Monday, 18 November 2013 10:53

የዘመን ንቅሳቴን እጮኻለሁ!

Written by  ከዮሐንስ ገ/መድኀን
Rate this item
(1 Vote)

                             ሰውዬው ጢማቸውን ማሳደግና ዘወትር ማለዳ ተነስተው እርጐ መጐንጨት ያዘወትራሉ፡፡ ታዲያ ማለዳ ማለዳ እርጐውን ተጐንጭተውና አጣጥመው እንደጨረሱ አፋቸውን ሲጉመጠመጡ፣ ከላይኛው የከንፈራቸው ጢም ውስጥ ሰርገው የሚቀሩትን የእርጐ ፍንጣቂዎች ይረሷቸዋል፡፡ ከአፍንጫቸው ሥራ የተረሱት እነዚያ የእርጐ ፍንጣቂዎች መዋል ማደር ሲጀምሩ ጠረናቸው እየተለወጠ የሚፈጥሩት ሽታ ጤና ነሳቸው፡፡ አንድ ቀን ማለዳ ላይ ባለቤታቸውን፡- 
“እዚህ ቤት የሞተ ዐይጥ አለ እንዴ?”
“ከመቼ ወዲህ አንቱዬ?”
“ታዲያ የሚሸተኝ ምንድን ነው? … የለ … የለም እዚህ ቤት የሞተ ዐይጥ አለ! ያውም የከረመ! … በይ የቤቱን ዕቃ በሙሉ እያወጣሽ ቤቱን አፅጂው!” ቀጭን ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ፡፡
“ካሉ ደግ አፀደዋለሁ”
“በይ አሁኑኑ ጀምሪ! እስተዚያው እኔም ዘወር ዘወር ብዬ ልምጣ!” ሰውየው ምላሽ ሳይጠብቁ ከዘራቸውን አንስተው ይወጣሉ፡፡ ነገር ግን ሰውዬው በየሄዱበት ቦታ ሁሉ ያ መጥፎ ጠረን ይከተላቸው ጀመር፡፡ እዚያ ቢሄዱ እዚህ ቢመጡም ያው ሆነባቸው፤ ወደቤታቸው እያዘገሙ ሳለ ሰውዬው እንዲህ አሉ፡- “ዛሬስ የኔ ቤት ብቻ አይደለም፤ አገሩ ሁሉ ገምቷል!”
                                                      * * *
የአንድ ዘመን ማሕበረሰብ ባህል፣ አስተሳሰብና የሚከተለው የፖለቲካ ሥርዓት በየግለሰቡ መልካም ስብዕና ላይ አሉታዊ ጫና ያሳድራል፡፡ በእያንዳንዱ ግለሰብ መልካም ስብዕና ላይ የየዘመኑ ሥርዓት የሚፈጥረው ዕድፍ እየተለመደ፣ ከእያንዳንዱ ማንነት ጋር ሲዋሀድ ያኔ ብክለቱ ይጀምራል፡፡ ይህን በተመለከተ የፖለቲካ ሳይንሱ ምሁር ካርል ማርክስ ሲናገር፡-
“አንድን ሥርዓት ለመጣል ሃያና ሰላሳ ዓመታት መታገል ያስፈልግ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከሥርዓቱ ዕድፍ ለመላቀቅ መቶና ከዚያም በላይ ዓመታት መታገል ያስፈልጋል፡፡”
ትናንት ከትናንት በስቲያና ዛሬ በኛ ማሕበረሰብ ውስጥ የተቀያየሩ የፖለቲካ ሥርዓቶች ያሸከሙን ዕድፍ ጠባሳው ሳይሽር ቁስሉ እያመረቀዘ አላራምድ ብሎናል፡፡ ትናንት ያረፈብን ዱላ ዛሬ ቀና ብለን እንዳንራመድ አስጐንብሶናል፡፡ የኛ ማሕበረሰብ የፖለቲካ ሥርዓቶች ያሸከሙን ዕዳ ምን ይመስላል?
የትናንት በስቲያው
በአንድ አጋጣሚ ከአንድ ወጣት ጋር ተገናኝተን ስናወጋ ያጫወተኝን ላካፍላችሁ ወደድሁ፡፡ የግል ሕይወቱን በተመለከተ እንዲህ ነበር ያወጋኝ፡፡
“አራት ወንድሞቼና ሁለት እህቶቼን ጨምሮ ከእናታችን ጋር ስምንት ሆነን ቀበሌ በሰጠን አንድ ክፍል ቤት ውስጥ እንኖራለን፡፡ አባታችን ወታደር ነበር፡፡ በሰሜኑ ጦር ግንባር ለረዥም ጊዜ ቆይቷል። ኢህአዴግ አዲስ አበባ ከገባ ጊዜ ጀምሮ ብዙዎች ሲመለሱ የኛም አባት ይመለስ ይሆናል እያልን በተስፋ በር በሩን እያየን ስንጠብቅ ከረምን፡፡ እስከ አሁን ድረስ በሕይወት ይኑር ወይ ይሙት የምናውቀው ነገር የለም፡፡ እማዬ እንጀራና አምባሻ እየሸጠች ነው የምታስተዳድረን፡፡ ያገኘነውን ተካፍለን ከጠፋም ቆሎ ቆርጥመን እናድራለን፡፡ እኔና ታናሽ እህቴ 12ኛ ክፍል ጨርሰናል፡፡ ውጤት ግን አልመጣልንም፡፡ የሁሉም ታላቅ እኔ በመሆኔ የእማዬን ድካም እያየሁ በዝምታ መቀመጥ አልቻልኩም፡፡ እንደምንም ተሯሩጬ ታናሽ እህቴን ኬክ ቤት አስቀጠርኳት፡፡”
“አንተስ?” አልኩት ንግግሩን አቋርጬ
“ሥራ ለማግኘት ብዙ ጣርኩ፡፡ አልተሳካልኝም ነበር፡፡ የኋላ ኋላ በአንድ የእንጨት ሥራ ድርጅት ውስጥ ሥራ አገኘሁ፡፡ ተመስገን ብዬ ሥራ ጀመርኩ። ከሶስት ወር በኋላ ግን ድርጅቱ ተዘጋ፡፡”
“ለምን?”
“የድርጅቱ ባለቤት ከሰርኩ አለ”
“ከዚያስ ሌላ ቦታ አልሞከርክም?”
“ለብዙ ጊዜ ሥራዬ ሥራ መፈለግ ብቻ ሆነ። ነገር ግን አልቻልኩም፡፡ አንድ ቀን ቁጭ ብዬ ሳሰላስል በአካባቢዬ የማያቸው የጉራጌ ብሔረሰብ ተወላጆች ለሥራ ያላቸው ታታሪነት ታሰበኝ፡፡ ሥራ ሳይንቁ ሊስትሮ ሆነው ይጀምሩና ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሱቅ ከፍተው ታገኛቸዋለህ፡፡ እኔስ ለምን በሊስትሮነት አልጀምርም? ብዬ አሰብኩኝ፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ራሴን ብችል እማዬን አገዝኳት ማለት ነው፡፡ ታናሽ እህቴ ኬክ ቤት ትሠራለች ብዬሃለሁ፡፡”
“እኔ ራሴን ከቻልኩ ለእማዬ ሁለት ሆድ ተቀነሰላት ማለት ነው”
በአነጋገሩ ፈገግ አልኩ፡፡
“የሊስትሮነት ሥራዬን ለመጀመር ግን የሠፈሬን ሰዎችና የጓደኞቼን ሽሙጥ በመፍራት ብዙ አቅማማሁ፡፡ የኋላ ኋላ ስለ እማዬ ሳስብ ቶሎ ለመጀመር ወሰንኩ”
“ስለ እማዬ ሳስብ ነው ያልከኝ?”
“አዎና! እማዬ ድንገት አንድ ነገር ብትሆን፣ ብትታመምብኝ ወይም አያድርገውና ብትሞትብኝ ፀፀቱን አልችለውም ብዬ ጫማ መስፋት ስለምችል፣ ከሊስትሮ ሥራ ጋር ደርቤ እዚያው ከሠፈራችን ጀመርኩ፡፡”
“እንዴት ነው ተሳካልህ?” አልኩት ጥንካሬውን እያደነቅሁ
“ምን ይሳካል ብለህ … በሁለተኛው ቀን ተቋረጠ።”
“ለምን?”
“ሥራውን እንደጀመርኩ በሁለተኛው ቀን እማዬ እየተንደረደረች መጣችና፡-
“አንተ የማትረባ! ብለህ ብለህ ተከብሬ በኖርኩበት ሠፈር ልታዋርደኝ ተነሳህ? … ይኸው ነው የቀረህ! … ምንም ብደኸይ … ምንም ጊዜ ቢጥለኝ … እ … የነማን ዘር መሰልኩህ! አንተ ዘር አሰዳቢ! … የፅጌ ልጅ ሊስትሮ ሆነ ብሎ አገር እንዲስቅብኝ ነው? … ቆሜ ነው ሞቼ!”
“እማዬ እንደዚያን ዕለት በንዴት ስትቃጠል አይቻት አላውቅም፡፡ የሊስትሮ ሳጥኔን ሰባበረቺውና አምባሻ ጋገረችበት እልሃለሁ! … አይ እማዬ በዚያች የሊስትሮ ሳጥን ስባሪ ስንት አምባሻ ጋግራበት ይሆን?” አለኝ ፈገግ ብሎ፡፡ ፈገግታውን አልተጋራሁትም፡፡
የትናንትናውስ?
ያኔ … የሰለሞናዊው ዘውድ ሥርዓት ማክተሚያ ሲቃረብ፣ ዳር እስከዳር የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ አመፅና የተማሪዎች የለውጥ ትግል ተጠቅሞ ወታደራዊው ደርግ በትረ-ሙሴውን ጨበጠ። ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት እስከሚቋቋም በጊዜያዊነት የሥልጣን መንበር ላይ የወጣው ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት፤ “የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ የሕዝብ ክፍል የለም” በሚል ሰበብ የጣመውን የሥልጣኝ መንበር ቀስ በቀስ እያመቻቸ መሠረቱን ማጠናከር ያዘ፤ “ኢትዮጵያ ትቅደም” በሚል መፈክር መሪነት፡፡ “ያለምንም ደም እንከኗ ይውደም በቆራጥ ልጆቿ ኢትዮጵያ ትቅደም” በሚል ዜማ፣ የለውጥ ፈላጊውን ስሜት ሊያረግብ ጣረ፡፡ በወቅቱ የነበረው ወጣት ትውልድ፣ በራሱ የሚተማመን ነበርና ይህን ወታደራዊ ብልጠት በዝምታ ሊያልፈው አልፈቀደም፡፡ አመፃቸውን ቀጠሉ፡፡ “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት አሁኑኑ!” እያሉ ጮኹ። ወታደራዊው መንግሥት እየጣፈጠው የመጣውን ሥልጣን ላለመነጠቅ ፈራ፡፡
መሠረታዊው ማንነቱና ሥልጣን ያለ መነጠቅ ፍላጐቱ ፍራቻን አስከትሎ ጭካኔን ወለደ፡፡ “ያለ ምንም ደም” የሚለው ዜማ ቀረና ስልሳዎቹን የአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት
“የማትረባ ፍየል ዘጠኝ ትወልዳለች
ልጆቿም ያልቃሉ እሷም ትሞታለች፡፡”
አስተጋባ፡፡
የያኔዎቹ ወጣቶች ለማስፈራሪያው ዜማ አልተበገሩም፡፡ ወታደራዊው መንግሥት ከሥልጣን እንዲወርድ በአቋማቸው ፀንተው ጮኹ። ወታደራዊው መንግሥት ያነገበውን መሣሪያ በማውረድ አፈ ሙዙን በወጣቶቹ ላይ ደገነ፡፡ ፍርሃቱ ጭካኔን ወለደ፡፡
ወጣቶቹም ወኔያቸውን አንግበው ከተደገነባቸው አፈ ሙዝ ፊት ለፊት በጽናት ቆሙ፡፡ በእኒያ ወጣቶች ደረት ላይ የተወደረው አፈ ሙዝ በጭካኔ ተሳበ፡፡ ጥይት በወጣቶቹ ላይ በጭካኔ ተርከፈከፈ፡፡ የምድረ ኢትዮጵያ ወጣት ታደነ፡፡ እሥር ቤቶች ተጣበቡ። የየቀበሌ ጽ/ቤቶች ወደ እሥር ቤት ተለወጡ፡፡ ግርፋትና ስቃይ በረከተ፡፡ የብዙ ሺህ ወጣቶች ሬሣ በየአውራ ጐዳናው፣ በአደባባዩና በየጢሻው እንደ ውሻ ሬሣ ተጣለ፡፡
በነዚያ ወጣቶች ላይ ፍርሃት በወለደው ጭካኔ የተዘራው ጥይት ለቀሩት ኢትዮጵያውያን ልጓም ሆነ፡፡ ጥርጣሬና ፍርሃት ነገሰ፡፡ በራስ መተማመን ጠፋ፡፡ ጠቢባን በቡርሻቸውም ሆነ በብዕራቸው ፈሩ፡፡ ፍርሃታቸው ማስመሰላቸውን እንደ ብልጠት ይቆጥሩት ዘንድ አስመረጣቸው፡፡ የመረጡትንም ተካኑበት፡፡
ይህን ጊዜ አዕምሮ ዛገ፡፡ እጆች ዛሉ፡፡ ጣቶችም ዶለዶሙ፡፡ ዐይኖች ወደ ውስጥ ማየታቸውን አቆሙ፡፡ ጆሮ ብቻ ዳባ አልለብስም አለ፡፡ ብዕር ማስመሰሉን አነባ…ጥበብ ወገቧ እስኪለመጥ ድረስ በሀዘን አቀረቀረች፡፡ እውነት ወዴት ነሽ? ውበት የት አለሽ? ከቶም ያለ የለም፡፡ ታዳጊዎች፤ ታላላቆቻቸው በብዕራቸውም በቡርሻቸውም በስብዕናቸውም ሲያስመስሉ አስተዋሉ፡፡ እያስተዋሉም ወደወጣትነት ተሸጋገሩ፡፡ አኢወማ ዘምሩ ሲላቸው ዘመሩ፡፡ መፈክር አሰሙ ሲላቸው በመሽቀዳደም ግራ እጃቸውን እያወጡ ፎከሩ፡፡
“ከመምሕሩ ደቀ መዝሙሩ” እንዲሉ ከታላላቆቻው እጥፍ ፈሪዎች፣ እጥፍ አስመሳዮች ሆኑ፡፡ ብሔራዊ ውትድርና መጣ፡፡ ሽሽት ተከተለ። ቤት ዘግቶ መደበቅ፤ ከአሁን አሁን ተያዝኩ የሚል ሥጋት አየለ፡፡ የእያንዳንዱ ወጣት ልብ ሥጋት እያባነነው፣ የፍርሃት ከበሮውን መደለቅ ተያያዘ። ታላላቆቻቸውን ጉራማይሌ ተነቀሱ፡፡ ከፈሩት ታላላቆቻቸው መቶ እጥፍ እየፈሩ፣ ከኒያ ፀንተው ከወደቁት ታላላቆቻቸው የወረሷት ትንሽዬ በራስ መተማመን ከፍርሃት ትንፋሻቸው ጋር እየተነፈሷት ብን ብላ ትጠፋባቸው ጀመር፡፡
ይህን ጊዜ ከፊሉ በአኢወማ ዙሪያ ማስመሰሉን ተካነበት፡፡ ከፊሉም ስደትን መረጠ፡፡ ጥቂቱም ሕይወቱን በዘዴ ለማክረም ውትድርና ተቀጠረ። በለስ ያልቀናው ብሔራዊ ውትድርና ዘመተ፡፡ ብዙዎቹ የሞት ገፈት ቀማሾች ሆኑ፡፡ የሞተውም ሞተ፡፡ የተረፈውም ሙት ደመ ነብሱ እየመራው፣ ከፍርሃቱና ከማስመሰሉ ጋር መወዛወዙን ቀጠለ፡፡
ሥፍራው ቢለያይም እኔና እናንተ ከእነሱ ጋር አለን፤ አሊያም የእነሱ ልጆች ነን፡፡
ትናንት የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች አመራርና አባላት የነበሩ ዛሬ ባሕር ማዶ ሆነው በሚያሳትሟቸው መፃሕፍት የሚያስነብቡን ትረካ፣ የትዝታ ድንኳን ጥለው ትናንትናቸውን እያለቀሱ፣ የኛን ዛሬ ሀዘንተኛ አድርገዋት፣ ነጠላዋን ካዘቀዘቀች’ኮ ከራረመች፡፡
ሁሉም “ትክክል ነበርኩ” እያለ በትዝታ የተወልን ሽንፈት፣ ትሩፋቱ ለቅሶ ብቻ ሆነ፡፡ የሀገራችን የትግል ታሪክ መቋጫው ምባ ብቻ ነው፤ በልቅሶ የተሞሸረ ሽንፈት፡፡ አቤት የዚች ምድር ለቅሶ! አቤት የዚች ምድር እምባ መብዛቱ! ዛሬም ድህነት ቅነሳ፣ ሙስና፣ የአመለካከት ለውጥ፣ ረሃብና ድርቅ በየመድረኩ ላይ አጀንዳ እየቀያየረ በባዶ አንጀታችን እናለቅሳለን። ያላየው ድርቅ ያልጐበኘው እምባችንን ብቻ ነው። ለቅሶ በኛ መንደር፣ ልቅሶ በኛ ቀዬ፣ ለቅሶ በኛ አደባባይ በሽበሽ ነው? የሰቀቀን ለቅሶ የሚያበቃበት ቀን እየናፈቀን በናፍቆት መኖሩ ተስፋ ሆነን እንዴ ጐበዝ? እንባችንን የምናብስበት የተስፋ መሀረብ ከቶ ከየት ይገኝ ይሆን?
አጋጣሚ ከሚያገጣጥመኝ የዘመኔ ዘመነኞች መሃል ጥቂት የማይባሉት “ነፋስ ሲነፍስ ጐንበስ ብሎ ማሳለፍን ከሣር ተማር!” የሚለውን ምሳሌያዊ አነጋገር አዘውትረው ሲናገሩ ሰማሁና፤
“ለምን?” ስላቸው
“መስለህ መኖር ካልቻልክ አከተመልህ ለመኖር ትንሽ ብልጥ መሆን አለብህ፤ ምስማሩን አሊያም መዶሻውን መሆን ያንተ ምርጫ ነው፤ ሲያዙህ እሺ አሜን እያልክ እንደሰው አምሮብህ ከሰው ሳታንስ መኖር ከቻልክ ሌላ ምን ትፈልጋለህ? ከጊዜው ጋር ተስማምቶ መኖር ብልጠትም ዕውቀትም ነው” አሉኝ፡፡
ምሳሌያዊ አነጋገር ከፍላጐት ጋር ተጣረሰ። አድርባይነት እንደ ብልጠትም ዕውቀትም ተቆጥሮ ብዙዎችን “ዐዋቂ” አሰኘ፡፡ ብዙዎች አድር ባይነታቸውን እንደ ብልጠት እየቆጠሩ፣ ህሊናቸው ላይ ተኝተው በብልጠታቸው ተኮፈሱ፡፡ አስመሳይነታቸው የኩራታቸው ምንጭ ሆነ፡፡
አንድ ወጣት ገጣሚ የቋጠረው ስንኝ ነብሴን ማርኮታል :-
“ሰውማ ሙዝ ሆና ተልጦ ቢበላ”
ውስጡ በተጣለ ላዩ በተበላ
ሰው እንደ ሙዝ ተልጦ ባይበላም የኔ ዘመን ዘመነኞች ግን አበላሉን ተክነውበታል! በአስመሳይ ክህሎቱ አንዱ አንደኛውን እንደ ሙዝ ሳይልጠው እርስ በርስ ይበላላ ይዟል፡፡ ያውም የሚጣለውንና የሚበላውን ሳይለይ፣ መብላቱን ወይም መበላቱን አሊያም መጣሉን ሳያውቅ ደመ ነብሱ እየመራው፣ በሆዱ ለሆዱ ስለሆዱ ብቻ መኖር መረጠ፡፡ የመረጠውንም እንደ ብልጠት ቆጠረው፡፡
ሁሉም ለሆዱ በሆዱ ሲጋፋ ህሊናውን ረሳ። የተጣለበትን ኃላፊነት ወደ ጐን በመተው ሰርቆና ዘርፎ አሊያም ዕምነት አጉድሎ ሀብታም ለመሆን መጣደፍ እንደ ጀብድ ተቆጥሮ ያስከብር ጀመር። ህሊናውን ሲረሳ ሰው የመሆኑን ክብር ከእግሮቹ ሥር ጣለና ራሱን በራሱ አቀለለ፤ ሰው ማለት ለሰው እንደገለባ ቀለለ፡፡ የሆዱን ሲያሳድድ አንዱ ላንዱ አልታኘከው እያለ እንደ አንጆ ሥጋ እርስ በርስ መጣጣል ተለመደ፡፡ ህሊና ረከሰ፤ ሥጋ ተወደደ፡፡
አንድ ኪሎ ሥጋ መቶ ስልሳ፤ መቶ ሰማኒያ ይሸጣል፤ ይቸበቸባል!
ሰው ዋጋ አላወጣም፡፡ ሰሞኑን የወጣና ሲኒማ አምፒየር በመታየት ላይ ያለው “ድሮና ዘንድሮ” የሚለው ፊልም “ሎጐ” እንዲህ ይላል:- “ከማትረባ ነብስ ድፍን መቶ ብር ሲጠፋ ያንገበግባል” ለመሆኑ የሰው ዋጋው ስንት ነው?
ልብ በሉ! እኔ በእናንተ ውስጥ አለሁ፡፡
የዘመኔ ዘመነኞች ሆይ፤ ማንነታችንን የሚያረክስና ስብዕናችንን የሚያዋረድ ዝቃጭ የሥርዓት ዕድፍ ተሸክመን እያለ…በድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቃ፣ ጉስቁልናዋ በዝቶ፣ የሰቆቃ ሲቃዋ ሰቀቀን ሆኖባት፣ ሀዘኗ ልክ አጥቶ የደም ዕምባዋን በምትናጥ ሀገረ ኢትዮጵያ፣ በዚች ምድረ ሀበሻ፣ መልካም ስብዕና ያለው ታታሪ ዜጋ ተፈጥሮ፣ ሀገራችን በዕድገቷ ሽቅብ ተመንጥቃ ለማየት መመኘት ይቻላል፤ ምኞት አይከለከልምና! ነገር ግን ይህ ምኞት “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” እንዲሉ ከግብራችን ጋር ያልተዋሀደ ከንቱ ምኞት ነው፡፡
እያንዳንዳችን ከተሸከምነው የሥርዓት ዕድፍ ራሳችንን ለማላቀቅ፣ ከራሳችን ጋር ግብግብ እንግጠም፡፡ በመጀመሪያ ከየራሳችን ማንነት ጋር መታገል እንጀምር፡፡ ይህን ስናደርግ እንደ አንድ ማህበረሰብ በኛ ራስ ወዳድነት የተበከለውን የዘመናችንን አየር ለማጽዳት አንድ እርምጃ ተራመድን ማለት ነው፡፡
አጀንዳ ሳንጨርስ፣ በዐውደ ጥናት ሰበብ የሕዝብ ገንዘብ ሳይባክን፣ የአመለካከት ለውጥ እውን የሚሆንበት ጅማሮ የሚታየውም ይህን ጊዜ ነው፡፡ መራሩን መድኃኒት ስንወስድ፣ ከራስ ማንነት ጋር ትግል ስንጀምር! ነገር ግን ዛሬ በአንድ ጊዜ ከየራሳችን ማንነት ጋር ትግል ብንጀምር እያንዳንዳችን የተሸከምነው ዕድፍ ተራግፎልን በራሱ የሚተማመን ትውልድ በኛ ሕብረተሰብ መሃል ዛሬውኑ አይፈጠርልንም፡፡ ይህን የምንጠብቅ ከሆነ ተሳስተናል፡፡ እኛ ችግኝ ተካዮች እንጂ ፍሬውን ተቋዳሽ አለመሆናችንን እንመን፡፡
የዘመኔ ዘመነኞች ሆይ፤ በዘመናችን የተከሰቱ ሥርዓቶች ያሸከሙን ዕድፍ መጥፎ ጠረን የዘመናችንን አየር በክሎታል፡፡ የመልካም ስብዕና፣ በራስ የመተማመን አየር አጥሮን ቁና ቁና እየተነፈስን፣ የአመለካከት ለውጥ እያልን በሚቆራረጥ ድምጽ መቃተት ጀምረናል፡፡ የሚያሸት አፍንጫ ካለን፡፡ ከህመማችን የሚፈውሰን ፍቱን መድኃኒት በእጃችን ውስጥ እያለ በዘመናችን መንገድ ላይ ማስመሰላችንን ተንተርሰን፣ በራስ ወዳድነት ቃሬዛ ላይ እንደተኛን በለመድነው ማስመስል “የሀኪም ያለህ” እያልን ማቃሰት ይዘናል፡፡ የመድኃኒቱ ፈዋሽነት አሊያም አጠቃቀሙ የጠፋብን አሳዛኝ የዘመን በሽተኞች! ከፊሎቻችን የመድኃኒቱ ፈዋሽነትና አወሳሰዱ ሳይጠፋብን፣ የመድኃኒቱን መራርነት ፈርተን ነው በማስመሰል “የሃኪም ያለህ” እያልን አማራጭ ፍለጋ ዘመናችንን የምናቃስተው፡፡ ዞሮ ዞሮ መድኃኒት የሚያስፈልገን በሽተኞች መሆናችን አያጠያይቅም፡፡
በየዕለቱ የሚወሰድና ለዓመታት የማያቋርጥ መራር መድኃኒት፣ ከማንም በላይ ከምንወደው ከራሳችን ማንነት ጋር መታገል ነው፡፡ ከእሬት የመረረ ቢሆንም ከጽኑ በሽታችን የሚፈውሰን መድኃኒት እሱ ነው፡፡
የዛሬው ቁስላችንን ሳይሆን የትናንት ጠባሳችንን በትዝታ እየታመምን፣ ዛሬን ዛሬን የምናለቅስበት እኛ፤ ከዛሬው ህመማችን ባሻገር የመልካምነታችን ንጋት ተስፋው እየታየን፣ በዘመናችን የምንደሰተው መቼ ይሆን?
የትውልድ ቀጣይነታችን ወንዙ በዘመን ሸለቆ ውስጥ ስለሌለ ሳይሆን፣ በራስ ወዳድነት ለቅሶ የዕምባ ጅረት እየሰራ ቁልቁል የመፍሰሱ ማክተሚያ መቼ ይሆን? የዘመናችን ውቅያኖስ በራስ ወዳድነታችን ሞገድ ተናውጧልና ባህሩ ፀጥ እንዲል ከዘመናችን መርከብ ላይ የምትወረውረው ዮናስ የት ነህ?
የዘመኔ ዘመነኞች ሆይ፤ ምጤ እናንተ ናችሁና… እናንተን እጮኻለሁ!
በእኔ ውስጥ ስላላችሁ እናንተን እጮኻለሁ!
ሰው መሆናችንን እያለምኩ እኛን እጮኻለሁ!
ጆሮዎቻችሁ ወደ ድምጼ አቅጣጫ ተቀስረው ጩኸቴን እስክታዳምጡ ድረስ እጮኻለሁ!
ሀዘኔን የሚያስረሳ፣ ሕልሜን ዕውን አድርጐ ተስፋዬን የሚያለመልም ድምጽ እስክሰማ ድረስ የዘመን ንቅሣቴን እጮኻለሁ!
“ሕይወት ከባድ ነች፤ የበጐች መንጋ የውሾች ግትልትል አይደለችም፡፡
እያንዳንዱ ውሻ ግን እንደየድምፁ ይጮኻል”
ማክሲም ጐርኪይ

Read 1558 times