Monday, 18 November 2013 10:59

የሁለት ደብዳቤዎች ወግ

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(1 Vote)

የሰው ልጅ፤ ፈጣሪ ለክቶ በሰፈረለት የህይወት ዘመኑ ውስጥ እንደየእጣ ክፍሉ ከሚያጋጥሙት እጅግ የከፋ የመከራና የፈተና አጋጣሚዎች መካከል አንዱ ስደት ነው፡፡ ስደት የሰውን ልጅ ከሰውነት ተራ ያስወጣል፡፡ ስደት የሰውን ልጅ ክቡር ስሙን ይነጥቃል፡፡ ስደት የሰውን ልጅ ከሰው ልጅነት ወደ ቁጥርነት ይለውጣል፡፡
ክቡር በሆነው የሰውነት ስማቸው ሳይሆን “ስደተኛ” በሚለው የወል ስማቸውና በየግል በተሰጣቸው ቁጥር ተለይተው የሚታወቁት ህዝቦች፣ ተወልደው ያደጉበትን፣ እትብታቸው የተቀበረበትን፣ ወግ ማዕረግ ያዩበትን ቀዬ ትተው እግራቸውን ወደተለያዩ አገራት በተለይም ወደ መካከለኛው ምስራቅ የአረብ ሀገራት ለስደት ከነቀሉበት ቀን አንስቶ ስደተኝነታቸው ፍፃሜውን እስከሚያገኝበት ጊዜ ድረስ በቃል እንዲህ ነው ተብሎ የማይነገር እንግልት፣ መከራ፣ ስቃይና ስምና ክብር የሌለውን ሞት ተሸክመውት አብረው ይኖራሉ፡፡
ወደእነዚህ የአረብ ሀገራት በህገጥ መንገድ ከሚሰደዱት ውስጥ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ስደተኞች፤ ለቤተሰቦቻቸው ከሚልኩት ዶላር በፊት ቀድሞ የሚደርሰው አስከሬናቸው የታሸገበት ሳጥን እንደሆነ በአብዛኞቻችን ዘንድ በግልጽ የታወቀ ነው፡፡
ሳኡዲ አረቢያ ወደ ሀገሯ በህገወጥ መንገድ የገቡ ስደተኞች ህጋዊ የመኖሪያና የስራ ፈቃድ እንዲያወጡ ሰጥታው የነበረው የጊዜ ገደብ ባለፈው ሳምንት ተጠናቋል፡፡ ይህን ተከትሎም የደህንነትና የፖሊስ ሃይሏ ህጋዊ የመኖሪያና የስራ ፈቃድ ባላወጡ ስደተኞች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ ትዕዛዝ ሰጥታለች፡፡ የደህንነትና የፖሊስ ሃይሏም በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት በስደተኞቹ ላይ ዙሪያ መለስ እርምጃውን መውሰድ ጀምሯል፡፡ እናም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ህገወጥ ስደተኞች ለሞት፤ ለእስርና ለከፍተኛ እንግልት ተዳርገዋል፡፡ ይህ አሳዛኝ ሁኔታ በሳኡዲ አረቢያ በስደት የሚኖሩ ልጆች ያሏቸውን ወላጆች ከወዲያ ወዲህ አራውጧቸዋል፡፡ ከእነዚህ ወላጆች መካከል በስደት ሳኡዲ አረቢያ ውስጥ የሚኖሩ ሴት ልጆች ያሏቸው ፊሊፒኒያዊትና ኢትዮጵያዊት እናት ከዚህ የሚከተለውን ደብዳቤአቸውን ጽፈው ወደ ሳኡዲ አረቢያ ልከዋል - ባለፈው ሳምንት ፡፡
ደብዳቤ አንድ
ለማቲልዳ ባንባንግ
ንጉስ አልሳውድ ጐዳና
ሪያድ ሳኡዲ አረቢያ
የተወደድሽው ልጅ ማቲልዳ፤ ይህን ደብዳቤ በሰላም እንደምታገኘው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በዚህ ደብዳቤ አማካኝነት አባትሽ ባንባንግ፣ ወንድሞችሽ ፖኩንና ሳሚ፣ ባጠቃላይ መላው ቤተሰቡ የናፍቆት ሰላምታቸውን ያቀርቡልሻል፡፡
ባለፈው ሳምንት ስልክ ደውለሽ በተነጋገርንበት ጊዜ እንደነገርኩሽ ሁሉ እኛ በጣም ደህና ነን፡፡ ሰሞኑን ሀገራችንን ከመታው ክፉ ሳይክሎን በክርስቶስና በእናቱ በድንገል ማርያም እርዳታ ተርፈናል፡፡ ሳይክሎኑ ባቅራቢያችን የሚገኙ ከተሞችን ጨርሶ ያልነበሩ ያህል አውድሞ የእኛን ከተማ ግን ሳይነካት ያለፈው በስላሴዎች ተአምር የተነሳ ነው፡፡
ልጄ ማቲልዳ - በሳኡዲ አረቢያ ስደተኞችን በተመለከተ የተነሳውን ግርግርና ፖሊሶች እየወሰዱት ያለውን እርምጃ በቴሌቪዥን እንዳየነው፣ በእውነቱ ስላንቺ ደህንነት ስጋት ገብቶን ነበር፡፡ በተለይ ሁለቱ ወንድሞችሽ ከቴሌቪዥኑ ላይ ተጣብቀው አልላቀቅ ብለው ነበር፡፡ ዜናው በሚቀርብበት በአንዱ ሰአት ላይ የሚያዩሽ ይመስላቸው ነበር፡፡ እነሱንም ሆነ እኔንና አባትሽን ገብቶን ከነበረው ከፍ ያለ ስጋት የገላገለን፣ ሁኔታው በተፈጠረ በማግስቱ የማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የውጭ ሀገር የፊሊፒንስ ሠራተኞች ጉዳይ ማስተባበሪያ ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች የሰጡን ደህንነትሽን የሚያረጋግጥ መረጃ ነው፡፡ ወደ ሳኡዲ አረቢያ የላከሽ የውጭ ሀገር ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲውም ያለሽበትን ሁኔታና ደህንነትሽን የሚገልጽ ደብዳቤ በሶስተኛው ቀን ማለዳ ላይ ለአባትሽ እንዲደርሰው አድርጓል፡፡
መንግስት የፊሊፒንስ የቤት ሰራተኞች ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገራት በተለይ ደግሞ ወደ ሳኡዲ አረቢያ እንዳይሄዱ ካቻምና ከከለከለ ወዲህ፣ ቀደም ብላችሁ የሄዳችሁትን የእናንተን ወሬ ካለፈው ጊዜ በተሻለ እየተከታተለ መናገር ጀምሯል፡፡ የሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲውም የመንግስትን ቅጣት እየፈራም ቢሆን በሁለት ወር ግፋ ካለም በሶስት ወር አንዴ ስልክ እየደወለ ስለ ደህንነትሽ ያገኘውን ወሬ ያቀብለናል፡፡
ውዷ ማቲልዳ:- ባለፈው ጊዜ በፃፍሽልን ደብዳቤዎችሽም ሆነ በስልክ በተነጋገርን ቁጥር ስራ አግኝተሽ ወደ ሳኡዲ ከመሄድሽ በፊት በማሰልጠኛ ተቋሙ ውስጥ ገብተሽ ተገቢውን የሙያ ስልጠና መውሰድሽ፣ ዘመናዊ የቤት ውስጥ መገልገያ መሳሪያዎችን በሚገባና ያለ አንዳች ችግር መጠቀም እንዳስቻለሽ እንዲሁም የአረቦችን፣ የእስያንና የአውሮፓውያንን ምግቦች እንደ ፈለግሽው ከሽነሸ ማዘጋጀትሽን ስለነገርሽን እኔም ሆነ አባትሽ በጣም ደስተኞች ነን፡፡ ከዚህ በፊት አስረሽ የነበረችው ሴትዮና የባሏ እናት ባንቺ ተደስተው እንዲያ ይወዱሽ የነበረውም በዚህ ትምህርት ባገኘሽው ሙያ የተነሳ ነበር፡፡
ልጄ ማቲልዳ:- ከሙያ ስልጠናው ጐን ለጐን ለአጭር ጊዜ የወሰድሽውን የአረብኛ ቋንቋ ትምህርት በሚገባ በማዳበር ከአሰሪዎችሽ ጋር ሆነ ከተቀረው የአገሬው ዜጋ ጋር ያለችግር መግባባት በመቻልሽ በእውነቱ ልትደነቂ ይገባል፡፡ እሰየው! እንኳንም ወንድሞችሽ እንዳሾፉብሽ አልቀረሽ!
ማቲልዳዬ :- የባለፈውን ስራሽን ለቀሽ በተሻለ ደመወዝ አሁን ካለሽበት ቤት መቀጠርሽ በእውነቱ መልካም ነገር ነው፡፡ በወሰድሽው እርምጃ በተለይ አባትሽ፣ ወንድሞችሽን ልክ እንዳንቺ አስተዋይ መሆን እንዳለባቸው ጧትና ማታ ሲጨቀጭቃቸው ነበር፡፡
የሆኖ ሆኖ ግን መቸም ምስጋና ላንቺ ይሁንና፤ ታናናሽ ወንድሞችሽ ትምህርታቸውን በርትተው በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡ አባትሽም በከተማችን ከሚገኘው የህብረት ስራ ባንክ ትንሽ ገንዘብ ተበድሮ የተወሰኑ ማሽኖችን በመግዛት፣ የእንጨት ስራ ወርክሾፑን በመጠኑም ቢሆን ማስፋፋት ችሏል። ስራውም ቢሆን ምንም አይልም፡፡ ስላሴዎች ይመስገኑ፡፡
የተወደድሽው ማቲልዳ:- በየወሩ የምትልኪው ገንዘብ፣ ለወንድሞችሽ ትምህርት ቤት ከሚውለው አንድ መቶ ሰባት ዶላር በቀር፣ ቀሪው ስድስት መቶ ዶላር ወደ ሳኡዲ ከመሄድሽ በፊት አባትሽ በስምሽ በከፈተልሽ የባንክ አካውንት ውስጥ እየተቀመጠልሽ ይገኛል፡፡ የአሁኑን የስራ ኮንትራትሽን ከዘጠኝ ወር በኋላ ስትጨርሺ፣ በምንም አይነት ምክንያት ሳታመነቺ ወደ ሀገርሽና ወደ እኔ እናትሽ ቤት ተመለሽ። እኛም እኮ በጣም እጅግ በጣም ናፍቀንሻል፤ የአባትሽ ናፍቆትማ ይቅር አይነሳ! ነጋ ጠባ አንዴ ልጅ በህልሜ ስትታየኝ አደረች ይላል፡፡ አንዴ ደግሞ ልጄ ቀኑን ሙሉ በአይኔ ውል ስትለኝ ዋለች ይላል። የናፍቆቱ ነገር ምኑ ቅጡ፡፡ ብቻ ልጄ ኮንትራትሽን እንደጨረስሽ፣ ሳትውይ ሳታድሪ በቶሎ ተመለሺ፡፡ በሳኡዲ አረቢያ ስራ ይዘሽ ከሄድሽ ጊዜ ጀምሮ እየላክሽ የተጠራቀመልሽ ገንዘብ፣ ከልጅነትሽ ጀምሮ ትመኝው የነበረውን የዲያንግና ባትቾየ (በፊሊፒንስ ተወዳጅ የሆነ የአሳ ምግብና ሾርባ) ሬስቶራንት ለመክፈት በቂ ይመስለኛል፡፡ ምናልባት ገንዘቡ የሚያንስሽ ከሆነም አባትሽ ከቁጠባ ማህበራቸው ሊበደርልሽ እንደሚችል ደጋግሞ ነግሮኛል፡፡
ማቲልዳዬ:- በይ እንግዲህ ደህና ሁኝ፡፡ እስክንገናኝ ድረስ የክርስቶስ እናት አትለይሽ፡፡ አክስትሽ ሚሸሊንና ባላ ጀኦል እንዲሁም አጐትሽ ሮዌ ሰላምታቸውን ያቀርቡልሻል፡፡
ደብዳቤ ሁለት
ይድረስ ለሃዋ ሰኢድ ሙሄ
ጅዳ - ሳኡዲ አረቢያ
ውድ ልጄ ሀዋ:- ከተለያየንበት ቀንና ሰአት አንስቶ ለጤናሽ እንደምን ትሆኛለሽ? እኔ አልሀምዱላሂ መቸም ከሞት ተርፌአለሁ፡፡ ሰሞኑን አገሩ በሞላ የሳኡዲ መንግስት አበሻውን ሙላ እየገደለ፣ እየደበደበና እያነቀ ዘብጥያ እየከተተ ነው እያለ ሞጥሮ ሲያወራ ስሰማ ጊዜ፣ አንቺን አንቆ እንዳይመልስሽ ብዬ ደንግጬ፣ ትንሽ ከሰሞኑ ሻል ብሎልኝ የነበረው በሽታ ከነጓዙ ጠቅልሎ አገረሸብኝ፡፡ አሁንማ እንጃልኝ እንዲያው እተርፍ ብለሽ ነው?
ውድ ልጄ ሀዋ:- የሳኡዲ መንግስት በዛ ሁላ የእኔ ቢጤ አበሻ ላይ እንዲህ ጨክኖ የተነሳው ምን ሆኖ ነው በይሳ? እንዲያው ምኑ ጂኒ ቢጠጋው ነው አንቺየ! ግን እንዲያው ለመሆኑ ያንቺሳ ነገር እንዴት ነው? ቦሊሶቹ አግኝተው አነቁሽ ወይስ እንዴት ነሽሳ! እኔማ ይህንን የሳኡዲ መንግስት በአበሻው ሁላ ተነሳ መባልን ስሰማ፣ እንዲያው አምርሬ አዝኘ ሳለቅስ ባጀሁ፡፡ ያለቀስኩትም የሚያስለቅሰኝም ሌላ ሳይሆን እድሌ ነው፡፡ ከድፍን ቤት ሙሉ ልጅ አንድ እንኳ ጧሪ ደጋፊ አለማውጣቴ ያስለቅሰኛል፡፡ የቀዬው ሰው ሁላ ቤት ሙሉ ልጅ ከመቀፍቀፍ በቀር ሌላ ሙያ የሌላት እያለ ነጋ ጠባ ያነውረኛል፡፡ የመሀመድ ኑር ይማም ሚስት እኮ ባቅሟ ከባሏ አፋታ ባህሬን የሰደደቻት ትልቋ ልጇ፣ በዚያው ሰሞን የሰደደችላትን ዘመን አመጣሽ ቀሚስ እየበተነች ስትወነንብኝ ትውላለች፡፡
ውድ ልጄ ሀዋ፤ ያን ጊዜ በየመን ከነራህመቶ ልጆች ጋር እንድትሄጂ ብዬ ለደላላው ያን ሁላ ገንዘብ አባትሽ የከፈለው፣ ጥማድ በሬውን ሽጦ እንደሆነ መቸም አታጭው፡፡ ከሄድሽ ጀምሮ ታዲያ እንደ ሰፈር ጓደኞችሽ እንኳን ዶላሩን ልትልኪ ቀርቶ መጋቢያሽንም እንዲህ ነው ሳትይ ስትቀሪ፣ አባትሽ ቅስሙ ተሰብሮ ወጀጅ ያረገው ጀምሮአል፡፡ እንኳን እንዳንቺ ያለው ልባም ይቅርና ስንቱ ገልቱ አልፎለት፣ ለናት አባቱ ዶላሩን እየላከ፣ አንቀባሮ በሚያሰልፍበት አገር፣ ያንቺ ነገር እንዲህ ሆኖ መቅረቱ ወላሂ በጣም ያሳዝናል፡፡ ለነገሩ ጠላቴ አንቺ ሳትሆኝ እድሌ ነው፡፡
ያንቺ ታላቅ ጓደኞቿን ተከትላ ስንት በረሃና ባህር አቋርጣ፣ ቤሩት ገብታ እየሰራችም ምንም እያለችም የምታገኛትን ለራሷ ሳትል ለእኛ እየላከች አንድ ሁለት አመት ደህና ቀጥ አድርጋ ይዛን ባጅታ ነበር፡፡ አባትሽም አምሮበት ደህና እንዲያው ሰው መስሎ ከርሞ ነበር፡፡ ግናስ የኔው ጠማማ እድል ተከትሏት፣ አሠሪ እመቤቷ በፈላ ውሃ ፊቷን ጠብሳ፣ መለመላዋን ስታባርራት ያገሩ ፖሊስም ለቀም አድርጐ ይዞ ጠርዞ ልኳት፣ የነፈረ አካሏን ይዛ ባዶ እጇን እያጨበጨበች መጣች፣ በኋላም “ሁለት አመት ሙሉ የላኩትን ገንዘብ ውለዱ” ብላ ቁም ስቅላችን ስታሳየን ኖራ፣ ዛሬ እዚህ ነኝ እንኳ ሳትለን የትሜናዋ ሄዳለች፡፡
አንቺዬ:- እንዲያው እኛ ቤት የገባው ሰይጣን ከቶ እንዴት ያለው ይሆን? የዚያች ያክስትሽ የአሻ መቁረጫ ልጇ ዘይነብ ብዙ ሳትከላተም፣ ባሬን ገባች ተብሎ ደስ ሲለነ ገና ሁለት ወር እንኳ ሳይሞላት፣ ያሰማችው ምጣድ በጀ አልል ብሏት፣ እሳቱ መላ አካላቷን ፈጅቷት ተብሎ፣ ሬሳዋ በሰንዱቅ ተጭኖ ለዚያች ከንቱ እናቷ መጣላት፡፡ የአባትሽ የወንድም ልጅ አሚናም እመቤቲቱ ሰይጣን ተጋብቷት፣ ከፎቅ ላይ ወርውራት ተብሎ ተጠርዛ መጥታ፣ እጅ እግሯ አይሰማ፣ ወገቧ አይላወስ፣ በድን ደንጊያ ሆና አለችው።
የሆነ ሆኖ ሃዋ:- እኔም ሆነ አባትሽ ተስፋችንን የጣልነው ባንቺ ላይ ነው፡፡ የሳኡዲው ቦሊስ አንቆ ጠርዞ እንዳይልክሽ፣ ቦሊሱ ባለበት መንደር እንጦለጦላለሁ ብለሽ ወት ወት እንዳትይ አደራ! እኔ እንደምታይኝ በበሽታ ተደይኜ ነው ያለሁ፡፡ አባትሽም ቢሆን እንዲያውም ነፍሱ ስላልወጣች እንጂ በጠና ተይዞ ነው ያለው፡፡
ወንድሞችሽና እህትቶችሽም ቢሆኑ ለትምህርት ቤት የሚከፍልላቸው ጠፍቶ፣ ይሄው የሰፈር አመድ ሲያቦሉ ይውላሉ፡፡ አያትሽ አያ ሙሄም በራብ የተወጋ ጐኑ እንዲያው አንድ ቀን እንኳ ቀና ሳይል፣ በባዶ ቤት እየተቆራመደ ይኖራል። እንዲያው አንደዜ እንኳ እጅሽን ሳትዘረጊለት ድፍት ብሎ ቢቀር ኋላ ይቆጭሻል፡፡
እና አሁንም የሆነ እንደሆነ ተጠርዞ ከሚመጣው አንድ አገር አበሻ የኛ አገር ልጅ፣ ተኛ ወገን የሆነውን ፈልጊና ዶላሩን ላኪልነ፡፡ አደራ በሰማይ አደራ በምድር በምድር! ኋላ እንዲችው ተቆራምደን “አዬ የልጅ ያለህ” እንዳልን፣ እኔም ሆነ አባትሽ ወንድምና እህቶችሽን ባዶ ቤት በትነን ብንሞት ይቆጭሻል፡፡
ያኔ አባቴ አባቴ ብትይ፣ እናቴ እናቴ እያልሽ ወዮ እላለሁ ብትይ ቀየውም፣ አድባሩም አያቆምሽ! እንግዲህ የዶላሩን ነገር አደራ! በሰማይ አደራ በምድር ብዬሻለሁ፡፡
ውድ እናትሽ፤ ሰይዳ ከድር

Read 2723 times