Monday, 18 November 2013 12:01

ባለ “4 ኮከቡ” ቤል ቪው ሆቴልና ስፓ ዛሬ ይመረቃል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 200 ሚ.ብር ይፈጃል
ለባህሬን የምትሮጠው አትሌት ማርያም የሱፍ ጀማልና ባለቤቷ አቶ ወንድወሰን ዲሶ (ታረቅ) በአዲስ አበባ ከተማ መገናኛ አካባቢ፣ ከዳያስፖራ አደባባይ ፊት ለፊት ዳገቱ ላይ ያሠሩት ዘመናዊ ባለ “4 ኮከቡ” ቤላ ቪው ሆቴልና ስፓ ዛሬ ይመረቃል፡፡
የቬላ ቪው ሆቴልና ስፓ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድወሰን ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፣ ሆቴሉ 35 ክፍሎችና ስፓ ሲኖረው፣ ስፓው በውበትና በትልቅነት በመዲናችን ብቻ ሳይሆን በአገራችንም የመጀመሪያው እንደሆነ ተናግሯል፡፡ በ “ሶፍ ኦማር” የተሰየሙ ስፓ፣ አዋሽ ሳውናና ስቲም፣ ዳሎል ጃኩዚ ትክክለኛው ሞሮኮ ባዝ፣ የእጅ፣ የእግርና የጥፍር መዋቢያ፣ የሴቶችና የወንዶች ፀጉር ቤት፣ ቦብ ማርሌ የፊት ማስዋቢያ እንዲሁም በላሊበላ፣ አክሱም፣ ፋሲለደስና ኮንሶ የተሰየሙ የማሳጅ ክፍሎች እንዳሉት ሥራ አስኪያጁ አብራርቷል፡፡
ሆቴሉ ላይ ሆኖ አዲስ አበባን መመልከት ልብ ይማርካል ያለው ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ከጀርባ ያለው ተራራ ፈረንሳይ ሌጋሲዮንን ከመጋረዱ በስተቀር በሁሉም አቅጣጫ ከተማዋን ፍንትው አድርጐ በማሳየት፣ በከተማዋ ካሉ ሆቴሎች ሁሉ ይልቃል ብሏል፡፡ ቬላ ቪው በፈረንሳይኛ “ጥሩ፣ ውብ፣ ቆንጆ፣ እይታ” ማለት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ባለ ስንት ኮከብ እንደሆነ ተጠይቆ ባለቤቱ ሲመልሱ፣ ከሆቴልና ቱሪዝም ሚ/ር የመጡ ባለሙያዎች ሆቴሉ ያሉትን ፋሲሊቲዎች ካዩ በኋላ፣4 ኮከብ ሊያሟላ እንደሚችል አረጋግጠው፣ “ከፈለጋችሁ 5 ኮከብ ጠይቁ” እንዳሏቸው ተናግሯል፡፡ ሆቴሉ የመዋኛ ገንዳና ከቤት ውጭ ስፖርቶች ማካሄጃ ቢኖረው፣ ባለ 5 ኮከብ ደረጃ ሊያሟላ እንደሚችል ጠቅሶ፣ መጀመሪያውኑ ዕቅዳቸው ባለ 4 ኮከብ ስለሆነ፣ በዚሁ ደረጃ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት እንደሚቀጥሉ ተናግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብ እንዳለ ሆኖ፣ ሆቴሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ የስዊስ፣ የፈረንሳይና የጣሊያን ምግብ እንደሚያዘጋጅ የገለፀው አቶ ወንድወሰን፣ ለዚህም በፓሪስ ሂልተንና በሌሎች ታዋቂ ሆቴሎች የሠራና ብዙ ልምድ ያለውን ፈረንሳዊ የምግብ አዘጋጅ (ሼፍ) መቅጠሩንና በፓሪስ ሂልተን በኃላፊነት ትሠራ የነበረችውን ፈረንሳዊት በኦፕሬሽን ማናጀርነት ማምጣቱን አስታውቋል። እንዲሁም ሠራተኞቹ እንግሊዝኛ፣ ጀርመንኛ፣ ዐረብኛ፣ ፈረንሳይኛና ኪስዋሂሊ አቀላጥፈው የሚናገሩ ስለሆነ፣ ከእንግዶች ጋር የመግባባት ችግር እንደማይኖርና ከፍተኛ ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አስታውቋል፡፡
የሆቴሉ ግንባታ 95 ከመቶ የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ ጥቂት የሚቀር ሥራ ስላለው ወጪው በትክክል ያለመሰላቱን ባለ ሀብቱ ጠቅሶ፣ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 200 ሚሊዮን ያህል ብር እንደሚፈጅና ለ143 ዜጐች የሥራ ዕድል መፈጠሩን፣ በአጠቃላይ ሥራው ሲጠናቀቅም የሠራተኞቹ ቁጥር 250 እንደሚደርስ ተናግሯል - አቶ ወንድወሰን፡፡
ከሁሉም በላይ የሚያስጨንቃቸው የእንግዶቻቸው ደኅንነት በመሆኑ፣ 67 የደህንነት መቆጣጠሪያ ካሜራዎችና እሳት ቢነሳ ጪስ ጠቋሚ መሳሪያዎች መተከላቸውን፣ በሪሞት መቆጣጠሪያ የሚታዘዙት አምፑሎች 12 ዓይነት ቀለም እንደሚፈነጥቁ፣ … ተገልጿል፡፡ ከጃፓን የተገዙት የመታጠቢያ ክፍል ዕቃዎች ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸው ሲሆን የ30 ዓመት ዋስትና የተረጋገጠላቸው መሆኑም ተነግሯል፡፡
የቤላ ቪው ሆቴል ግንባታ ስድስት ዓመት ያህል እንደፈጀ የጠቀሰው አቶ ወንድወሰን፣ ቦታው ዳገት ላይ በመሆኑ በተፈጠረው አስቸጋሪነት፣ የሚያምርና የሚያኮራ ነገር ለመሥራት በመፈለጋቸውና አንድ አገልግሎት ሰጪ መ/ቤት በፈፀመባቸው በደል፣ ግንባታው ሊዘገይ መቻሉን ገልጿል። የተፈፀመባቸው በደል ምን እንደሆነ ተጠይቆ ሲመልስ፣ “ጥሩ መ/ቤቶች የመኖራቸውን ያህል በደል የፈፀመብንም አለ፡፡ ሙስና ገንዘብ መስጠትና መቀበል ብቻ ሳይሆን የመልካም አስተዳደር ጉድለትም ሙስና ነው፡፡ ይህን ኢንቨስተሮችን የሚያባርር በደል፣ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ማወቅ አለበት፡፡ አራት ኪሎ የሚገኘው የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን ጽ/ቤት ከፍተኛ በደል አድርሶብናል፡፡ ያልገባንበት ባለሥልጣንና ኃላፊ ቢሮ የለም፡፡ ሊያነጋግሩን እንኳ ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ ይኼ ሆቴል ሥራው ያለቀው ከአምስት ወር በፊት ነው፡፡ መብራት ስለሌለን፣ የተገጠሙትን ዘመናዊ መሳሪያዎች መሞከር አልቻልንም፡፡ እንቢ ብለውን ቆይተው “እንግዲያውስ አገሪቷን ጥለን እንወጣለን” ስንላቸው በስንት መከራ ባለፈው ሳምንት አስገቡልን፡፡ የዚያኑ ያህል ጥሩ መ/ቤቶችም ስላሉ መመስገን አለባቸው። ቴሌና የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን እራሳቸው አስገብተውና ፈትሸው ነው ያስረከቡን፡፡ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ የመብራት ኃይል በደል በእኛ ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎችንም እያስለቀሰ ነው፡፡ አንተ ዕድለኛ ነህ፤ እኛ ከ8 ወር በላይ ጠብቀን አልሆነልንም’ ያሉኝ አሉ” በማለት ምሬቱን ገልጿል፡፡
ለበርካታ ዓመታት ስዊስ የኖረው አቶ ወንድወሰን አትሌት የነበረ ሲሆን፣በአሁኑ ወቅት የባለቤቱ የማርያምና የባህሬን ብሔራዊ አትሌቲክስ ቡድን አሠልጣኝ ነው፡፡  

Read 2749 times