Saturday, 16 November 2013 14:44

የአቶ መለስ “ራዕይ” የግለሰብ አምልኮን ማጥፋት አልነበረምን!?

Written by  ፍፁም ገ/እግዚአብሔር
Rate this item
(7 votes)

“የአፍሪካ ውድቀት ሁሌም የግለሰቦች አምልኮ ነው”

ነሐሴ 15 ቀን 2004 ዓ.ም፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህልፈተ ሕይወት የተሰማበት አስደንጋጭ ቀን ነበር፡፡ በአድናቂዎቻቸውም በተቺዎቻቸውም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ከፍተኛ የሀዘን ድባብ ተፈጥሮ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አጥብቀው በሚነቅፏቸው ወይም እንደሚጠሏቸው በይፋ በሚናገሩ ዜጐች ዘንድ ሁሉ የተደበላለቀ ስሜት የፈጠረ ክስተት ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ የአቶ መለስ የጤና ሁኔታን አስመልክቶ በየጊዜው ትኩስ መረጃ የማግኘት እድል የተነፈገው ህዝብ፣ ድንገት በተነገረው ህልፈታቸው ከመጠን በላይ መረበሹ ወይም በአስደንጋጭ መንፈስ ውስጥ መግባቱ ብዙ ላይገርም ይችል ይሆናል፡፡

ሀገራዊ መልክ ያለው የሚመስለው ቀዝቃዛ የመንፈስ ህብረት ግን ወደለየለት ተስፋ መቁረጥና የእርስበርስ ግጭት ሊያመራ ይችላል እስከሚል አስደንጋጭ ሁኔታ ድረስ፣ ከፍ ያለ ስጋት መፍጠሩን የሚያናፍሱ ዜጐች ነበሩ በማለት፣ ባለፈው ወር ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በዋና ፀሐፊው በኩል በይፋ ሲወቅስም ተሰምቷል፡፡ እንደተባለው አቶ መለስ የዚች ሀገር እጣ ፈንታ ወሣኝ ብቸኛ አሳቢ፣ ተመራማሪ፣ ድህነትን ተረት አድራጊ መሪ፣ የልማታዊ ንድፈ ሃሳብ ቀማሪ፣ በተለይም ለገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የህልውናው ፈጣሪ ስለመሆናቸው በተለያዩ የመንግስት የመገናኛ ብዙሀን በየቀኑ እስከ ዶቃ ማሰሪያው ሲሞላ የነበረ ህዝብ፣ የሰውዬውን ህልፈት በድንገት ሲሰማ ባይደነብር፣ ተስፋ ባይቆርጥ ነበረ የሚገርመው፡፡

የህልውናው መሠረት የሆኑት ታላቅ መሪ ለዘላለሙ ሲለዩት፣በአስደንጋጭ የፍርሃት ቆፈን ባይቀፈደድ ነበር የሚደንቀው፡፡ ለሁሉም ሀገራዊ ችግሮቹ ብቸኛ መፍትሔ አፍላቂ የሆኑትን “መተኪያ የሌላቸው” ብልህ ሰው ድንገት ሲያጣቸው፣ መንፈሱ በሀዘን ባይሰበር ነበር የሚያሳዝነው፤ የአብዛኛው ህዝብ የመንፈስ ስብራት እውነተኛ መረጃ ከነበረ፡፡ ሁሉንም ነገር የሆኑትን መሪውን ያጣ አውራ የፖለቲካ ድርጅት ምን ቀርቶት፣ ምን ይዞ ነው ሀገር የሚመራው!? ብለው የሚጠይቁ ጥቂት አስተዋይ ዜጐች እንኳ ሊፈታተነኝ ይችላሉ ብሎ አለመጠርጠሩ ደግሞ፣ ሌላ ግርምት የሚፈጥር የሀገሪቱ መሪር ሀቅ ይመስለኛል፡፡ ቅጥ ያጣ ፕሮፖጋንዳ፣ ቅጥ ያጣ የዘመን መንፈስ ሊፈጥር እንደሚችል አስተውሎቱ ያነሰ ይመስለኛል፡፡ በለብለብ የፕሮፖጋንዳ እውቀት እንዲንሣፈፍ የሚፈለግ ዜጋ፣ በለብለብ ሆይ ሆይታ ሣይታወቅ ዚቅ ሊወርድ ይችላል፤ ያልተፈለገ የመዝቀጥ አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል፡፡

የትውልድን ነፃ የማሰብ ፈቃድና አቅም የሚያኮስስ፣ የርዕዮተ ዓለም መሣከር ሁሉ የሚፈጥር ተግባር ነው ማለት ይቻላል፡፡ በትክክለኛ አስተሳሰብ ላይ በጥናት ያልተመሠረተ የፕሮፖጋንዳ ሥራ፣ ውጤቱ ክሽፈት እንደሆነ በብሔር ፖለቲካ ተወጥራ እስከመበተን የደረሰችው የስታሊንን የቀድሞ ሀገር ሶቭየት ህብረትን ብቻ ማስታወስ ይበቃል፡፡ በሌላ በኩል ኢህአዴግ የአቶ መለስን ሃሳብና ተግባር ያለመጠን እየለጠጠ፣ሰዋዊ ግብራቸውን ወደ መልአክነት ሲለውጠው፣ “ኢህአዴግ የመላዕክት ስብስብ አይደለም፤ ስህተት አይሰራም ማለት አልችልም” ያሉትን እንኳ ለአፍታ አስታውሶ፣ ከፕሮፓጋንዳው ሊታረም ቀርቶ ሊሽኮረመም አልፈለገም፡፡

ለዚህም ነው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥትና የኢህአዴግ ወፍራም ባለሥልጣናት ሳይቀሩ፣ በተገኘው አጋጣሚ የአቶ መለስን ራዕይ አስፈፃሚ ስለመሆናቸው በተደጋጋሚ ሲናዘዙና ቃል ሲመዙ የሚታየው፡፡ በርግጥ፣ እንደ አቶ ስብሃት ነጋ ያሉት ነባር የህወሓት ታጋይ፣ “የኢህአዴግ እንጂ፣ የመለስ ራዕይ የሚባል የለም” በማለት የአሠላለፍ ለውጥ የሚያደርጉበት አጋጣሚ እንዳለ መዘንጋት አይቻልም፡፡ አቶ መለስ ለአፍታ ሕይወት ዘርተው እየሆነ ያለውን ቢያዩ ሊበሣጩ ሁሉ እንደሚችሉ የሚመሰክሩላቸው የቅርብ ወዳጆች ያሏቸው መሆኑ ይነገራል፡፡ ባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብም “መለስ የታይታ ነገር አይወድም፤ ለህዝብ ያደረገውን እንዲነገር አይፈልግም፤ ህዝብ እንጂ ግለሰብ ታሪክ አይሰራም የሚል አቋም ያለው…ለህዝብ የተሰዋ ጀግና…” በማለት ግለሰባዊ አምልኮን እንደሚቃወሙ አሥረድተዋል፡፡

የሚገርመው ግን፣ የኢህአዴግም በሉ የመንግሥት ተጠሪዎች ከአቶ መለስ አቋም ጋር እልህ የተጋቡ ይመስል፣ ሁሉንም ድርጅታዊና መንግስታዊ ሥራዎች በአቶ መለስ ስም መጥራት ወይም የእርሳቸው መታሰቢያ ማድረግ ወይም እርሳቸው አቅድውት እንደነበር መመስከር አልያም የእርሳቸው ራዕይ እንደሆነ ማስነገሩን አሁንም ቀጥለውበታል። እንደተባለው ከአቋማቸው ጋር እልህ ካልተጋቡ በቀር፣ እንዴት በአንደበታቸው እንደተናገሩት፣ በኋላም በመጽሐፍ መልክ እንደታተመ የሚታወቀውን አቋማቸውን ተመልክተው፣ እንደ አቶ ስብሃት ነጋ የፕሮፖጋንዳ ሥልቱን መቀየር ተሣናቸው? ብሎ መጠየቅ ይቻላል፡፡ የመንግስትም በሉ የኢህአዴግ ፕሮፖጋንዳን የሚያሠራጩ፣ በአቶ መለስ ስም ምለው የሚያድሩ ካድሬዎች ባይሰሙትም ወይም ባያነቡትም፣ አቶ መለስ ግን፣ “የአፍሪካ ውድቀት ሁሌም የግለሰቦች አምልኮ ነው፡፡ ስሞቻቸውም ሁሌ በመ ፊደል ዘር የሚጀምር ይመስላል፡፡ በዚህ ረገድ ሞቡቱ እና መንግሥቱ ነበሩን፡፡ መለስን ከዚህ ዝርዝር ውስጥ ማስገባት አልፈልግም” ከማለት ያገዳቸው አልነበረም፤ ሊያግዷቸውም አይችሉም፡፡ ለነገሩ አርቆ የሚያስብ የመንግስትም በሉት የድርጅቱ ብልህ ካድሬ ካለ፣ የአፍሪካ ሀገራትን ሁሉ እያጠፋ እንዳለ በማስረጃ አስደግፈው የተቃወሙት “የግለሰብ አምልኮን አሸባሪነት” ለማጥናት ይነቃ ነበረ። የግለሰቦችን ራዕይ በእውቀትና በእውነት መዝኖ ለሀገር ጥቅም ማዋል የሚሻ የበሰለ የፖለቲካ ተንታኝ ካለ ደግሞ፣ “የአፍሪካ ውድቀት ሁሌም የግለሰቦች አምልኮ ነው” ያሉት ተጠየቂያዊ ሃሳብ፣ “የአቶ መለስ ራዕይ” ብሎ ሊያስተጋባው፣ ሊያስተነትነው ይችል ነበረ፡፡ ለነገሩ አሁንም ጊዜ አለ!

Read 2539 times