Monday, 18 November 2013 10:37

የሳዑዲ የኃይል እርምጃ ያስከተለው ቀውስ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

               ዘንድሮ ብቻ ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሄዱ ኢትዮጵያውያን ብዛት ከ160ሺ በላይ ናቸው፡፡ የሳኡዲ አረቢያ መንግስት በአገሪቱ ያሉ ህገወጥ ስደተኞች ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ እንዲያወጡ ያስቀመጠው ቀነ ገደብ የሰባት ወራት እድሜ ነበረው፡፡ ቀነ ገደቡ ባለፈው ሳምንት እሁድ መጠናቀቁን ተከትሎ በኋላ የአገሪቱ ፀጥታ ሃይሎች ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ህገወጥ ያሏቸውን የተለያዩ አገራት ዜጐችን በማሳደድ በማቆያ ካምፕ ውስጥ እየሰበሰቧቸው ይገኛል፡፡ 
ይሄንን ሰዶ ማሳደድ በመቃወም በሳኡዲ የተለያዩ ከተሞች በተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ አራት ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል፡፡ ከዋና ከተማዋ ሪያድ በስተደቡብ በምትገኘውና በርካታ ስደተኞች በሚኖሩባት ማኑፋሃ በተለይ ኢትዮጵያውያን አመፅ የተቀላቀለበት ከፍተኛ ተቃውሞ እንዳደረጉ ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡ ስደተኞች ለተቃውሞ ሰልፍ ገጀራና የተለያዩ መሳሪያዎችን ይዘው የወጡ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ተሽከርካሪዎችንም አጋይተዋል፡፡ ይሄን ተከትሎም የፀጥታ ኃይሎች እርምጃ መባባሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተለያዩ ቦታዎች ከተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች ጋር በተያያዘ 60 ያህል የሳዑዲ ዜጎች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ከ100 በላይ ስደተኞች ቆስለዋል ተብሏል፡፡
እስካሁን 23ሺ ያህል ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ለአገሪቱ መንግሥት እጃቸውን የሰጡ ሲሆን 10ሺህ የሚደርሱ ህገወጥ ስደተኞች ከፀጥታ ኃይሎች አደን ለመሰወር ሲሉ ስራቸውን አቁመው በተለያዩ ስፍራዎች እንደተሸሸጉ ተነግሯል፡፡
የሳኡዲ ፖሊስ፤ ህገወጥ ስደተኞች ይበዙባቸዋል የተባሉ የሸቀጣሸቀጥ ሱቆች፣ የግንባታ ሳይቶች፣ ምግብ ቤቶች እና የንግድ ማዕከሎችን በመክበብ አሰሳውን አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ በቅርቡ ደግሞ የቤት ለቤት አሰሳ እንደሚጀምር ታውቋል፡፡ የሳዑዲ ዜጎች በ99 የስልክ ቁጥር በመደወል ህገወጥ ስደተኞችን እንዲጠቁሙም ጥሪ ቀርቧል፡፡
ባለፉት ሰባት ወራት በሳዑዲ የነበሩ ከ1 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ አገራት ህገወይ ስደተኞች ወደየአገራቸው የተላኩ ሲሆን ዳግም ወደ ሳዑዲ እንዳይመለሱም እገዳ ተጥሎባቸዋል፡፡ ከ4 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ስደተኞች ደግሞ የሳዑዲ መንግስት የሚሰጠውን የመኖርያ ፈቃድ በማውጣት፤ ህጋዊ የስራ ፈቃድ እና ውል ይዘው ኑሯቸውን ቀጥለዋል፡፡
የማሳደድ ዘመቻው ለምን?
ሳዑዲ አረቢያ ከ28 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ሲሆን 9 ሚሊዮን የሚሆኑት የተለያዩ አገራት ስደተኞች ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከልም ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ያህሉ ህገወጥ እንደሆኑ ይገመታል፡፡
ህገወጥ ስደተኞችን ከአገር የማባረሩ እርምጃ የተጠነሰሰው የስደተኞች ቁጥር መጨመር የሳኡዲ ዜጐችን ለስራ አጥነት ዳርጓል፣ የሥራ ተነሳሽነትንም አዳክሟል በሚል ቢሆንም ሳዑዲ ከራሷ ዜጐች ውጭ 1 ሚሊዮን ተጨማሪ የሰው ሃይል እንደሚያስፈልጋት መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በህገወጥ ስደተኞች ላይ የሚደረገው ዘመቻ እንዲጠናከር የሚፈልጉት የሳኡዲ ህግ አውጭ አካላት፤ ስደተኞችን ከማሳደድ ባሻገርም በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ የሳዑዲ ዜጎች ላይም ጥብቅ እርምጃ እንዲወሰድ እየመከሩ ነው ተብሏል፡፡
ከሳዑዲ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ አብዛኞቹ ህገወጥ ስደተኞች በዝሙት እና በመጠጥ ንግድ፣ በዝርፊያ እና ሌሎች የወንጀል ተግባራት ላይ የተሰማሩ ሲሆን ይሄም ሳዑዲን ለከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ እንዲሁም ለባህልና ሃይማኖት ብረዛ ሊዳርጋት ይችላል የሚል ስጋት በንጉሳውያን ቤተሰቡና በመንግሥት ዘንድ እንደተፈጠረ ታውቋል፡፡
ሳዑዲን ጨምሮ በመካከለኛው ምስራቅ አገራት፣ በስደተኛ ሰራተኞች ላይ የሚደርሰው በደልና ስቃይ ከየትኛውም የዓለም ክፍል የከፋ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ስደተኞች ላይ ፆታዊ ጥቃቶች እና ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይፈፀሙባቸዋል፡፡ ለስራቸው ተገቢውን ክፍያ እንደማያገኙና በቀን መስራት ከሚገባቸው ሰዓት እጥፍ እንደሚሰሩም ይታወቃል፡፡ በሳምንት ከ108 ሰዓታት በላይ የሚሰሩ ስደተኞች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከሃይማኖት ጋር በተያያዘም ለከፍተኛ እንግልት የሚዳረጉ ጥቂት አይደሉም ይባላል፡፡
ተቀማጭነቱን በአውስትራሊያ ያደረገው “ዎክ ፍሪ ፋውንዴሽን” የተባለ ተቋም ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ “ዘመናዊ ባርነት” በሚል በ162 የዓለም አገራት ላይ ባካሄደው ጥናት፣ ከ38 ቢሊዮን በላይ ህዝቦች ለህገ ወጥ ዝውውር፣ ለአስገዳጅ ስራዎችና፣ ለጉልበት ብዝበዛ መጋለጣቸውን ይፋ አድርጓል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚገመቱት በመካከለኛው ምስራቅ በከፋ ባርነት ውስጥ የሚገኙ ናቸው ብሏል - ተቋሙ፡፡
መሳደዱ ኢትዮጵያውያን ላይ በዝቷል
የሰዶ ማሳደድ ዘመቻው ፈተና ከእስያውያን ይልቅ በአፍሪካውያን ስደተኞች ላይ የበዛ ሆኗል። በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያውያን አበሳቸውን እየበሉ ነው፡፡ የሩቅ ምስራቅ አገራት፡- ፊሊፒንስ፤ ስሪላንካና ኢንዶኔዥያ ዜጎችም መሰቃየታቸው አልቀረም - እንደ ኢትዮጵያውያኑ ባይሆንም፡፡ መሳደዱ በአፍሪካውያን ላይ ያየለው አብዛኞቹ በህገወጥ መንገድ ሳዑዲ የገቡ በመሆናቸው እንደሆነም ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በ13 የተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ተበትነው የሚገኙ ሲሆን፤ በሳዑዲ፣ ኩዌት፣ ባህሬን፣ ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ፣ ኳታርና የመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ይሆናሉ። ወደ መካከለኛው ምስራቅ ለስራ ከሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ውስጥ 40 በመቶ ያህሉ ህገወጥ ሲሆኑ በየዓመቱ ከ6ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በህገወጥነት ተጠርዘው ወደ አገራቸው እንደሚላኩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ሳዑዲዎችም ተቸግረዋል
በአገሪቱ በሚኖሩ ህገወጥ ስደተኞች ላይ በተከፈተው የማደንና የማሳደድ ዘመቻ፣ የሳዑዲ ዜጐች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችም ተስተጓጉለዋል፡፡ ሱቆችና ምግብ ቤቶች እንዲሁም መዝናኛዎች በሠራተኞች እጦት እንደተቸገሩና የተዘጉም እንዳሉ ታውቋል። ትልልቅ የገበያ ማዕከላት ተዘግተዋል፤ በርካታ የግንባታ ስራዎችም እየተጓተቱ ነው፡፡ “አረቢያን ኒውስ” የተባለ ጋዜጣ እንደዘገበው፤ የሰዶ ማሳደድ ዘመቻው ሳምንት እንኳን ሳይሞላው በየቅጥር ግቢያቸው ያለልክ በተከመረ ቆሻሻ የተማረሩ ብዙ ሺ ትምህርት ቤቶች ቅሬታቸውን እያሰሙ ነው፡፡
በሳዑዲ ሴቶች መኪና ማሽከርከር አይፈቀድላቸውም፡፡ በሾፌርነት ተቀጥረው ሲሰሩ የቆዩ ስደተኞች ከሳዑዲ መባረራቸውን ተከትሎ፣ በርካታ የቤተሰብ አባላት ወደ ስራ ከመሄድ የተስተጓጐሉ ሲሆን ልጆቻቸውን ወደ ተማሪ ቤት መላክና ገበያ መውጣት እንዳልቻሉም ታውቋል፡፡ በሳኡዲ ከግማሽ ሚ. በላይ የሚሆኑ ስደተኞች በሾፌርነት ተቀጥረው ይሰሩ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

Read 766 times