Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 03 December 2011 08:06

ለራሳችን እንወቅበት፤ እንንቃ!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ባለፈው ሳምንት የስደትን ጉዳይ አንስተን እንደተነጋገርነው በተለያዩ የውጭ ሀገራት ተሠደው በስራ ላይ ከተሠማሩ ዜጐቻቸው በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገቢ በማግኘት ቻይናን፣ ሜክሲኮን፣ ህንድንና ፊሊፒንስን የሚወዳደር ሀገር እስካሁን አልተገኘም፡፡ እነዚህ ሀገራት ከፍተኛ መጠን ያለው ገቢ በየአመቱ የሚያገኙት እንዲሁ በአቦ ሠጡኝ ሳይሆን ወደ ውጭ ሀገራት በስራ የሚሠማሩ ዜጐቻቸውን የተሻለ ገቢና ደህንነታቸውም በተሻለ የተጠበቀ እንዲሆን የሚያስችል መሠረታዊና ተገቢ ስልጠና በመስጠታቸው ነው፡፡ ይህን በማድረጋቸው ገቢያቸው ሲጨምር በየእለቱ በሳጥን እየታሸገ የሚላከው የዜጐቻቸው አስከሬን መጠን በእጅጉ ይቀንሳል፡፡

የዚህን ጉዳይ ፊት ወደ እኛ ሀገር መልሰን ብንመረምረው የምናገኘው መልስ የሌሎቹ ተቃራኒ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ሀገራችን በውጭ ሀገራት ተሠደው ከሚኖሩ ዜጐቿ በየአመቱ የምታገኘው ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ እርግጥ የመሆኑን ያህል በየእለቱ የምንቀበለው አስከሬንና አካላቸው የጐደለ ዜጐቻችን ቁጥር የዚያኑ ያህል ሽቅብ መወንጨፉን አላቆመም፡፡ ከሁሉም የባሠው ጉዳይ ደግሞ በስደት ላይ እያሉ ከሚደርስ አሳዛኝና አሠቃቂ ዜና የኢትዮጵያውያንን ስም ሳይሠሙ ውሎ ማደር የአለመቻሉ ነገር ነው፡፡ ከሌላው የስደት መንገድ ይልቅ በየመን በኩል በሚደረገው ስደት ይህን ያህል ስደተኞች በህገወጥ መንገድ ወደ የመን ለመግባት ሲሞክሩ ጀልባው ተሠብሮ ወይም ተገልብጦ በመስመጡ ከሞቱት ውስጥ ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ህገወጥ ስደተኞች ናቸዉ ወይም ደግም ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ህገወጥ የኢትዮጵያ ስደተኞች በየመን መውጪያ መግቢያ አጥተው ወይም በጥበቃ ሀይሎች ታግተው አሳር መከራቸውን እየበሉ ይገኛሉ የሚል ዜና በተደጋጋሚ ከመስማታችን የተነሳ ማዘን ወይም መደንገጣችንን ከተውነው ቆይተናል፡፡ 
በሆነ አጋጣሚ ከገጠማቸው የስደት ችግርና ፈተና አምልጠው፣ እዚያም ቤት ያለው የሚሸመጠጥ ዶላር ሳይሆን እሳት ነው በሚል ሌሎችን ከመሠል የስደት አደጋና ፈተና ለመጠበቅ እንዲረዳ በማሠብ፣ አንዳንዶች የህይወት ገጠመኛቸውን ለማጋራት ቢችሉም “ብልህና አስተዋይ የሆነው እርሱ ከጐረቤቶቹ ይማራል” የሚለው የአይሁን ሚሽናህ ሁነኛ አባባል ሠሚ ጆሮና አስተዋይ ልቦና ያገኘ አይመስልም፡፡
የሌሎችን ገጠመኝ ለሚያዳምጡት ኢትዮጵያውያን ያዳመጡት የስደት ታሪክ የእድለ ቢሱ ተራኪ እንጂ የእነሱ ታሪክ አይደለም፡፡ እናም የእነሱን የስደት ቀን በተስፋም በስለትም ነቅተው ይጠባበቃሉ፡፡ ቀኑ የደረሠ ሲመስላቸውም ጨርቄን፣ ማቄን ሳይሉ ለህጋዊነት ቅንጣት ታክል ቁብ ሳይሠጡ፣ የውቅያኖሱን ማዕበልና ምህረት የለሹን የባህር ሻርክ ሳይፈሩ ይመርሻሉ - ወደ ስደት፡፡ የሞቱና የእንግልቱ አስደንጋጭ ዜናና ታሪክም ጊዜውንና ውሉን ሳይስት እንዲሁ ይቀጥላል፡፡
እንግዲህ የጉዳዩ እውነታ እንዲህ ከሆነ፣ ሊነሳ የሚገባው አብይ ቁም ነገር ስደቱን ማቆም ካልቻልን የስደተኛውን ችግር በተቻለ አቅም ለመቀነስና የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ምን ማድረግ ይገባል የሚለው ነው፡፡ የዚህ መስክ ችግር መንግስትንም ሆነ ኅብረተሠቡን የሚነካና እርስ በርሱ የተሳሠረ ስለሆነ መፍትሔውም የሚገኘው ከመንግስትና ከራሱ ከህብረተሰቡም ነው፡፡
የሀገራችን መንግስት እንደ ሌላ እንደማንኛውም መንግስት ከውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚላከውንና ከአመት አመት እያደገ የመጣውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ አንዲትም ሠባራ ሳንቲም ሳትጐድልበት ማግኘት ይፈልጋል፡፡
መንግስት ዲያስፖራ እያለ የሚጠራቸውን እነዚህኑ በውጭ የሚኖሩ ዜጐቹን ጉዳይ የሚከታተል አንድ ክፍል በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኩል እንደከፈተ ተናግሯል፡፡ በፖሊሲ ደረጃ የታወቀ መንግስታዊ አቋምና አሠራር እንዲኖረኝ በማሠብም፣ የዲያስፖራ ፖሊሲ ቀርጬ ለውይይት እያቀረብኩ ነው ማለቱንም በቅርቡ ሠምተናል፡፡ ነገር ግን በውጭ ሀገራት በተለይ ደግሞ በመካከለኛው ምስራቅ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥረው የሚሠሩትን ኢትዮጵያዊያንን የእለት ተዕለት ችግርና ሠቆቃ በተገቢው መንገድና በወቅቱ እየተከታተለ ድጋፍና መፍትሔ የሚያስገኝ ተጨባጭ ስራ በማከናወኑ በኩል መንግስት አሁንም ገና እጅግ ብዙ ስራ መስራት ይቀረዋል፡፡
የፊሊፒንስ መንግስት እንደሚያደርገው የመሠረታዊ ሙያ ማሻሻያ ሥልጠና የሚሰጡ ተቋማትን በመዘርጋት ስልጠና መስጠት ወይም ደግሞ ሌሎች አካላት እንዲሠጡ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ከመንግስት የሚጠበቅ ሀላፊነት እንደሆነ የዘነጋነው ይመስላል፡፡
መንግስት በተለያዩ ሀገራት በተለይ ደግሞ ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ በርካታ ስደተኛ የቤት ሠራተኞች በሚኖሩባቸዉ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በዲፕሎማትነት እየወከለ የሚልካቸው አምባሳደሮች፤ የተወከሉበትን ስራ በማከናወኑ በኩል ያላቸው የብቃት፣ የተነሳሽነትና የችሎታ ሁኔታም ሁሌም ቅሬታና ስሞታ የሚቀርብበት ጉዳይ ነው፡፡ የተለያየ ችግር ደርሶባቸውና ህይወታቸውን ብቻ አትርፈው ወደ ሀገራቸው የገቡ በርካታ ኢትዮጵያውያን፣ ላጋጠማቸው የተለያየ ችግር መፍትሄና ድጋፍ ለማፈላለግ በዚያ ሀገር ወደሚገኙት የኢትዮጵያ መንግስት ወኪሎች ከመሄድ ይልቅ ወደተለያዩ የሠብአዊ እርዳታ ሠጪ ተቋማት በተለይም ወደ አለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት መሄድ የተሻለ አማራጭና የተሻለ እርዳታ እንደሚያስገኝ አስረግጠው ይናገራሉ፡፡
ስለዚህ መንግስት ከእንደዚህ ያለ ወቀሳ ለመዳንና ይልቁንም ከመስኩ የተሻለ ጥቅም ማግኘት ከፈለገ እንዲያደርግ የሚመከረው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ እንደተለመደው ክፉ ክፉውን ሳይሆን የፊሊፒንስን መልካም ተሞክሮ እንዲኮርጅ፡፡
የህብረተሰቡን ጉዳይ ብናነሳ ደግሞ የምናገኘው ሁኔታ ግራ የሚያጋባና ከፊሊፒንስ ሊዎናራ ሳንቶስ ታሪክ ፍፁም ተቃራኒ የሆነ ነው፡፡ በውጭ ሀገራት በህጋዊም ሆነ በህገወጥ መንገድ ለስራ ከሚሄዱት ውስጥ ስለሚሄዱበት የውጭ ሀገር ባህልና ስለ ህዝቡ የአኗኗር ዘይቤ ለማወቅ ቅንጣት ታህል የሚሞክሩ ለአድባሯ አንድ ሰው ማግኘት ከተቻለ በእርግጥ እንደተአምር ይቆጠራል፡፡
ከሞላጐደል ሁሉም በሚባል ሁኔታ በውጭ ሀገራት ስራ ለሚያስቀጥራቸው ኤጀንሲ ወይም ደላላ በአስር ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ በአራጣ ተበድረውም ይሁን ተለቅተው ብቻ ከየትም ብለው ለመክፈል ጨርሰው አያመነቱም፡፡ ቢበዛ አንድና ሁለት ሺ ብር ሊያስወጣቸው የሚችል፣ ነገር ግን እዚያ የሚጠብቃቸውን ፈተና በእጅጉ የሚያቀልላቸውን ምናልባትም ህይወታቸውን ከሚያሳጣ ችግር ሊታደጋቸው ለሚችለው መሠረታዊ የቋንቋና የቤት ውስጥ ሙያ ችሎታ ሥልጠና ለመከታተል ግን ፍላጐቱም ሆነ ቁርጠኛነቱ የላቸውም፡፡ የሃያ ሁለት አመት ወጣት የሆነችው የሀዋ ሰኢድ ታሪክ ይህንን እውነታ ይበልጥ ያስረዳናል፡፡
“እድሜዬ ሃያ ሁለት አመት ነው፡፡ ተወልጄ ያደኩት ወሎ ሀይቅ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ለቤተሰቦቼ የመጀመርያ ልጅ ነኝ፡፡ ትምህርቴን እስከ ሰባተኛ ድረስ ተምሬአለሁ፡፡ ለነገሩ ተምሬአለሁ ከምልህ ፊደል ቆጥሬአለሁ ብልህ ይቀላል፡፡ የቀን የሌሊት ህልሜ አረብ ሀገር ሄዶ ሠርቶ መክበር ወላጆቼን ሸጋ አድርጐ መጦር ብቻ ነበር፡፡ እዚያ በምትኖረው የአክስቴ ልጅ አማካኝነትም ቪዛ ተገኝቶልኝ አባቴ ሁለት በሬዎቹን ሸጦ በሰጠኝ ገንዘብ፣ ከዛሬ አራት አመት በፊት ወደ ባህሬን ሄጄ ሰው ቤት ተቀጠርኩ፡፡ ስሄድ በጣም ደስ ብሎኝ ነበር፡፡
ስራ እንጀመርኩ ግን ችግር ገጠመኝ፡፡ በጣም ትልቅ ችግር ገጠመኝ፡፡ አረቢኛ መናገርም ሆነ መስማት አልችልበትም፡፡ እንግሊዝኛም ጨርሶ አይቀናኝም፡፡ አሠሪዎቼ በተለይ ደግሞ ማዳም ምን እንደምትለኝ ጨርሶ አይገባኝም፡፡ የሆነ ነገር ተናግራ ለፍልፋ ለፍልፋ ስታበቃ ፀጉሯን ይዛ እንደ እብድ ትጮሀለች፡፡ እኔ ምኑም አይገባኝም፡፡ በረድ ሲልላት ጆሮዬን እየጐተተች ትለፈልፍብኛለች፡፡ እኔ ግን እንዲያው ምኑም አይገባኝ፡፡ ልጆቿ በስልክ ሲነጋገሩ የሰማሁትን ይዤ “ማአሌሽ ማአሌሽ” ስላትም የበለጠ ታብድብኛለች፡፡ ከቤት ወለልና ግድግዳ አጠባው በቀር የሠራሁትን ምግብማ ጨርሰው ነክተውት አያውቁም፡፡ ማዳም በዚያ በአረብኛዋ እየለፈለፈች የሠራሁትን ምግብ የቆሻሻ በርሚሉ ውስጥ ትደፋዋለች፡፡ “አባትየው ማታ ማታ በክርታስ የታሸገ ነገር ይዞ እየመጣ ለልጆቹ ያበላቸዋል፡፡ ልጆቹ ቆሻሻ ነሽ እያሉ አንድም ቀን ተጠግተውኝ አያውቁም፡፡ ማዳም የመጣባት ቀን በያዘችው ነገር እየወረወረች ትማታለች፡፡ ሁለት ቀን በብርጭቆና በትልቅ ጭልፋ አናቴን ፈንክታኝ ታውቃለች፡፡
“ከሁለት ወር ቆይታ በሁዋላ ደመወዜን እንኳ ሳትሰጠኝ ለኤጀንሲው አስረክባ ጥላኝ ሄደች፡፡ ከዚያ ካንዱ ቤት አንዱ እያልኩ ድፍን አመት ሙሉ ተንከራትቼ ሰባራ ሳንቲም ሳልይዝ፣ አባቴን ጥሪት አልባ አድርጌ አክስሬው ተጠርዤ መጣሁ፡፡ አሁን ያጐቴ ልጅ ኳታር ስራ አለ ብላኝ ልትወስደኝ ፕሮሰስ እየጨረስኩ ነው፡፡ ኤጀንሲው ኳታሮች ይሻላሉ ብሎኛል፡፡ እንግዲህ ደግሞ መቸም አላህ ያውቅልኛል፡፡”
የሀዋ ታሪክ ይህ ነው፡፡ እንደ እሷ አይነት ታሪክ ያላቸውን ዜጐቻችንን ፈልጐ ማግኘትም ጨርሶ የሚከብድ ጉዳይ አይደለም፡፡ ምናልባት የሀዋን ታሪክ ከሌሎች የሚለየው ነገር ቢኖር ቋንቋና የምግብ ዝግጅት ሙያ አለመቻሏ የፈጠረባትን ችግር እያወቀች ይህንን ለማሻሻል ምንም አይነት ጥረት ሳታደርግ፣ እንደገና በቤት ሠራተኛነት ለመቀጠር ወደ ኳታር ለመሄድ መዘጋጀቷ ነው፡፡ ካዛንቺስ በሚገኘው በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ አካባቢ፣ ወደ አረብ ሀገራት ለመሄድ ጉዳያቸውን ከሚከታተሉት እጅግ በርካታ እህቶቻችን ከአንዷ ጋር የተደረገ ወግ የሚተለውን ይመስላል፡፡
ወደ የት ልትሄጂ እየሞከርሽ ነው?
ባህሬን
በደላላ ነው በኤጀንሲ?
በኤጀንሲ ነው እንጂ
ስንት ከፈልሽ?
ይሄማ ምኑ ይነገራል … ብዙ ነው፡፡
ቋንቋ ትችያለሽ … አረብኛ? እንግሊዝኛ?
እዛ ሄጄ እለምደው የለ፡፡ ሴቱ ሁሉ እዛ ሄዶ አይደል የሚለምደው፡፡
የቤት ሙያ … ባልትና ማለት … የአረብ ምግብ አሠራር ትችያለሽ?
ሩዝ መቀቀል … አረቦች ሩዝ አይደል የሚበሉ፡፡ ታዲያ ሩዝ መቀቀል ምን ያቅታል! ሌላ ካለ እዛ ሄጄ እለምደዋለሁ፡፡
ልብስ መተኮስ፣ በዎሽንግ ማሽን ማጠብ … ምናምንስ ትችያለሽ?
ኧረ አንተ ተወኝ! ከዚህ ልሂድ እንጂ ሁሉንም እዛው እለምደዋለሁ፡፡ ሴቱ ሁሉ እዛ ሄዶ አይደል ባንዴው የሚለምደው፡፡
ይሄ ወግ ከላይ ያነሳነውን ዋነኛ ሀሳብ በበቂ ሁኔታ ያስረዳል፡፡ እናም የእህቶቻችን ቸልተኝነትና ሊደርስባቸው የሚችለውን ፈተና መገመት ቀላል ነው፡፡ እዚያ ሄጄ እለምደዋለሁ በሚል ቸል ያሉት የቋንቋም ሆነ ሌሎች የሙያ ስልጠናዎች አንዳንዴ ቀለል ሲል አካልን ከበድ ሲል ደግሞ ህይወታቸውን ሊያስከፍላቸው ይችላል፡፡
በውጭ ሀገር ስራ አስቀጣሪ የሆኑ ኤጀንሲዎችም ወደ ውጭ የሚልኳቸውን ሠራተኞች መላካቸውን እንጂ የስነምግባር የትምህርትና የሙያ ችሎታቸውን ነገር ከነአካቴውም የሚያስቡት አይመስልም፡፡ ከላኳቸውም በኋላ ቢያንስ አስቀጥረው የላኳቸው የስራ ኮንትራት እስከሚጠናቀቅ ድረስ እንኳ የሚያደርጉላቸው ክትትል ጨርሶ የለም ቢባል ይሻላል፡፡ ዋነኛ ስራቸው ስራ ያስቀጠሩበትን ወይም የደለሉበትን በሺ የሚቆጠር ገንዘብ ተቀብሎና ተቀጣሪውን ወደ ውጭ ልኮ ቁጭ ወይም ጭጭ ማለት ይመስላል፡፡
ወደ ውጭ ሀገር ለስራ የሚልኳቸውን የቤት ሠራተኞች ከመላካቸው በፊት የሚሄዱበትን አገር ቋንቋ፣ የህዝቡን ባህልና የአኗኗር ዘይቤ እንዲሁም ስነምግባር፤ የሚሄዱበትን ሀገር ባህላዊም ሆነ ዘመናዊ የምግብ አሠራር፣ የቤት ንጽህና አያያዝ፣ ዘመናዊ የምግብ ማብሰያና የንጽህና መስጫ መሳሪያዎች አጠቃቀም በተመለከተ ስልጠና መስጠት ቢችሉ ጥቅሙ እጥፍና ፈርጀ ብዙ ነው፡፡ ለእነሱ ተጨማሪ ስራና እንዲህ በቀላሉ የማይደርቅ የገቢ ምንጭ ከማምጣታቸው ባሻገር ለተቀጣሪዎች የስራም የደህንነትም ዋስትና ነው፡፡ የዚህ ድምር ውጤት ለህዝብም ለሀገርም ተጨማሪ ገቢና ጥቅም አለው፡፡
ይህን ጉዳይ በውጭ ሀገር ስራ አስቀጣሪ የሆናችሁም ሆነ ሌሎች የሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት ወይም ባለሀብቶች በጥሞና አስባችሁት በተግባር ብትንቀሳቀሱ ለራሳችሁም ሆነ ለህዝቡ በቀላሉ ብርሃን መሆን ትችላላችሁ ለራሳችን እራሳችን እንወቅበት፡፡ እንንቃ!

 

Read 4391 times Last modified on Saturday, 03 December 2011 08:07

Latest from