Sunday, 24 November 2013 17:18

የአውሮፓ ህብረት 5.3 ቢሊዮን ብር ለኢትዮጵያ ሰጠ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

የአውሮፓ ህብረት 5.3 ቢሊዮን ብር የልማት እርዳታ ለኢትዮጵያ የሰጠ ሲሆን፤  የልማት እርዳታው ኢትዮጵያ ለምታካሂደው መጠነ ሰፊ የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ የትምህርት የጤናና መሰል መሰረታዊ አገልግሎቶች ግንባታና ጥበቃ፣ለድርቅ መከላከያና መቋቋሚያ እንዲሁም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለምታደርጋቸው የልማት እንቅስቃሴዎች ማስፋፊያ የሚውል እንደሆነ ታውቋል፡፡
ከህብረቱ የኢትዮጵያ ልዑክ ፅ/ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከተሰጠው የ5.3 ቢሊዮን ብር የልማት እርዳታ ውስጥ 1.8 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ኢትዮጵያ ለምታካሂደው መጠነ ሰፊ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ሲውል፣ አንድ ቢሊዮን ብር ደግሞ ድርቅን ለመከላከልና ለመቋቋም ለሚደረገው የልማት እንቅስቃሴ የሚውል ነው፡፡ የተቀረው ገንዘብ ደግሞ ለጤና፣ለትምህርትና መሰል መሰረታዊ አገልግሎቶች ግንባታና ጥበቃ እንዲሁም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚውል ታውቋል፡፡ የልማት እርዳታው ስምምነት የአውሮፓ ኮሚሽን የልማት ኮሚሽነር አንድሪስ ፒባልግስና በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ደኤታ አቶ አህመድ ሽዴ መካከል የፊታችን ሰኞ ይፈረማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከጽ/ቤቱ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ግንባር ቀደም ከሆኑት የኢትዮጵያ የልማት አጋሮች መካከል ዋነኛው ሲሆን የህብረቱና የኢትዮጵያ የልማት ትብብር ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ ከ1975 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ የልማት እንቅስቃሴ በገንዘብና በቴክኒክ ሲረዳ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

Read 1820 times