Saturday, 30 November 2013 11:52

የቀዩ ሞት ጭምብል

Written by  ድርሰት - ኤድጋር አለን ፖ ትርጉም - ፈለቀ የማርውሃ አበበ
Rate this item
(4 votes)

ቀዩ ሞት ሀገሬውን ሲያስገብር ነው የኖረው!
እንዲህ ያለ ወዲያውኑ አዋክቦ ፀጥ የሚያደርግ አሰቃቂ ገዳይ፣ እንዲህ አይነት አሰቃቂና ለማየት የሚዘገንን መቅሰፍት

ታይቶም አይታወቅ፡፡ ግብሩ ደም ነበረ - በደም ልክፍቱ ለቅፅበት ተጣብቶ አፍታ ሳይሰጥ በደም አበላ መድፈቅ፡፡ በቃ

ድንገት ጠቅ! የሚያደርግ ህመም ይፈጥርና በጭንቅላት ውስጥ ቅዥብርብር ያለ አዙሪት ይለቅቃል፡፡ ወዲያው በሰውነት

ላይ ምንም አይነት ቁስልም ሆነ ጭረት ሳይኖር፤ ብቻ  ከሰራ አካላት ደም እያንዥቀዥቀ ያዘንባል፤ ከዚያ...ሞት!!

በለከፈው ሰው ገላ፤ በተለይም በፊቱ ላይ እየበሳሳ ከሚፈጥራቸው ፍም የመሳሰሉ ቀዳዳዎች ደም እየተንዥረዥረ ሲወርድ

የሚያዩ ያልተያዙ ሰዎችም ህመምተኛውን ከመርዳት ይልቅ ለመሸሽ ይገደዳሉ፡፡ በፍርሃት ተርበድብደው እግሬ አውጭኝ

ይላሉ፡፡ ልክፍቱ የደረሰበት ግለሰብም ቢሆን ህመሙ ከጀመረው አንስቶ ነፍሱ እስክትወጣ ድረስ የሚቆይበት ጊዜ በጣም

ረዘመ ቢባል ከግማሽ ሰዓት አይበልጥም፡፡
የሀገሪቷ ገዥ የነበረው ፐሬስፔሮ ግን፤ ደስተኛ፣ ጀግና እና ብልህ ሰው ነበር፡፡ በቀዩ ሞት ሳቢያ ከግዛቱ ነዋሪዎች ግማሹ

ህዝብ ማለቁን ሲገነዘብ፤ አንድ ሺህ ያህል ጤንነታቸው የተጠበቀ የመንግስቱን ሹማምንት፡ ዘመድ አዝማዱንና  ባለፀጋ

ወደጆቹን አስጠርቶ፤ አብረውት እንዲኖሩ እርቆ ወደሚገኝ ሌላ ቤተ መንግስቱ ይዟቸው ሄደ፡፡
የህንፃውን ንድፍ እራሱ ፐሮስፔሮ  አዘጋጅቶ፤ዙሪያ ገባው በከበሩ ማዕድናት  ተንቆጥቁጦ እንዲሰራ በሰጠው ቀጭን

ትዕዛዝ በጥንቃቄ የተገነባ አስፈሪ ግርማ ሞገስ ያለው እጅግ ግዙፍ ቤተመንግስት ነበር፡፡ ዙሪያውም ሰማይ የነካ

በሚመስል ጠንካራ የድንጋይ አጥር ታጥሯል፡፡ መግቢያዎቹም በጣም ትልልቅ የብረት በሮች ናቸው፡፡ ክቡር እምክቡራኑ

ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ፤ ከእንግዲህ ከእነርሱ ሌላ ማንም ወደ ውስጥ አልፎ እንዳይገባ በሚያስተማምን ሁኔታ፣ በመዶሻ

እየቀጠቀጡ የመገጣጠሚያ ብሎኖቹንና ቅርቃሮቹን ሁሉ በብርቱ አጠባብቀው ሲያበቁ እሳት አቀጣጥለው፣ ትልልቆቹን

የብረት በሮች  እንዳይላወሱና ነፋስም እንዳያሾልኩ አድርገው በየዷቸው፡፡ ከዚህ በኋላ አሰቃቂው መርገምት፤ ቀዩ ሞት

ያሳደረባቸውን ስጋት ወዲያ አሸቀንጥረው እፎይ አሉ፡፡ ከቤተ መንግስቱ ውጭ ያለውን ዓለም «የራሱ ጉዳይ!» ብለው

ረሱት ፡፡
ፕሮስፔሮ፤ ለተከበሩት ወዳጆቹ፤ ምቾታቸውን የሚጠብቁና እርካታ የሚያስገኙላቸውን አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ

አቅርቦላቸው ነበር፡፡ በቀልዳቸው ለዛ እያዝናኑ ሳቅ የሚያዘንቡ ጨዋታ አዋቂ ዚቀኞች አሉ፤ ስመ ጥር ገጣሚያን ውዳሴ

ቅኔ እየተቀኙ ሀሴት ይዘራሉ፤ እውቅ ድምፃዊያን በመረዋ ድምፃቸው የየዘፈኑን አይነት ያወርዱታል፤ በባሌት የዳንስ

ጥበብ የሰለጠኑ ተወዛዋዦሀት እንደ እንዝርት ይሾራሉ፤ በዜማ ቅኝት የተካኑ የመሣሪያ ተጫዋቾችን ያሰለፈው ኦርኬስትራ

ሙዚቃውን ሌት ተቀን ያንቆረቁረዋል፤ በየቀኑ ጭፈራ አለ፤ ቆነጃጅቶች ተውበው ይሽቀረቀራሉ፤ በየገበታው ላይ እጅ

የሚያስቆረጥም ምግብ በያይነቱ ሞልቶ እንደተትረፈረፈ ነው፤ የወይን ዋንጫዎቻቸው ቲፍፍ ብለው እንደሞሉ ናቸው...

ሁሉ በሽ በሽ! በአይበገሬ የድንጋይ አጥር በተከለለው የቤተ መንግስቱ እልፍኝ ውስጥ ሁሉ ሙሉ ነው፡፡ የከበባቸው

የጠንካራ አጥር ከለላ በዚያ እስከኖሩ ድረስ ስለደህንነታቸው ጉዳይ እንዳይጨነቁ አስተማማኝ ዋስትና ሆኖላቸዋል፡፡

ከቅፅሩ ውጭ ግን ቀዩ ሞት ይንጎራደድ ነበር፡፡
በዚያ፤ ከጭንቀት ነፃ በሆነ ሰላማዊ ሥፍራ መኖር በጀመሩ በአስረኛው ወራቸው መጨረሻ አካባቢ ነበር፣ ፕሮስፔሮ፤

ታላቅ የጭምብል ዳንስ ምሽት አዘጋጅቶ፤ ወዳጆቹን ሁሉ የጠራቸው። ማንኛውም ሰው ባለባበሱ ተውቦ እንዲገኝና ወደ

ዳንስ አዳራሹ በሚገባ ጊዜም ቢቻል ሙሉ ፊቱን ካልሆነ ግን ቢያንስ ዓይኖቹን በጭምብል እንዲሸፍን የጋበዛቸውን

ክቡራን ወዳጆቹን ጠይቋል - ፕሮስፔሮ፡፡
እንዲያ ዓይነት የጭምብል ዳንኪራ ምሽት ግብዣ፣ የታላቅ ባለፀግነት መገለጫ ነበር፡፡ ሰፊው እልፍኝም በግብዣው

የሚታደሙት ክቡራኑ የፕሮስፔሮ ወዳጆች መርጠው የሚጨፍሩባቸው ሰባት የተለያዩ ክፍሎች ነበሩት፡፡ አብዛኞቹ የዱሮ

ቤተመንግስቶች የዳንስ አዳራሾች የክፍሎቹ አሸናሸን ካንዱ ክፍል  ሆነው ባንድ ጊዜ ዙሪያውንና ሌሎቹን ክፍሎች

ውስጣቸው ድረስ በደንብ ለማየት ለመተያየት እንዲቻል ልቅ ተደርገው ነበር የሚሰሩት፡፡ የዚህኛው ቤተ መንግስት

አሰራር ግን ከዚህ የተለየ ነበር፡፡ ከአንዱ ክፍል በር ሆነው ማየት ቢቻል ምናልባት ሌላኛውን አንድ ክፍል ብቻ ነው።

አንዱ ክፍል ከሌላው በሃያና በሰላሣ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ሌላ አቅጣጫ በሚታጠፍ የግድግዳ ማዕዘን ተከልሏል፡፡

እያንዳንዱ ክፍሎች ውስጥ በስተግራ ወይ በስተቀኝ ግድግዳዎቻቸው በኩል መሀል ለመሀል ከፍ ብለው የሚታዩ

መስኮቶች አሏቸው። የየመስኮቶቹ መስተዋት እንደየክፍሎቻቸው ቀለም አይነት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ክፍል

ግድግዳዎች በሰማያዊ መጋረጃ የተሸፈኑ ስለሆነ የመስኮቱ መስተዋትም ሰማያዊ ነው፡፡ የሁለተኛው ክፍል መጋረጃዎች

ሀምራዊ ቀለም ስላላቸው የመስኮቱ መስተዋትም እንዲሁ ሀምራዊ ነው፡፡ በሦስተኛው አረንጓዴ ክፍልም እንዲሁ አረንጓዴ

መስኮት፡፡ የአራተኛው መጋረጃና መስኮት ቢጫ፤ አምስተኛውም ነጭ፤ ስድስተኛውም ወይን ጠጅ ነበሩ፡፡ ሰባተኛው

ክፍል ግድግዳ ላይ የተጋረደው መጋረጃ ግን ውድ በሆነ ለስላሳማ ጨርቅ የተሰራ ጥቁር መጋረጃ ነበር፡፡ ልክ እንደ

ጨለማ የጠቆረ። ወለሉም እንዲሁ ከመጋረጃው የባሰ ድብን ያለ ጥቁር ስጋጃ ተነጥፎበታል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ግን

እንደሌላኛዎቹ ክፍሎች የግድግዳው መጋረጃና የመስኮቱ መስተዋት መልካቸው ተመሣሣይ አልነበረም፡፡ ወለሉና

ግድግዳው ጥቁር፤ የመስኮቱ መስተዋት ግን ቀይ ነበር፡፡ ደማቅ፤ ደም መሣይ ቀይ።
ሁሉም ክፍሎች ከውጭ ከሚቀጣጠለው የእሣት ነበልባል በየመስኮታቸው አልፎ በሚገባው ብርሃን ደምቀዋል፡፡ የእሣቱ

ወጋገን በዳንሰኞቹ  ላይ ሲያርፍ በነጸብራቁ የሚፈጠረው ጥላ ያልተለመደ አይነት ነው፡፡ የሰባተኛው ክፍል ድባብ ደግሞ

ከሁሉም ክፍሎች የተለየ ነበር፡፡ ደም ከሚመስለው የመስኮቱ መስተዋት አልፎ በጥቁር መጋረጃዎቹ ላይ  የተረጨው

የእሣት ብርሃን ለመላው ታዳሚያን በጣም የሚያስፈራ ነገር ሆኖባቸዋል። ወደዚያ ክፍል ድንገት በገቡ ሰዎች ፊት ላይ

የሚፈጥርባቸው ደስ የማይል ቀፋፊ ገፅታ ስለነበር፤ ሣይፈሩ ደፍረው በዚያ ጥቁር ግድግዳና ወለል መሀል በረበበው

አስጨናቂ ብርሃን  ወደ ክፍሉ ውስጥ መዝለቅ የሞከሩ በጣም ጥቂቶች ብቻ ነበሩ፡፡ በዚሁ ክፍል ውስጥ፤ ከጥቁር

እንጨት የተሰራ፤ ቁመቱ ጣሪያውን  ሊነካ ምንም ያልቀረው በጣም ግዙፍ ሰዓት ተገትሯል። እያንዳንዷን ሰከንድ

ሲቆጥር በቀስታ የሚሰማ ሲሆን፤ በየሙሉ ሰዓቱ ላይ ግን፤ ኩልል ብሎ በሚወርድ፤ ሙዚቃዊ ቃና ባለው ከፍተኛ

ድምጽ፤ ጮክ ብሎ ሲናገር ይሰማል። ልክ በዚያ ቅፅበትም የኦርኬስትራው ሙዚቀኞች ሙዚቃቸውን፣ ዳንሰኞቹም

ውዝዋዜያቸውን ያቋርጣሉ፡፡ ሰአት በሰው አንደበት ማውራቱ ግራ የሚያጋባቸው ዳንሰኞች መወዛወዛቸውን ገታ

አድርገው፣ ሰዓቱን እንደሞኝ ፈዝዘው ያዳምጡታል። አንዳንዶቹም ሰአቱ ተናግሮ እስኪጨርስ እጆቻቸውን አሻግረው

እየተነካኩ ይንሾካሾካሉ፤ ፊታቸው በፍርሃት ይቀላል። የሰአቱ ድምፅ ሲቆም ማጉረምረም ይነግሳል፡፡ በሁሉም ላይ

የአግራሞት ፈገግታ ይሰፍርባቸዋል፡፡ እናም ከሌላ ስልሣ ደቂቃዎች በኋላ፣ ከሌላ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰከንዶች

በኋላም ሰዓቱ በድጋሚ ይጮሀል፤ መላው ታዳሚዎቹም እንዲሁ እንደቀድሞው ድንገት ሙዚቃና ጭፈራቸውን ትተው፤

ማንኛውንም እንቅስቃሴያቸውን ገትተው ድርቅ ብለው ይቀራሉ።
ከመቼውም ጊዜ የተለየ ፍፁም ሀሴት የተሞላበትና ውብ የሆነ የጭምብል ዳንስ ምሽት ነበር፡፡ የታዳሚዎቹ አልባሳት፤

የተጫሙት ጫማና የተንቆጠቆጡባቸው ጌጣጌጦች ወደር የማይገኝላቸው ልዩና እፁብ ድንቅ የሚሰኙ ነበሩ። በአዳራሹ

መብራቶች ውስጥ ዳንሰኞቹ ልክ በአስፈሪ ሕልሞች ውስጥ እንደሚታዩ የቅዠት አለም ምስል ይመስላሉ፡፡ እናም እነዚያ

የሕልም አለም አይነት ሰዎች እንደገቡበት ክፍሎች ቀለም መልካቸው እየተለዋወጠ፣ እንደ ጥላ እየተንሳፈፉ ይደንሳሉ፡፡

እነርሱ የሙዚቃውን ምት እየተከተሉ የሚጨፍሩ ሳይሆን፤ ሙዚቃው ከእነርሱ ውዝዋዜ ውስጥ ተቃኝቶ የሚወጣ ነው

የሚመስለው፡፡ ያም ሆኖ ግን ማናቸውም ወደ ሰባተኛው ክፍል ከመግባት ተቆጥበዋል፡፡ በዚያ ክፍል ውስጥ፤ በመስኮቱ

መስተዋት የሚያንፀባርቀው ቀይ ብርሃንና የግድግዳው መጋረጃዎች ጥቁረት ከፍተኛ ፍርሃት ፈጥሮባቸዋል፡፡ በአጋጣሚ

ወደዚያ የገባ ሰውም ቢኖር ድንገት የትልቁን ጥቁር ሰዓት አስደንጋጭ ድምጽ በቅርበት ሲሰማ ተፈናጥሮ ይወጣል፡፡
ሌሎቹ ክፍሎች ግን በውብ መዓዛ ታውደው፤ በደስታ ፀዳል ፈክተው፤ በሰው ተጨናንቀዋል፡፡ ሰዓቱ፤ ከሌሊቱ ስድስት

ሰዓት መሆኑን እስኪያስተጋባ ድረስ ጭፈራው ቀልጦ ነበር፡፡ ሰዓቱ፤ ስድስት ሰዓት መሆኑን ሲናገር፤ አሁንም ሙዚቃው

እረጭ አለ፡፡ ዳንሰኞቹም እስካሁን ያደርጉት እንደነበረው፤ የሰዓቱ አስጨናቂ ድምፅ እስኪያበቃ ድረስ ከውዝዋዜያቸው

ተገትተው መጠባበቅ ጀመሩ፡፡ ሰዓቱ፤ ንግግሩን ከመጨረሱ በፊት፤ ከዳንሰኞቹ መሀል አብዛኛዎቹ፤ ከመጀመሪያው

ሰማያዊ ክፍል ውስጥ፤ እስካሁን ያልነበረ ባለጭምብል አስተዋሉ፡፡ ቀስ በቀስም፤ አንዱ ለሌላው በቀስታ ማንሾካሾክ

ጀመረና በታዳሚዎቹ መሀል፤ መጀመሪያ የመደነቅ፤ ከዚያም የፍርሃትና የመርበድበድ ስሜት ተሰራጨ፡፡
እንዲህ ባሉ የተከበሩ ሰዎች መሀል፤ ይህን አይነት ባለጭምብል ድንገት ሲከሰት ፍርሃት መንዛቱ አያስገርምም፡፡

ከመሀላቸው «በመኖርና በአለመኖር መካከል ቅንጣት ታህል ልዩነት አይታየኝም፤ እንዲያውም ሞት የሚፈራ ሰው

ያስቀኛል!» የሚል ጀግና ቢኖር እንኳ፤ ቢያንስ እንግዳው ባልተፈቀደ አለባበስ በመታደሙ ብቻ ትኩረት እንዲሰጠው

የሚያስገድደው አንዳች ስሜት በውስጡ ይጫራል፡፡ እንግዳው ረዥምና መጣጣ ቀጭን ሆኖ፤ ልክ ለቀብር እንደተዘጋጀ

አስከሬን ከፀጉሩ እስከ ጥፍሩ በመገነዣ ጨርቅ ተሸፍኗል፡፡ ፊቱን የሸፈነበት ጭምብልም... እውነት ጭምብልስ ነው? ...

እና ፊቱን በሸፈነበት ጭምብልና በሞተ ሰው ፊት መካከል ያለውን ልዩነት በጣም በቅርበት ተጠግቶ ያየ ሰው እንኳ

ለመረዳት አይችልም፡፡ ይኼ ሁሉ እሺ ይሁን ቢባል እንኳ፤ ይህ ማንም የማያውቀው እንግዳ ባለጭምብል፤ በአካኋኑ

ቁርጥ ቀዩ ሞትን መስሎ ነው የመጣው! ቁልቁል በቁሙ አጣፍቶ የለበሰው እራፊ ጨርቅ በደም ነጠብጣብ

ተዥጐርጉሯል፡፡ ፊቱን የሸፈነበትን ጭምብልም እንዲሁ ያ አስበርጋጊ ቀይ የደም ነጠብጣብ ወርሶታል፡፡ ደግሞ

ጭምብልም አይመስልም - አ...ዎ! የገዛ ራሱ መልክ ነው!
 ፕሮስፔሮ ይህንን አስደንጋጭ ክስተት እንዳየ፤ በመጀመሪያ በፍርሃት ተውጦ ቆይቶ፤ ከዚያ ደግሞ ድንገት በቁጣ ቱግ

አለ፡፡
«የማነው ደፋር!» ሲል አምባረቀ
«ያዙት! ያዙና ቀፍድዱት! ጭምብሉን ከፊቱ ላይ ገፋችሁ… የማናባቱ ጋጠወጥ!ስድ! ባለጌ! መሆኑን አረጋግጡ! ጎህ

ሲቀድ ወስደን እናንጠለጥለዋለን!»
ፕሮስፔሮ፤ ይህንን ያለው ከሰማያዊ ክፍል ውስጥ ቆሞ ቢሆንም፤ ድምፁ ግን በዙሪያው ባሉ በሰባቱም ክፍሎች ውስጥ

ጥርት ብሎ ያስተጋባ ነበር፡፡ መጀመሪያ ላይ፤ ልክ ፕሮስፔሮ ቀጭን ትዕዛዝ እንዳስተላለፈ፤ ከዳንሰኞቹ መሀል ወደ

እንግዳው ባለ ጭምብል እየተንደረደሩ ነበሩ። ግን፤ ግማሽ መንገድ ደርሰው በያሉበት ቀጥ አሉ፡፡ ከዚያ በላይ ወደፊት

አንዲትም ጋት ፈቅ ብሎ በእንግዳው ላይ እጁን ለማሣረፍ የደፈረ ማንም አልነበረም። ሁሉም በፍርሃት ተዋጡ፡፡

እንግዳው ግን፤ እየተንጐማለለ ወደ ሁለተኛው ክፍል መራመድ ጀመረ፡፡ አፉን ከፍቶ በመደነቅ የሚያስተውለው

ፕሮስፔሮን ናቅ አድርጐት በጐኑ አልፎት ሄደ፡፡ ታዳሚዎቹ፤ የክፍሉን የመሀል ወለል እየለቀቁ ወደ ኋላ ሲያፈገፍጉ፤

እንግዳው ለአፍታም ቆም ሳይል፣ ቀብረር ባለና በተመጠነ አረማመድ፣ ከሰማያዊው ክፍል ወደ ሀምራዊው ክፍል፤

ከሀምራዊው ክፍል ወደ አረንጓዴው ክፍል፤ ከአረንጓዴው ክፍል ወደ ቢጫው፤ ከዚያ ወደ ነጩ፤ ወደ ወይን ጠጁ ተራ

በተራ ተሽከረከረ፡፡  
ልክ እንግዳው ሰባተኛው ክፍል ሲደርስ ፕሮስፔሮ በቁጣ እመር ብሎ በስድስቱም ክፍሎች ገብቶ እየወጣ ማሰስ ጀመረ፡፡

ማንም አጅቦት ሊከተለው የደፈረ ሰው አልነበረም። እሱ ግን፤ ከቁመቱ የሚረዝም ስለታም ሻምላ ጨብጦ፤ ከእንግዳው

ጋር ሊፋለም ተዘጋጅቷል። ባለጭምብሉን እንግዳ ከርቀት እንዳየውም፤ በቀስታ ኮቴውን አጥፍቶ ከኋላው እያደባ

እየተከተለ፤ ልክ ሊደረስበት ሦሰት አራት እርምጃዎች ሲቀሩት፤ እንግዳው ድንገት ዞር! ብሎ ቆመና፤ በፀጥታ፤ ታ

የፕሮስፔሮን አይኖች በቀሳፊ አተያይ ሰርስሮ አያቸው፡፡ ፕሮስፔሮ እሪ...! ብሎ ከፍተኛ ጮኸት አሰማ፤ ይዞት የነበረው

ሻምላም ከእጁ ላይ ተሽቀንጥሮ፤ ስለቱ እየተብለጨለጨ ጥቁሩ ወለል ላይ አረፈ፡፡ ወዲያውም በወደቀው የራሱ ሻምላ

ስለት ላይ፤ ራሱ ፕሮስፔሮ ተዘረረበትና፤ ሞተ፡፡ በዚያን ጊዜ ታዳሚዎቹ እየተሯሯጡ ወደ ጥቁሩ ክፍል መጡ፡፡ ገዘፍ

ገዘፍ ያሉትና ክንደ ብርቱዎቹ ወንዶች፤ በቁመቱ ከትልቁ የግድግዳ ሰዓት መሳ ለመሳ ሆኖ የቆመውን የዚያን ቀውላላ

ባለጭምብል ገፅታ ጨምድደው ሊይዙት ሞከሩ፡፡ ግን፤ እጆቻቸውን ሰድደው እላዩ ላይ ባሳረፉ ጊዜ፤ ከተሸፈነበት

መገነዣ ጨርቅ ስር የጨበጡት ነገር አልነበረም፡፡ ስጋ እና አጥንትም ሆነ አንዳችም የሚዳሰስ ነገር የሌለው አካል አልባ

ነበር ... በቃ ምንም ... ኦና!
ያኔ ነበር፤ ሁሉም፤ ራሱ ቀዩ ሞት እንደ ሌባ እኩለ ሌሊትን ተታክኮ መከሰቱን የተረዱት። እያንዳንዱ ታዳሚም ተራ

በተራ እየተርገፈገፈ መነጠፍ ጀመረ - እንደወደቀም ወዲያውኑ ፀጥ! ቤተ መንግስቱ ውስጥና በዙሪያው ተቀጣጥለው

ሲንቦገቦጉ የነበሩት  የእሣት ብርሃናትም ሁሉ ወደሙ፡፡ ልክ የመጨረሻው ሰው መሬት በወደቀበት ቅፅበትም ሰዓቱም

መቁጠሩን አቆመ። ያም ውብ እልፍኝ በፅልመትና በሞት ብካይ ተዋጠ፡፡ እነሆ፤ ቀዩ ሞትም፤ ሁሉንም በእኩልነት

አንበርክኮ ይገዛ ዘንድ፤ለዘለአለም ተንሰራፍቶ ነገሰ፡፡


Read 3972 times