Sunday, 24 November 2013 17:34

የመለስ ራዕይ፣ አቋም ለሌላቸው፣ “የጋዜጠኞች ማህበራት” ቦታ የለውም!

Written by  ፍፁም ገ/እግዚአብሔር
Rate this item
(8 votes)

                     ከሣምንት በፊት በአፍሪካ ህብረት የተካሄደውን የአፍሪካ ሚዲያ የመሪዎች ፎረም፣ ለእኛው ኢቴቪም፤ የማይረሡ ዝግጅቶችን፣ የሚያሥደምሙ የጋዜጠኞች ማህበራት ቅንብርብር መድረኮችን፣ “ለምንወደውና ለሚወደን ህዝቦቹ” እንዲያሣይ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖለት አልፏል፡፡ የሚዲያ ፎረሙን ምክንያት በማድረግ፣ ሙያዊ ሣይሆን ተቋማዊ የሚመሥል የአቋም መግለጫ ለማስተላለፍ፣ ለአቅመ ጋዜጠኝነት የበቁ የመሠሉት የጋዜጠኞች ማህበራት፣ ሥለ ኢህአዴግ የፕሬሥ ነፃነት አከባበር ሲያሥተነትኑ፣ ስለየትኛዋ አገር እንደሚናገሩ ግራ ተጋብቼ ነበር፡፡
የጋዜጠኞች ማህበራት በጥምረት፣ የፕሬሥ ነፃነትን በማክበር ጉዳይ ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ሁሉ ምሣሌ ልትሆን እንደምትችል አድርገው ሲብራሩ ሣይሆን “ሲያቅራሩ”፣ “ኧረ ህዝብና መንግሥት ባትፈሩ፣ ቆምንለት የምትሉትን ራዕይ ፍሩ” የሚል አንድ የኢህአዴግ ታማኝ ካድሬ እንዴት ይጠፋል? ያሥብላል፡፡ የማህበራቱ መሪዎች በኢቴቪ ሢታዩ ከንግግራቸው አነጋገራቸው፣ ከልብ ባይነታቸው፣ ልበ ሙሉነታቸው ይገርማል፤ እንደውም አንባቢያን ካልታዘባችሁኝ፣ “ጋዜጠኞቹ” በልበ ሙሉነት ያቀረቡት ንግግር ከማስረገም አልፎም፣ “አሥቀንቶኛል” ብል ደስ ይለኛል፤ እውነቴን ነው … መንግሥት እራሡ ያልካደው የኢትዮጵያን የፕሬስ ጣጣ እንከን የለሽ አድርጐ የማውጋት ድፍረት፣ ያውም በመላው ዓለም በሚተላለፍ የቴሌቪዥን መስኮት ፊት ቀርቦ በልበ ሙሉነት የመግለጽ “ነፃነት” በርግጥም የሚያሥቀና ይመሥለኛል፡፡ ታዲያ፣ በጋዜጠኞቹ መግለጫ እየተገረምኩ፣ የእኔ የመረጃ ድርቀት ወይሥ የእነሡ ድፍረት እንዲህ የሚያብከነክነኝ? እያልኩ ከራሤ ጋር ሣወጋ ቆይቼ ነበረ፡፡ ደግነቱ ግን የዛሬ ሣምንት በዚሁ ጋዜጣ ላይ፣ “የጋዜጠኞች” ማህበራቱን ኢህአዴግ ራሱ ታዝቧቸዋል!” የሚል ርዕስ ሣነብ፣ እራሴን ከመውቀሥ ተገላገልኩ፡፡ ወዲያው በጋዜጣው የፊት ለፊት ገጽ የተጠቆመውን ርዕስ ዱካ ፍለጋ ገፆች ገላለጥኩ፡፡
“የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያሥታውቃል” እንዲሉ፣ በተገረምኩበት ርዕስ፣ ሥር የቀረበው ጽሁፍ በሚገባ ቀልቤን ገዝቶት አገኘሁት፡፡ በምፀታዊ የፖለቲካ አሽሙራቸው የታወቁት አቶ ኤልያስ፣ ዛሬም የጋዜጠኞቹን ስሜታዊ መግለጫ፣ በተጠያቂያዊው መረጃ አለዝበው፣ በፈገግታ ሞሽረው ነበር ያቀረቡት፡፡
የፖለቲካ በፈገግታው አምደኛ፣ የጋዜጠኞች ማህበራቱን መግለጫ የጋዜጠኞች ሣይሆን የ‘አብዮታዊ መንግሥት’ ወይም ‘ድርጅት’ ነበረ የሚመስለው በማለት፣ መግለጫ አቅራቢ ጋዜጠኞች፣ የመድረክ ትወናውን ብቻ ሣይሆን፣ ቃለ ተውኔቱንም ከኢህአዴግ ጽንፈኛ ካድሬዎች የኮረጁት እንደሚመሥል በወጉ ነው ያሥተነተኑት፡፡
የተባለውን ለማስረገጥ የአምደኛው ምፀታዊና አሽሙራዊ ትችት እንደሚከተለው ማጣቀስ ይቻላል፤ የጋዜጠኞች ማህበራቱ ካቀረቧቸው ጽንፍ ላይ የቆሙ መግለጫዎች መካከል፣ “አንደኛው ደግሞ ከኢህአዴግ ቃል በቃል የተኮረጀ ነው (ኮማ ሣይቀር!) ልዩነቱ ምን መሰላችሁ? ኢህአዴግ በተደጋጋሚ ‘በኢትዮጵያ ውስጥ ከሙያቸው ጋር በተያያዘ የታሰሩ ጋዜጠኞች የሉም’ የሚል ምላሽ ሲሰጥ ደንፍቶ አያውቅም፡፡ እነሱ ግን ቀላል ቀወጡት! አገር ይያዝልን እኮ ነው ያሉት፡፡ ቦታው ሥላልተመቻቸው ነው እንጂ ሽለላና ቀረርቶ ሁሉ ዳድቷቸው ነበር፡፡ (ኢህአዴግ ራሱ እኮ ሳይታዘባቸው አይቀርም) እኔማ ምነው በገመገመልኝ ብዬ ነበር፡፡ ለካሥ የኢህአዴግ አባል አይደሉም (ናቸው እንዴ?)”  በአሽሙራዊ መጣጥፉ ላይ በቅንፍ ውስጥ የቀረቡት ገለፃዎች የምር እያሣቁ ዘና አድርገውኛል፡፡ ለነገሩ በመጀመሪያ ቅንፍ ውስጥ የሰፈረው ገለፃ፣ ማለቴ “ኮማ ሣይቀር!” የሚለው ከማዝናናት አልፎ በትዝታ ውስጥም አስምጦኝ ነበረ፡፡ “ኮማ ሣይቀር!” የሚለውን ከማን ንግግር ላይ ነበር የሰማሁት የሚለው ትንሽ አሥቆዘመኝ፡፡ በኋላ ግን፣ ነፍሣቸውን ይማር ከአቶ መለስ ዜናዊ ንግግር ውሰጥ እንዳዳመጥኩት ትዝ አለኝ፡፡ የሚገርመው ደግሞ ንግግሩን ለማስታወሥ ሥሞክር ርዕሠ ጉዳዩ፣ “የፀረ ሽብር አዋጁ” ነበር፡፡
አቶ መለስ፣ ስለ ፀረ ሽብር አዋጁ በፓርላማ ተገኝተው መግለጫ ሲሰጡ፣ “የፀረ ሽብር አዋጁ ህገ መንግሥቱን ይጥሣል፤ አንዳንድ ጽንፈኛ ካድሬዎችም ላልተገባ ተግባር ያውሉታል፤ የዜጐች ሰአብዊ መብቶች እንዲገሰግሡ የህግ ድጋፍ ይሆናል …” የሚሉ የተለያዩ ሙግቶች ቀርበውባቸው ነበረ፡፡ ባለ “ራዕዩ መሪ” ታዲያ አፍ የሚያዘጋ መልሥ አብሠለሠሉና “የፀረ ሽብር አዋጁ ቃል በቃል ከምዕራባዊያኑ የተገለበጠ ነው - ኮማ ሣይቀር!” የሚል ምላሽ መሥጠታቸውን አልረሣውም፡፡
እናም፣ “ኮማ ሣይቀር” የሚለው፣ “የኢህአዴግ አባል አይደሉም እንዴ?” ከሚለው ጠያቂ አሽሙር ጋር ተጣምረው፣ “ኢህአዴግ ራሱ ታዝቧቸዋል!” በሚል መሪ ቃል መቋጨቱ፣ የጋዜጠኛ ማህበራቱን አቋም የምር እንድንጠይቅ ያሥገድዳል፡፡ የማህበራቱ መሪዎች፣ ስብዕናን ጥያቄ ውስጥ የሚጥለውም ይመሥላል፡፡ “በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት ከየትኛውም የአፍሪካ ሀገራት የበለጠ ተከብሯል” የሚለው ስሜታዊና ደፋር አቋም፣ እንደተባለውም በኢህአዴግ “ትዝብት ላይ የሚጥል ቅሌት” መሥሎ የሚታይ አይመሥልም ማለት ሁሉ ይከብዳል፡፡
ኢህአዴግ በባለ ራዕዩ መሪው፤ በአቶ መለስ ሀሣብ የተጠመቀ የማያወላውል ድርጅት ከሆነ በርግጥም፣ “ወላዋይና አድርባይ” ባህርያትን፣ በፅኑ ይቃወማቸዋል ብሎ ማሠብ ይቻላል፡፡ ባህርያቱን ከተቃወመ ደግሞ፣ የባህርያቱ መገለጫ የሆኑ ተክለ ሰውነቶችንም፣ በተለይ ለእርሡ የሚጠቅሙት ከሆነ በፊት ለፊት ላይቃወማቸው ይችላል፤ የቀደመ መሪውን “ራዕይ” የሚያሥፈጽም ድርጅት መሆኑ አፋዊ ሣይሆን ልባዊ ከሆነ ደግሞ በፊት ለፊት የማይቃወማቸው አድርባይ ሰዎችን ቢያንሥ ሊታዘባቸው እንደሚችል ግን ግልፅ ነው፡፡ ካልሆነ፣ የመሪውን የአደራ ቃል የበላ፣ ራዕያቸውን ማስቀጠል የማይችል ተክለ አቋም እየገነባ ነው ሊባል ሁሉ ይችላልና፡፡
ለዚህ ሀሣቤ ደግሞ፣ የአቶ መለሥ ራዕይ፣ “የጋዜጠኞች ማህበራቱን አቋም” እንደሚቃወም ማስረገጥ ብቻ የሚበቃ ይመሥለኛል፡፡ አቶ መለስ በአንድ ወቅት ስለሚወዱትና ስለሚጠሉት ሰው ሁኔታ ሲጠየቁ የመለሱትን ምላሽ ቃል በቃል መጥቀሥ ይቻላልና፤ “ቢከፋም ቢለማም አቋም ያለው ሰው አከብራለሁ፡፡ አቋም የሌለውና ወላዋይ ሰው በአጋጣሚ እንኳን ደጋፊ ቢሆን ብዙም አይመቸኝም፡፡ ስለዚህ ለኔ የመጀመሪያና ዋናው መለኪያ አድርጌ የምወስደው፣ አንድ ሰው የሚያምንበትንና የማያምንበትን ተገንዝቦ፣ አቋሙን በሚገባ የሚያውቅና ላመነበት በፅናት የሚታገል ከሆነ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ሰው ነው ጥሩ ሰው የምለው፡፡ ፅኑ አቋም ብቻ ሣይሆን ፅኑና ጥሩ አቋም ያለው ሰው ደግሞ የበለጠ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡”

Read 2267 times