Monday, 18 November 2013 10:41

እንደገና ፊደል እንደገና ---- የሞክሼ ፊደላት ጉዳይ!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

              “እንደገና ፊደል እንደገና” የሚያሰኘን እያረፈ የሚነሳው የፊደል ማሻሻል ጥያቄ ጉዳይ ነው። ጥያቄውን የሚያነሱት ምሑራን ምክንያታቸው ምንድነው? በተለይ ጐልቶ የሚነሳው የሞክሼ ፊደላት ጉዳይ ነው፤ እነዚህንስ መነካካቱ ያስፈለጋቸው ለምንድነው የሚለውን በቅድሚያ መመልከቱ ተገቢ ይመስላል፡፡ ከሞክሼዎቹ የተወሰኑትን የማስወገዱ እርምጃ የሚያስከትለውን ጉዳት/ጉድለት ደግሞ ከዚያ በኋላ እንመለከተዋለን፡፡ 
አሁን እስኪ ሞክሼ ፊደላቱን ለማጉደል ምን ምን ዓይነት ምክንያቶች እንደሚሰሙ እያነሳን እንመልከት-
አንድ ድምጽ፣ አንድ ምልክት
ትክክል፡፡ አንድ ምልክት አንድን ድምጽ ወይም ክፍለ ቃል፣ አንድ ክፍለ ቃልም በአንድ ምልክት መወከል አለበት፡፡ ማንም ሊገምት እንደሚችለው፣ እነዚህ ምልክቶችም እያንዳንዳቸው አንድን ድምጽ ለመወከል የተሠሩ ናቸው፡፡ ብዙዎች አንዱን ድምጽ ሊወክሉ አልተሠሩም፡፡ በእርግጥም አልነበሩም፡፡
እንዲህ የሆነው ከጊዜ በኋላ ነው፡፡ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ከአባ ሰላማ ወዲህ ነው ይላሉ፡፡ ግን አይደለም፡፡ ከዚያ ወዲህ፡፡ ቢያንስ በጽሕፈት ላይ ሲቀያየሩ አይታዩም፡፡ ድምፃቸው አንድ ኾነ ተብሎ በጽሕፈትም የአንዱን ለአንዱ ማድረግ ይታይ ነበረ፡፡ ከዚህም ሌላ በአባ ሰላማ ጊዜ ኅርሙኅ ተጨምሯል። እነዚያ አንድ እየኾኑ ይሕን ይጨምራሉ አይባልም። ደሞም የዚህኛውም ድምጽ አንድ ሆኖ ተገኝቷልና በአባ ሰላማ ጊዜ ሲጨመርም አንድ ድምጽ ይዞ ተጨመረ ማለትን ይመስላል፡፡
በሚገባ የታወቀው ይህ የድምጽ አንድነት የታየው፣ በመጽሐፈ ጥበብ እንደተገለፀው፣ ከልብነ ድንግል ዘመን ወዲህ ነው፡፡ የአምስት መቶ ዘመን ዕድሜ አለው ማለት ነው፡፡ በዚሁ መጽሐፍ የየራሳቸው ድምጽም ተመዝግቧል፡፡ ፍሬ ነገሩ ግን ድምፃቸው በግዴለሽነት ተመሳሰለ ብሎ እንዲወገዱ መጠየቅ አለበት ወይ? የሚለው ይሆናል፡፡ ይህ ምልክቶቹን ድምጽን ለመወከል የተሠሩ በማድረግ፣ ሥነ ልሣናዊ ዕቃዎች ብቻ በማድረግ፣ ስንፍናን እና ጉድለትን በጉድለት መተካትና ማረም፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ምልክቶቹ ያላቸውን ሌሎች አገልግሎቶችና ውክልናዎች እንዳሉ መጣል መሆኑን ካለማየት የሚመጣ ጥያቄ ነው፡፡ በአጭሩ፣ የሰነፍ፣ የደካማና የታካች አቋራጭ መንገድ ነው፡፡
የፊደላት ብዛት
የፊደላት ብዛት ጥያቄ የሚነሣው ይበልጡን በአጠቃላይ ፊደሉን ከመነካካት ጥያቄ ጋር ነው። ከሞክሼ ፊደላት አንጻር አይደለም፡፡ ምናልባት “ፊደሉም ብዙ ምልክቶች ያሉት ነውና ሞክሼዎቹ ሲቀነሱ ያነንም ጥያቄ ይመልስልናል” በሚል ግንዛቤ እንደ አንድ ነጥብ ይነሳ ይሆናል፡፡ ከዚህ ውጭ ፊደሎቹ የበዙት አንዱን ድምጽ የሚወክሉ ከአንድ በላይ የሆኑ ፊደላት ስላሉ ነው የሚል የለም፡፡
እዚህ ላይ ግን ጠቅላላ በፊደል ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችንም ለመመልከት ያህል አንስተነዋል፡፡
የፊደል ብዛት ጥያቄ በአማርኛም ሆነ በግዕዝ የሚጠየቀው ፊደላቱን ካለመለየት የተነሣ ነው። ፊደላት የገበታ እና የርባታ ተብለው ይለያሉ። የየትኛውም ቋንቋ ፊደል ምን ያህል እንደሆነ ሲጠየቅ የሚነገረውም የገበታው ፊደል ብዛት ነው። የኢትዮጵያው ፊደል በዝቷል ሲባል ግን በቁጥር የሚነገረው የገበታው ከርባታው ሳይለይ ነው፡፡ ለምሣሌ፣ የአማርኛውን ብንወስድ ጠቅላላ ብዛቱ ወደ ሦስት መቶ የሚጠጋ ተደርጐ ይነገራል፡፡ ይህም:-
እያንዳንዱ የገበታ ፊደል በ7 ተባዝቶ - 238
ዲቃሎቹ (4x5) = = 20
ፍንጽቆቹ = 21
ጠቅላላ 279 ይሆናሉ፡፡
እንዲህ በመሆኑ በዝቷል ነው የሚሉት። በዝተዋል ተብለው መቆጠር የነበረባቸው ግን እንዲህ አልነበረም፡፡ ለየትኛውም ባለ ጽሕፈት ቋንቋ የፊደላት ብዛት ሲጠየቅ ይህን ያህል ነው የሚባለው የገበታው ፊደል ብቻ ነው፡፡ እንግሊዝኛ 26 ፊደል አለው፤ ግሪክ 28 አለው፡፡
ዓረብ 29 አለው፤ የሩስያ 33 ፊደል የሚባለው የገበታ ፊደሉ ብቻ ተቆጥሮ ነው፡፡ የርባታ ፊደሎቻቸውን/ምልክቶቻቸውን/ እንደ አንድ እየቆጠርን እንጠቁም ቢባል፣ እንደ እንግሊዝኛ ያለው ለአማርኛ ከተቆጠረውም በእጥፍና ከዚያ በላይ የሆነ ብዛት ይኖረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ያለው የርባታ ሥርዓት በነ ዳንኤልስ “አቡጊዳ” የተባለው ዓይነት ሆኖ፣ በመሠረታዊው ፊደል ላይ የተለያዩ ጭማሪዎች በማድረግ አንድ ምልክት እየተደረገ የሚሠራ በመኾኑ እነዚያንም ደርቦ በመቁጠር ቁጥሩን ማብዛቱ ተገቢ አይደለም። መሠረታዊዎቹ ስንት ናቸው ብሎ ነው መቁጠር፡፡ በዚህ መሠረት ለግዕዝ 26 ፊደላት፣ ለአማርኛ ደግሞ 34 ፊደላት ብቻ ይኖሯቸዋል፡፡
እንደዚያም ቢኾን የሞክሼ ፊደላቱ ቢቀነሱ ያን ያህል ወደ 300 የተጠጉ ናቸው ካሏቸው ውስጥ ምን ያህሉን ነው የሚቀንሱላቸው?... በአጠቃላይ፣ ከሞክሼ ፊደላቱም አኳያም ሆነ ከሌላ፣ የፊደል ብዛት ጥያቄው ተገቢ ጥያቄ አይኾንም፡፡ ፊደላቱም ብዙ አይደሉም፡፡
የቴክኖሎጂ ውጤት ለኾኑ መጻፊያዎች ቸገረ፡-
ይህ ጥያቄ አስቀድሞ “ታይፕ ራይተር” በነበረበት ወቅት፣ በተለይ መጀመሪያ ላይ እንደ አንድ ችግር ተነስቶ ነበር፡፡ በዚህ ፊደሉን የመነካካት፣ እንዲያውም የመለወጥ ጥያቄ እስከ ማንሳት ድረስ ያሳሰቡት፣ በአስፋው ዳምጤ “ጐምቱ አብዮተኞች” ተብለው የተጠሩ እነ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ አንስተውት ነበር፡፡ ይህንን መነሻ አድርጐ የፊደል ነካኪዎችን ታሪክ የጠቃቀሰ የዶ/ር መርሻ አለኸኝ ጥናታዊ ወረቀት፣ ታይፕ ራይተሩ ራሱ ለፊደል እንዲመች ኾነና ፊደሉ ከመቀየር እንደተረፈ ጠቁሟል፡፡ አሁን ደግሞ እንደ አዲስ ለኮምፒውተሩ እንዲመች የሚል ሐሳብ ነው የሚነሳው፡፡ ለኮምፒውተሩ ያልተመቹ ፊደላት ሳይኖሩ ይህን ጥያቄ ለምን እንደሚያነሱት ለማንም አይገባም፡፡ ደግሞም የፊደላቱ ድምፅ አንድ መኾን በቴክኖሎጂው ላይ የሚያመጣው የተለየ ችግር ምን ሊኾን እንደሚችልም አይገባንም። በማንኛውም ቢኾን ስለቴክኖሎጂ ተብሎ ያለው ነገር ይቀነስ ማለት ደግሞ በጭራሽ ተገቢነት አይኖረውም፡፡ ቴክኖሎጂው ለእነዚያ ተብሎ ይሠራል እንጂ፣ እነዚያ ለቴክኖሎጂው አይሠሩም። ለእንግሊዝኛው ወይም ለላቴኑ ፊደላት እንዲኾኑ ተበጁ እንጂ ለቴክኖሎጂው ሲባል እንግሊዝኛው፣ ላቲኑ - ሌላውም በጭራሽ አልተነካም፡፡ ቴክኖሎጂ ያለውን በሚመጥንና በሚያካትት መጠን ይሠራል እንጂ ያለው ነገር ለቴክኖሎጂው ሲባል መሠረቱን እንዲለቅ አይደረግም፡፡ ስለዚህ ጥያቄውን የማይረባና ተገቢ ያልኾነ አድርገን እንጥለዋለን፡፡
የሥነ ጽሑፍ ዕድገት ጥያቄ፡-
“የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ” የማለትም ያህል ይሆናል፡፡ ከፊደላቱ የተወሰኑትን አጉድሎ የየትኛውም ቋንቋ ሥነ ጽሑፍ አልተመነደገም። በሞክሼ ፊደላት ሰበብ ይህ የስነ ጽሑፍ ዕድገት ይጠቀስ እንደኾነ አፍን ሞልቶ መናገር ባይቻልም፣ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ፣ ዘንድሮም የነዚህን የሞክሼ ፊደላትን ነገር የሚያነሳሱት ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ፣ በአንድ የመጽሔት ጽሑፋቸው ላይ ፊደላቱ ከገበታው መገኘታቸውን በማማረር፣ “የድሮን ነገር ለመጠበቅ ወግ ሲባል የዛሬው ዘመኑ እንዲጋረድብን /እንዲጨልምብን” መደረግ እንደሌለበት በሚከብድ ኃይለ ቃል የጻፉትን በማሰብ፣ የእነዚህ ፊደላት መኖር እንዲያ ያለ ጽልመት ውስጥ እንደሚጨምረን የታሰበው ምናልባት ከዚህ የሥነ ጽሑፍ ዕድገት ጋር ታስቦ ይኾን እላለሁ፡፡
ይህ የስነ ጽሑፍ ዕድገት ጥያቄ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት ተቋም አስቀድሞ እንደ አንድ ነጥብ ሲጠቀስ እናስታውሳለን፡፡ ለሞክሼዎቹ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በፊደላቱ ላይ ለሚወሰድ እርምጃ የተጠቀሰ ነበር፡፡
የስነ ጽሑፍ ዕድገት ጥያቄ ፊደልን በማጉደልና በመለወጥ ረገድ ከሚነሣ ይልቅ እንዳሉ ቢቀመጡ ከሚናገረው ወገን ቢጠቀስ የበለጠ በተመቸ ነበር። ፊደልን በመነካካት (በመቀየር፣ በማጉደል …) ስነ ጽሑፍ እንዴትም ኾኖ እንደማይበለጽግ ሲታሰብ፣ ጥያቄው ጩኸትን የመቀማት ያህል ኾኖ ይታሰባል። ይልቅስ ዛሬ ድምፃቸው አንድ ኾነ ተብሎ እንዳሻ በመጻፍ የሚታየውን ጉድለት ለማስቀረት፣ የነዚያን አገባብ ለይቶ ዐውቆ፣ ማሳወቅና መጠቀም እንጂ፣ የነዚህ መኖርስ ስነ ጽሑፍን ሊበድለው አይችልም።
ለማጠቃለል፣ በሞክሼ ፊደላቱ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ያሉት ሰበቦች እነዚህን የመሰሉ ሲኾኑ፣ አንዳቸውም ግን ሚዛንን ሊያነሱ ቀርቶ እንደ ምክንያት እንኳ ሊቆጠሩ አቅም ያላቸው አይደሉም። ይልቅስ በተቃራኒው፣ “ማሻሻል” በምትል መልካም ቃል የሚታሰበው የመቀየር፣ የማጉደልና ሌላም እርምጃ ቢፈጸም የሚደርሰው ጥፋትና ጉድለት ብሶ እንደሚገኝ ማስተዋል ይገባል፡፡

Read 2551 times