Saturday, 16 November 2013 14:04

የባለሀብቱ የአቶ ምህረተአብ ክስ የሙስና ባለመሆኑ በሌላ ችሎት እንዲታይ ተበየነ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

ከገቢዎችና ጉምሩክ የሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ በከባድ ሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ከታሰሩት ባለሀብቶች መካከል የምፋሞ ትሬዲንግ ባለቤት የአቶ ምህረተአብ አብርሃና ኩባንያቸውን ጉዳይ የመረመረው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት፤ ጉዳያቸው የሙስና ክስ ባለመሆኑ በሌላ ችሎት እንዲታይ ሲል ከትናንት በስቲያ ብይን ሰጠ፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ፤ በአቶ ምሕረተአብ አብርሃና ኩባንያቸው ምፋሞ ትሬዲንግ ኃላፊ. የተ የግ. ኩባንያ ላይ አምስት ክሶች ማቅረቡ የሚታወስ ሲሆን በጥቅሉ የክሶቹ ይዘት ኩባንያው ከ1998 እስከ 2004 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ መክፈል የነበረበትን 3.5 ሚሊዮን ብር የመንግስት ገቢ ግብር አልከፈለም፤ ስራ አስኪያጁ አቶ ምሕረተአብም ጉዳዩን ተከታትለው አላስፈፀሙም የሚል ነበር፡፡ ክሱን ተከትሎ የተከሣሽ ጠበቃ ለፍ/ቤቱ ባቀረቡት መቃወሚያ፤ ክሶቹ የሙስና አይደሉም፣ የገቢ ግብር አዋጅን የተመለከቱ ናቸው ያሉ ሲሆን አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ የሙስና ክስ ባይሆንም ከገቢዎችና ጉምሩክ በተሠጠኝ ውክልና ነው ክሱን ያቀረብኩት ብሏል፡፡

በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት ከትናንት በስቲያ የዋለው ችሎትም፤ በተከሣሽ ጠበቃ በኩል የቀረቡትን ምላሾችና ችሎቱ በጉዳዩ ላይ ያለውን ስልጣን መመርመሩን አስታውቆ፤ 15ኛ ወንጀል ችሎት ከ10 አመት በላይ የሚያስቀጡ የሙስና ወንጀሎችን ብቻ እንዲመለከት ስልጣን የተሠጠው መሆኑን አመልክቷል፡፡ ፍ/ቤቱ በሰጠውም ብይን፤ ጉዳዩ የሙስና አለመሆኑን አቃቤ ህግ ራሱ ያረጋገጠው በመሆኑና 15ኛ ወንጀል ችሎት የሙስና ያልሆኑ ጉዳዮችን የማየት ስልጣን ስለሌለው፣ የአቶ ምህረተአብ አብርሃ ጉዳይ በሌላ ችሎት እንዲታይ አዝዟል፡፡

በተከሣሽ ጠበቃ የቀረቡት ሌሎች የመቃወሚያ ነጥቦችም ጉዳዩን እንዲመለከት ስልጣን በተሰጠው ችሎት በኩል የሚታይ እንደሆነ ፍ/ቤቱ አስታውቋል፡፡ ባለሃብቱ አቶ ምሕረተአብ አብርሃ፤ በሽግግር መንግስቱ ወቅትና ከዚያ በኋላ የሃገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት የአቶ ስዬ አብርሃ ወንድም ሲሆኑ፤ በግንቦት ወር 2005 ዓ.ም የገቢዎችና ጉምሩክ ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፋንታን ጨምሮ የመ/ቤቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ባለሀብቶች በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ሲታሰሩ አብረው የታሠሩ ናቸው፡፡

Read 2763 times