Monday, 18 November 2013 11:34

እሳቱ

Written by  ድርሰት - ሺ ፓንግ ፋን ትርጉም - ፈለቀ የማርውሃ አበበ
Rate this item
(8 votes)

                       በባህል አብዮቱ ወቅት፤ ቀይ ቃፊሮቹ፤ በየደረሱበት ያገኙትን ማናቸውንም አይነት ምስሎች እየሸረካከቱ፣ እየቦጫጨቁ ይጥሉ ጀመር፡፡ ከሊቀመንበር ማኦ ምስል በቀር፡፡ የሀገረ ቻይናን ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሳ ቅርሶች ሁሉ እንክትክት አድርገው እየሰባበሩ ዱቄት አደረጉት፡፡ አንድም የመጽሀፍ ዘር የተባለ ሳይቀራቸው፤ ከያለበት ሰብስበው በማውጣት እሳት ለቀቁበት፡፡ ከሊቀመንበር ማኦ መጻሕፍት በቀር፡፡
በተቃዋሚ ጎራ የተፈረጁ ቤተሰቦች ዕጣ ፈንታ እጅግ መራር ነበር፡፡ ቀይ ቃፊሮቹ፤ ድንገት በራቸውን በርግደው ይገቡና ጓዳ ጎድጓዳቸውን ይበረብራሉ፤ የቤት እቃዎቻቸውን፡- ብስክሌት፣ የግርግዳ ሰአት፣ ጥሩ ጥሩ ልብሶችንና የህፃናት መጫወቻዎችንም ሳይቀር፤ ዋጋ ያወጣልናል ብለው የገመቱትን ነገር ሁሉ እየሰበሰቡ ይወስዳሉ። የማይፈልጉትን እንኳን አይተዉትም፤ ወደ ውጪ እየወረወሩ ከስክሰው ያደቅቁታል እንጂ፡፡ በቤተሰቡ አባላትም ላይ ጭካኔ የተሞላበት ድብደባ ይፈጽማሉ፡፡ አንዳንድ ልጃገረዶች፤በቤተሰቦቻቸው ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ ያረገቡ መስሏቸው ለአብዮተኞቹና ጭፍሮቻቸው ክቡር ገላቸውን አበርክተዋል፡፡
በመንደሩ ውስጥ የሚኖሩ ድሃ ጭሰኞች፣ የበኩር ልጅ የሆነ አንድ መልከ ጥፉ ጎረምሳ ነበረ። ዕድሜው ከሰላሳዎቹ ቢዘልልም ሰነፍ፣ ዘልዛላና ጅላጅል ቢጤ ስለሆነ ትዳር ያልያዘ ‹‹ቆሞ ቀር›› ነው። “ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል” እንዲሉ፤ በሀገሬው የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ምስቅልቅል እንደጥሩ አጋጣሚ ቆጥሮ፣ በአንድ እጁ ማስፈራሪያ፣ መሸንቆጫ ጉማሬ አለንጋውን፤ በሌላ እጁ ቡትሌውን ጨብጦ፤ አዛዥ ናዛዥ ሆኖ ቁጭ አለ። ሀይ ባይ አጣ፡፡ በአሳቻ ሰአት ወጣት ልጃገረዶች ባሉበት የተቃዋሚ ቤተሰቦች ቤት እንዳሻው ዘው እያለ፤እምቡጥ ኮረዳዎቹን እያርበደበደ፤ እምቢኝ ብለው ሲተናነቁት እጃቸውን ጠምዝዞ ገፍትሮ በመጣል ጉልበት ከድቷቸው በወደቁበት ጨምድዶ ይዟቸው፤ አይናቸውን እያቁለጨለጩ ሲንፈራገጡ፤ይበልጥ ትንፋሽ አሳጥቶ ጉሮሯቸውን አንቆ በመያዝ፤ ልብሳቸውን እየሸነታተረ፤ አስገድዶ ይደፍራቸዋል፤ በእንባ እየታጠቡ፡፡
አቶ ሻንግ ደግሞ፤ ዕድሜያቸው ከስድሳው የገፋ፤ በሰዎች ዘንድ በፀባይና ምግባራቸው የተከበሩ አዛውንት ናቸው፡፡ አብዛኛውን ዘመናቸውንም ያሳለፉት የባለጸጋ ነጋዴዎችንና የባለስልጣን ቤተሰቦች ልጆችን፤ ቱባውን የቻይና ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶችን፣ የኪነ ጥበባት፣ ኃይማኖታዊ ፍልስፍና … ትውፊታዊ አንድምታዎችን እውቀት በማስተማር ነው፡፡
ከሦስት ትውልዳቸው ጀምሮ በቅብብሎሽ የመጣውን ጥንታዊውን ዕምቅ ጥበብ ስለወረሱም፤ በጥልቅ ልቦና የተፀነሱ በርካታ የፈጠራ ስራዎችን አምጠው የወለዱ፤ ሰማየ ሰማያት የመጠቁ ረቂቅ ቅኔዎችን ስንኝ የሰደሩ… እንዲሁም ልዩ ግንዛቤ እሚሻውን የቻይናን የፊደል አፃፃፍና ትርጓሜ (ካሊግራፊ) ክህሎት ያካበቱ ‹‹አራት አይና›› ልሂቅ ናቸው፡፡ ይኸውም አፍ በእጅ የሚያሲዝ አድናቆትን የተናኘ ጉምቱ ስብዕናቸው፤ ከሚኖሩበት መንደር አልፎ በሌሎቹም አጎራባች ከተሞች ሁሉ፤ እንደ ብርቅ የሚታዩ ስመ ጥር ሰው አድርጓቸዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ዝናቸውን ያገነነው ግን ያሏቸው የመጻሕፍት ብዛት ነው፡፡
ከአያት ቅድመ አያቶቻቸው ጀምሮ፤ ቤተሰቦቻቸው ሁሉ ከፍተኛ የንባብ ፍቅር ያደረባቸው ነበሩ፡፡ የርሳቸው የመጽሀፍ ቁርኝት ደግሞ እብድ ሊያሰኛቸው የሚያደርስ ነው። ከሚያገኙት ገቢ አብዛኛውን ለመጻሕፍት መግዣ ያውላሉ፡፡ እንዲያውም፤ አንዳንድ ሰዎች፤ ‹ለመጽሀፍ መግዣ ያወጡትን ገንዘብ… እርሻ ቢያስፋፉበት ኖሮ፤ እንዴት ያሉ የመሬት ከበርቴ መሆን በቻሉ ነበር!› ይሏቸዋል፡፡ በመጻሕፍት ስብስቦቻቸው አይነት፤ በሰሜን ቻይና ውስጥ አቻ አይገኝላቸውም። በቁጥር ከሦስት ሺህ በላይ መጻሕፍት አሏቸው፡፡ አንዳንዶቹ በዋጋ የማይተመኑና በሚንግ ና ሶንግ ዘመን (ከአምስት እስከ ስምንት መቶ አመታት በፊት) የተደጎሱ ናቸው፡፡ አቶ ሻንግ፤ በደብሊው ከተማ በተካሄደው የፖለቲካ ምክክር መድረክ ላይ፤ በክብር አባልነት ተጋብዘው የተሳተፉበት ጊዜም ነበር፡፡
ከ1949ኙ ለውጥ በኋላ ግን አቶ ሻንግ፤ ወደ ቀድሞው የመምህርነት ሞያ አልተመለሱም፡፡ ወደ ትውልድ መንደራቸው አቅንተው በጭሰኝነት መተዳደር ጀመሩ፡፡ ስለ ግብርና መጠነኛ ዕውቀት ስለነበራቸው፤ የመንደሩ ነዋሪዎች መልካም አቀባበል ነበር ያደረጉላቸው፡፡ አዛውንቱ ፤ አስተዋይ፣ ታማኝና ግብረገብ አዋቂ ከመሆናቸውም ባሻገር፣ የአዲስ አመት ብስራት መግለጫዎችን፣ በመንደሪቱ ውስጥ ለሚደገሱ የሠርግ በዐላት የሚሆኑ መጥሪያዎችን በማዘጋጀት፣ ስዕሎችን በመሳልና ግጥሞችን በመፃፍም ስለሚተባበሩ፤ በነዋሪዎቹ ዘንድ ተወዳጅ ሰው ሆኑ፡፡ እናም፤ እንደ አንድ ምስኪን ጭሰኛ ተረጋግተው በሚመሩት ሰላማዊ የገጠር ህይወት፤ ከፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ጦስ ሉተርፉ ችለዋል፡፡
የግርግሩ ወቅት ግን፤ እገሌ ከእገሌ፣ ትንሽ ትልቅ ሳይል፤ በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላሉት ሆነ በጭሰኝነት ለሚንገታገቱት ድሆች ሳይቀር እረፍት የሚነሳ አስከፊ ጊዜ ሆነ፡፡ ዜጎች፤ በየጣራቸው ስር የሚገኙ መጻሕፍቶቻቸውን አንዲትም ሳያስቀሩ መቀዳደድ ወይም ማቃጠልና ይህንኑም ድርጊታቸውን በየመንደሮቻቸው ታጥቀው ለሚንጎማለሉት የቀይ ቃፊሮቹ ጭፍሮች አሊያም ለአዛዥ ካድሬዎቻቸው ያሉበት ድረስ ሄደው የማሳወቅ ግዴታ ተጥሎባቸው ነበር፡፡ አዬ የቀን ጎዶሎ! እንግዲህ የአቶ ሻንግ መጻሕፍት ዕጣቸው ምን ይሆን? አዛውንቱ ያሉዋቸው መጻሕፍት ከሦስት ሺህ በላይ ስለሆኑ፤ እንዲህ በቀላሉ ካንዱ ስርቻ የሚሸጎጡ፣ ወይም አንዱጋ የሚደረጉ አይደሉም - መቸም፡፡ አቶ ሻንግ ደግሞ፤ መጻሕፍታቸው፤ በሌላ ማንም ባዕድ እጅ ንክች እንዲደረግባቸው ከቶም አይሹም፡፡ ምን ሲደረግ! ‹‹መፅሀፍቶቼ ለእኔ ህይወቴ ናቸው!›› ይላሉ፡፡
የዛን እለት ግን አይቀሬው መከራ እውን ሆነ፡፡ የሆነው ሁሉ የሆነው… እሳቸው በሌሉበት ነበር፡፡
ሚስታቸው፤ መቼም ይሁን መች፤ ያው የእነርሱም ተራ ሲደርስ፤ በድንገት መዝጊያቸው በሀይል ተከፍቶ፤ ቤታቸው እንደሚበረበር ታውቅ ነበርና፤ አዛውንቱ፤ አይናቸው ሥር መጻሕፍቶቻቸው ሲቃጠሉ እንዳያዩ ስትል፤ራቅ ያለ ስፍራ የሚኖሩ ዘመዶቻቸውን ጠይቀው እንዲመጡ አግባብታ ሸኘቻቸው፡፡ ወዲያውም፣ ጊዜ ሳታጠፋ፣ በርራ በመንደሩ ወደሚያንዣብቡት ቀይ ቃፊሮች ዘንድ ሄዳ፤ እጅ መንሳት፤ ባለቤቷ አቶ ሻንግ በሌሉበት፤ አሁኑኑ በፍጥነት መጥተው፤ መጻሕፍቶቹን ከቤት በመውሰድ ውለታ እንዲውሉላት ተማፀነቻቸው፡፡
መጻሕፍቱ፤ ተለቃቅመው ተወስደው ዋና ከተማ ሲደርሱ፤ ቀይ ቃፊሮቹ ባስመዘገቡት ታላቅ ስኬት፣ ከአዛዦቻቸው ሙገሳና ውዳሴ ተዥጎደጎደላቸው። ምክንያቱም፤ እስከዛሬ ከዜጎች ታዛ ወጥተው ከታዩት መጻሕፍት ሁሉ በብዛት በመብለጣቸውና ከመጻሕፍቱ ጋርም፤ አዛውንቱ እድሜ ዘመናቸውን ሙሉ ሲጠበቡባቸው የኖሩት ሁለገብ የጥናትና ምርምር ዶሴዎች፤ ውብ የፈጠራ ድርሰቶች፣ በርካታ ያለቁ የስዕል ቅቦች፣ በእንጥልጥል ያሉ ያልተቋጩ ስራዎች፣ አዳዲስ ጅምር ንድፎችና ቁጥራቸው የማይታወቅ ቅኔዎች ጥራዞችም አብረው ተጭነው ነበር፡፡ አብዮተኞቹ አደልበው ለሚመገቧቸው አሳማዎች የሦስት ቀን መኖ በመሆን፤ የተረፈውም ለምግብ ማብሰያ ማገዶነት ውሎ ባለስልጣናቱን ከቀለብ ወጪ አድኗቸዋል፡፡
አቶ ሻንግ፤ ዘመድ ጥየቃ ከሄዱበት ተመልሰው የሆነውን ነገር ሁሉ በሰሙ ጊዜ፤ ራሳቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው መሬት ላይ ተዘረሩ፡፡ ልጆቻቸው፤ አፋፍሰው ተሸክመው፤ ወደ ቤት አስገቧቸው፡፡ አልጋ ላይ አስተኟቸውና ሀኪም በቶሎ መጥቶ እንዲያያቸው አደረጉ፡፡
ከሳምንት በኋላ፤ አዛውንቱ ከህመማቸው ቢያገግሙም፣ በዕድሜያቸው ላይ አስር አመታት ያህል የጨመሩ መስለው፤ እርጅት ብለው ታዩ፡፡ ቀኑን ሙሉ፤ ተጠራርገው የተወሰዱት መጻሕፍቶቻቸው ለዘመናት በክብር የኖሩበትን፤ እራቁቱን የቀረ ባዶ መደርደሪያ፤ ትክ! ብለው እያዩ፤ በፅናት ሲሰበስቧቸው የኖሩት የመጻሕፍት አይነት ድቅን ሲሉባቸው፤ ተንሰቅስቀው ያነባሉ፡፡
እነዚያ እፁብ ድንቅ መጻሕፍት የተደራጁት፤ ከቅድመ አያታቸው ዘመን ጀምሮ እስከ ሦስት ተከታታይ ትውልድ የቤተሰቦቻቸው ውርስ ነበሩ። እርሳቸውም በተራቸው እየገዙ፤ ላባቸውን ጠብ አድርገው፣ ደም ተፍተው ሰርተው ከሚያገኟት ገቢ ላይ እየቆጠቡና ላደረባቸው የንባብ ፍቅር ተሸንፈው፤ ጦም እያደሩም ጭምር ነበር ያጠራቀሟቸው፡፡
‹‹እኮ መፅሀፎቼ ምን በደሉ? አምላኬ ሆይ!›› እያሉ ያለቅሳሉ፡፡ ግን ደግሞ፤ በድብቅ እንጂ፤ ፊት ለፊት ሀዘንን መግለፅ በአብዮቱ የተከለከለ ነው! ቤትን ዘግቶ መነፋረቅ ይቻላል!!! ነው ህጉ፡፡ ባለቤታቸው፤ ሀዘናቸውን እንዲረሱ የምትችለውን ሁሉ ብትጥርም ከንቱ ድካም ሆነባት፡፡ አዛውንቱ፤ ለአምሳያ ታሪክ ትዝብታቸው እንዲህ ሲሉ ስንኝ ቋጥሩ...
ሺህ መጻሕፍት ተቃጥለው
ጢሱ ነክቶ ሰማይ፤
ንጉሠ ነገስት ቺን
አይን ኖረው እሚያይ፡፡
(ንጉሠ ነገስት ቺን፤ በፈላጭ ቆራጭ አገዛዙ የታወቀ፣ ከሁለት ሺህ ሁለት መቶ አመታት በፊት በነበረው የንግሥና ዘመኑ፤ የትየለሌ መጻሕፍትን በማቃጠሉና አምስት መቶ ያህል ልሂቃን ዜጎችን በመፍጀቱ የሚታወቅ ግፈኛ ንጉሥ ነበር፡፡)
ሊቀመንበር ማኦ እንዲህ ብለዋል፡-
‹‹ከእኛ ጋ ሲነፃፀር፤ ንጉሠ ነገስት ቺን ምንም ነበር፤ እኛ በቁርጠኛው አመራራችን፤ በልሂቃን ነን ባይ ዜጎቻችን ላይ የወሰድነው የማያዳግም ቆራጥ እርምጃ፤ ከእሱ መቶ እጥፍ የሚያስከነዳ ነዋ!››
እጅግ ብርቅና ውድ የሆኑ ቅርሶች ሁሉ እሳት ተማገዱ፡፡ መጻሕፍት,፣ ረቂቅ የስዕል ጥበብ ውጤቶች፤ቤተሰቦች ከጥንት በውርስ የተላለፈላቸውና ለረዥም ዘመናት በክብር የያዙዋቸው የትውልዳቸው የዘር ሀረግ መጠበቂያ መዛግብት፤ እናም አሮጊቶች ከልጃገረድነት ዕድሜያቸው ጀምሮ ከየቁምሳጥኖቻቸው አናት ላይ በልዩ ሙዳየ ሳጥን ከፍ አድርገው ሰቅለው,፣ እስከዚህ ጊዜ ድረስ በትዝታው እየታደሱ በስስት ያቆዩዋቸው፡ ለማይደገመው የሠርግ ቀናቸው የለበሷቸው ውብና ደማማቅ አልባሳት ሁሉ፡፡
የተቃዋሚ ጎራ አባላቱና ቤተሰቦቻቸው፤ ገና ለአካለ መጠን ያልደረሱ እምቦቃቅላ ልጆቻቸውን ጭምር ይዘው፤ በእሳቱ ዙሪያ እንዲሰባሰቡ፤ ከዚያም ፊት ለፊታቸው የሚንቀለቀለውን ነበልባል ከብበው፣ በደንብ ጥስቅ አድርጎ እንዲቆረቁራቸው ታስቦበት ኮረት በተነሰነሰበት ጉርብጥብጥ መሬት ላይ፤ ልብሳቸውን ወደ ባታቸው እየሰበሰቡ,፣ በሌጣው ጉልበታቸው እንዲንበረከኩ ተገደዱ፡፡
ቀይ ቃፊሮቹ፤ ከኋላቸው ዙሪያቸውን እየተሯሯጡና በቁጣ እያምባረቁባቸው፤ እጃቸው የገባውንም አፈፍ አርገው እያምቸለቸሉ ያሰቃዩዋቸዋል፡፡ ጀርባቸውን ይዠልጧቸዋል። ሴቶቹን በፀጉራቸው መሬት ለመሬት እየጎተቱና ዞማቸውን ቆዳቸው ስር ገብተው እየመደመዱ፤ በአናታቸው አመድና ትቢያ ይነሰንሱባቸዋል፡፡
በድንገት፤ አንዱ ጠብደል ቀይ ቃፊር፤ ‹‹ጩኹ!›› የሚል ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ ከዚያም እየፎከረ,፣ እየፎገራ፤ ‹‹እናንተ ጭራቅና ሰይጣኖች ናችሁ! እኛ አብዮት ነው ያቀጣጠልነው፤ የአብዮታችን ወጋገን ደግሞ፤ ነበልባሏ አራስ ልጅም ልትበላ ትችላለች! እህ ምን ታመጣላችሁ እሺ?! በሉ‚ኮ ለእነርሱ አልቅሱላቸው! ለአብዮታችን ለምንሰዋቸው ጨቅላዎች!እ?! አልቅሱኮ ነው የምለው!! በሉኮ አልቅሱ!!!›› እያለና አስሩን እየዘላበደ፡ እየደነፋ፣ እያቅራራ፤ በያዘው አንጀት የሚያሳርር ብረት አለንጋ ያለ ርህራሄ ይነርታቸው ጀመር። ከመሀከላቸው፤ ስቃዩን መቋቋም ያቃታቸው፤ ራሳቸውን መርዳት የማይችሉ አቅመ ደካሞች፤ ጉልበታቸው እየተብረከረከ ወደሚግለበለበው እሳት ወደቁ፡፡ ከመላ አካላቸው ሁሉ በፊት፤ ፀጉርና የአይን ሽፋሽፍቶቻቸው በነበልባሉ ሲንጨረጨሩ፣ ሽታው አካባቢውን ያቆንሰዋል፡፡
አንዲት ለጋ ቀምበጥ፤ በእድሜ የገፉትን የምስኪን እናትና አባቷን ሰቆቃ ማየት ከአቅሟ በላይ ሆኖባት፣ ድምጿን ከፍ አድርጋ ‹‹እኔን ግደሉኝ! ቤተሰቦቼን ተዉአቸው! እባካችሁ ልለምናችሁ?! በእነሱ ፈንታ ይኸው እኔን ግደሉኝ?!›› አለች፡፡ ግን ማንም ጉዳዬ ያላት አልነበረም፡፡ ወዲያውም ራሷን ወደ እሳቱ ወረወረች፡፡ ሙሉ ለሙሉ የወደቀችበት እሳት በቅፅበት ከፀጉርና ሽፋሽፍቷ ጀምሮ ልብሶቿን እያያያዘና እያቀጣጠለ አገነተራት፡፡ ሁለት ደጋግ ሰዎች፤ ጎትተው ወደ ዳር አወጧት፡፡ ሆኖም ግን እሳቱ መላ አካሏን ፈጅቶ በልቷታል፡፡ አንድም ያልተቃጠለ የሰውነት ክፍል አልነበራትም፡፡ በተለይ ፊቷ ክፉኛ በመጎዳቱ፤ መልኳን አይቶ ለመለየት አስቸጋሪ ነበር። ስምንቱ የእጅ ጣቶቿም ተጎርደው ስለወደቁ፤ በቀድሞ ቦታቸው ላይ ምልክታቸው ብቻ ቀረ፡፡
ይህቺ መከረኛ ውብ ወጣት፤ምንም በማታውቀው ጉዳይ፤ ‹‹ያለፈው ስርአት ርዝራዦች ዲቃላ!›› በሚል ነው በተቃዋሚነት የተኮነነችው፡፡ የሀኪም እርዳታ ማግኘት የሚታሰብ አልነበረምና፤ ለረዥም ጊዜ ሳትገላበጥ በአንድ ጎኗ ብቻ በተኛችበት ደንዝዛ ከረመች፡፡ ቆይቶም ዘመዶቿ፤ በእሳት ነፍሮ የተወለጫጨመ ሰውነቷን አጣጥበው ሲያበቁ፤ ባህላዊ መድኃኒት ነው ያሉትን ቅጠል ጨምቀው አሻሹላት፡፡
ሆኖም ግን፤ የደረሰባት ቃጠሎ፤ በወቅቱ ተገቢውን ህክምና ስላላገኘ፤ ፊቷ የቋጠረው ደምና መግል እያደር እያዠ፣ እያመረቀዘ፤ ፍፁም ሌላ አይነት አስፈሪ ግን ደግሞ አንጀት የሚያላውስ አሳዛኝ አይነት ገፅታ ይፈጥር ጀመር፡፡ በእቶኑ ስለት ተቆርጥመው የተጎነደሹ ውብ ጣቶቿ ተተክለውባቸው የነበሩት፤ በእሳቱ ረመጥ ነፍረው፣ አርረው የከሰሉት የእጅ መዳፎቿም፤ ፈጽሞ መንቀሳቀስ የማይችሉ፤ በድን ሆነው ቀሩ፡፡
ምንጭ - (Australian Short Stories No.58 -1997. THE FIRE Shi Pang Fan.)

ከሦስት ትውልዳቸው ጀምሮ በቅብብሎሽ የመጣውን ጥንታዊውን ዕምቅ ጥበብ ስለወረሱም፤ በጥልቅ ልቦና የተፀነሱ በርካታ የፈጠራ ስራዎችን አምጠው የወለዱ፤ ሰማየ ሰማያት የመጠቁ ረቂቅ ቅኔዎችን ስንኝ የሰደሩ… እንዲሁም ልዩ ግንዛቤ እሚሻውን የቻይናን የፊደል አፃፃፍና ትርጓሜ (ካሊግራፊ) ክህሎት ያካበቱ ‹‹አራት አይና›› ልሂቅ ናቸው፡፡ ይኸውም አፍ በእጅ የሚያሲዝ አድናቆትን የተናኘ ጉምቱ ስብዕናቸው፤ ከሚኖሩበት መንደር አልፎ በሌሎቹም አጎራባች ከተሞች ሁሉ፤ እንደ ብርቅ የሚታዩ ስመ ጥር ሰው አድርጓቸዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ዝናቸውን ያገነነው ግን ያሏቸው የመጻሕፍት ብዛት ነው፡፡

Read 3251 times Last modified on Monday, 18 November 2013 11:51