Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 03 December 2011 08:03

ኢህአዴግና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቦታ ይለዋወጣሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ዋናው ችግር፤ ፓርቲዎች በሃሳብ መለያየታቸው ሳይሆን በሃሳብ መስማማታቸው ነው
ድሮ፤ “ኢህአዴግ የሻእቢያ ቅጥረኛ ነው” - ተቃዋሚ ፓርቲዎች።
ዛሬ፤ “ተቃዋሚዎች የሻእቢያ ተላላኪ ናቸው” - ኢህአዴግ።
በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካው፤ ባለፉት አምስት አመታት እየተንሰራፋና ስር እየሰደደ በመጣው የመንግስት ቁጥጥር ሳቢያ ስጋት ያደረበት ሰው፤ “የኢህአዴግንና የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲን ፍቅር” ሲያይ ... ስጋቱ ወደ ፍርሃት ሊለወጥበት ይችላል። በእፎይታ ወደ ነፃነት መራመድ ጀምረናል በሚል ተስፋ፤ እርምጃው እንዲፈጥን የምንመኝ ከሆነ፤ ጊዜው አስደሳች አይደለም፤ የሚያሰጋ እንጂ። ደግሞም፤ የአንድ ፓርቲ አምባገነንነት በነገሰበት ፖለቲካ፤ እንዲሁም ንብረት በሚወረስበት የቁጥጥር ኢኮኖሚ ውስጥ፤ በዜጎች ላይ የሚያደርሰው ስቃይ ዘግናኝ ነው። እናም ገና ከሩቁ ያሰጋል፤ ያስፈራል።


ግን ከምር፤ ኢህአዴግ ቀስ በቀስ የቀድሞ ኮሙኒስትነቱ እያገረሸበት ነው እንዴ? ይህን ጥያቄ በሌላ ጥያቄ መልሶ የሚያፋጥጥ አይጠፋም - “ለመሆኑ ኢህአዴግ ከኮሙኒዝም መች ተላቀቀ?” በማለት። በእርግጥም፤ ነገርዬው በቀላሉ የማይራገፍ ክፉ በሽታ ሳይሆን አይቀርም። የኢህአዴግ ብቻም አይደለም። በኮሙኒዝም ጥርሳቸውን የነቀሉ የአገራችን አንጋፋ ፓርቲዎችንና ፖለቲከኞችን ተመልከቷቸው። ላይ ላዩን እንጂ ሙሉ ለሙሉ ነቅሎ አልወጣላቸውም።
ኢህአዴግና ብዙዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ በዋና ዋና የፖለቲካና የኢኮኖሚ አስተሳሰብ በጣም ተቀራራቢና ተመሳሳይ ሆነው የሚታዩትኮ አለምክንያት አይደለም። በማርክሲዝም ሌኒንዝም ጡጦ ያደጉ ናቸው። ለማብጠልጠል እንዳይመስላችሁ። የ1960ዎቹ “አብዮተኞች”፤ እያንዳንዱ ህፃን በኮሙኒዝም መጠመቅ አለበት ብለው በመፅሄት ያሳተሙትን አይቼ ነው - የመፅሄቱ የፊት ሽፋን ላይ የሚታየው የህፃን ስእል፤ “ማሌ” የሚል የተፃፈበትን ጡጦ ይጠባል። ማርክሲዝም ሌኒንዝም መሆኑ ነው። ያንን ጡጦ፤ በወፍራሙ ወይም በስሱ ያልተጋተ አንጋፋ ፓርቲ የለም ማለት ይቻላል። አዳዲሶቹ ፓርቲዎችም ቢሆኑ፤ ከቫይረሱ አላመለጡም።
በእርግጥ የአገራችን ፓርቲዎች፤ እንደድሮው “አብዮታዊ አምባገነንነትን” በማስፈን ተቀናቃኞችን ሁሉ ለማጥፋትና ዜጎችን በአፈና ለመግዛት እንፈልጋለን እያሉ በይፋ መፈክር አያሰሙም። አንጋፋ ፓርቲዎቻችን እና ፖለቲከኞቻችን ድሮ የጨፈሩበት ያ የአምባገነንነት መፈክር ዛሬ የለም።
ነገር ግን፤ ሙሉ ለሙሉ አራግፈውታል ማለት አይደለም። ብዙዎቹ የአገራችን ፓርቲዎች ዛሬም እንደምናያቸው፤ ፍላጎታቸው ተመሳሳይ ነው - ስልጣንን በብቸኝነት የሚቆጣጠር፤ ፉክክር በሌለበት ምርጫ ሁሌም የሚያሸንፍ ገናና ፓርቲ ለመሆን ይፈልጋሉ። አንዱ ፓርቲ ሌላኛውን እንደተፎካካሪ ሳይሆን እንደጠላት ያያል። “ደመኛ ጠላቶቻችን” የሚለው አባባል አስታወሳችሁ?
በጠላትነት ለመፈረጅና ለማሳደድ የሚያገለግሉ የስድብ ቃላት እልፍ ናቸው። ከሃዲ፣ ባንዳ፣ ተንበርካኪ፣ ተገንጣይ፣ አስገንጣይ፣ አጥፍቶ ጠፊ፣ አሸባሪ፣ ሰርጎ ገብ፣ ነጭ ለባሽ፣ ምንደኛ፣ የምእራባዊያን ሰላይ፣ የውጭ ሃይሎች ተላላኪ... ዘርዝረን ለመጨረስ ብንችል እንኳ ዋጋ የለውም። ነገ ሌላ አዲስ የጠላትነት ቃል ፋሽን ሆኖ ይመጣል። በዚያ ላይ “ፀረ” የምትለዋ ተቀፅላ አለች። ፀረህዝብ፣ ፀረአንድነት፣ ፀረአገር፣ ፀረልማት፣ ፀረሰላም፣ ፀረህገመንግስት... የስድብና የውንጀላ ምርጫ እንደልብ ነው።
ይህም ብቻ አይደለም። አንዱ ፓርቲ ሲጠቀምበት የነበረ ቃል፤ ከጊዜ በኋላ ሌላኛው ይጠቀምበታል። ቦታ እንደመለዋወጥ ነው። ከጥቂት አመታት በፊት በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ ኢህአዴግን እንዴት ያወግዙ እንደነበር አስታውሱ ... “በአገር ላይ ክህደት የፈፀመ፤ የአገርን ጥቅም ለውጭ ሃይሎች አሳልፎ የሚሰጥ ተንበርካኪ፤ የምእራባዊያን ተላላኪ፤ የሻእቢያ ቅጥረኛ... “። ዛሬስ? ኢህአዴግ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በክህደት ወንጀል ሲከሳቸው አይተናል። “የውጭ ሃይሎች ተላላኪ፤ የሻእቢያ ነጭ ለባሽ...” ሲላቸውም እንሰማለን። ተቃዋሚ ፓርቲዎችም፤ የአፀፋ ምላሽ አያጡም።
እስቲ አስቡት። አንዱ ፓርቲ፤ ሌሎቹን ፓርቲዎች ፀረአንድነትና አስገንጣይ፣ ፀረሰላምና ፀረልማት፣ ከሃዲና ነጭ ለባሽ፣ ባንዳና አሸባሪ ብሎ እየፈረጀ፤ እንዴት አገር ጤና ይሆናል? እንዴትስ ስልጡን ፖለቲካ ሊገነባ ይችላል? ፓርቲዎች በጠላትነት በተፋጠጡበት አገር ውስጥ፤ “የእያንዳንዱ ሰው ነፃነት የተከበረበትና ፓርቲዎች የሚፎካከሩበት ስልጡን ፖለቲካ” ሊያብብ አይችልም። ለምን?
የኢህአዴግ ወይም የአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ሆናችሁ አስቡት። ምን ታያችሁ? እንግዲህ፤ “ሌሎች መሪዎችና ሌሎች ፓርቲዎች ጠላቶቼ ናቸው” የሚል ነው መነሻችሁ። ስለዚህ...፤ “እነሱ ስልጣን ከያዙ አገሪቱን ከፋፍለውና ሸጠው፣ አሸብረውና አጥፍተው፤ ህዝቡን አናቁረውና ረግጠው፣ አናውጠውና አደህይተው እንጦረጦስ ይወርዳሉ”... እና ምን ይሻላል? “አይኔ እያየ፤ ሌሎች መሪዎችና ሌሎች ፓርቲዎች ስልጣን መያዝ የለባቸው። ስልጣን ይዘው ከሆነም፤ እነሱን አያርገኝ” የሚል ቁጣ አያቃጥላችሁም?
በመንግስታዊ የኢኮኖሚ ቁጥጥር የታጀበ፤ እንዲህ አይነቱ ኋላቀር የመጠፋፋት ፖለቲካ አለምክንያት አልመጣም። ሁሉም ፓርቲዎች ከሚስማሙበት መሰረታዊና የተሳሳተ አስተሳሰብ የሚመነጭ ነው። የሚስማሙበት የጋራ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አስተሳሰባቸው ምን እንደሆነ አታውቁም? ኧረ በግልፅ ይታወቃል። “ህዝባዊ ወይም አገራዊ” አስተሳሰብ ልትሉት ትችላላችሁ - ህዝባዊነት (Socialism, Communism) ወይም አገራዊነት (Nationalism)። “ለአገር ጥቅም እና ለህዝብ ፍላጎት ሲባል ማንኛውንም ማድረግ ይቻላል” የሚል አስተሳሰብ። የዚህን አስተሳሰብ ጉድ ለማውጣት፤ ትንሽ ዘርዘር አድርገን፤ በቅርቡ ካየናቸው ክስተቶች ጋርም አያይዘን እንመልከተው።
አንደኛ፤ “አገርን ይጠቅማል ወይም ህዝብ ይፈልገዋል የሚባል ነገር ሲመጣ፤ ማንኛውንም ዜጋ ይህንን እንዲፈፅምና እንዲያሟላ ማስገደድ ይቻላል” ማለት ነው። “የግል ነፃነት፤ መብት ይከበር” ብሎ መከራከር ተቀባይነት አይኖረውም። “ቅድሚ ለአገር ጥቅም፤ ቅድሚያ ለህዝብ ፍላጎት” በሚል ሰበብ... ለምሳሌ አንድ ነጋዴ ከውጭ ያስመጣውን ዘይት በግድ ለመንግስት እንዲያስረክብ ማዘዝ፤ ዜጎች በግድ የጡረታ ቀረጥ እንዲከፍሉ ማወጅ፤ ባንኮች በግድ የመንግስት ቦንድ እንዲገዙ ወይም ነዋሪዎች ቤታቸውን አፍርሰው ከመኖሪያ አካባቢያቸው እንዲፈናቀሉ ድንገት መወሰን ይቻላል። የስራ ቦታና ብድር ለማግኘት ወጣቶች በማህበር እንዲደራጁ፤ ነጋዴዎች ቢያከስራቸውም መንግስት ባወጣው ተመን እንዲሸጡ ማስገደድም ይቻላል - ለህዝብ ጥቅም ወይም ለአገር ልማት በሚል እስከሆነ ድረስ። አዲሱ የሊዝ አዋጅ እንደሚደነግገውም፤ ማዘጋጃ ቤት እዳ አልከፈልክም ብሎ ካመነ ለፍርድ ቤት ክስ ማቅረብ ሳያስፈልገው ንብረት መውረስ ይችላል - ለአገርና ለህዝብ ሲባል።
ሁለተኛ፤ “|አገርን ይጎዳል ወይም ህዝብ አይፈልገውም” የተባለ ነገር ሲመጣ፤ ማንኛውንም ዜጋ ከማናቸውም ድርጊት መከልከልና ማገድ ይቻላል - ዘይት ከውጭ አስመጥቶ እንዳይነግድ፤ መሬት ገዝቶ ወይም ተከራይቶ እንዳይገነባ፤ ባለታክሲው ተዟዙሮ እንዳይሰራ መከልከል፤ ቴሌቪዥን ጣቢያ እንዳያቋቁም፤ ተቃውሞና ትችት በቲቪ እንዳያቀርብ መገደብ፤ መንግስት በሚፈልጋቸው መስኮች ካልሆነ በቀር በቂ ብድር እንዳያገኝ መዝጋት፤ የግል ኮሌጆች በርቀት ትምህርት ተማሪዎችን እንዳይመዘግቡና የህግ ትምህርት እንዳይሰጡ ማገድ ... ከዚህም በተጨማሪ ማለቂያ በሌላቸው እልፍ ቁጥጥሮች ማደናቀፍ ይቻላል። ይሄ ነው፤ ህዝባዊ ወይም አገራዊ አስተሳሰብ።
የአገራችን ፓርቲዎች፤ በዚህ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። የጡረታ ታክስ በግዴታ ማስከፈልን የተቃወመ ፓርቲ አጋጥሟችኋል? እስካሁን የለም። መንግስት እንዳሻው ብር የማተም ስልጣን እንዳይኖረውና መጠን እንዲበጅለት ለማድረግ የህግ ረቂቅ ያዘጋጀ ፓርቲ ወይም ፖለቲከኛ አለ? በጭራሽ። ብር በገፍ የሚታተመው፤ “ለአገር ልማት ወይም ለህዝብ ጥቅም” በሚል እስከሆነ ድረስ፤ የዜጎች የቁጠባ ሂሳብ ዋጋ ቢያጣ ችግር የለውም። ብዙዎቹ ፓርቲዎች በዚህ አስተሳሰብ ይስማማሉ። ታዲያ ልዩነታቸው የቱ ላይ ነው? አንደኛ፤ “በቅድሚያ የትኞቹ ዜጎች ላይ ግዴታ እንጫንባቸው? በየትኛው መስክ ክልከላውን እናክብደው?” በሚሉ ጥቃቅን ዝርዝር ጉዳዮች ዙሪያ ፓርቲዎች ሊለያዩ ይችላሉ። ያን ያህልም ለውጥ የሚያመጣ ልዩነት አይደለም። ሁለተኛ፤ “የሚያስገድድ አዛዥና የሚከለክል አጋጅ ማን ይሁን? ማን ስልጣን ይዞ እንዳሻው ይግዛ? እኔ ልሁን፤ እኔ ልግዛ” በሚለው ጉዳይ ፓርቲዎቹ በጣም ይለያያሉ - እናም የስልጣን ፉክክር ሳይሆን ትንቅንቅ ይነግሳል። በጠላትነት ወደ መጠፋፋት ያመራሉ። ዋናው ችግር ግን፤ የሚለያዩበት ጉዳይ መኖሩ ሳይሆን፤ በጋራ የተስማሙበት መሰረታዊ አስተሳሰብ የተሳሳተ መሆኑ ነው - “ህዝባዊ ወይም አገራዊ አስተሳሰብ”።
የዚህ ተቃራኒ አስተሳሰብ አለ - “የፖለቲካ ስርአት ዋና አስኳል የግለሰብ መብት (የእያንዳንዱ ሰው ነፃነት) መሆን አለበት” የሚል። እናም፤ የመንግስት ስራ፤ የእያንዳንዱን ሰው ነፃነት ማስከበር ብቻ ይሆናል። በዚህ አስተሳሰብ መሰረት፤ መንግስት፤ የሰዎችን ህይወትና ንብረት ከጥቃት የመጠበቅ ሃላፊነቱን ብቻ እንዲሰራ ብናደርግ ኖሮ፤ ያን ያህል የስልጣን ሽኩቻ አይኖርም ነበር። ዘበኛ ወይም ጠባቂ ለመሆን፤ ብዙ ትንቅንቅ ይፈጠራል? አይፈጠርም። በዚያ ላይ፤ የትኛውም ፓርቲና መሪ ስልጣን ቢይዝ፤ ተፎካካሪዎችን የማጥፋት ወይም ሌሎች ዜጎችን የማዋከብና የማፈን ስልጣን ስለማይኖረው ችግር አያመጣም። በተቃራኒው “በህዝባዊ ወይም በአገራዊ አስተሳሰብ” ተመርተን፤ መንግስት፤ በሰዎች ህይወትና ንብረት ላይ የማዘዝ ስልጣን እንዲኖረው ከተስማማን ግን፤ ሽኩቻውና ትንቅንቁ የሞት ሽረት ጉዳይ ይሆናል። መንግስት የሰውን ነፃነት እንደፈለገው የመጣስና ያሻውን ነገር የመፈፀም ስልጣን እንዲኖረው ፈቀደናል ማለት ነው። ትርጉሙ ግልፅ አይደለም? መዘዙ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ አይታያችሁም? በቃ... መንግስት አድራጊ ፈጣሪ ይሆናል። ማንኛውም ፓርቲ ወይም መሪ ስልጣን ላይ ቢወጣ፤ ያሰኘውን ያህል የዜጎችን መብት መርገጥ ይችላል - “ለህዝብ ጥቅምና ለብሄረሰቦች እኩልነት ፤ ለአገር ልማትና ለአገር አንድነት” እያለ። ብዙ ፓርቲዎችና ብዙ ዜጎች ግን፤ ይህንኑን “ህዝባዊ ወይም አገራዊ” አስተሳሰብ ይዘው፤ ትርጉሙንና መዘዙን ላለማየት አይናቸውን ይጨፍናሉ። “ልቦናቸው” ግን ያውቀዋል። ለዚህም ነው፤ የአንደኛው ፓርቲ ስልጣን መያዝ፤ ለሌላኛው የህልውና አደጋ ሆኖ የሚታየው። ስልጣን የያዘ ፓርቲ፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን መወንጀልና ማሰር፤ ዜጎችን ማዋከብና ማሳደድ እንደሚችል አሳምረው ያውቁታል። ሌላኛው ፓርቲ ስልጣን ከያዘ፤ ይሄኛው ፓርቲ ውንጀላና እስር እንደሚጠብቀው፤ ወከባና ስደት እንሚጋረጥበት ይገባዋል። ታዲያ ፓርቲዎቹ በጠላትነት መተያየታቸው ይገርማል?

 

Read 3358 times Last modified on Saturday, 03 December 2011 08:06