Monday, 25 November 2013 11:30

አባ ወራው…!

Written by  ዋሲሁን በላይ (አዋበ)
Rate this item
(2 votes)

…ጨረቃዋ አጠገቧ ያሉትን ከዋክብቶች…እንደጠጠር ልቅም አድርጋ ቅልልቦሽ የምትጫወት የገጠር ልጃገረድ ትመስላለች፡፡ ሳቋ አይፎርሽም፡፡ መልኳ ግን ያልታጠበ የድሃ ትሪ አይነት ነገር ነው፡፡ (ልጅ ሆነን ማርያም ልጇን አቅፋ ትታያለች የምንላት አይነት አይደለችም)
አቶ ባይጨክን…ከባለቤታቸው ከወ/ሮ ይጋርዱሽ ጋር በረንዳ ላይ ተቀምጠው የጋለ ወግ እየጠረቁ ነው፤  ቀድሞ የነበረው ንዴታቸው በመጠኑም ቢሆን በረድ ያለ ይመስላል…አንጋጠው ጨረቃዋን በትዝብት እየገረመሙ ወሬአቸው ለባለቤታቸው ይሁን ለጨረቃዋ ሳይለይ ያወራሉ… “እቺ ሐገር ሰው አጥታለች፤ እስቲ ይሁን…ተቆርቋሪ የሌላት ቤተክርስቲያን መሆኗም አይደል…ጉድ እኮ ነው ጽናጽሏን ሲወስዱ፣ ከበሮዋ ለዳንኪራ ሲደለቅ፣ በገናዋ ለአለም ሙዚቃ አስረሽ ምችው ማጀቢያ ሲሆን…መቋሚያዋ እንደ ጥምቀት ሽመል ሲቆጠር…ተው የብቻችን የሆነውን አትንኩ! የሚል ጠፋ፤ አሁን ደግሞ ጭርሱኑ ጠቅለው የራሳቸው ሊያደርጓት አሠፈሠፉ”
ወ/ሮ ይጋርዱሽ ሙሉቀን ይዘውት የነበረውን ሰፌድ ከነስንዴው ከአጠገባቸው ለማንሳት እየቃጡ ነበር…የባለቤታቸው መብሰክሰክ የጤና አልመስል ቢላቸው፣ ሰፌዱ ላይ ያለውን አንስቶ ከማስገባት ባለቤታቸውን ይዞ መግባት አንገብግቧቸዋል፡፡ እህል አይደሉ እፍስ አርገው አያስገቧቸው … ጨንቋቸው አብረው አንጋጠጡ፡፡ “ባያስቆጡን፣ ባያስኮርፉን ምናል?!” እያሉ መቆጨታቸው አሁን እሳቸውንም ሳያውቁት እየቆጠቆጣቸው ነው፡፡
“እንደው የቲቶ አባት … ሙሉቀን እንዲህ በንዴት መቃጠል ምን ሊረባዎ ነው? አንዳንዴ መልስ የሌለው ጥያቄ እያመጡ ግራ ገብትዎት እኔንስ ግራ ባያጋቡኝ ምናለበት...”
“አንቺ ምንሽ ተነካ! ከእነ ልጆችሽ ተረት ተረት ወይም ኩምክና የማወራ እየመሰላችሁ፣ ሳቃችሁ ጣሪያ ነክቷል…! እንዴት ሰው አንድ ተቆርቋሪ ያጣል!?”
“አይ…እርስዎ ደግሞ ከእኛ ከፍ ያሉት መመለስና “ሐይ” ባይ ያጡለትን እርስዎ ብቻዎትን ሊወጡት ነው…ደግሞስ ራሱ ባለቤቱ አንድዬ ዝም ያለውን እኛ ምን ቤት ነን”
“እምትተኚ ከሆነ ገብተሽ ተኚ…ቆመሽም አላማረብሽ”
“እርስዎስ?” ወ/ሮ ይጋርዱሽ የተለየ ስሜት ተሰማቸው፡፡
“ከጨረቃዋ ጋር እማወራው አለኝ…ቢያንስ ሐሳቤን ባትደግፍ አትነቅፈኝም”
አገጫቸውን አስደግፈው በተከዙበት ምርኩዝ መሬቱን በቁጭት ደቀደቁ!
ከአሮጌው ጣውላ የሚወጣው ድምጽ፣ የአቶ ባይጨክንን መትከንከን ይበልጥ ቅላፄና ውበት ሰጠው፡፡
“አይ እንግዲህ ይገቡ እንደሁ ይግቡ…ምነው እቴ!”
ወ/ሮ ይጋርዱሽ የባላቸውን ፀባይ ያውቃሉ…የውሸት ቆጣ ሲሉባቸው ሁሉንም ነገር ተወት አድርገው ወደነበሩበት እንደሚመለሱ፡፡ ዛሬ ግን መረር ያለ ሆነባቸው፡፡
“ነገርኩሽ እኮ ሰሚ ሰው ከሌለ፣ ከፈጣሪ የእጁ ስራ ጋር ባወራ ምናለበት?”
“ምን ቸገረኝ ብርዱ ሲቆነድድዎ ይገቡ የለ…ኋላ እዚህ ጋ ወጋኝ፣ እዚህ ጋ ቆረጠመኝ፣ እሺኝ ቢሉ…ድቆሳ እንደሚጠብቅዎ አይዘንጉ…” አፋቸው በተናገረው ውሸት ሆዳቸው እያዘነ፣ ትተዋቸው በሠፌዱ ላይ ያለውን እህል የተለቀመውን ካልተለቀመው ደባልቀው ገቡ፡፡ አቶ ባይጨክን ሽቅብ አንጋጠው ቀሩ፡፡
ወ/ሮ ይጋርዱሽ በባለቤታቸው መጨከን ስላልቻሉ ጋቢ ይዘው ወጡ…“ጦሱ ለእኔው ነው የሚተርፈው…” ጋቢውን ነጠል አድርገው ከትከሻቸው ላይ ደረቡላቸው…እሳቸው የለበሱትን ነጠላ ጋቢ ደግሞ ለሁለት አጥፈው ጉልበታቸው ላይ ጣል አደረጉላቸው፡፡
“ነፍሴን እምነት እየበረዳት ሥጋዬን ሸማ ብታለብሽው እንደምን ሊሞቀኝ?”
አሁንም በአይናቸው ስለት ሠማዩን እንደወጉ ናቸው፡፡
“አይ እንግዲህ ምነው አይፈላሰሙብኝ…ጃጁ ልበል እርስዎ ሰውዬ?”
የተላጠ ትሪ የመሰለችዋ ጨረቃ እየደመቀች እየደመቀች…ኮከቦቹ በድምቀቷ ተሸማቀው ከአጠገቧ እየራቁ እየራቁ ለመጥፋት ተቃርበዋል፡፡
“ግቢ እስቲ ይበርድሻል?”
“ለእኔ ማሰቡን ትተው ለራስዎ በተጨነቁ”
“ተይኝ አልኩሽ እኮ!” አሁንም ጨረቃዋን ሠርስረው አፈጠጡባት…ድንገት የውጪው በር “ቃ” ብሎ ሲከፈት የሁለቱም ዓይኖች እኩል ዞሩ…ቲቶ ነበር … እናትና አባቱ በረንዳ ላይ ሆነው ሲያያቸው ፍቅር እደሳ መስሎ ተሰማው መሠለኝ ገና ከበር ጥርሱን ፈልቅቆ ቀረባቸው፤ “እንዴት አመሻችሁ ጐረምሶቹ?” ወ/ሮ ይጋርዱሽ ሳቃቸው ቀደማቸው፡፡
“እንዴት አመሹ ሽማግሌው?” ለቀልዱ ቀልድ ወረወሩለት፡፡
“የምን ትዝታ እየቆሰቆሳችሁ ነው?”
“አባትህ የድሮው ትዝ አላቸው መሰለኝ አልገባም ብለውኝ እርሳቸውን እያባበልኩ ነው”
“አውርጄ ካልሠጠሁሽ እያለ እንዳይሆን ጨረቃዋን? አባዬ እንደምን አመሸህ?”
ምርኩዛቸውን ባገጫቸው ተደግፈው በራሳቸው ሃሳብ ተመስጠዋል…
“አባዬ እንደምን አመሸህ? ስላመሸሁ ይቅርታ?” ሰምተው እንዳልሰሙ መልስ ነፈጉት፡፡
“ተዋቸው እስቲ…እርጅና የተጫጫነው አዕምሮ ቶሎ አይነቃም!”
“የጥቅምት ብርድ እንኳን የእናንተን የወጣቶቹን ገላ አይደለም እኛ ሥንት ያየነውንም ያንሰፈስፋል…በሉ ግቡ…” ቲቶ ሳቁ አምልጦት የእናቱን ትከሻ ተደግፎ ተንፈቀፈቀ …
“ከዚህ አይዘልም የእናንተ ቧልት! እየሳቃችሁ የእጃችሁን ታስነጥቃላችሁ”
“እስቲ እሺ ካሉህ … ይዘሃቸው ግባ” አባትና ልጅን ትተው ወደ ውስጥ ገቡ፡፡
ቲቶ የአባቱን መተከዝ ተመልክቶ በግድ አስነስቶ ይዟቸው ገባ፡፡
ጨረቃዋ…የተላላጠ ፊቷን እያወዛች…ያለስንቅ እንደሚጓዝ መንገደኛ ቀስ እያለች ጉዞዋን ቀጠለች…
*   *   *
በጅማ ረከቦት የታዘለው ስኒ ንጣቱ የወተት ጥርስ የመሰለ ነው፡፡ ወ/ሮ ይጋርዱሽ ተርከክ ያለው እሳት ላይ ተጥዶ የሚንደቀደቀደውን ቡና እንዳመል እንዳመሉ ቀንሰው፣ በያዙት ቡና መንደቅደቁን እያባረዱ … በደንብ ካንተከተኩት በኋላ አወረዱት፡፡ አቶ ባይጨክን ከቤተ እግዚአብሔር እንደተመለሱ ወዲያው ነበር ቁርሶ የቀረበላቸው፣ እንደነገሩ ቀመስመስ አድርገው የሚወዱትን ቡና እየተጠባበቁ ነው፡፡ የማታው ስሜታቸው አሁንም በልብና በፊታቸው ላይ ደልደል ብሎ እንደተቀመጠ ያስታውቃል፡፡
ቲቶና ሁለቱ እህቶቹ ከመኝታ ቤት እየተሳሳቁ ሳሎን ከወላጆቻው ጋር ተቀላቀሉ …አባታቸው የበፊት ሳቂታ ፊትና ተጫዋችነታቸውን ባደራ በሊታ እንደተነጠቁ ዝም ብለዋል፡፡ ልጆቹ የተለየውን ዝምታ ተመልክተው የሆነ ነገር እንደተፈጠረ ከማታው መነሻ አሁን ደመደሙ፡፡ ሁለቱ ሴቶች ተቻኩለው አባታቸው አጠገብ ተቀመጡ፡፡
ቲቶ ነገሩን በግርምት ቃኝቶ ያለወትሮው እንዲህ ውርጭ የመታውን የቤቱን ሰላም ለመመለስ ከእናቱ አጠገብ ተቀመጠ፡፡ “እስቲ ራቅ በል አመድ ይቦንብሃል”
“ተይው… አመዳም ፊት ላይ አመድ ቢነሰነስ ብርቅ ነው እንዴ?”
“አመዳም መሆንህን ማወቁ በራሱ ትልቅነት ነው…” አባቷ አጠገብ የተቀመጠችው ታናሹ ፈትለወርቅ ነበረች፡፡ “አንቺ የግድግዳ ጌጥ … አገልግል የመሰልሽ ልጅ ዝም አትይም?” በቀኝ በኩል ያለችው ስርጉተ ማርያም፤ የአባቷን እጅ እያሻሸች የሚሆነውን አይኗን ከብለለል እያደረገች ትመለከታለች፡፡
“እስቲ ቡናውን በፀጥታ እንጠጣበት…ይሄ መልክ የሌለው ቀልዳችሁን ቀነስ አድርጉት…” ወ/ሮ ይጋርዱሽ ቡናው እንዲሰክን የጀበናውን አፍንጫ ዘቅዘቅ አድርገው አስተካከሉት፡፡
“እማዬ ደግሞ ቤቱ ሰው የሌለበት እንዲመስል ፈለግሽ?” ፈትለወርቅ ቁንጥንጥ እያለች አባቷ ላይ ተጣበቀች፡፡
“እናንተ ልጆች፤ ከግራ ከቀኝ አጣበቃችሁኝ እኮ!” የአቶ ባይጨክን ድምጽ በኩርፊያና ቁጣ እንደታፈነ ያስታውቃል፡፡
“አባዬ ምን ሆነህ ነው?” ፈትለወርቅ እጃቸውን እየዳበሰች ይሁን እያፍተለተለች ባለየ መልኩ ጠየቀቻቸው፡፡
ስርጉተማርያም የአባቷ ደጋፊ መሆኗ የታወቀ ነው፡፡ “እስቲ ተይው ዝም ካለ ዝም ነው!”
ቲቶ በአይኑ ተቆጣት፣ ስርጉተማርያም “አልገባኝም” አይነት አፍጣ በአይኗ ጥያቄ ወረወረችለት፣ ቲቶ ለፈትለወርቅ “አዋሪው” አይነት በምልክት ነገራት፡፡
“አባ…ማታም ተቆጥተህ ግቡ አልከን…አሁን እሺ ስሞትልህ ምን ሆነህ ነው? ሳናስበው አስቀየምንህ እንዴ?”
አቶ ባይጨክን ሁሉንም ከገረመሙ በኋላ፤
“አሲዳም ዘመን! አሲዳም ዘመን ላይ ትጥለኝ አምላኬ!” ቀና ብለው ጣሪያው ሥር ያለ ይመስል ፈጣሪን ተመለከቱት፡፡
“ዘመኑ ደግሞ ምን በደለ…?” ወ/ሮ ይጋርዱሽ ለጨዋታው ብለው ነበር፡፡
“ኤዲያ! ዘመኑ ነው እንጂ እንቅልፋም፣ ትውልድ ተሸክሞ እሹሩሩ የሚል…”
“ተሳስተሃል አባዬ…ትውልዱ ነው እንቅልፋም ዘመን ለማንቃት እየጣረ ያለው…”
ቲቶ ማውራታቸው በመጠኑም ቢሆን ደስ ብሎታል፡፡
“ያው ነው ቀልቀሎ ሥልቻ ስልቻ ቀልቀሎ!” ሳያስቡት ገንፈል ገንፈል አሉ፡፡
“ታዲያ ምን ያስቆጣዎታል? እርስዎ ሰውዬ ሲያበዙት ደግሞ አይታወቅዎትም…እርስዎ የፈለጉትን ሰው ካልተከተለ ትክክል የሆነ አይመስልዎትም ልበል…”
“አንቺ ሴት…በቤታችን ህገመንግስት መሠረት ባንቺ የእምነት ነፃነት (አስተሳሰብ) ጣልቃ አልገባም፡፡ በእኔም የእምነት ነፃነት ማንም ጣልቃ መግባት የለበትም”
የለበሱት ጋቢ ተንሸራቶ ሊከዳቸው ሲል፣ አጣፍተው ከትከሻቸው አደረጉት፡፡
“ድሮውንስ በእኔ መብት ሊገቡ ያምርዎት ነበር? ወቸው ጉድ … ይጋርዱሽ እያደርሽ እማትሠሚው ጉድ የለ” ቤቱ አዝሎት የነበረውን ቀዝቃዛ ውርጭ በሳቃቸው ድራሹን ለማጥፋት ይመስላል…እሚያስቅ ሳቅ ሳቁ፡፡
“እስቲ እንካ ቲቶ … የቡና ቁርስ አሲዝልኝ” ቲቶ የዘረጉለትን በቀለም ያጌጠ እርቦ ተቀብሎ፣ መጀመሪያ ለአባቱ ዘረጋ “በቃኝ!” አሉት በእጃቸው፡፡ ሁለቱም እህቶቹ እኩል በእናት እጅ የተገመደለውን አምባሻ አነሱ፡፡
ፈትለወርቅ ከያዘችው ላይ ቆርሳ ለአባቷ በግድ አጐረሰቻቸው “አባባ የታወቀ ነው … በማንም የእምነት መብት ጣልቃ ገብቶ አያውቅም!”
“ድሮውንስ ሊገቡ ያምራቸው ነበር” ከቲቶ ጋር ስምም የሆኑ ያህል በአይን ተግባቡ፡፡ ልጆቹ የአባታቸውን፣ እሳቸው ደግሞ የባላቸውን ከድብርት መውጣት ፈልገዋል፡፡
“ማን ወንድ የሆነ ነው መብቴን የሚገፍ!” ወ/ሮ ይጋርዱሽ ድጋሚ የቀልድ ትኩስነታቸውን አወጁ… “አልገባም እያልኩሽ አትሰሚም” ቀዝቀዘዋል፡፡
“ማሰብዎ በራሱ ጽንፈኝነት እያውጠነጠኑ እንደሆነ ያሳብቅዎታል”
“እየው እንግዲህ … ነገሩን ሁላ ፖለቲካ ስታደርገው…”
“ሞኝ ንዎ ልበል …እያንዳንዷ ፖለቲካ መጠንሰሻዋ መኖሪያ ቤት እኮ ነው … ከቤት የተጠነሰሰ ፖለቲካ እኮ ነው ሀገሬው የሚጠጣው፡፡”
ልጆቹ፤ የእናትና የአባታቸውን የቃላት ልውውጥ የጠረጴዛ ቴኒስ እንደሚመለከት ሰው፣ አይናቸውን ከወዲያ ወዲህ እያንከባለሉ በጥምር ያያሉ፡፡ ሁሌም የእናትና የአባታቸው ጨዋታ ትምህርት ቤታቸው ነው፤ መከባበርን፣ መፋቀርን፣ ይማሩበታል…
“ነግሬሻለሁ … በቤታችን የእምነት ህግ መሠረት፣ የፈቀድሽውን እና የወደድሽውን ማመን መብትሽ ነው፤ እኔ ባልሽ የልጆችሽ አባት እንጂ ባላንጣሽ አይደለሁም … ስለዚህ “ጣልቃ ገብነት” የሚባለው ክፉ ደንቃራ ህሊናችን ውስጥ መታሰብ የለበትም…በልዩነት ተስማምቶ መኖር ይቻላል፡፡”
“ደንቡን መጣስ ከአክራሪነት ያስመድባል…” አሁንም ከት ብለው ሳቁ፡፡
“ምን ካለበት የተጋባበት”… እያሉ ተፍነከነኩ፡፡ ኩልል አድርገው የቀዱትን ቡና ነጭ ጥርስ በመሰለው ስኒያቸው ቀድተው ቲቶን አስነሱት፡፡
ሁሉም አቦል ቡናውን ሳይሆን ወሬውን የሚጠጣ ይመስል በችኮላ ጨልጠው ስኒዎቹን መለሱ፡፡ ወ/ሮ ይጋርዱሽ ስኒዎቹን አጠገባቸው ካለው የኮኮስ ጣሳ እየነከሩ ካለቀለቀቁ በኋላ ረከቦቱ ላይ ደረደሩ፡፡ በመጠኑ ፀጥ ያለውን አየር ለመገርሰስ ይመስላል ስርጉተማርያም “እማማ ያለችው የበላይ አካሉን ደንብ አለማክበር … ከአክራሪነትም ያስመድባል ነው”
አቶ ባይጨክን ስርጉተማርያምን ገርመም አድርገው “ይሔው ነው እንግዲህ … ላልመጣ በሽታ መጀመሪያ ክትባት ብለው በሽታውን እንድንለማመድ ትንሹን በሽታ ይወጉናል፣ ያኔ ከውስጣችን ጋር ተስማምቶ ይኖራል፤ ህይወትም እንዲሁ ናት…ትንሿን ጥያቄ ስንፈራ ለትልቁ ወገቤን እንላለን፣ እንጂ የመጠየቅ መብቱ የለንም…በትንሹ ትልቁን ተለማምደነው…ጭቆና ተስማምቶን ‘አሜን’ ይሆናል ባህሪያችን፡፡ ያኔ የማንም መፈንጪያ እንሆናለን፡፡”
ፈትለወርቅ መልሳ የአባቷን እጅ ያዘች … በፍቅር ነው ያቀፈችው፡፡ አባቷ ያወሩት የሁላቸውም የውስጥ ጥያቄ ነው… “አባባ እውነቱን ነው …” አፏን ለእውነታቸው አላቀቀች፡፡ “ተያቸው ልጄ … አሁን አንገቴን ለሰይፍ … ደረቴን ለመድፍ የምሰጥለት ጉዳይ መጥቷል … ከዚህ በላይ መታገስ አይሆንልኝም!?” ወ/ሮ ይጋረዱሽ ሰረቅ አድርገው ተመለከቷቸው … “አቤት አቤት አልቀረብዎትም … በያዙት ጭራ ለዝንብ እማይጨክኑ ለምኑ ነው አንገትና ደረት የሚሰጡት?”
“ሙያ በልብ ነው! ወትሮም መሞት እንጂ መግደል አላማችን አይደለም!”
“እኮ እንዴት እንዴት?” የባለቤታቸው ምሬት እሚጋባ መሰላቸው፡፡
“የንቦቹን ቀፎ በጭስ አስክሮ ማሩን ለመውሰድ ቢቃጣም … ንቦቹ በጭስ አይበረግጉም!…እኛን የፈጣሪ ጭስ አፍኖ ካልገደለን በቀር…” ወ/ሮ ይጋርዱሽ ይሔን አባባላቸውን ማስጨረስ አልቻሉም፡፡
“እንደው እርስዎ ሰውዬ ምናባቴ ባረግዎ ነው የሚሻለው?” ልጆቹ በድራማው ተመስጠዋል… “ብለው ብለው የፓርቲውን ምልክት በሰበብ አስባቡ ማስተዋወቅ ጀመሩ ማለት ነው?”
“አይ ሞኞ!” አቶ ባይጨክን ሙሉ በሙሉ ወደ ባለቤታቸው ዞሩ፡፡
“ንብን ለእነሱ ብቻ በውርስ የሠጠው ማነው? ነገሩ ወዲህ ነው ባክሽ… ለትንሿ ዝምታችን ስንብሰከሰክ፣ ትልቁ ላይ ልባችን ፈሠሠ!”
“አይ ወዲያ የምን አማርኛ እያወሩ አለመግባባት ነው” ወ/ሮ ይጋርዱሽ ገብቷቸው እንዳልገባቸው የመሰሉት፣ ዝም ካሉ ባለቤታቸው ተመልሰው በቁዘማ ቆፈን ስለሚቀየዱ ነው፤፡፡“እውነትዎን ነው” ካሉ ጨዋታው ፈረሰ ዳቦው ተቆረሰ ይሆናል። ዝም አስባዩ ዝምታ ደግሞ በቤቱ ላይ እንደልቡ ይፈነጫል፡፡
“እውነት ስትጮህ እምነት ስትገፋ፣ ለሌሎች ቅዠት ይመስላል…”
“አባባ፤ ሃይማኖት እኮ ፈሪዎች የሚሸሸጉበት ተቋም ነው፤ በዚህ በዲሞክራሲ ጊዜ ሐይማኖት ጥያቄ ሆኖ መቅረብ የለበትም፡፡” አለ ቲቶ፡፡
“አበስኩ ገበርኩ! ምነው ሞቼ ባረፍኩት! መቸም ባየ በሰማ አይፈርድም እንጂ የሰማዩ አባቴ እንደው በመብረቅ ፍግም ቢያደርግልኝ ምን ነበር…”
ሁሉም ግማሽ ሳቅ ሳቁ…ስርጉተ ማርያም ነገሩን ለማሟሟቅ ይመስላል…
“ቲቶ እኮ እውነቱን ነው አባዬ…”
“ይሔን ብሎ ቲቶ … ቡቱቶ ነው! ሃያ ሶስት አመት ሙሉ እሹሩሩ ያልኩህ በቂ ነው … ከዚህ በኋላ ቤቴን ለቀቅ! ራስህን ቻል!” ወ/ሮ ይጋርዱሽ ሲስቁ … ሁለተኛውን ለመቅዳት ያነሱት ጀበናቸው ከእጃቸው አምልጧቸው ነበር፡፡
“አባዬ…”
“አትጥራኝ…” ቁጣቸው ፊታቸው ላይ ይነበባል፡፡
“አባ…ዘመኑ የመሰማማት እና የመስማማት ነው…”
“ድንቄም የመሰማማትና የመሥማማት!” አፈጠጡበት፡፡
“ቢሆንም እየውልህ … እቺ ሀገር የሚያምርባት ፀጥ ብላ ልማቷን አፋጥና … ካደጉት ሀገር ተርታ መመደብ ነው እንጂ በውስጧ የተሰገሰጉት በእምነት ጥላ ተጠልለው ሽብርተኝነትና አክራሪነትን እሚያቀነቅኑ ቀንዳቸውን ቢያሾሉም እኛ ከመስበር ወደኋላ አንልም!”
“ምን ማለት ነው ሽብር? … ምንስ ማለት ነው አክራሪነት? እኔ ገንዘቤን ሐይማኖቴን አጥብቄ ካልያዝኩ ምኑ ላይ ነው ሰውነቴ? ማጥበቄ ነው ማክረሬ?!” ቁጣቸው እሚበርድ አይመስልም፡፡
“በእምነት ሽፋን ሀገር ማፍረስን ምን አመጣው?” ወ/ሮ ይጋርዱሽ በወሬው ተመስጠው የቀዱት ቡና ቀዘቀዘ፡፡
“ይሁና…” ስርጉተማርያም አንገት ላይ የታሰረውን ማተብ እየዳበሱ… “ያለሙት የማይሆነው፣ ያሰቡት የማይሳካው … ዳኛ ስለሆንን ሳይሆን ፈጣሪ ስላልፈቀደ ነው፤ እባብን ረግጠው … አንበሳን አዘው … አምላካቸውን ቀን ከሌሊት በፀሎት የሚለምኑት የቅዱሳን ፀሎት ለጨካኞች አሳልፎ የሚሰጠን ይመስላችኋል? አትሞኙ! ‘ለአመፀኛ ህዝብ አመፀኛ መንግስት ያዝለታል’ ይላል፡፡ የሆነው … የሆነው እንዲሆን ሆኖ ነው፡፡”
“እየው አባዬ … ደግሞ ዙረህ ዙረህ ነገሩን በሙሉ ፖለቲካ ታደርገዋለህ… አሁን መንግስት እዚህ ነገር ውስጥ ምን አገባው?” ተለሳልሰው ሽርተቴ ገቡባቸው…” እኔ ምለው…የዚህ ቤት ሐይማኖት ምንድነው?” ሁሉም ፀጥ አሉ “መልሱልኝ እንጂ?!” አቶ ባይጨክን የምር ተቆጡ፡፡ ከተቀመጠበት ተነሱ፤ ፈትለወርቅ ቀና ብላ አየቻቸው፡፡ ስርጉተማርያም የሆነ ርህራሄ ልቧን ጐበኘው፡፡
“አባ፤ ያንተ እምነት ነው የኛም እምነት…” ስርጉተማርያም ነበረች
“እኔ ስላመንኩ ሳይሆን መርምራችሁ ማመን አለባችሁ!”
“ያባቴንማ አሳልፌ አልሰጥም!” ፈትለወርቅ ሳታስበው ተንገፈገፈች
“ፉከራ አታድርጊው … እምነት ማመን ነው! የሌላውን ሳይነቅፉና ሳያንቋሽሹ የራስን ብቻ ማመን አጥብቆ!”
“አባዬ፤ ዲሞክራሲ’ኮ የለገሰን ነፃነት፣ የፈለግነውን እንድንከተል ነው…” ቲቶ ነበር፡፡
“ሞኞ! የራስህን ስትከተል የሌላውን እየረገጥክና እያጥላላህ አይደለማ!” ዝም አለ ቲቶ
“እቺ ሀገር ሰው ትፈልጋለች…እናትና አባቶቿን እየናቀችና እየዘለፈች የትም አትደርስም! የአፍ ቅብብሉ በእውነት መለወጥ ይኖርበታል፤ በእምነትም ቢሆን እንደዛው! እውነቱ ታሽቶ መውጣት አለበት! እግር አጥበን የተቀበልናቸው ሁላ ዛሬ በእግራቸው ሊረግጡን አሰፍስፈው ይገኛሉ! እውነቱን፣ እምነቱን፣ መናገር ይጠበቅብናል…”
“ወጣም ወረደ እኛ የለገስናችሁ ነፃነት የዲሞክራሲያችን ነፀብራቅ ነው፡፡”
“ጣቃ ይመስል አትቀደድ! ለእኔ ነፃነት የለገሰኝ ያንተ ነፃነት ሳይሆን መስቀል ላይ ተሰቅሎ፣ ሞቶ ህይወቴን ያወጀው መድኃኒዓለም ነው፡፡”
“ይኼ የድክመት መሸፈኛ ነው” ከእናቱ ጋር ተጠቃቀሰ፤ ቲቶ፡፡  
“ተወው እስቲ…ማጣፍያው ያጠረ እለት ‘ወይኔ’ ቢሉ ዋጋ የለውም!”
“የቲቶ አባት … መቋጫ የሌው ነገር አይተርትሩ … ‘ዝም አይነቅዝም”
“እድሜና ጤና ይስጣችሁና የሚታየውን እዩ … ሌላ ምን ልበላችሁ … የራስን መጠየቅ፣ ማስከበር ወንጀል አይደለምና ጠይቁ!”
ልባቸውን በተከፈተው መስኮት ፊትለፊታቸው ካለው ተራራ ላይ ላኩት …
ልጆቹና እናታቸው … በአባታቸው ምሬት አዘል ንግግር ግራ ተጋብተዋል …
ቀልድን ሲቀልዱት የልብን እውነት ሸርሽሮ ይጥላል፡፡ ከዝምታ ማውራትን መርጠዋል፡፡ ዝም እንዲሉ … እነሱም ዝም አላሉም፡፡

Read 3671 times