Saturday, 16 November 2013 14:37

የ16 አመቱ ታዳጊ በእግር ኳስ ሰበብ በእኩዮቹ መገደሉን ወላጆች ገለፁ

Written by  ማህሌት ፋሲል
Rate this item
(15 votes)

ረቡዕ ምሽት በጩቤ የተወጋው የ16 አመቱ ዳዊት መስፍን፤ በመኖሪያ ቤቱ ደጃፍ የሞተ ሲሆን፣ በእግር ኳስ ሰበብ በተከሰተ ፀብ ግድያውን ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሶስት ታዳጊዎች በፖሊስ ተይዘዋል፡፡ ዳዊት እና ተጠርጣሪዎች ከአንድ አመት በፊት በእግር ኳስ ክበብ ተጣልተው እንደነበር የሚናገሩት የሟች እናት፣ ብዙ ጊዜ ይዝቱበት ነበር ብለዋል፡፡

በዛቻ ብቻ ሳይመለሱ፣ ታላቅ ወንድሙን በጩቤ ወግተው ለመግደል ሞክረው ነበር የሚሉት እኚሁ እናት፤ የግድያ ሙከራውን ለፖሊስ አመልክተን ለጊዜው ቢታሰሩም ወዲያው ተለቀቁ በማለት ያስታውሳሉ፡፡ ረቡዕ ማታ ከሁለት ሰዓት በኋላ ስልክ ተደውሎለት ከቤት የወጣው ዳዊት፤ ሳይመለስ እንደቀረ እናቱ ገልፀው፣ ወንድሙና ጓደኛው በር ላይ ሞቶ እንዳገኙት ተናግረዋል፡፡

የ10ኛ ክፍል የምስራቅ ጐህ ትምህርት ቤት ተማሪ የነበረው ዳዊት፤ ፀብ የማይወድ ልጅ እንደነበር የሚናገሩት አባቱ አቶ መስፍን አስራት፤ ተጠርጣሪዎቹ ከዚህ በፊት ቤተክርስቲያን አግኝተውት ሊጣሉት ፈልገው ነበር ብለዋል፡፡ ሲተናኮሉት ቆይተው ረቡዕ ምሽት ገደሉት፤ በዚያው ምሽት ተይዘው ጩቤውን ለፖሊስ አሳይተዋል ብለዋል አቶ መስፍን፡፡ ፖሊስ በበኩሉ ጉዳዩን እያጣራ መሆኑን ገልጿል፡፡

Read 5836 times