Saturday, 30 November 2013 10:52

ስራ ፈጣሪ የብልጽግና ጀግኖችን ብናከብር፣ ለስደት ባልተዳረግን!

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(5 votes)

ጀግኖችን ብናከብር፣ ለስደት ባልተዳረግን!
መንግስትንና እርዳታን ማምለካችን ይቁም

በሳዑዲ አረቢያ የተሰቃዩ ስደተኞች፣ እንደ እንስሳ እየታደኑና እየታጐሩ ሲባረሩ፣ ብዙዎቻችን በንዴት እርር ብለናል፣

በቁጭት ተንጨርጭረናል፡፡ ነገር ግን የንዴታችንና የቁጭታችን ያህል፤ በሰከነ አእምሮ የሚያዛልቅ ነገር ለማሰብ

የምንፈልግ አይመስልም፡፡ እንደ አያያዛችን ከሆነማ፤ የዛሬው አሳዛኝ ትዕይንት፣ (አዲስ ካለመሆኑም በተጨማሪ) ነገ ከነገ

ወዲያም መደገሙ አይቀርም፡፡
ካሁን በፊትምኮ በሶማሊያና በየመን በኩል ወደ ሳዑዲ አረቢያ የተሰደዱ  ብዙ ሺ ወጣቶች በተደጋጋሚ ከሪያድ እና

ከጂዳ እየታፈሱ ተባረዋል። ይሄውና ዛሬም እየተባረሩ ነው፡፡ እንዲህም ሆኖ፣ ሳዑዲ ለመግባት በየመን በኩል የሚደረገው

የስደት ጉዞ አልተቋረጠም፡፡ ምን አለፋችሁ! አንዳችም አዲስ ነገር አልተፈጠረም፡፡ አንዲት መላ ካልተዘየደ፣ አዙሪቱ

አይቆምም፡፡ ሰሞኑን ያየነው የሰዶ ማሳደድ ግርግር ሲረግብ፣ ቁጭታችንና ንዴታችን ሲበርድ፤ ወደ ድሮው እንመለሳለን፡፡
በእርግጥ፣ በደላሎችና በኤጀንሲዎች ላይ የጀመርነውን ከንቱ የውግዘት ዘመቻ ለማቆም ፍቃደኞች አንሆንም፡፡ የኩነኔ

መዓት እናወርድባቸዋለን፡፡ በስደት ላይ የሚደርሱ መከራዎችንና ስቃዮችን እየዘረዘርን እለት በእለት መለፈፋችንንም

እንቀጥልበታለን፡፡ የመንቀሳቀስ መብትን የሚጥሱ የጉዞ እገዳዎችንም በሰበብ አስባቡ ማራዘም እንችላለን፡፡ “እኔ

አውቅልሃለሁ” በሚል ስሜት አዛዥ ናዛዥ የመሆን አባዜያችንን በቀላሉ አንለቀውም፡፡ አዛኝ ተቆርቋሪ መምሰልም

እንችልበታለን፡፡
ከስደት ተባርረው ለሚመለሱ ወገኖች፣ የትራንስፖርት ወጪ መሸፈንና ህክምና መስጠት፣ የእለት ረሃብ ማስታገሻ ምግብ

ማቅረብና የእርዳታ ማሰባሰቢያ የባንክ ሂሳብ መክፈት የመሳሰሉ ልግስናዎችንም በሆይ ሆይታ ለተወሰነ ጊዜ ማቆየት

አያቅተንም፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው?
ይሄ ሁሉ ቅንጣት መፍትሔ አይሆንም፡፡ ለምን በሉ፡፡ እስካሁን መች መፍትሔ ሲያመጣ አየን? አላመጣም፡፡

“ብንተባበርና ብንረዳዳ ይሄ ሁሉ ስቃይ አይፈጠርም ነበር” የሚሉ ሰዎች መኖራቸውን አጥቼው አይደለም፡፡ “በአገር

ውስጥ ሰርቶ መኖር ይቻላል” የሚለውን መፈክር ሳልሰማ የቀረሁም አይምሰላችሁ፡፡ ነገር ግን ሰሞኑን የተሰራጨ ሌላ

ዜናም ሰምቻለሁ፡፡ እናቱን የገደለ አንድ የገጠር ወጣት በፍርድ ቤት የእስር ቅጣት እንደተወሰነበት የሚገልጽ ዜና ነው፡፡

ወጣቱ እናቱን የገደላቸው የእርሻ መሬት አላወረሰችንም በሚል ምክንያት እንደሆነ በዜናው ተጠቅሷል፡፡ ደግነቱ

አብዛኛው ወጣት የዚህን ያህል ክፉ ጭካኔ የተጠናወተው አይደለም፡፡ ታዲያ፣ ጭቃኔ ያልተጠናወተው፣ ሳይቸገር ቀርቶ

አይደለም፡፡
አብዛኛው የገጠር ቤተሰብ የሚተዳደርበት የእርሻ ቦታ፣ ከግማሽ ሄክታር ያነሰ ነው፡፡ የየቤተሰቡ የእርሻ ማሳ የእግር ኳስ

ሜዳ እንኳ አታክልም ማለት ነው፡፡  ይህችው ማሳ ለአምስት ልጆች ስትከፋፈል ይታያችሁ፡፡ ከእርሻ በስተቀር ሌላ

ምንም የመተዳደሪያ ስራ የሌላቸው ወደ ሚሊዮን የሚጠጉ መሬት አልባ ወጣቶች በየአመቱ እንደሚፈጠሩ አስቡት፡፡
ብዙዎቹ የገጠር ወጣቶች መሄጃ መድረሻ የላቸውም፡፡ መሬትን ጠፍጥፈው መስራት አይችሉም፡፡ ከተማ ሄደው

እንዳይሰሩ፤ የሚያወላዳ የስራ እድል አያገኙም፡፡ በየከተማው በስራ አጥነት የሚሰቃይ ወጣት ሞልቷል  - ለዚያውም

የተማረ ወጣት፡፡ ለነገሩ ተሻምተው ስራ ቢያገኙ እንኳ፣ በዛሬ ደሞዝ እህል በልቶ ማደር አይታሰብም፡፡ የዛሬ ብር ምን

እርባና አለውና! ባለፉት 6 አመታት በመንግስት ቅጥ የለሽ የገንዘብ ህትመት ሳቢያ  የዋጋ ንረት ሲግለበለብ፣ የአገራችን

ብር ክብር አጥቶ  ረክሷል። ከ6 አመት በፊት አራት ኩንታል ጤፍ ለመግዛት የሚያስችል ሁለት ሺ ብር፣ ዛሬ የአንድ

ኩንታል ዋጋ ሆኗል፡፡
ታዲያ መሬት ያጣ የገጠር ወጣትና፣ በልቶ ለማደር የሚበቃ ደሞዝ የሩቅ ህልም የሆነበት የከተማ ተመራቂ ምን

ይዋጠው?
በየወሩ 15ሺ ያህል ወጣቶች በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እየተመዘገቡ፣ 10ሺ ያህል ደግሞ በየአቅጣጫው

ድንበር እየጣሱ ሲሰደዱ የቆዩት፣ ወደው አይደለም፡፡ መሄጃ መድረሻ ጠፍቷቸው፣ አማራጭ መላ አጥተው ነው ብዙዎቹ

ወጣቶች የሚሰደዱት፡፡ እንደ ድሮው ልምድ፣ ድህነትን ታቅፈው በተስፋ ቢስነት ተኮራምተው መቀመጥን ትተዋል፡፡
ታዲያ፣ ደላሎችንና ኤጀንሲዎችን ስናወግዝ ብንከርም፣ ለእነዚህ ችግረኛ ወጣቶች መፍትሔ ይሆናቸዋል? “ስደት

በአመለካከት መጓደል ሳቢያ የሚከሰት ነው” እያልን ስለ አገር ልማት ስንደሰኩል ብንውል፤ የኛ መፈክር ለገጠሩ ወጣት

የእርሻ ማሳ አይሆንለትም፡፡ ወይም ለከተማው ወጣት መተዳደሪያ ደሞዝ አያስገኝለትም፡፡ “እንተባበር፣ እንረዳዳ” ብለን

የዛሬን ምሳ ብናበላቸው፣ ለጊዜው መልካም የልግስና ተግባር ቢሆንም፤ የኛ አዘኔታና ልግስና የነገን ረሃብ

አያስታግስላቸውም፤ ለከርሞ የኑሮ ጣጣቸውን አይሸፍንላቸውም፡፡
“መንግስትስ?” ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። በእርግጥም፣ የመንግስት አፍ አያርፍም፡፡ “የኑሮ ማቋቋሚያ እሰጣለሁ”፤

“የስራ ዕድል እፈጥራለሁ” እያለ ያላወራበት ጊዜ የለም፡፡
ተስፋችንን በመንግስት ላይ ጥለን ስንት አመታት ተቆጠሩ? እውነትም፣ መንግስት “ለስራ ፈጠራ” እና “ለማቋቋሚያ” ብዙ

ገንዘብ ማፍሰሱ አልቀረም። ለዚህም በተለይ በከተሞች አካባቢ ግማሽ ያህሉን የዜጐች ገቢ በመንግስት ይወሰዳል፡፡ ነገር

ግን፣ ጠብ ያለ ነገር የለም፡፡ “አነስተኛና ጥቃቅን አምራቾችን አበራክታለሁ” እያለ ለበርካታ አመታት “ስትራቴጂና

ፓኬጅ” ከመደርደር ባያርፍም፣ ከድሮው የተለየ ስንዝር ያህል የመሻሻል ምልክት አለመታየቱ መንግስት ራሱ አምኗል፡፡

ደግሞስ መንግስት ራሱ የፈጠረውን የዋጋ ንረት በቢዝነስ ሰዎች ላይ እያላከከ፣ በአጭበርባሪትና በስግብግብት

ሲወነጅላቸው እየታየ፣ ለስራ ፈጠራ የሚነሳሱ ወጣቶች እንዲበራከቱ መጠበቁ አይገርምም?
ምን ለማለት ፈልጌ ነው? የመሬት አልባና የስራ አጥ ወጣቶችን ዋነኛ ችግር ምን እንደሆነ እንገንዘብ። ያኔ፤ ደላሎችንና

ኤጀንሲዎችን በመኮነን፣ ወይም የስደት አስከፊነትን በመስከበክ መፍትሔ እንደማናገኝ እንረዳለን እያልኩ ነው፡፡ እንደ

ወትሮው መንግስትን እያመለክን ተስፋችንን ብንጥልበት፤ ወይም እንደለመድነው ከሁሉም በላይ የእለት ምጽዋትንና

እርዳታን ብናሞግስ ቅንጣት ታክል ለውጥ አናመጣም፡፡ ከጥንት እስከዛሬ ሽራፊ ለውጥ ያላመጡልንን ነገሮች የሙጢኝ

ይዘን የምንቀጥል ከሆነም፤ የእስከዛሬው የኑሮ ችግር፣ ስደትና ስቃይ ወደፊትም መደገማቸው አይቀርም፡፡
እንዲህ ስባል ግን፣ ለውጥ ማምጣትና መሻሻል አይቻልም ማለቴ አይደለም፡፡ እስከዛሬ የዘነጋነውን፣ የሳትነውንና ችላ

ያልነውን ነገር አናጢን፡፡ ሌሎች አገሮች ከችጋር ተላቅቀለው የበለፀጉበትንም መንገድ እንመልከት፡፡ ከአሜሪካ እስከ

ጃፓን፣ ከእንግሊዝ እስከ ደቡብ ኮሪያ… ገና ወደ ብልጽግና እየተራመደች የምትገኘው ቻይና ሳትቀር፣ የስኬታቸው ዋና

ምንጭ ተመሳሳይ ነው - የስራ ፈጠራ ቢዝነስ!
የአገራችን ሰው ደግሞ በተቃራኒው ቢዝነስን ከቁም ነገር አይቆጥረውም፤ እንዲያውም በጠላትነት እስከማየት ይደርሳል፡፡

መንግስትንና ራሽንን፣ እርዳታንና ምጽዋትን ነው የሚያመልከው፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ በርካታ የአፍሪካ አገራት፣ ምስራቅ ጀርመንና ሰሜን ኮሪያ፣ እነ ራሺያና ቬትናም፣…በአጠቃላይ

ተስፋቸውን በመንግስት ላይ የጣሉ የቀድሞ ሶሻሊስት አገራት ሁሉ፣ በኢኮኖሚ የቱን ያህል ተንኮታኩተው እንደነበር

አታስታውሱም? ከሃያ አመታት ወዲህ በተሰወነ ደረጃ የስራ ፈጠራ ቢዝነስ ሲፈቀድ ነው ብዙዎቹ ያንሰራሩት፡፡

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ያለቁባት ቻይና እንኳ፣ ለግል ኢንቨስትመንትና ለቢዝነስ በሯን ስትከፍት ነው ወደ

ብልጽግና ግስጋሴ የተሸጋገረችው፡፡
ጉዳዩ ያን ያህልም ውስብስብ አይደለም። የመንግስት እጅ ውስጥ የገባ ገንዘብ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ሲመደብ፣ በሙስና፣

በዝርክርክነትና በተንዛዛ ቢሮክራሲ ይባክናል፡፡ እንዲያ በከንቱ ሃብታቸውን የሚያባክኑ የቢዝነስ ሰዎች ብዙ አይደሉም፡፡
ለነገሩ እዚሁ አገራችን ውስጥ በአንድ በኩል፣ እንደ ጣና በለስ በግል ኩባንያዎች አማካኝነት የተገነቡ የኤሌክትሪክ

ማመንጫ ግድቦችን፣ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ተንዳሆ፣ ከሰም እና ርብ የመሳሰሉ በመንግስት ድርጅቶች አማካኝነት

የተጀመሩና ለበርካታ አመታት የተጓተቱ የግድብ ግንባታዎችን ማነፃፀር ይቻላል፡፡ በመንግስት ድርጅቶች የተያዙ

ግድቦች፣ ግንባታቸው እየተጓተተ የመጠናቀቂያ ጊዜያቸው ከ6 አመት በላይ ተራዝሟል፡፡ እውነታውን የዚህን ያህል

ያፈጠጠ ቢሆንም፣ እንደወትሮው ተስፋችንን ሁሉ በስራ ፈጠራ ቢዝነስ ላይ ሳይሆን በመንግስት ፕሮጀክቶች ላይ

መጣላችንን አላቆምንም፡፡
ይህ ብቻ አይደለም ችግሩ፡፡ ከግል ኢንቨስትመንትና ከትርፋማ ቢዝነስ ይልቅ፣ ለምጽዋት ተግባራትና ለእርዳታ ጥሪዎች

የላቀ ክብር እንሰጣለን፡፡ በእርግጥ፣ አመልማል አባተ እንዳደረገችው፣ 5ሺ ለሚሆኑ የስደት ተመላሾች ምሳ ማቅረብ

ትልቅ የልግስና ተግባር ነው፡፡ ሊመሰገንም ይገባዋል፡፡ ለ5ሺ ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥር ቢዝነስ ግን፣ ሺ ጊዜ እጥፍ

ድርብ ምስጋናና አድናቆት ይገባዋል፡፡ የአንድ ቀን የምሳ ግብዣ ማግኘት የእለቱን ረሃብ ያስታግሳል፡፡ የስራ እድል

ማግኘት ግን፣ ለዘለቄታው ከተመጽዋችነት ያላቅቃል፡፡ ብዙ ሺ ሰዎች ራሳቸውን ችለው ሰው የመሆን ክብር የሚቀዳጁት፣

የቢዝነስ ሰዎች በሚፈጥሩት የስራ እድል ነው፡፡ የዛሬ ረሃባቸውን ማስታገስ ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ ሺ ሰዎች የብዙ ሺ ቀናት

ኑሯቸውን የሚያደላድሉበት ትልቅ ፀጋ ነው - የስራ ፈጠራ ቢዝነስ፡፡
እናም ተስፋችንን በመንግስት ላይ መጣላችንን ትተን፣ ለምፅዋትና ለእርዳታ የላቀ ክብር መስጠታችንን አርመን፤ ለስራ

ፈጠራ ቢዝነስ ቅድሚያ በመስጠት፣ የቅዱስነቱ ያህል ታላቅ ክብር እንደሚገባው ስንገነዘብ ነው እንደሌሎች አገራት

መበልፀግ የምንችለው፤ ያኔም ነው ከስደት ስቃይ የምንገላገለው፡፡   

Read 4428 times