Sunday, 24 November 2013 17:36

አረቦችና ስደተኛ ዜጐች

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(2 votes)

ማንኛውም ሀገር በህገወጥ መንገድ የራሱ ዜጐች ያልሆኑ ሰዎች ወደ ግዛቱ በማናቸውም አይነት መንገድ ዘልቀው እንዳይገቡ አቅሙ የፈቀደውን ያህል ጥበቃና ቁጥጥር በድንበሩ ላይ ያደርጋል፡፡ በዚህ መሃል ጥበቃና ቁጥጥሩን ጥሰው ወደ ግዛቱ ለመግባት ሲሞክሩ አሊያም ገብተው ያገኛቸውን ሰዎች በህገወጥነት ወንጀል ከሶ እንዳወጣው ህግና ደንብ መሠረት ተገቢ ነው ያለውን ቅጣት ወይ በእስር፣ ወይም ከሀገሩ በማስወጣትና ወደ መጡበት በመመለስ ወይም በሌላ የቅጣት አይነት ይቀጣል፡፡ የተለያዩ የአለም ሀገራት፣ በተለያየ ወቅትና አጋጣሚ ይህንን ሲያደርጉ በሚገባ አይተናል፡፡
ይህን የመሰለውን ጉዳይ በተመለከተ ሌላም አንድ አብይ ጉዳይ አለ፡፡ ማንኛውም ሀገር እንኳን በህገወጥ መንገድ ወደ ግዛቱ የገቡትን ስደተኞች ይቅርና በወግ በማዕረግ የገቡትንም ቢሆን “የአይናችሁን ቀለም አልወደድኩትም” የሚል መናኛ ምክንያት በማቅረብ ብቻ ከግዛቱ ለማስወጣት መብቱ ጥብቅና በእጁ ነው፡፡ በረጅሙ የአለማችን የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የተለያዩ ሀገራት በተለያየ ጊዜና አጋጣሚ ይህን መሰሉን ድርጊት ለበርካታ ጊዜያት ሲፈጽሙት ኖረዋል፡፡
ይህን ድርጊት አለማቀፋዊ ትኩረት እንዲያገኝ የሚያደርገው አንዱ ዋነኛ ነገር የሀገራቱ የድርጊት አፈፃፀም ሁኔታ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ሀገራት ከግዛታቸው የሚያባርሯቸውን ህገወጥ ሆነ ህጋዊ ስደተኞች ሰብአዊ መብትና ክብራቸውን ለመጠበቅ የቻሉትን ሁሉ ሲያደርጉ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ስደተኞቹን ማናቸውንም አይነት ዘዴ ተጠቅመው ማባረራቸውን እንጂ ለሰብአዊ መብታቸውና ክብራቸው መጠበቅ ቁብ የለሽ ናቸው፡፡
ሳኡዲት አረብ በህገወጥ መንገድ ወደ ግዛቷ ዘልቀው የገቡ ስደተኞኖች ህጋዊ እንዲሆኑ የሁለት አመት የጊዜ ገደብ  አስቀምጣላቸው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በህገወጥ መንገድ ወደ ግዛቷ የገቡ የየመን፣ የባንግላዲሽ፣ የስሪላንካ፣ የፓኪስታን፣ የህንድ፣ የፊሊፒንስ፣ ወዘተ ስደተኞች ህጋዊ መሆን ችለዋል፡፡
የዚህኑ ያህል ደግሞ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ህገወጥ ስደተኞች፤ ህጋዊ መሆን ሳይቻላቸው ቀርቷል፡፡ ሁኔታውን በሚገባ የሚያውቁ የስደተኛ እርዳታ ባለሙያዎች፤ ከእነዚህ ስደተኞች ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ኢትዮጵየውያን ስደተኞች መሆናቸውን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ያወጣው የሁለት አመት የጊዜ ገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ በወሰደው አስገዳጅ የሃይል እርምጃ፤ በተለይ በህገወጥ ኢትዮጵየውያን ስደተኞች ላይ የተፈጠረው ሁኔታ ያረጋገጠልን እውነታም ይህንኑ ነው፡፡
የሳኡዲ አረቢያ መንግስት አውጥቶት በነበረው የጊዜ ገደብ ውስጥ ህጋዊ መሆን ባልቻሉ ስደተኞች ላይ ሊወስደው የሚችለውን አስገዳጅ የሃይል እርምጃ በልባምነት አስቀድመው መገመት የቻሉ እንደ የመን፣ ፊሊፒንስ፣ ስሪላንካ፣ ባንግላዴሽና ፓኪስታን ያሉ ሀገራት አስፈላጊውን ርብርብ በተገቢው ትጋት በማከናወን፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ህገ ወጥ ስደተኞቻቸውን ወደ ሀገራቸው በመመለስ ዜጐቻቸውን ከከፍተኛ ስቃይና መከራ መታደግ ችለዋል፡፡
በሳኡዲ አረቢያ ከሚገኙትና በወጣው የጊዜ ገደብ ውስጥ ህጋዊ መሆን ካልቻሉ ህገወጥ ስደተኞች ውስጥ ከሁሉም በበለጠ ቁጥርና ከሁሉም እጅግ በከፋ ሁኔታ የሳኡዲ አረቢያ ፖሊስና የሳኡዲ ስርአት አልበኛ የመንደር ዱርዬዎች አሰቃቂ የግድያ፣ የድብደባ፣ የአስገድዶ መድፈር፣ የዘረፋና፣ የእስር ሰለባዎች የሆኑት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ናቸው፡፡
የሳኡዲ ፖሊስና ህገወጥ የመንደር ዱርዬዎች በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የፈፀሙት እጅግ አስከፊ ግፍና በደል በሳኡዲ አረቢያ የፖለቲካና የማህበራዊ ኑሮ ታሪክ ላይ ለረጅም ዘመን እጅግ መጥፎ የሆነ ጥቁር ጥላውን አጥልቶ የሚኖር፣ በዚህ የሰለጠነ ዘመንና፣ የሰለጠነ አለም ውስጥ ይደረጋል ተብሎ የማይገመት እጅግ አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ የሳኡዲ አረቢያ መንግስት እንኳን ህገወጥ ናቸው ላላቸው የሌላ ሀገር ዜጐች ይቅርና ለራሱ ሀገር ዜጐች የሰብአዊ መብት መከበር ምንም አይነት ደንታ የሌለው መንግስት መሆኑ፣ መላው አለም ያወቀውና ፀሀይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ያላንዳች ጥበቃና ከለላ በእጁ የሚገኙትን ስደተኞች በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ያን የመሰለ እጅግ ወራዳ ግፍ፣ ድፍን አለሙ ሁሉ እያየው በጠራራ ፀሀይ ይፈጽማል ተብሎ ጨርሶ አልተገመተም ነበር፡፡
በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከዳር ዳር ከፍተኛ የውርደትና የመጠቃት ስሜት የፈጠረባቸው ይህ የሳኡዲ አረቢያ እንስሳዊ ድርጊት ነው፡፡ አለመጠን ያንገበገባቸው ደግሞ እንደ ሌሎቹ ሀገራት መንግስታት የኢትዮጵያ መንግስት እነዚያን የግፍ አበሳ የወረደባቸውን ዜጐች፣ ባፋጣኝ ለመታደግ አሳይቷል ያሉት ከፍተኛ ዳተኝነት ነው፡፡ የተሰማቸውን ከፍተኛ ቁጣም ከአዲስ አበባ እስከ አሜሪካና ካናዳ፣ ከአፍሪካ እስከ መካከለኛው ምስራቅ ድረስ በአንድነት ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ፤ የሳኡዲ አረቢያን መንግስት በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ በፈፀመው እጅግ ነውረኛ ድርጊት ባወገዙበት በእነዚህ በርካታ የተቃውሞ ሰልፎች ውስጥ ምናልባትም በሁሉም በሚባል መልኩ ያነሱት አንድ አብይ ጉዳይ ኢትዮጵያውያን ሰሞኑን እንደተሰማው ዓይነት ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዳይፈፀምባቸው ምን ሰርተዋል? ምንስ ዓይነት ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ አድርገዋል የሚለው ነው፡፡ ሳኡዲ አረቢያ በእስልምና ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገውን የሙስሊሞችን ስደት ወይም ሂጅራና ይህንንም ተከትሎ የእምነቱ መስራች አባት የሆኑት ነብዩ መሀመድ (ሰ.ወ.ወ)፤ ስለ ኢትዮጵያ የተናገሩትንና መላ ሙስሊሞች እንዲፈፅሙት ያዘዙትን ትዕዛዝ እንዲያስታውሱ ያቀረቡት ጥያቄ ወይም ማሳሰቢያ ነው፡፡ ሆኖም ይሄን ነገር አረቦቹ እንዲያጤኑ ምን ያህል ከልብ ተንቀሳቅሰናል ነው-ጥያቄው፡፡ ሌላው ደግሞ የአገራችን ዲፕሎማቶች ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ሰሞኑን እንደተሰማው ዓይነት ኢሰብዓዊ ድርጊት እንዳይፈፀምባቸው ምን ሰርተዋል? ምንስ ዓይነት ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ አድርገዋል የሚለው ነው፡፡ በመጨረሻው ሰዓት መንግስት የተረባረበበትን ስደተኞችን የማስመለስ ጥረት ቀድሞውኑ ለማድረግ ምን ያዘው? ብለንም መጠየቃችን አይቀርም፡፡ አሁንም ቢሆን ካለፈው ስህተት ተምረን በየአረብ አገራቱ ላሉ ዜጐቻችን የተሻለ ጥበቃና ከለላ ማድረግ ተገቢ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡

Read 4888 times