Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 26 November 2011 09:29

ዋልያዎቹ ለዋንጫ ተጠበቁ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የ2011 ታስከር ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ ትናንት በታንዛኒያ ዋና ከተማ ዳሬሰላም የተጀመረ ሲሆን ዋልያዎቹ የሚባለው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የዋንጫ ድል ያስመዘግባሉ በሚል ግምት ካገኙት ብሄራዊ ቡድኖች ተርታ ተሰለፈ፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በሻምፒዮናው በጥሩ ብቃት ለመሳተፍ ወደ ታንዛኒያ ትናንት ተጉዟል፡፡በሌላ በኩል የሴካፋ ምክር ቤት ፕሬዝዳንቱን እና ሌሎች አመራሮችን ለመምረጥ ባለፈው ሃሙስ ስብሰባ ማድረጉ ሲታወቅ በፕሬዝዳንት ምርጫው የዞኑን ምክር ቤት ላለፉት 4 ዓመታት ያገለገሉት የታንዛኒያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሊየዳጋር ቴንጋና የጅቡቲው ተወካይ ፋዱል ሁሴን ከባድ ፉክክር ሲያደርጉ ቆይተው ነበር፡፡

የጅቡቲው ተወካይ በምርጫው ቀን ከቀሩ በሃላ ሊየዳጋር ቴንጋ የሴካፋ ምክር ቤትን ለሚቀጥሉት 4 ዓመታት በፕሬዝዳንትነት መምራታቸውን እንዲቀጥሉ ከውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡ ሻምፒዮናው ትናንት በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲጀመር ብሩንዲ ከሶማሊያ እንዲሁም ኡጋንዳ ከዛንዚባር ተጋጥመዋል፡፡ የሶማሊያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከአገሪቱ የስፖርት ሚኒስትር ጋር በተፈጠረ አለመግባባት እንዲፈርስ የተደረገ ቢሆንም ብሄራዊ ቡድኑ ለሻምፒዮናው ተሳትፎ ታንዛኒያ ከገቡት የመጀመርያው ከመሆኑም በላይ የመክፈቻውን ጨዋታ ከብሩንዲ ጋር አድርጓል፡፡ በሻምፒዮናው ከሚሳተፉ 12 ብሄራዊ ቡድኖች 7ቱ ታንዛኒያ መግባታቸው ሲታወቅ ቀሪዎቹ እስከ ነገ ተጠቃለው እንደሚገቡ ተነግሯል፡፡ በሻምፒዮናው ላይ ኤርትራ በገንዘብ እጥረት ተሳትፎዋን ከሰረዘች በሃላ በምድብ ድልድሉ ለውጥ ተደርጓል፡፡ በዚህ መሰረት አስቀድሞ በወጣው ድልድል በምድብ 1 ከሩዋንዳ፤ ታንዛኒያና ጅቡቲ ጋር ተደልድላ የነበረችው ኢትዮጵያ ምድብ 3 ላይ ኤርትራን እንድተተካ ሆኗል፡፡ በአዲሱ የምድብ ድልድል መሰረት በምድብ 1 ታንዛኒያ ሩዋንዳ ናሚቢያና ጅቡቲ፤ በምድብ 2 ኡጋንዳ ብሩንዲ ዛንዚባርና ሶማሊያ እንዲሁም የሞት ምድብ በተባለው ምድብ ሶስት ሱዳን ኬንያ ማላዊና ኢትዮጵያ ተመድበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የምድቡን የመጀመርያ ጨዋታ ሰኞ ላይ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈች ብቸኛዋ የሴካፋ ተወካይ ከሆነችው ሱዳን ጋር ያደርጋል፡፡ ረቡእ ሁለተኛ ጨዋታውን ከኬንያ ጋር ያደርግና አርብ ከማላዊ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ የምድብ ትንቅንቁን ይፈፅማል፡፡በታንዛኒያው ቢራ ጠማቂ ኩባንያ ሰርንጄቲ ብሬወሪስ በ480 ሺ ዶላር ስፖንሰር በሆነው የሴካፋ ሻምፒዮና ለአሸናፊው 30ሺ ዶላር የሚሸለም ሲሆን ለሁለተኛ 20ሺ ለሶስተኛ 15ሺ ዶላር ይበረከታል፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን ሶስቱንም ጨዋታዎች በዳሬሰላም ያደርጋል፡፡

 

Read 3574 times Last modified on Saturday, 26 November 2011 09:30