Saturday, 16 November 2013 14:48

የኢቴቪ ማሣና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ

Written by  ሳምሶን ጌታቸው ተ.ሥ
Rate this item
(8 votes)

አንዳንድ ጊዜ፤ አብረውት ሊኖሩ ግድ የሚል ክፉ ዓመል ያለበትን ተቋም ወይም ግለሰብ ባሕርይውን ተረድቶ መቀበል መቻል ቢያንስ ቢያንስ በየዕለቱ ሲነጫነጩ ከመኖር ይታደግ ይሆናል፡፡ ነገር ግን፤ የዚያ ክፉ ዓመል ባለቤት ድርጊት ሕይወትን በቀጥታ የሚያጠፋ ሆኖ ሲገኝስ? አመሉ እስኪቃና በትንሹ ተራ እሰጥ-አገባ ውስጥ እየተዘፈቁ መበጣበጥ አይቀሬ ነው፡፡ አብረው አንድ ቤት ውስጥ የታሰሩት ሠው “ክፍሉን አቃጥለዋል” ብሎ ቢነሳ ዝም ማለት አይቻል ነገር! ባለፈው ማክሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2006 ዓ.ም ከምሽት ሁለት ሠዓት የኢቴቪ ዜና እወጃ ላይ አንድ ለተአማኒነቱና “የሚያውቁ ሠዎችስ ምን ይሉኝ ይሆን?” ብሎ ያልተጨነቀ ዜና ተላልፎ ነበር፡፡ ዜናው በጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ፊት አውራሪነት፣ በአርሲ ዞን ሁለት ወረዳዎች ውስጥ የተፈፀመ የእርሻ ልማት ጀብድን የሚመሰክር ነበር፡፡ ዜናው፤ የአካባቢው ነዋሪዎች መሬትን በማጠንፈፍና በመስመር በመዝራት ከዚህ ቀደም (በሀገራችን ይቅርና በምርታማው የኢቴቪ ማሣ ላይ እንኳ) ከተመዘገቡት ሁሉ እጅግ የላቀና ክብረወሰን የጨበጠ የምርት መጠን እንደሚጠበቅ የሚያትት ነበር፡፡

እንደዘገባውና ጠ/ሚኒስትሩም ደጋግመው ሲናገሩ እንደተደመጠው፤ በዞኗ ሁለት ወረዳዎች ይገኛል ካለ በኋላ፤ የሚጠበቀው የስንዴ ምርት መጠን ግን በሄክታር አንድ መቶ ሃያ ኩንታል ነው የሚል ነበር። ይሄንን የሁለት ሰዓቱን ዜና ብቻዬን ስላዳመጥኩትና ጆሮዬንም ማመን ስላቃተኝ፣ የድጋሚውን ዜና ከምሽቱ አራት ሠዓት ላይ ጠብቄ ከአንድ ሌላ እማኝ የሚሆን ሠው ጋር አብሬ አዳመጥኩት፡፡ ልክ ነው፡፡ በሄክታር አንድ መቶ ሃያ ኩንታል፤ በድጋሚ ስህተቱ ተደገመ፡፡ ወይ የቁጥርን ነገር አለማወቅ! መቼም ዜናውን፤ የለመድናቸው የኢቴቪ ጋዜጠኞችና አንድን የስንዴ ሰብል ዘለላ የፓፓዬ ዛፍ ለማሳከል የሚጥረው ካሜራቸው ሆነው፤ ዜናውን በምስል ብቻ አግዝፈውት ቢያልፉ ኖሮ እኛም ያው እንዳልሰማ ሆነን ማሳለፍ ባልከበደን ነበር፡፡

ችግሩ፤ የሀገሪቱ የመጨረሻው ከፍተኛ ባለሥልጣን በሥፍራው ተገኝተው፤ ይጠበቃል ስለተባለው የምርት መጠን የስህተቱ “አብሳሪ” ሆነው መሣተፋቸው ነው፡፡ ላለፉት አንድና ሁለት ዓመታት ያህል ስንዴ በሄክታር ስልሳ ኩንታል ተገኘ የሚለው ልፈፋ ለሙያው ቅርበት ባላቸው ሠዎች ዘንድ አልዋጥ ማለቱ አስገራሚነቱ ሳያበቃ፤ በሄክታር በአንድ ጊዜ መቶ ሃያ ኩንታል ማምረት ችለናል፤ ወደሚለው መሸጋገሩ ቅዠት ማብዛታችንን ይመሰክርብናል፡፡ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ አማካዩ የስንዴ ምርት መጠን በሄክታር ሰላሳ ኩንታል አካባቢ መሆኑ የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ ከፍተኛ የስንዴ አምራች የሚባሉ ሀገራት ምርታቸው በሄክታር ከሃምሳና ስልሳ ኩንታሎች እንደማያልፍ መረጃው በየድረ-ገፁ ቢታሰስ ይገኛል። በተመሣሣይም፤ በኢትዮጵያ እንደ ባሌ ባሉ ለስንዴ ምርት እጅግ ተስማሚ የአየር ንብረትና የቦታ አቀማመጥ ባላቸው ሥፍራዎች እንኳ፤ (ያውም ዘመናዊ የእርሻ መንገዶችን በመጠቀም የሚገኘው) ከፍተኛው አማካይ የምርት መጠን፤ በሄክታር ስልሳ አምስት /35/ ኩንታል አካባቢ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚሁ አካባቢ ያለው የምርት መጠን በገበሬ ማሳ ሲሆን መጠኑ ከጠቀስኩት አነስ ይልና፤ በአማካይ ከሃያ አምስት እስከ ሰላሳ ኩንታል በሄክታር ይሆናል።

ይኼ እውነታ ከጠ/ሚኒስትሩም ሆነ ከአማካሪ ባለሙያዎቻቸው የተሰወረ እንዳልሆነ እሙን ነው። ታዲያ ዋናው ጉዳይ ምንድነው? ጠ/ሚኒስትሩ ማስተላለፍ የፈለጉት ዋና መልዕክትና የዘገባውም ዋና ዓላማ፤ በትንሽ ማሳና በአነስተኛ ገበሬ የእርሻ ምርት ሊያድግ ያዳግተዋል፤ የሚሉ እውቀትን የተንተራሱ ተከራካሪዎችን አፍ ለማስያዝ የታለመ ነበር ዜናው፡፡ ከአንድ ወገን ጋር የተገባውን የ”እንችላለን” “የለም አትችሉም” ክርክር፤ በአፋዊ ሙግት ለመርታት ሲባል ብቻ፤ ፍፁም ከእውነታ ያፈነገጡ ውጤቶችን አስመዝግበናል ማለት… ያውም በሀገር መሪ ደረጃ ከትዝብትም በላይ ያሳዝናል፡፡

ጉዳዩ፤ የሀገሪቱን ሰዎች ከመጉዳቱና ከማሳዘኑ አልፎ፤ ለሌላ ታዛቢም አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ምክንያቱም፤ መቼም አንድ የሀገር መሪ፣ በብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ያውም የመጀመሪያ ዜና ሆኖ ንግግራቸው ሲቀርብ፣ የዓለም ዓቀፍ ሠዎችም ምን ብለው ይሆን ብለው ትርጓሜውን በጉጉት መስማታቸው የማይቀር ነው፡፡ ታዲያ እንዲህ ያለ ከእውነታና ከሳይንሳዊ መስፈርቶች ያፈነገጠ ንግግር ሲሰሙ… በሌሎች ጉዳዮች ላይ የጠ/ሚኒስትሩ ተአማኒነት መጠራጠራቸው ይቀራል? ባላንጣን ለማብሸቅ እና ጓዳናችን ሁሉ በስኬት የተሞላ ነው ብሎ ንግግርን ለማሳመር ሲባል ብቻ በሀገራዊ እቅድና ውሳኔዎች ላይ ፍፁም አሉታዊ ተፅዕኖዎችን የሚያመጡ የሀሰት ውጤቶች ተመዘገቡ ማለት ብዙ መዘዝ አለው፡፡ ይኼው በየጊዜው በየወረዳዎች “ከዕቅድ በላይ እየተመረቱ ነው” የሚባለው የምርት መጠን መንግሥት ለሚያከናውናቸው እቅዶችና ውሳኔዎች በታሳቢነት መወሰዳቸው የማይቀር ነው፡፡ ለምሣሌ ትክክለኛው የምርት መጠን ታውቆ ቢሆን ኖሮ፤ ምናልባት፤ ሀገሪቱ ተጨማሪ የስንዴ ምርት በግዢም ሆነ በእርዳታ በወቅቱ ልታስገባ ይቻላት ነበር። ነገር ግን እንደተመረተ የታመነው ወይም እንዲታመን የተወሰነው መጠን ከሀገሪቱ ፍላጎት በላይ ነው የሚል ሊሆን ይችላል፡፡

ስለዚህ በመቀጠል የስንዴ ምርትን ወደ ውጭ ሀገራት ኤክስፖርት እናደርጋለን ተብሎ ይወሰናል፡፡ ከዚያም፤ በሀገሪቱ ከፍተኛ የምርት እጥረትና የዋጋ ንረት ሲከሰት፤ የተለያዩ ሰበቦች ከመንግሥት ወገን መደመጥ ይጀምራሉ፡፡ ሀብታም ገበሬዎች ምርታቸውን መሸጥ ስላልፈለጉ ወይም ስግብግብ ነጋዴዎች ምርቱን በመጋዘናቸው ስላከማቹ… ወይም ሚሊዬነር ገበሬዎች ስንዴን በተለያየ መልክ መመገብ ስለጀመሩ …. የማያልቅ ንዝንዝ፡፡ ጉዳቱ በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ በሀገራችን በተቋም ደረጃ ብዛትም ጥራትም ያለው የተማረና የሰለጠነ የሠው ሀይል ካላቸው መ/ቤቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት ሊጠቀስ በሚችለው ግብርና ምርምር ተቋም ላይም አሉታዊ ተፅዕኖው ሊንፀባረቅ ይችላል። እንዴት? ቢባል፤ በየዓመቱ የአንድና ሁለት ኩንታል ለውጥ /ያውም/ ከተቻለ የምርት ዕድገት ለውጥ ማምጣት እጅግ ትልቅ ስኬት ሆኖ ሳለ፤ በፖለቲካዊ ውሳኔ በብዙ ልፋት የሚደረስበት የምርታማነት መጠን “ከመድረሻው ጣራ በላይ ተደርሷል” መባሉ ተነሳሽነታቸውን ያሽመደምደዋል። አሁን በገበሬ ማሳ ማግኘት የሚቻለውን ሰላሳ ኩንታል የማይሞላ ምርት፤ (በብዙ ምርምር ጥረት) ሠላሳ አምስት ኩንታል የሚያደርስ ውጤት በአንድ የግብርና ባለሙያ ቢገኝ፣ ምን ብሎ ሪፖርት ያደርጋል? ምክንያቱም፤ ገበሬው አንድ መቶ ሃያ ኩንታል የሚያመርትበት ደረጃ ቀደም ብሎ (በዜናው አማካኝነት) መድረሱን ሰምቷል፡፡

በዘመናዊ ግብርና ድርጅቶችና በመንግሥት ስር በሚገኙ እንደባሌ ግብርና መሥሪያ ቤቶች እንኳ ተመርቶ የማያውቅ ምርት (ለገበሬ ማሳ ያውም እርሻውም - ውቅያውም በበሬ፣ ምርት ስብሰባው በማጭድ፣ የግብዓት መጠኑ በበቂ ሳይሟላ!) የዓለምን የጊነስ ክብረወሰን የሚወዳደር ምርት አምርተናል ማለት፤ ጉዳዩን ለሚያውቅ ሠው ጥፋ ጥፋ የሚል ስሜት ያጭርበታል፡፡ በአመራረት የተሻለ ደረጃ የደረሱ ሀገራትን ተሞክሮ ወደ ሀገር ቤት አምጥቶ ለማስፋፋት ከመጣጣር ይልቅ የመጨረሻ ኋላ ቀር የአስተራረስ ዘዴን ይዞ መድረሻውን አልፈነዋል ማለት ምን ይሉት ፈሊጥ ይሆን?! በብዙ ሚሊዮን ብር ከውጭ ሀገራት የእርሻ መሣሪያዎችን እያስመጣ ዘመናዊ የእርሻ ድርጅቶችን የሚመራ ባለሀብት፣ እንዲህ በቀላሉ በበሬ እርሻ ከሶስትና ከአራት እጥፍ በላይ ምርት ተመርቶ ከተበለጠ ልፋቱ ሁሉ ከንቱ ነበር ማለት ነው፡፡ በየዓመቱ ምርትን አሳደግሁኝ በማለት ሥልጣንን ለማዳበርና የበላይ አለቃን ይሁንታ ለማግኘት ከየወረዳዎቹ የሚቀርቡ “የአድገናል - አምርተናል” የቁጥር ጨዋታዎች፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ቁጥር የማያውቁ ሕዝቦች እስክንመስል ድረስ በድፍረት እየተለፈፈ ይገኛል፡፡ የቀድሞ ምክትል ጠ/ሚኒስትርና ግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትር አቶ አዲሱ ለገሠ፤ ወደሥልጣን ማብቅያቸው ሰሞን… አንድ ያስተላለፉት ትዕዛዝ በዚሁ ጋዜጣ ተፅፎ ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ ጉዳዩ ምን መሰላችሁ? በወቅቱ ከተለያዩ ወረዳዎች የቀረበላቸውን “ምርት በምርት ሆነናል” የሚል ሪፖርት ካዳመጡ በኋላ፤ በጣም ተቆጥተው አንዳንዶቹ ከፍተኛ መጋነን እንዳለባቸው ስለታወቃቸው ተስተካክለው ይመለሱ ማለታቸውን አንብቤአለሁ፡፡ ባልተለመደ መልኩ የተደመጠው የሚኒስትሩ ተግሳፅ አስገርሞኝም አስደምሞኝም ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው… የገፋበት የለም እንጂ?! ምንአልባት አቶ አዲሱ፤ ድርጅታቸው ከያዘው የ“አጋኖ አምርተናል” አባዜ በማፈንገጣቸው ሂሳቸውን ውጠው ይሆናል። ማን ያውቃል?!

Read 2508 times