Saturday, 16 November 2013 14:16

“መንግስት ጠንካራ ጋዜጦችን ዘግቶ፣ ጋዜጠኞችን እስር ቤት አጉሯል” - (አንድነት ፓርቲ)

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

በኢትዮጵያ ያለው የመንግስት ስርአት በርካታ ጋዜጠኞችን እስር ቤት አጉሯል፣ ጠንካራ የግል ጋዜጦችንም ዘግቷል ያለው አንድነት ፓርቲ፤ የሚዲያ ነፃነት እንዲረጋገጥና፣ የታሰሩ ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠየቀ፡፡ ፓርቲው ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ፤ ሰሞኑን በአዲስ አበባ በተዘጋጀው ስድስተኛው የአፍሪካ ሚዲያ መሪዎች ፎረም ላይ የተገኙ የሚዲያ ባለቤቶችና አዘጋጆች፤ በሀገሪቱ ስላለው ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ ችግር፣ ስፋትና ጥልቀት፣ ቃሊቲ ሄደው የታሰሩ ጋዜጠኞችን በማነጋገር ማረጋገጥ ይችላሉ ብሏል፡፡

ጉባኤው በኢትዮጵያ መካሄዱን እንዳልተቃወመ የጠቆመው ፓርቲው፣ በገዢዎች የሚታፈነው የአፍሪካ ሚዲያ ላይ ለውጥ ያመጣል የሚል ተስፋ ግን የለኝም ብሏል፡፡ ሚዲያውን የሚጨቁኑትና የሃሳብ ልዕልና እንዳይኖረው የሚያደርጉት አምባገነን መሪዎች መሆናቸውን በመግለፅ፡፡ “በኢትዮጵያ የግል ጋዜጦችና መፅሄቶች ተልካሻ ሰበብ እየተፈለገ ይዘጋሉ፤ ሥርዓቱን የሚተቹ ጋዜጠኞች አገር ጥለው እንዲሰደዱ ይደረጋሉ፤ ወደ እስር ቤትም ይወረወራሉ” ያለው ፓርቲው፤ በተለይ የነፃው ፕሬስ በመንግስት የተቀነባበረ ከፍተኛ ጥቃት ይፈፀምበታል ብሏል፡፡

ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ የተካሄደውን የአፍሪካ ሚዲያ መሪዎች ፎረም መጠናቀቅ ተከትሎ “በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ታስረዋል” የሚለውን የተሳታፊዎች የጋራ አቋም በመቃወም በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ሶስት የጋዜጠኞች ማህበራት በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ “አንድም ጋዜጠኛ በሙያው ምክንያት አልታሰረም፤ የፕሬስ ነፃነት ከማንኛውም የአፍሪካ አገራት በተሻለ ተከብሯል” ማለታቸው ይታወሳል፡፡

Read 1888 times