Saturday, 30 November 2013 11:19

በ700 ሚ.ብር የእርሻ ሥራ ላይ የተሰማራው ግሪን ኮፊ አግሮ ኢንዱስትሪ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(4 votes)

አንድም የአገር ውስጥ ባንክ እርሻችንን አልጐበኘም
ከፒቲኤ ባንክ 3 ሚ.ዶላር ተበድረን ሰርተን ከፍለናል
በቀጣዩ ዓመት የተቆላ ቡናና የማር ማቀነባበሪያ ፋብሪካ እንከፍታለን

ቤተሰባቸው ገበሬና ነጋዴ ነበሩ፡፡ አባታቸው የግብርና ውጤቶችን ወደ አዲስ አበባ እያመጡ፣ ከዚህ ደግሞ ሸቀጣ-ሸቀጥ

ወደ መቀሌ እየወሰዱ ይነግዱ ነበር፡፡ ቤተሰባቸውን እየረዱ ስላደጉ፣ እንደአባታቸው የመሆን ፍላጐት አደረባቸው፡፡

ስለዚህ ከጀርመን፣ ከዱባይ …፣ የተለያዩ መሳሪያዎች እያመጡ ይሸጡ ነበር፡፡ በዚህ ብቻ መወሰን አልፈለጉም፡፡
ከውጭ ዕቃዎችን ሲያስገቡ በተጓዳኝ ወደ ውጪም (ኤክስፖርት) የሚደረግ የአገር ውስጥ ምርት መኖር አለበት በማለት

አሰቡ፡፡ ለዚህ እንደ አማራጭ የወሰዱት ቡናን ነው፡፡ ስለዚህ፣ በ1988 ዓ.ም ግሪን ኮፊ የተባለ ድርጅት አቋቁመው ወደ

እርሻ እንደገቡ ይናገራሉ-የዛሬው ግሪን ኮፊ አግሮ ኢንዱስትሪ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደለ አብረሃ፡፡
አቶ ታደለ ተወልደው ያደጉት መቀሌ ከተማ ነው። በትምህርት በንግድ ዲፕሎማ ሲኖራቸው፣ በዚሁ ዘርፍ የተለያዩ

ኮርሶች መውሰዳቸውን ይናገራሉ፡፡ ከ18 ዓመት በፊት ብዙ ሰው ደፍሮ ወደማይሞክረው የእርሻ ዘርፍ ገብተው ዛሬ አንቱ

የተባሉ ዘመናዊ ገበሬ ሆነዋል፡፡ ስኬትና አርአያነታቸው ለሎችም ትምህርት ይሆናል ብዬ ስላሰብኩ፣ ከአቶ ታደለ ጋር

ያደረግነውን ውይይት ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡
በ1988 ዓ.ም በደቡብ ክልል በከፋ ዞን ጨና ወረዳ 1000 ሄክታር መሬት ወስደን ቡና መትከል የጀመርን የመጀመሪያው

የግል ድርጅት እኛ ነን። ከዚያ አንድ ዓመት በፊት በደቡብ ክልል ጌጄኦ ዞን በዲላ ከተማ አንድ ሄክታር መሬት ገዝተን፣

ቡና መፈልፈያ ወፍጮ አቋቁመን ነበር፡፡ ነገር ግን በአካባቢያችን የራሳችን የቡና መሬት መኖር አለበት ብለን ስላሰብን፤

ያንን የቡና መፈልፈያ፣ ለሸሪካችን በመተው ወደ ከፋ ዞረን ቡና መትከል ጀመርን፡፡
በየዓመቱ አንድ ሁለት ሄክታር መሬት እየተከልን፣ አንድ ሺውን ሄክታር በ1993 አካባቢ ጨረስነው፡፡ በወቅቱ፣ ትልቁ

የቡና እርሻ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ያሉት የግል እርሻዎች የእኛና የሚድሮክ ሲሆኑ፣ ትልቁ የእኛ ነው፡፡ የመጀመሪያውን

መሬት ቡና ተክለንበት እንደጨረስን መሬት ጠይቀን በከፋ ዞን ዴቻ ወረዳ አንድ ሺህ ሄክታር ተሰጠን፡፡
ሁለት ሺውን ሄክታር መሬት አልምተን እንደጨረስን፣ በ1998 ዓ.ም፣ የደቡብ ክልል፣ ብዙ ሠራተኛ ያላቸው፤

ለኤክስፖርት አስተዋጽኦ ያደረጉ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ያደረጉ፣ ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር የጠበቀ ቁርኝት ያላቸውና

የተለያየ ድጋፍ ያደረጉ፣ በእርሻና በኢንዱስትሪ የተሳተፉ፣ … በሚል ውድድር አካሂዶ ነበር፡፡ በዚያ ውድድር እኛ በእርሻና

በአግሮ ኢንዱስትሪ አንደኛ ስለወጣን የእውቅና ሰርቲፊኬት ተሸለምን፡፡
በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ደሞዝ እንከፍላለን። ለአካባቢው ኅብረተሰብ የውሃ፣ የጤናና የትምህርት፣ … አገልግሎት ድጋፍ

እናደርጋለን፡፡ ገበሬው እኛ ጋ ያየውን የቡና አተካከል፣ እቤቱ ሲመለስ ተግባራዊ ያደርጋል፣ … ምን ልበልህ ምንም

ያልነበረበት አካባቢ ከፍተኛ ለውጥ አመጣ፡፡ ዞኑም ባገኘነውና በአካባቢው በተፈጠረው ለውጥ በመደሰት ተጨማሪ 500

ሄክታር መሬት እንድናለማ ሰጠን፡፡ የአካባቢው ሕዝብ ተጠቃሚነትና ለውጥ እየጨመረ ሄደ፡፡
እንደዚህ እያልን ከቆየ በኋላ ከሦስት ዓመት በፊት፣  የመንግሥት የቡና ተክል የነበረው የቴፒ ቡና ተክል ሊሸጥ ጨረታ

ወጣ፡፡ እኛም በጨረታው ተሳትፈን፣ ቴፒ የእርሻ ልማትን ከመንግሥት ጋር በጆይንት ቬንቸር ገዛነው፡፡ በበቃን ሚድሮክ

ወሰደው፡፡ ቴፒ ሰፊ ሲሆን ከ10ሺህ በላይ ሠራተኛ አለው፡፡ እርሻው ውስጥ ሁለት 2ኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ስድስት አንደኛ

ደረጃ ት/ቤት፣ 10 ያህል መዋለ ሕፃናት፣ ስድስት ሳይት፣ ጤና ጣቢያ፣ ክሊኒክ፣ ፋርማሲ፣ ሆስፒታል ሁሉም ነገር

ስላለው ትልቅ ከተማ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በቴፒ ከተማ እንደ ቢሮና እንደ መዝናኛ ክበብ የሚያገለግለው ትልቁ

እንግዳ ማረፊያ የእኛ ነው፡፡
እስከዚያ ድረስ ምንም ችግር አልገጠማችሁም?    
ኦ! በዘዴና ብርታት አለፍነው እንጂ በተለይ በ1993/94 ዓ.ም ከፍተኛ የገንዘብ ጥረት አጋጥሞን ነበር፡፡ በዚያን ዘመን

ከባንክ ብድር ጠይቀን ነበር። ባንክ ለእርሻ ብድር ስለማይሰጥ ከለከለን፡፡ ምንም አማራጭ ስናጣ ፒቲኤ (የምሥራቅና

ደቡባዊ አገሮች ልማት ባንክ) ጠየቅን፡፡ ባንኩም ከኬንያና ከሌሎች አገሮች ባለሙያዎች ልኮ እርሻችንን ጐበኙና በጣም

ተገረሙ፡፡ ባንኩ፤ ምንም አላቅማማም፣ ወዲያውኑ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ብድር ፈቅዶልን፣ 10 የተለያዩ ከባድ

መሳሪያዎች ገዝቶ ሰጠን፡፡ ከፒቲኤ ተበድረን ተሳክቶልን በመክፈል እኛ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹ ነን፡፡ ከዚያ በፊት

ለጫማ ፋብሪካ ሰጥቶ አልተሳካለትም፡፡
አሁንም ላቀድናቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች ከባንኩ ብድር ለመጠየቅ አሰበናል፡፡ “ግሪን ኮፊ አግሮ ኢንዱስትሪ ከ20

ሚሊዮን ዶላር በታች አይጠይቀንም፤ እኛም አንሰጥም፡፡ ቶሎ በሉ እንጂ!” እያሉን ነው፡፡ እኛ ከባንኩ ጋር ቤተኛ ነን፡፡

እዚህ አገር ያለ አንድም ባንክ እርሻችንን ጐብኝቶ አያውቅም፡፡ እነሱ ግን ብዙ ጊዜ መጥተው አይተውናል፡፡ እነሱ፣

የእርሻ ችግር ይገባቸዋል፡፡ መጥተው አይተው ችግር ካለብን የግድ ክፈሉ አይሉንም፤ ስታገኙ ትከፍላላችሁ ብለው

ያልፉናል፡፡
መጀመሪያ ሥራ ስትጀምሩ ኢንቨስትመንታችሁ ምን ያህል ነበር?
የመጀመሪያውን 100 ሄክታር ያለማነው በ30 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ አሁን ግን 30 ሚሊዮን ብር ለ1000 ሄክታር ቀርቶ

ለሁለት ሄክታር እንኳ አይበቃም፡፡ ያኔ፣ ጊዜው ጥሩ ስለነበረ፣ ለቀን ሠራተኛ የምንከፍለው 3.50 ነበር፡፡ ዛሬ ግን በቀን

60 እና 70 ብር ነው የሚከፈለው፡፡ የቡና ሥራ ደግሞ ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ ከፍተኛ የሰው ኃይል የሚፈልግ ነው፡፡
ያኔ ምን ያህል ሠራተኛ ነበራችሁ? አሁንስ?
ያኔ 1,500 ያህል ሠራተኞች ነበሩን፡፡ አሁን ቴፒን ጨምሮ ከ20 በላይ ሠራተኞች አሉን፡፡ የቡና ሥራ ወቅታዊ ስለሆነ፣

በለቀማና በእንክብካቤ ጊዜ የጊዜያዊ ሠራተኞች ቁጥር ይጨምራል፡፡ ቋሚ ሠራተኞች ከ6 ሺህ እስከ 7ሺህ ይሆናሉ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ፣ የገበሬውን ዘመድና ከተለያዩ ዞኖች ሰዎች እናመጣለን፡፡ በትላንትናው ዕለት እንኳ ወደ 2,600

ሰዎች አምጥተዋል፡፡ በዘመቻ የሚሠራው ሁልጊዜ አይደለም፡፡ በሳምንት ሦስት ቀን ሰኞ፣ ረቡዕና ዓርብ ነው፡፡
አሁን ካፒታላችሁ ምን ያህል ነው?
የሁለቱም እርሻ የተለያየ ነው፡፡ የቴፒ ወደ 500 ሚሊየን፣ የመጀመሪያው ደግሞ ወደ 200 ሚሊዮን ብር ነው፡፡
ስኬታችሁ ያስገኘላችሁ ምን እውቅና አለ?
አዎ! አምና እስካሁን ባለው የእርሻና የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ በደቡብ ክልል በተካሄደው ውድድር፣ እኛ በእርሻ፣

ቢጂአይ ደግሞ በኢንዱስትሪ አሸናፊዎች ነበርን፡፡ ከዚያ በኋላ አምና በባህርዳር ከተማ የገበሬዎች በዓል ነበር፡፡ በዚያ

በዓል ላይ፣ ከገበሬዎች ጋር በመሥራትና በኤክስፖርትና በሌላውም ሁሉ ለውጥ በማምጣት ከመላ ኢትዮጵያ 1ኛ ሆነን

ተሸልመናል፡፡
በዓመት ምን ያህል ቡና ወደ ውጭ ትልካላችሁ?
በእርሻችን የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ስላሉን በኮንስትራክሽን እንሳተፋለን፡፡ ሌላውና ዋነኛው ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ

ለሙከራ በ200 ሄክታር መሬት ላይ የተተከለ ብቸኛ የፓልም ኦይል ተክል አለን፡፡ ቴፒ እርሻው ላይ የተተከለ መጠነኛ

የዘይት ፋብሪካም አለን፡፡፡ ፓልም ላይ ኢንቨስት ወይም ጥናት አደርጋለሁ የሚል ሰው እኛ ጋ ነው የሚመጣው፡፡
ሌላ ደግሞ የንብ እርባታ አለን፡፡ እርሻው ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ቀፎዎች አሉን፡፡ ከአሁን በፊት ሁለት ጊዜ ማር

ኤክስፖርት አድርገናል፡፡ አሁን ምርቱን ለመጨመርና በብዛት ወደ ውጭ ለመላክ ፋብሪካ እየተከልን ነው፡፡
ቅመማ ቅመም ደግሞ ከ500 እስከ 600 ሄክታር የሚሆን እርሻ አለ፡፡ ሄል፣ ቁንዶ በርበሬ፣ ዝንጅብል፣ ኮረሪማ፣ …

እናመርታለን፡፡ ካሁን በፊት ሁለት ጊዜ ኤክስፖርት አድርገናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከውጪው ገበያ የአገር ውስጥ ዋጋ

ስለሚበልጥ እዚሁ ጨረታ አውጥተን እንሸጣለን፡፡
200 ሄክታር የአትክልት እርሻም አለን፡፡ ማንጐ፣ ብርቱካን፣ አቡካዶ፣ ሙዝ፣ … አለን፡፡ እነዚህም እዚሁ በሚሊዮን

ብሮች ይሸጣሉ፡፡ ለሠራተኛው በቆሎ ይዘራል፣ ወፍጮ ቤቶች፣ ዳቦ ቤቶች፣ … በቡና ለቀማ ጊዜ ለሠራተኛው

የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ አለ፡፡
እዚህ ይህ ማሽን ምንድነው የሚሠራው?
ይኼ ማሽን ፒቲኤ ባንክ በ1.1 ሚሊዮን ዩሮ ከጀርመን የገዛልን እጅግ ዘመናዊ የቡና ፕሮሰስ ማድረጊያ መሳሪያ ነው፡፡

መሳሪያው፣ ድምፅ የለው፣ አቧራ የለው፣ ብናኝ የለው፣ አስፈላጊ ሲሆን ጣሪያው ተከፋች ነው፤ በአጠቃላይ ሙቀትና

ቅዝቃዜ መቆጣጠሪያና አቧራ መምጠጫ አለው፡፡
ሁለት ዓይነት ቡና ነው ወደዚህ የሚመጣው፤ የታጠበና ያልታጠበ ይባላል፡፡ የታጠበ የሚባለው፣ የበሰለው ቀይ የቡና

ፍሬ ተለቅሞ፣ በወፍጮ ተፈልፍሎ፣ታጥቦና ደርቆ ከነገለባው ይመጣል፡፡ ያ ቡና እዚህ ማሽን ውስጥ ገብቶ ሲፈለፈል

ቡናው ከገለባው ይለያል፡፡ ያ ቡና እንግዲህ የተሰባበረና፣ አፈርና ቆሻሻው ተለቅሞ፣ ተመዝኖ ኤክስፖርት ይደረጋል፡፡

ያልታጠበው ቡና፣ እዚያው ከነልባሱ (ጀንፈል) ደርቆ፣ በደረቅ የቡና ወፍጮ ተፈልፍሎ መጥቶ የታጠበው ቡና

በሚያልፍበት ሂደት ያልፋል፡፡
እዚህ ስንት ሠራተኛ አላችሁ?
በአንድ ፈረቃ 300 ሠራተኞች አሉ፡፡ ሚያዝያና መጋቢት ሥራ ስለሚበዛ በሦስት ፈረቃ ስንሠራ ቡና ለቃሚ ሴቶች

900፣ ካቦ ጫኝና አውራጅ፣ … ሲደመሩ፣ ከ1000 በላይ ሠራተኞች ይኖሩናል። በሁለት ፈረቃ ከሆነ ደግሞ 600

ሠራተኞች ይኖራሉ፡፡ ከዚያ በታች ግን አይወርድም፡፡
ቡናውን ከእርሻ ወደዚህ የምታመጡት በኪራይ መኪና ነው?
አይደለም፤ በራሳችን መኪኖች ነው፡፡ 10 ከባድ መኪኖች ስላሉን በእነሱ እናመጣለን፡፡ ከዚህ ደግሞ ሲሚንቶ፣ ማዳበሪያ፣

ኬሚካል፣ የሠራተኞች የሥራ ልብስ፣ … ጭነው ይመለሳሉ፡፡ ወደ ጅቡቲ የምንልከው ግን በድርጅቶች መኪና ነው፡፡

ሥራ በሚበዛበት ጊዜ መኪኖች ስለማይገኙ መዘግየት ይፈጠራል፡፡ ያንን ክፍተት ለመሙላት የራሳችን መኪኖች

እንዲኖረን እያሰብን ነው፡፡
ለመንግሥት ግብርና ታክስ በዓመት ስንት ትከፍላላችሁ?
የቴፒ እርሻ ገና ነው፡፡ በበፊተኞቹ ግን በአጠቃላይ ከ40 እስከ 50 ሚሊዮን ብር እንከፍላለን፡፡
በዚህ ጊዜ ውስጥ ያጋጠማችሁ ትልቅ ፈተና ምንድነው?
እኛ አገር ያለው ፈተና ሁለት ዓይነት ነው። አንደኛው፣ እንደ ዘንድሮ የቡና ዋጋ በጣም ወድቆ አያውቅም፡፡
በዛሬው ቀን (ባለፈው ረቡዕ) በኒውዮርክ ገበያ አንድ ፓውንድ 1.05 ዶላር ነው። (አንድ ኪሎ 2.2 ፓውንድ ነው) አምና

በዚህ ጊዜ ቡና በጣም ወድቋል በተባለበት ጊዜ፣ አንድ ፓውንድ ቡና 1.50 ዶላር ነበር፡፡ ከዚያ በፊት 2.20 እና 2.50

ዶላር ነበር፡፡ ከፍተኛው 3.50 ዶላር ነበር። ቡና እጅግ ለመውደቁ በ3.50 እና በ1.05 መካከል ያለውን ልዩነት ማየት

ይበቃል፡፡ አምና በጣም ሞተ እያልን 1.50 ነበር፤ ዘንድሮ 1.05 ዶላር።
በውጭ የቡና ዋጋ በጣም ቀንሶ እዚህ የቡና ለቃሚዎች ዋጋ ጨምሯል፡፡ በፊት ለአንድ ኪሎ ቡና ለቀማ 0.50ሳ. ነበር

የምንከፍለው፡፡ አሁን በኪሎ እስከ 2 ብር እንከፍላለን፡፡ አንድ ኪሎ ንፁህ ቡና ለማግኘት 6 ኪሎ እሸት ቡና መለቀም

አለበት። የሠራተኛ ጉልበት፣ 3ብር፣ 5ብር፣ 10፣15፣ … እያለ አሁን በቀን 70 እና 80 ብር ደርሷል፡፡ የዓለም የቡና ዋጋ

ግን እጅግ አሽቆልቁሏል፡፡ በቡና ንግድ የተሰማሩ ሁሉ ኪሳራ ላይ ናቸው፡፡ አምና፣ ዘንድሮ ይሻለዋል ብለን በተስፋ

ጠብቀን ነበር፤ ከአምናው የበለጠ ሞተ፡፡
 አሁንም በሚመጣው ዓመት የተሻለ ይሆናል ብለን በተስፋ መጠበቅ ነው፡፡ ሊሻልም ሊብስም ይችላል፡፡ የቡና ገበሬ

ሕይወት ይኼ ነው - በተስፋ መኖር፡፡
የወደፊት ዕቅዳችሁ ምንድነው?
የማር ፋብሪካ አቋቁመን ማር አሽገን ለመላክ ከሁለት ኩባንያዎች ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ (ሮስትድ ኮፊ) ለማቅረብ፣

ጥናቱን ጨርሰናል፤ ይህ ሥራ ከባድ ነው፡፡ እንዲሁ ዘለህ የምትገባበት አይደለም-አደጋ አለው፡፡ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር

እየተነጋገርን ነው፡፡ ስለዚህ በሚቀጥለው ዓመት ይሳካል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡
ከአገር ውስጥ ባንኮች እስካሁን ምንም አልወሰዳችሁም?
አይ! አሁን ለቡና ለቀማ ከአዋሽ ኢንተርናሽናልና ከዳሽን ባንክ ጋር እየሠራን ነው፡፡ ከእነዚህ በስተቀር ከሌሎች ባንኮች

ጋር አልሠራንም፡፡ እስካሁን በራሳችን ገንዘብ ነው ስንሠራ የነበረው፡፡
አቶ ታደለ አብረሃ ባለ ትዳርና የአራት ልጆች አባት ሲሆኑ፣ ልጆቹ እየተማሩ ናቸው፡፡ የትልቁ ልጅ ዕድሜ 14 ዓመት

ሲሆን ትንሿ ሴት ልጅ ደግሞ ስምንት ዓመቷ ነው፡፡

Read 3647 times