Sunday, 24 November 2013 17:17

የገናን ባዛር ለማዘጋጀት፣ “አፍሮ ዳን” በ3.8ሚ. ብር አሸነፈ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

እስካሁን ከ40 በላይ የውጭ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ ታውቋል
ለባዛሩ ፒስኩየሮች ይመጣሉ ተብሏል

የፈረንጆች አዲስ አመት፣ የፈረንጆች ገና እና የኢትዮጵያ የገና በዓል አንድ ሰሞን የሚከበሩበት የገናን ባዛርና ኤግዚቢሽንን ለማዘጋጀት በወጣው ጨረታ “አፍሮ ዳን” በ3.8 ሚሊዮን ብር ማሸነፉ ተገለፀ፡፡
የድርጅቱ ሀላፊዎች ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ እስካሁን በባዛሩ ላይ ለመሳተፍ 400 ኩባንያዎች የተመዘገቡ ሲሆን የውጭ አገር ነጋዴዎች 47 ቦታዎችን መያዛቸውን የ “አፍሮ ዳን” ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል ወርቅሸት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ ነጋዴዎቹ ከግብፅ፣ ከቱርክ፣ ከህንድና ከቻይና እንደሚሳተፉ የገለፁት አቶ ዳንኤል፤ ከአገር ውስጥም ከ10 በላይ አልባሳት አምራቾች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡ በአብዛኛው በቤት እቃ፣ በምግብ፣ በሙሽራ ልብስ፣ በህፃናት አልባሳት፣ በፋስት ፉድ፣ በስጦታ እቃዎችና በመሰል ዘርፎች የተሰማሩ ኩባንያዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑም ተገልጿል፡፡ የባዛሩን የመዝናኛ ዘርፍ በተመለከተ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ሙዚቀኞች እንደሚሳተፉ የተናገሩት የመዝናኛው ዘርፍ ሃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ቴዲአብ፤ በመስከረም አጋማሽ ላይ በሚሌኒየም አዳራሽ ስራቸውን ያቀረቡት ፒስኩየሮች እንደሚሳተፉ በመግለጫው ላይ አስታውቀዋል፡፡ 30 ት/ቤቶች በዳንስ፣ በስዕልና በሌሎች ዘርፎች የተሰጥኦ ውድድር እንደሚያደርጉና አሸናፊዎች እንደሚሸለሙ የተገለፀ ሲሆን ይሄም ባዛሩን ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ለየት እንደሚያደርገው ተነግሯል፡፡ በፊት በርካታ ጠጅ አቅራቢዎች በባዛሮች ላይ ይሳተፉ እንደነበር ያስታወሱት የባዛሩ አሸናፊዎች፤ ይሄም ለመሳከርና ለብጥብጥ ይዳርግ ነበር በማለት አሁን ግን ሶስት ጠጅ አቅራቢዎች ብቻ እንደሚገቡ ጠቁመዋል፡፡ የፀጥታን ጉዳይ በተመለከተም ከመንግስት ጋር በቅርበት እየሰሩ እንደሆነ የድርጅቱ ባለቤት ተናግረዋል፡፡ የባዛሩን ጨረታ በ3.8 ሚሊዮን ብር ገደማ ቢያሸንፉም ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ የ6 ሚሊዮን ብር  እንደሆነ የገለፁት አቶ ዳንኤል፤ በባዛርና ኤግዚቢሽኑ ላይ ባህላቸውንና እሴታቸውን እንዲያስተዋውቁ ለ102 ኤምባሲዎች ግብዣ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡ ባዛርና ኤግዚቢሽኑን ፋፋ፣ ቃሊቲ ብስኩት፣ አምባሳደር ልብስ ስፌት፣ ቴክኖ ሞባይል፣ ኤልጂ ኤሌክትሮኒክስና የተለያዩ ቢራ ፋብሪካዎች ስፖንሰር እንዳደረጉት ታውቋል፡፡
ጨረታውን በምን መስፈርት እንዳሸነፉ የተጠየቁት አቶ ዳንኤል፤ “በፊት በፕሮፖዛል ነበር፤ አሁን ግን በገንዘብ ሆኗል፤ ስለዚህ በገንዘብ ብልጫ አሸንፈናል” ቢሉም እነሱ ግን ውድድሩ በፕሮፖዛል ቢሆን ይመርጡ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡

Read 2072 times