Saturday, 30 November 2013 11:35

...ኑሮ የሚኖረው ወደፊት እንጂ...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(0 votes)

እንደ ኤሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2007 ተሸሽሎ የወጣው ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፈውን ኤችአይቪ ቫይረስ ለመግታት የሚያስችለው መመሪያ እንደሚገልጸው ስርጭቱ በጊዜው በብሄራዊ ደረጃ 2.1% ሲሆን በከተማ 7.7% እና በገጠር ደግሞ 0.9%  ይገመታል፡፡ 977.394/ ያህል ሰዎች በኢትዮጵያ ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖሩም የተሸሻለው መመሪያ የሚያመለክት ሲሆን ከዚህ ውስጥ 41% ወንዶች 59% ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡ ወደ 75.420/ ያህል እርጉዝ  ሴቶች ከቫይ ረሱ ጋር እንደሚኖሩም ይህ በ2007/ የወጣው መመሪያ ይገልጻል፡፡ ከፍተኛው ስርጭት የሚታየ ውም እድሜያቸው ከ15-24 አመት በሚገመቱት ሲሆን ከፍተኛውን ቁጥር በከተማም ሆነ በገጠር የሚይዙትም ሴቶች ናቸው፡፡
ኤችአይቪ ኤይድስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ለ4/ አመት ያህል ከግል የህክምና ተቋማት ጋር በመስራት ላይ ይገኛል። ፕሮጀክቶቹም የተነደፉት በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ሲሆን በዚህ እትም የምንመለከተው በኢትዮጵያ ሰሜናዊ አቅጣጫ ያለውን እንቅስቃሴ ይሆናል፡፡
ዶ/ር ቴዎድሮስ ማለደ በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር የPMICT ኤችአይቪ ኤይድስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚያስችል ፕሮግራም ክሊኒካል ሜንተርና የቡድን መሪ በመሆን የሚሰሩ ናቸው፡፡እሳቸው እንደሚገልጹት የ PMICT ፕሮግራሙ በሰሜኑ አቅጣጫ የተዘረጋባቸው ቦታዎች በአማራ ክልል በደብረ ማርቆስ፣ ቡሬ እና ባህርዳር እንዲሁም በደብረብርሀን ደሴ የሚገኙ የግል የህክምና ተቋማት ናቸው፡፡ በማርቆስ፣ ባህርዳር አካባቢ በአጠቃላይ ስድስት የግል የህክምና ተቋማት በፕሮግራሙ የተካተቱ ሲሆን እነርሱም የማርቆስ መካከለኛ ክሊኒክ፣ በደብረማርቆስ ቡሬ ላይ የሚገኘው የቅ ዱስ ጊዮርጊስ ከፍተኛ ሆስፒታል፣ በባህርዳር የጋምቢ ቲቺንግ ሆስፒታል፣ አፍላጋትና አብራክ ሆስፒታልና በጸጋ የሚባለው ከፍ ተኛ ክሊኒክ በድጋፍ ሰጪዎች አማንኝነት ከማህበሩ ድጋፍ የሚያገኙ ናቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ ለህብረተሰቡ የሚያደርጉትን ድጋፍ በማገዝ ረገድ ስልጠናዎችንና አንዳንድ የነክኒንል እና የአቅርቦት አገልግሎትን የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ያቀርባል ፡፡
በጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በፕሮጀክቱ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች በተወሰነ ጊዜ እየተዙዋዙዋሩ ያለውን አሰራር የሚጎበኙ ሲሆን የዚህ አምድ አዘጋጅም በጋራ በመጉዋዝ የተለያዩ የግል የህክምና ተቋማትን በመጎብኘት የሚከተለውን ለንባብ ብላለች፡፡
በቡሬ የቅዱስ ጊዮርጊስ ከፍተኛ ሆስፒታል የ ሓል..ማ አገልግሎት በሚሰጥበት ክፍል አንድ ባልና ሚስት ከሕክምና ባለሙያ ጋር ተቀምጠዋል፡፡
“...እኔ  ስሜ ወ/ሮ ገነት ገላው ይባላል፡፡ እድሜዬ 25/ አመት ሲሆን የሁለት ልጆች እናት ነኝ፡፡ አሁን ሶስተኛውን ልጅ የአምስት ወር እርጉዝ ነኝ፡፡ ከዚህ ሆስፒታል የመጣሁት ምርመራ ለማድረግ ነው፡፡ በእርግጥ የመጣሁት ለመጀ መሪያ ጊዜ ነው፡፡ አድራሻዬ ከገጠር ሲሆን በአቅራቢያዬ ባሉ የጤና ተቋ ማት ለመመርመር ከአንዴም ሶስት ጊዜ ሄጄ ላገኛቸው አልቻልኩም፡፡ ስለዚህ አሁን ጽንሱ እየከበደኝ አስቸግሮኝ ወደዚህ መጣሁ፡፡
---------////-----------
“...እኔ ደረጀ ጥበቡ እባላለሁ፡፡ እድሜዬ 29/ አመት ሲሆን እስከ አምስተኛ ክፍል ተምሬአለሁ፡፡ የወ/ር ገነት ባለቤት ነኝ፡፡ ባለቤቴን ሂጂና ታከሚ ስላት ...አረ አላገኘሁዋቸውም ትላለች። ዛሬም ሄዳ የሉም ሆነ...ነገም ሄዳ የሉም ሲሆን ጊዜ ...አይ እንግዲህስ ወደ ከተማው ፈቅ ብለን ሌላ ሕክምና እንፈልግ ብዬ እኔ ነኝ ይዣት የመጣሁት፡፡ እኔ በብዙዎች ዘንድ ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ችግር ሲፈጠር ስለማስተውል የእርሱዋን ሁኔታ በንቃት እከታተላለሁ፡፡ የምፈልገው አራት ልጅ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ልጅ ከወለድን በሁዋላ ስለዘላቂው መከላከያ እናስባለን፡፡ እስከአሁንም ጊዜያዊዎቹን እየተጠቀመች ነው፡፡
---------////-----------
ከላይ ሀሳባቸውን የገለጹት ባልና ሚስት ባሉበት ክፍል የሚደረገውን ምርመራ ማወቅ አለማ ወቃቸውንና የሚኖራቸውን ስሜት እንዲገልጹ ተጠይቀው ነበር፡፡ በመጀመሪያ አቶ ደረጀ የሚከተለውን ብለዋል፡፡
“...በእርግጥ አሁን ያለነው ኤችአይቪ ኤይድስ መኖር ያለመኖሩ ከሚረጋገጥበት ክፍል ነው፡፡ እኔ በበኩሌ...አለ ቢባልም ምንም ግድ የለኝም፡፡ ምክንያቱም ኑሮ የሚኖረው ወደፊት እንጂ ወደሁዋላ አይደለምና ነው፡፡ ባለፈ ነገር ከመብሰልሰል ወደፊት ስለሚሆነው ነገር ጠንቅቆ ማስተዋል ይበጃል፡፡ ስለዚህ ኤችአይቪ በደምህ አለ ብባል...ምን ማድረግ እንደአለብኝ...እራሴን እንዴት መርዳት አለብኝ ብዬ ከሐኪም ጋር ተማክሬ የሚበጀውን አደርጋለሁ እንጂ ለሆነ ነገርማ ወደሁዋላ ተመልሼ ምንም አልጨነቅም፡፡ መጠንቀቅ አስቀድሞ ነበር እንጂ...”
--------////----------
የባልተቤትየዋ ወ/ሮ ገነት መልስ የሚከተለው ነው፡፡
“...ምን ችግር አለ? ባይሆን ጥሩ ነው፡፡ ከሆነ ደግሞ ምንም የሚያስጨንቅ ነገር የለም፡፡ በዚህ ጉዳይ አንተ ነህ አንቺ ነሽ መባባልም የለብንም፡፡ በቃ...የመጣውን ነገር ተቀብለን እንደአመጣጡ መሆን ነው፡፡ ምንም ችግር የለም፡፡ በእርግጥ እኔና እርሱ ሁልጊዜ እንነጋገራለን፡፡ ልጆቻችንን በጥንቃቄ ማሳደግ እንዳለብን... እራሳ ችንንም መጠበቅ እንደሚገባን...እንመካከራለን፡፡ እንግዲህ ከዚህ አልፎ ቫይረሱ በደማችን ከተገኘ ደግሞ ኑሮአችንን ሳንበትን አንተ ነህ...አንቺ ነሽ ሳንባባል እን ዲሁ እንደተዋደድን እንኖራለን፡፡”
-----------////---------
    ባልና ሚስቱ ለምክር አገልግሎት የቀረቡበት ከፍል ያገኘነው ባለሙያ ክሊኒካል ነርስ ነው፡፡ ስንታየሁ ይባላል፡፡ ስንታየሁ እንደሚገልጸው ለክትትል ከሚመጡት ውስጥ ብዙዎቹ የሚነገራቸውን የሚቀበሉ ምንም የማያስቸግሩ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ታካሚዎች ቫይረሱ በደማ ቸው ቢገኝም እንኩዋን ከቫይረሱ ነጻ የሆኑ ሕጻናትን መውለድ እንደሚገባቸው እና ለዚህ ደግሞ ዋነኛዎቹ ፈጻሚዎች መሆናቸውን አበክረን ስለምንነግራቸው በትክክል የመድሀነቱ ተጠቃሚ በመሆን ውጤት ላይ መድረስ የሚፈልጉ ይሆናሉ፡፡ በሆስፒታሉ ለዚህ አገልግሎት የሚቀርቡ ታካሚ ዎች በጣም በርካታ ናቸው፡፡ ለምሳሌም በወር እስከ 44/ የሚደርሱ ታካሚዎች ተጠቃ ሚዎች ይሆናሉ፡፡  በእርግጥ አንዳንዶች የመደናገጥ ሁኔታ ቢታይባቸውም እኛም ባገኘነው ስል ጠና መሰረት በተቻለ መጠን የማረጋጋት ስራችንን ከሰራን በሁዋላ ወደትክክለኛው ሁኔታ እን መራቸዋለን። ሁኔታውን ትንሽ ቀደም ካለው ጊዜ ጋር ስናነጻጽረው እጅግ የተሻሻለ እና የሚያስ ደስት ባህርይ እና የስርጭት አድማሱም መቀነሱን የሚያመላክቱ ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡ ታካሚ ዎች የምክር አገልግሎት ሲሰጣቸው የሚነገራቸውን የመስማት እና በትክክል የመተግበር እር ምጃን ስለሚያሳዩ ወደፊት ለሚኖረው ከኤችአይቪ ነጻ የሆነ ትውልድን የማፍራት እቅድ ተግባ ራዊነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡
ሌላው የህክምና ባለሙያ መወሻ መንገሻ ይባላል፡፡ እሱ እንደሚገልጸው “...ከአሁን ቀደም ያለውን ሁኔታ ከአሁኑ ጋር ስናነጻጸር ብዙ የተለዩ ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡ ለምሳሌም...በአሁኑ ወቅት ታካሚዎች በሙሉ ፈቃደኘነት ...ምን ችግር አለ? በማለት የሚነገራቸውን ለመቀበል ዝግጁ ሲሆኑ ቀደም ሲል ግን እንኩዋንስ የሚነገራቸውን በጸጋ ሊቀበሉ ቀርቶ ወደምርመራው ክፍል እንኩዋን ለመግባት የሚያንገራግሩ ነበሩ። ቀደም ባለው ጊዜ አንዳንድ እናቶች እራሳ ቸውን ከማወቅ እና መፍትሔውን ከመሻት ይልቅ ችግሩን ደብቀው እራሳቸውንም ሳይረዱ የእርግዝና ውን ጊዜ ስለሚቀጥሉ ከቫይረሱ ነጻ የሆነ ልጅ ለማፍራት ቸገር እንደነበር አይዘነ ጋም፡፡ አሁን የሚመጡ ታካሚዎች ግን ከእንደዚህ ያለው እምነት ተላቀው ለምክር አገል ግሎቱ በፈቃደኝነት ስለሚቀርቡ እና በሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጣቸውን ምክር ስለሚ ቀበሉ ከቫይረሱ ነጻ የሆነ ልጅ እያገኙ መሆኑ ትልቅ ልዩነት ነው፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ወቅት እናቶች በኤችአይቪ ቫይረስ ምክንያት መሞታቸው ሙሉ በሙሉ ቀርቶአል ለማለት ባያስደፍርም በእጅጉ መቀነሱን ግን መናገር ይቻላል፡፡”
ከኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር የስራውን እንቅስቃሴ ለመመልከት የወጣው ቡድን በየተቋማቱ ያሉትን የስራ ሁኔታዎች እና ያጋጠሙ ችግሮችን የሚመረምር ሲሆን ጉድለቱንም ለማሟላት የራሱን እርምጃ ይወስዳል። ዶ/ር ..ዎድሮስ ማለደ የቡድኑ መሪ እንደሚሉት .....በጋራ የምንንቀሳቀሰው በአሰራር ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ነው፡፡ ማህበሩ ስራውን የሚሰራው እንደ አንድ ባለድርሻ አካል በመሆን ከመንግስት እና ድጋፍ ሰጪ አካላት ጋር በመተባበር ስለሆነ ማነቆ የሚሆኑ ነገሮች በጊዜው መፍትሔ የሚያገኙበትን መንገድ እንቀይሳለን፡፡ብዙ ጊዜ የሚገጥመው ችግር የኤችአይቪ መመርመሪያ ኪት እጥረት ሲሆን ይህም በአገር አቀፍ ደረጃ የነበረ ችግር ነው፡፡ አሁን ግን ችግሩ ሙሉ በሙሉ የተቀረፈ ስለሆነ የነበረው የአሰራር ሁኔታም እየተቀየረ ያለበት ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡ በዚህም ረገድ መንግስት ከፍተኛውን ድርሻ ወስዶ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ስጋትን ቀንሶአል፡፡.. ብለዋል።

Read 2074 times