶሮ ይመስላል ይላሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ አስፋልት ዳር

የበቀለ ጥድ ነው እያሉ ሲከራከሩ ይሰማኛል” እያልኩ ነበር ያ ሁሉ ሰው ሲስቅ የነበረው፡፡ “ለማንኛውም እዚህ መሀላችሁ

ያቆመኝ የቅርስ ጥበቃና ባለደራ ባለስልጣን ሲሆን ዋና አላማው ከሙዚየም የማይወጡ ቅርሶችን እንደኔ ባለ ተንቀሳቃሽ

ቅርስ ለመለወጥ ባለው ፅኑ ፍላጐት ነው” ስል የነበረውን የሳቅ ሁካታ በቦታው ስለነበርሽ ታስታውሽዋለሽ። እንዲህ

እንዲህ እያልኩ ነው ቀልድ የጀመርኩት፡፡
በነገራችን ላይ አሁን ያለህን የሰውነት አቋም የያዝከው ስትወለድ ጀምሮ ነው ወይስ ከተወለድክና ካደግክ በኋላ?
ቤተሰቦቼ እንደነገሩኝ ከሆነ ኖርማል ነበርኩኝ፤ በህፃንነቴ ከሰራተኛ እጅ ላይ አምልጬ ወድቄ በደረሰብኝ ጉዳት ነው

ይህን አይነት አቋም ሊኖረኝ የቻለው፡፡ በፊት በፊት አንገት የሚደግፍ ነገር ነበረኝ፤ ካደግሁ በኋላ ትቼው ነው፡፡ ምቾት

ስለማይሰጠኝ እያለቀስኩ ሳስቸግር አውጥተው ጣሉልኝ፡፡
ባለህ የሰውነት አቋም የተነሳ ምን የሚሰማህ ነገር አለ?
በነገራችን ላይ እንደዚህ መሆኔ ራሱ ትዝ አይለኝም! ትዝ የሚለኝ ራቁቴን ሆኜ በቁም ሳጥን መስታወት ፊት ስቆም ብቻ

ነው፡፡ ራሴን እንደረጅም ሰው ነው የምቆጥረው እና አስቤውና አሰላስዬው አላውቅም፡፡
እኔም ሆንኩ ብዙ ሰው በትወና ያውቅሀል ብዬ የማስበው በ“ሳምራዊ” ፊልም ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት ላይ ነው፡፡

በዚህ ፊልም ላይ የአስተናጋጁን ገፀባህሪ ተላብሰህ ለመጫወት እድሉን እንዴት አገኘህ?
በወቅቱ የፊልሙ ባለቤት አርቲስት ዮሐንስ ፈለቀ “ሳምራዊ” ፊልምን መስራት ይፈልግ ነበርና ከ“ስርዬት” ደራሲ ደረጀ

ፍቅሩ ጋር ይገናኛሉ፡፡ እኔም ለአስተናጋጅነት ካስት ተደረግሁኝ፡፡ በዛን ጊዜ የምተውናት ክፍል በጣም አጭር ነበረች፡፡

ዮሀንስና ደረጀ ከተወያዩ በኋላ፣ እኔ የምጫወተውን ክፍል በደንብ አሰፉት፡፡ ጥሩ ተጫወትኩት፡፡ በዚህ የተነሳ

ለ“ሳምራዊ” ቁጥር ሁለት ፊልም ታጭቼ እሱንም ሰራሁ ማለት ነው፡፡
“ሳምራዊ” ቁጥር አንድ ላይ አስተናጋጅ ሆነህ ስትሰራ የሚያስፈራሩህ ሰዎች ራቁትህን ይዘውህ ስትንቀጠቀጥ ይታያል፡፡

እኔ ልክ እንዳየሁህ ደንግጬ ነበር፡፡ በወቅቱ የሌሎች ተመልካቾች ስሜት እንዴት ነበር? የደረሰህ አስተያየት ካለ

ብትነግረኝ?
እውነቱን ልንገርሽ … ብዙዎች የሰውነት ቅርፅ ተወዳደርበት ነው ያሉኝ፡፡ ይህንን ሰውነት ይዘህ ቁጭ ትላለህ እንዴ

ብለው ወቅሰውኛል፡፡ አንቺ ላታምኚኝ ትችያለሽ፤ አንዳንዶቹ ጩኸታቸውን ለቀውታል፤ ሌሎቹ እንዲህ አይነት ሰው

ራቁቱን ስናይ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ እና ቁጭ ብዬ ፊልሙን እንደተመልካች ሳይ፣ ልክ ራቁቴን

ስመጣ ተመልካቹ ሁሉ ጩኸቱን ይለቀዋል።
ለምን ይመስልሀል?
አንቺ ለምን ይመስልሻል፤ ቅርፄን ወደውት ነዋ! አንዳንዴ እኔን ያዝናናኛል፡፡ እኔን ካዝናናኝ ሌላውም እንደሚዝናና

ይሰማኛል፤ ዘና ያለ ስሜት ይፈጥርብኛል፡፡ ምክንያቱም አንቺ በምትፈጥሪው ነገር ሰዎችን ማዝናናት ከቻልሽ የበለጠ

ፈጠራ ለመስራት ትተጊያለሽ፡፡ እኔ ስንፍና ነው እንጂ ብዙ መስራት እችል ነበር፡፡ ለምሳሌ ጓደኞቼ የስልካቸው ባትሪ

ሲያብጥ “ወይኔ ባትሪው ጐበጠ” ሲሉ ዞር ብዬ አትሳደቡ እላቸዋለሁ፤ ወዲያውኑ ሳቅ ይጀመራል። እነሱ ስለ ባትሪው

መጉበጥ ነው በትክክል የሚያወሩት፤ ሳያስቡት ከራሴ ጋር አገናኝቼ ስናገር ይስቃሉ እና ለፈጠራ ነው የምትዘጋጂው፡፡
ከ“ሳምራዊ” ፊልም በኋላ ምን ሰራህ?
ከሳምራዊ በኋላ “ላገባ ነው”፣ “ማቶት”፣ “ላም አለኝ” የተሰኙ ፊልሞች ላይ ሰርቻለሁ፡፡ “ላም አለኝ” የቤዛ ሀይሉ ፊልም

ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ቤዛን ላመሰግናት እፈልጋለሁ፡፡ በጣም ጠንካራ ልጅ ናት፡፡ ይህ ፊልም ሁለተኛዋ ነው፡፡

ልትበረታታ ይገባታል፡፡ የደረጀ ፍቅሩ “አፍሮኒዝም” የዮሀንስ ፈለቀ “ሄሎ ኢትዮጵያ” ፊልም ላይም ሰርቻለሁ። “ሄሎ

ኢትዮጵያ” አሁንም በዓለም ሲኒማ እየታየ ይገኛል፡፡ በዚህ ፊልም ላይ ለራሱ ህይወት ግዴለሽ የሆነን ልጅ ገፀ-ባህሪ ነው

የተጫወትኩት፡፡ ግዴለሽ ሆኖ ግን የሚፈጥራቸው ነገሮች ለሌሎች ሰዎች ጥሩና ጠቃሚ ይሆናሉ እና ገፀ-ባህሪውን

እወደዋለሁ፡፡
አጫጭር ዘጋቢ (ዶክሜንታሪ) ፊልሞችን እንደሰራህ ሰምቻለሁ …  
አዎ ሰርቻለሁ፡፡ ከስፔናዊያን ጋር ነው የሰራሁት፡፡ ይህን ስራ አርቲስት ዮሐንስ ፈለቀ ነው ያገናኘኝ፡፡ በመጀመሪያ እኔና

አርቲስት ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) ያለንበት “where is my dog?” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ሰራሁ፡፡ ዩቲዩብ ላይ

ብትገቢ ታገኝዋለሽ፡፡ ቀጥሎ “Children” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ሰራሁ፡፡ አሁን በቅርቡ ደግሞ ከስፔናውያኑ ጋር “ችግር

አለ” የሚል ዘጋቢ ፊልም ሰርቻለሁ፡፡ አዶልፍ ሂትለርን ሆኜ ነው የተጫወትኩት፡፡ ስፔን አገር ተወዳድሮ አንደኛ ወጥቷል

ፊልሙ፡፡ እነዚሁ ስፔናዊያን በቅርቡ ሙሉ ፊልም ለመስራት በጀት መድበው ይመጣሉ፡፡
ጥሩ ተከፈለህ ታዲያ?
በጣም የተጋነነ ጥቅም አታገኚም ግን ያለው ነገር ያበረታታል፡፡ ከስፔናዊያኑ ጋር ስሰራ ከገንዘቡ ይልቅ ለአክተሮች

ያላቸው መረዳት ያስደንቃል፤ ያስደስታል፡፡ አንዳንዴ ስሰራ ይደነቃሉ፡፡ “እንዲህ አይነት ልጅ ማግኘት ያስደንቃል”

ይላሉ፡፡ በውጭው አለም ብትኖር ምን አይነት እድሎች ይኖሩህ ነበር ይሉኛል፡፡ አረዳዳቸው አብሬያቸው እንድሰራ

ይገፋፋኛል፡፡ በቅርቡ ይመጣሉ፤ እዚህ ሲመጡ ማናጀራቸው ዮሐንስ ፈለቀ ነው፡፡
እስካሁን ትወናው ላይ ነው የታየኸው፡፡ ፊልም (ቴአትር) መፃፍና ማዘጋጀትስ አትሞክርም?
ፑሽኪን በነበርኩበት ጊዜ እዚያ የሚታዩ ስራዎችን ነበር የምፅፈው፡፡ አሁን አሁን ፊልሞች ሲሰሩ ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ

የሚሰሩት ስራ ላይ ሀሳብ የማዳበር፣ ሀሳብ የማዋጣት ስራዎችን እሰራለሁ። አንዳንዴ ስንፍናውም አለ እንጂ ሀሳቡ

ይኖራል፡፡
በባህሪህ ምን አይነት ሰው ነህ? ዝምተኛ ወይስ ተጫዋች?  
አይ … እኔ እንኳን ክፍት አፍ ቢጤ ነኝ፡፡
እንዴት?
ዝም ካልኩ መናገር የማልችል ዲዳ የሆንኩ ስለሚመስለኝ እለፈልፋለሁ፡፡ አወራለሁ፡፡  
አሁን ከማን ጋ ነው የምትኖረው? ለቤተሰብህ ስንተኛ ልጅ ነህ? ትዳር ይዘሀል?
ከቤተሰቦቼ ጋር ነው የምኖረው፤ አምስተኛ ልጅ ነኝ፡፡ ገና አላገባሁም፡፡
የማግባት ፍላጐት የለህም?
አለኝ ግን ዝም ብሎ ይገባል እንዴ? እንዴት ያለ ነገር ነው? ጊዜና ወቅት አለው፡፡
እድሜህ ስንት ነው?
ሰላሳዎቹን እያለፈ ነው፤ ወደ 34 አካባቢ ነኝ  
ታዲያ ከዚህ በላይ ምን ይጠበቃል?
ቀንድ!
ቀንድ ካላወጣህ አታገባም ማለት ነው?
መሆኑ ነዋ!
ፍቅረኛ ነበረችህ?
ነበረችኝ፡፡ ከቤተሰቧ ጋር ውጭ ሄደች፤ ተለያየን፡፡ አሪፍ ሰው ነበረች፤ አሁን አንገናኝም፡፡ ሌላ ጓደኛም አልያዝኩም፡፡
እሷን እየጠበቅህ ነው ወይስ ፍቅር እንደኩፍኝ በልጅነትህ ወጣልህ?
አልወጣልኝም፤ ወጣ ገባ እያለ ነው
ስለ ፍቅር ስታስብ የሚያስገርምህ ነገር አለ?
ስታፈቅሪ ያፈቀርሻትን ሴት ወንድሟ ሲያቅፋት እንኳን ትናደጃለሽ እኮ፡፡ ወንድሟ መሆኑን እያወቅሽ እኮ ነው፡፡ ካለፈ

በኋላ ግን ያስቅሻል፤ ምን ነክቶኝ ነው ትያለሽ፡፡
በስራ ላይ እያለህ በርካታ አዝናኝ፣ አስገራሚና አሳዛኝ ገጠመኞች ሊኖሩህ እንደሚችሉ እገምታለሁ። እስቲ ከገጠመኞችህ

አካፍለኝ …
ብዙ አጋጣሚዎች አሉ፡፡ አንዳንዴ እስከ ህይወት ማጣት የሚቀርቡ ገጠመኞች ይኖራሉ። ለምሳሌ “የአፍሮኒዝም” ፊልም

የመጨረሻው ቀን ቀረፃ ላይ ነው ነገርዬው የተከሰተው፡፡ ትዕይንቱ ላይ አንዱ ካራቲስት ከፊት ይዞ ኋላ ላለው ካራቲስት

ነው የሚወረውረኝ፡፡ ቀረፃው ተጀምሯል፡፡ የፊተኛው ይዞ ሲወረውረኝ የኋለኛው ፈፅሞ ረስቶኛል፡፡ ስለዚህ

እንደወረወረኝ ሄጄ በጭንቅላቴ ድንጋይ ላይ ቆምኩኝ፡፡ በእግሬ አይደለም ያልኩሽ በጭንቅላቴ ነው፡፡
ከዚያስ ተረፍክ?
ተርፌማ ነው አሁን የማዋራሽ፡፡ ካሜራ ማኑ በድንጋጤ ካሜራውን ለቆታል፡፡ ተስፉ ብርሃኔ “በመድሀኒያለም” ብሎ

መሬት ላይ ቁጭ አለ፡፡ ሌሎቹ የሚይዙ የሚጨብጡትን አጥተዋል፡፡ እኔ እራሴ የዛን ቀን ያየሁትንና የተብለጨለጨብኝን

የከለር አይነት ድጋሚ የማየው አይመስለኝም፡፡ የእኛ አገር ፊልም ያው ኢንሹራንስ የለውም፡፡ ብትሄጂም በቃ እስካሁን

ተረስተሽ ነበር፡፡ እስክረጋጋ ተቋረጠና ቆይተን ቀረፃው ተጀመረ፡፡
ሌላ ገጠመኝ?  
“ሄሎ ኢትዮጵያ”ን እየሰራን ነው፡፡ ከከተማ ውጭ ነው፡፡ አንዱ ሄዶ ሳያስፈቅድ የሰው ፈረስ ይዞ ይመጣል፡፡ ለቀረፃው

ፈረስ ያስፈልግ ነበር፡፡ የፈረሱ ባለቤት የድንጋይ እሩምታ ጀመረ፡፡ ከዚያ ሲያግዙን የነበሩትም የአካባቢው ሰዎች

ለሰውየው ተደርበው፣ እኛን በድንጋይ ጠመዱን፡፡ እግሬ አውጭኝ ብለን ፖሊስ ጣቢያ ገባን፡፡
ከመሀላችሁ የተጐዳ ነበር … በድንጋይ ውርወራው?
በአጋጣሚ አልተጐዳንም፤ በኋላማ የጨበጣ ውጊያ ሆነ፤ እጅ በእጅ ተያያዝን እኮ፡፡ ፈረንጆቹ ሁሉ መደባደብ ጀመሩ፡፡
ፈረሴን መልሱ ማለት ሲገባው፣ ሞቅ ብሎት መጥቶ ድንጋይ ነው ያነሳው። በአገራችን ፀጉረ ልውጥ መሆናችን የገባን ያን

ጊዜ ነው፡፡
ገጠመኞችህ ተመችተውኛል፤ ሌላ ገጠመኝ ይኖርሀል?
አንድ ጊዜ “ሳምራዊ” ፊልምን ስንቀርፅ ጅብ አጋጠመን፡፡ ምሽት ላይ ነው ቀረፃው፡፡ ጫካ ውስጥ ነው፡፡ መጀመሪያ

መብራት ሲበራ ምንም ነገር አልነበረም፡፡ መብራት ሲጠፋ ጅቦች ከበውናል፡፡  
ስንት ናቸው?
ሶስት ወይም አራት ይሆናሉ፡፡ ከዚያ መጯጯህ ተጀመረ፤ ማን ያረጋጋ?
ወንዶች አይደላችሁም እንዴ? ምን እንዲህ ያደርጋችኋል?
እንዴ! ምን ነካሽ ጅብ ቆሞ ወንድነት አለ እንዴ? አልሞከርሻትም ያቺን ስሜት … ሽንትሽ እኮ ነው የሚመጣው፡፡
መጨረሻ ላይ እንዴት ሆናችሁ? ከመሀላችሁ ደፈር ያለ የለም?
በእግዜር ኪነ-ጥበብ ተረፍን፡፡ በቃ መሯሯጥ ተጀመረ፡፡ ለነገሩ ጅቦቹ እግዜር ይስጣቸው! ምንም አላሉንም፡፡ በሰዓቱ ግን

በጣም ያስደነግጣል፡፡ ደፈር ያለው ካሜራማኑ ነው፤ ምክንያቱም ካሜራዎቹ የእሱ ናቸዋ! ምን ያድርግ?
ዳይሬክተሩ ዮሀንስ ፈለቀስ ሮጠ?
አይባልም እንጂ ያልሮጠ የለም፡፡ አንድ ሌላ ገጠመኝ ልጨምርልሽ?
አርገኸው ነው?
አንዴ ደግሞ “Where is my dog”ን ለመቅረፅ ቆሼ የሚባለው ቦታ (ረጲ ነው መሰለኝ የሚባለው) ሄድን፡፡ ቆሻሻው

አካባቢ ቆሜ ቀረፃው እየሄደ ሳለ፣ አንድ ትልቅ ጆፌ አሞራ ይዞኝ ሊሄድ ሲል እግዜር ነው ያተረፈኝ፡፡ እኔ ምን መስዬ

እንደታየሁት አላውቅም፡፡ በጣም ነበር የደነገጥኩት፡፡ ብቻ አሁን አላስታውስም እንጂ ብዙ አስገራሚ ገጠመኞች ነበሩኝ፡፡

ሳስታውስ እነግርሻለሁ፡፡
ቤተሰብህ በስራህ ዙሪያ ድጋፍ ያደርግልሀል?
ስጀምር ደስተኞች አልነበሩም፡፡ እንደማንኛውም ቤተሰብ ዶክተር እንድትሆኚላቸው ነው የሚፈልጉት። ነገር ግን በስራዬ

እያሳመንኳቸው መጣሁ፤ አሁን ደስተኛ ናቸው፡፡
እንደ ጋዜጠኛም ያደርግሀል ልበል?
በትንሹ! ዮፍታሄ ሲኒማ ያሳትመው የነበረውን “ዮፍታሄ” መፅሄት ከአንድ ጓደኛዬ ጋር እናዘጋጅ ነበር፤ አሁን ቆሟል፡፡
ካስክ እንዴት እንደሚያቃጥል ቀምሰኸዋላ?
በ“አፍሮኒዝም” ያልቀመስኩት የለም፡፡
ወደፊት ምን አስበሀል?
በቀጣይ መድረክ ላይ ያቀረብኳቸውን ቀልዶቼን በቪሲዲ የማሳተምና ሌሎች ስራዎችንም የመስራት ሀሳብ አለኝ፡፡
ከኮሜዲያን የማን አድናቂ ነህ?
ተስፋዬ ካሳ የማይተካ ኮሜዲያን ነው፤ በጣም አደንቀዋለሁ፤ አብርሀም አስመላሽም ይመቸኛል፡፡ በህይወት ካሉት

ክበበው ገዳን አደንቀዋለሁ፡፡
ቀጠን ያልክ ነህ፡፡ ለመሆኑ ኪሎህ ስንት ነው?
ኪሎ ላይ ወጥቼ አላውቅም፤ እስካሁን በግራም ነው የምመዘነው፡፡  
ልክ እንደወርቅ ማለት ነው?
ታዲያ! እኔስ ወርቅ አይደለሁ እንዴ!
እሱማ ነህ፡፡ ለመሆኑ ምግብ ላይ እንዴት ነህ?
ከጠጠር ውጭ የማልበላው ነገር የለም፤ ያገኘሁትን ነው የምበላው፡፡  
እስካሁን ያላነሳነውና መጨመር የምፈልገው ነገር ካለ?
በስራዬ የሚያበረታቱኝና አይዞህ የሚሉኝን የኪነ-ጥበብ አድናቂዎች አመሰግናለሁ፡፡ ጓደኞቼን ዮሐንስ ተፈራን (ዳጊ

ማኛ)፣ ተስፉ ብርሃኔን፣ ዮሀንስ ፈለቀንና ደረጀ ፍቅሩን በጣም አመሰግናቸዋለሁ፡፡ ሁሌም ከጐኔ በመሆን የጓደኝነት

ፍቅራቸውን ይለግሱኛል፡፡ በርካታ ስራዎችን እንድሰራ ሁኔታዎችን ያመቻቹልኛል፡፡ ከልቤ አመሰግናቸዋለሁ፡፡

እወዳቸዋለሁ፡፡ በመጨረሻም በጣም እንደማከብረው፣ እንደማደንቀውና እንደምወደው እንዲያውቅልኝ የምፈልገው

ከያኒው ፈለቀ የማር ውሀ አበበ፣ መልዕክቴ ይድረሰው፤ አመሰግናለሁ፡፡ 

Read 5657 times