Saturday, 09 November 2013 12:12

የነፍስ ‘ሰርጀሪ’

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(5 votes)

(በዘገባ ላይ የተመሰረተ አጭር ልብ ወለድ)

            ቴሌቪዥኑ የሰዓቱን ዜና አገባደደ… ቴሌቪዥኑ የዘመኑን መብረቅ አወረደ!!… ‘የዶክተር ፊሊጶስ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ’ የሚል ጉርምርምታን ተከትሎ የወረደው መብረቅ፣ እሴተን አልጋዋ ላይ እንዳለች አደረቃት፡፡ ዶክተር ፊሊጶስ መርሻ አረፉ፡፡ ስንቶችን ከህመም የፈወሱት፣ ስንቶችን ከሞት ያዳኑት፣ ታዋቂው የቀዶ ህክምና ሀኪም ዶክተር ፊሊጶስ፣ በድንገተኛ አደጋ ህይወታቸው አለፈ። የሌሊት ተረኛ ሆነው ሲሰሩ ካደሩበት ሆስፒታል መርሴድስ መኪናቸውን እያሽከረከሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲጓዙ፣ ፍሬን የበጠሰ ጦሰኛ ሚኒባስ እላያቸው ላይ ወጣባቸው፡፡ ታዋቂው የቀዶ ህክምና ሀኪም፣ ለህክምና ሳይደርሱ መንገድ ላይ ተፈጸሙ፡፡ ከአገሪቱ ስመጥር የህክምና ባለሙያዎች አንዱ መሆናቸው የሚነገርላቸው ዶክተር ፊሊጶስ፣ በድንገተኛ አደጋ ስለመሞታቸው ተነገረ - ብዙዎችም ደነገጡ፡፡ ቀብራቸውን በቴሌቪዥን አይተው ክፉኛ ከደነገጡና ካዘኑ ብዙዎች መካከል፣ እሴተ አንዷ ናት፡፡

(ይቅርታ… አንዷ አይደለችም)፡፡ እንደዋዛ አንዷ ናት ብሎ እሷን ከብዙዎች መቀላቀል፣ ድንጋጤና ሃዘኗን ማቅለል፣ ጉዳቷን ማሳነስ ይሆናል። ዜና አንባቢው ቀጥሏል… “በቀብር ስነስርዓቱ ላይ የተነበበው የህይወት ታሪካቸው እንደሚያሳየው፣ ዶክተር ፊሊጶስ መርሻ ህዝባቸውን በትጋት ሲያገለግሉ የኖሩ ምስጉን ባለሙያ፣ ቸርና ለተቸገረ አዛኝ እንዲሁም …” “አይደሉም!... በጭራሽ ለተቸገረ አዛኝ አይደሉም!...” በንዴት ጦፋ ከአልጋዋ ዘላ ወረደች፡፡ “… ዶክተር ፊሊጶስ መርሻ ባለትዳርና…” ዜና አንባቢው እስኪጨርስ አልታገሰችውም፡፡ ቴሌቪዥኑን ዘግታ ጸጉሯን እየነጨች ተወራጨች፡፡ የማይነጥፍ እንባ ረጨች፡፡ “ለተቸገረ የሚያዝን ሰው፣ ‘እረዳሻለሁ’ ብሎ የገባውን ቃል አያጥፍም!... አይዞሽ ብሎ ተስፋ ከሰጠ በኋላ ሜዳ ላይ ጥሎ አይሄድም!... ውሸት ነው!... እሳቸው ለተቸገረ አያዝኑም!... ፍጹም ውሸት ነው!...” አልጋዋ ላይ ተደፍታ ስቅስቅ ብላ አለቀሰች፡፡ ‘ከጭንቀት ነጻ ያወጡኛል’ ያለቻቸው ብቸኛ ሰው፣ ከጭንቀቷ ጋር ጥለዋት ሞቱ፡፡ ‘ራሴን እየወቀስኩ ከመኖር ይገላግሉኛል፣ የሃጢያተኝነት ስሜቴን ያጥቡልኛል’ ብላ ተስፋ ያደረገችባቸው ዶክተር ፊሊጶስ ቃላቸውን አፈረሱ፡፡ አርብ ከሰዓት በኋላ ወደ ቢሯቸው ተመልሳ እንድትመጣ ቀጠሮ ሰጥተዋት፣ ሰኞ ጠዋት ወደማይመለሱበት እብስ አሉ፡፡ አርብ ከሰዓት በኋላ ከዶክተሩ ጋር ተገናኝታ፣ እውነቱን እስኪነግሯትና የዕድሜ ልክ ጥያቄዋን እስኪፈቱላት ቸኩላ ነበር፡፡ ከሚያስጨንቃት የሃጢያተኝነት ስሜት ነጻ የምትወጣው እሳቸውን ስታገኝ ብቻ ነው፡፡ እሳቸውን ማግኘት፣ እንጥፍጣፊ የመኖር ሰበብ ማግኘት ነበር፡፡

መኖሯ ትርጉም አልባ ሆኖባት ስትሰቃይ ኖራለች፡፡ መፈጠሯን እንድትወደው የሚያደርግ አንዳች እንኳን ምክንያት የላትም፡፡ ከመኖር ያተረፈችው መሳቀቅና ባይተዋርነትን ብቻ ነው፡፡ እየተሳቀቀች ነው ልጅነቷን ያሳለፈችው። አፈር መፍጨት፣ ውሃ መራጨት ብሎ ነገር በእሷ ልጅነት ውስጥ የለም፡፡ ከዕድሜ እኩዮቿ ጋር አልተጫወተችም፡፡ አልፈነደቀችም፡፡ ቅስም ሰባሪ ስም ከሰጧት የመንደሩ ልጆች እየሸሸች ነው ያደገችው፡፡ “ጠባሴ!” እያሉ ነበር የሚጠሯት፡፡ አባቷ ያወጡላትን ስም ትተው፣ ከደረቷ እስከ እምብርቷ በሚዘልቀው የገላዋ ጠባሳ ነበር የሚጠሯት፡፡ ይህን ስም መስማት አሳቅቋት፣ ባዶ ቤት ተደብቃ ነው ልጅነቷን የገፋችው፡፡ ባዶ ቤት… እህት ወንድም አልቦ… ያለ እናት… ከጡረተኛ አባት በቀር ወዳጅ ዘመድ የማይጎበኘው ባዶ ቤት ነው ያደገችው - ባይተዋር ሆና፡፡ ሳታውቀው ራሷን አድጋ አገኘችው - ወጣትነት ላይ ቆማ፡፡ ከእለታት አንድ ቀን በረከት የሚባል ሰው መጣ። በረከት ሰዓሊው… ወደተገፋችው እሴተ ገፍቶ መጣ፡፡ “መርጬሻለሁ” አላት፡፡ ፍቅር የሚባል ነገር እንዳለ አስታወሳት፡፡

ብቸኝነቷን አፍርሶ ሁሉንም የሚያስረሳትን፣ የህይወቷን ጣዕም የሚቀይር፣ ፍቅር የሚባል ቅመም ይዞላት መምጣቱን አበሰራት፡፡ ለአመታት ያቀረቀረችዋን እሴተን፣ በረከት የሚባል ወንድ ደጋግፎ ቀና አደረጋት፡፡ አንድ ቀን እንዲሁ በረከት የሚባለው ሰው ሄደ። በረከት ፍቅረኛዋ… ገፍቶ መጥቶ ከጎኗ የቆመው በረከት፣ ብዙም ሳይቆይ ገፍቷት ሄደ፡፡ ደስ ብሏት ሳትጨርስ፣ ቀና ብላ ሳታበቃ፣ እንዳትቃና አድርጎ ሰብሯት ሄደ፡፡ ‘ፍቅር ነው ያመጣኝ’ ያላት በረከት፣ የሄደበትን ምክንያት ሳይነግራት ድንገት ከጎኗ ተሰወረ፡፡ ለነገሩ ባይነግራትም ምክንያቱን ታውቀዋለች፡፡ በዚያች የተኮነነች የመጨረሻ ምሽት፣ እዛች የተረገመች የኪራይ ጫጉላ ውስጥ የሆነውን ሁሉ አትረሳውም፡፡ በውስጡ የተለኮሰውን ነዲድ ስሜት፣ ፋታ የነሳውን የወሲብ አምሮት፣ ችኮላና ጥድፊያውን አትረሳውም፡፡

ልብሷን ላለማውለቅ መፈለጓንና በጭንቀት ተውጣ ከአልጋው ጫፍ ላይ ተኮራምታ መቀመጧን፣ ከመግደርደር እንደቆጠረው አትዘነጋውም፡፡ ተጣድፎ ልብሱን ሲያወላልቅ ፊቱ ላይ ይግለበለብ የነበረውን ወላፈን ታስታውሰዋለች። ከንፈሯን እያኘከ ትንፋሽ እስኪያጥራት ስሞ፣ አዘናግቶ ልብሷን እስኪያወልቅላት ድረስ በስሜት ሲርገፈገፍ ነበር፡፡ ስስ ቲ-ሸርቷን እስኪያወልቅላት ድረስ በስሜት ተወጥሮ ከላይዋ ላይ ሲቃትት አይታዋለች፡፡ እርቃን ገላዋን ሲመለከት በድንጋጤ ከል የለበሰ ፊቱን፣ የተረበሸ ስሜቱን፣ የረገበ አምሮቱን፣ የተነፈሰ ወንድነቱን… ሁሉንም በእንባዋ መነፅር ስር አይታለች። ወንድነቱ እሱ እንዳለው በሱስ ሰበብ በድንገት እንዳልተልፈሰፈሰ ታውቃለች። የናፈቀውን ወሲብ በወጉ እንዳይፈጽም በድንገት ያኮላሸው ገላዋ ላይ ያለው ጉድ መሆኑን ነጋሪ አያሻትም፡፡ ከዚያች ምሽት አንስቶ አድራሻውን ያጠፋበትንና ስልኳን የማያነሳበትን ምክንያት ጠንቅቃ ታውቃለች። ይህ ከደረቷ አንስቶ እስከ እምብርቷ የሚወርድ ጦሰኛ ጠባሳ ነው፡፡ ለመኖሬ ትርጉም ይሰጠዋል ብላ ተስፋ ያደረገችበት በረከት፣ ተስፋዋን ገድሎባት ሄደ፡፡

ከዚህ በኋላ መኖር፣ ለረዥም ስቃይ ራስን ማዘጋጀት ሆኖ ታያት፡፡ ለዚህ ነው መርዝ ጠጥታ ለመሞት የወሰነችው፡፡ ወደ ሞት የሚወስዳትን መርዝ ጨልጣ ሳትጨርሰው አባቷ ደረሱባት፡፡ “ምነው ልጄ!?... እኔን ለማን ጥለሽኝ ለመሄድ ጨከንሽ!?” እያሉ አቅፈዋት ተንሰቀሰቁ፡፡ አንድ ልጃቸውን አጥተው ባዶ ቤት ብቻቸውን ሲቀሩ ታይቷቸው በፍርሃት እየተንቀጠቀጡ፣ በእንባ እየታጠቡ አምርረው ወቀሷት፡፡ በረከት ተደብቋት ሄዶ እንደቀረው፣ እሷም ተደብቃቸው ወደሞት ሄዳ ልትቀር መወሰኗን አወቁ፡፡ “ለምን ብለሽ ይሄን ክፉ ነገር አሰብሽ ልጄ?... እስኪ ንገሪኝ…” አሏት፡፡ “አንተ ንገረኝ!” አለቻቸው እንደ እብድ እያደረጋት፡፡ ስለ ሁሉም ነገር ነገሯት፡፡ “በልጅነትሽ የፈላ ውሃ ተደፍቶብሽ ነው” እያሉ ሲነግሯት ስለኖሩት የደረቷ ላይ ጠባሳ እውነቱን ተነፈሱላት፡፡ እናቷም በነቀርሳ ህመም ሳይሆን፣ እሷን እርጉዝ ሆነው በቀዶ ህክምና ሲገላገሉ በወሊድ እንደሞቱ አረዷት፡፡ ሃኪሞቹ እናቷን ለማዳን ባይችሉም ጽንሱን ለማትረፍ ሲረባረቡ፣ በእናትየዋ ማህጸን ውስጥ ፈፅሞ ያልጠበቁት ዱብዕዳ ይገጥማቸዋል - ሁለት የተጣበቁ ጽንሶች፡፡

ጽንሶቹ ልባቸውን ጨምሮ የተወሰነ የሰውነት ክፍላቸውን የሚጋሩ ሆኖ መገኘቱ ህክምናውን አደገኛ እንዳደረገው፣ ሀኪሞቹም ጽንሶቹን በቀዶ ህክምና በመለያየት አንደኛው ጽንስ ለማትረፍ መገደዳቸውን ነገሯት፡፡ መንታ እህቷ ሞታ፣ እሷ መትረፏንም አረዷት፡፡ በወቅቱ አስቸጋሪውን ቀዶ ህክምና በስኬታማ ሁኔታ ያጠናቀቀው የሃኪሞች ቡድን ከፍተኛ አድናቆት ማትረፉን፣ የቡድኑ መሪ የነበሩት ዶክተርም በቴሌቪዥን ቃለ መጠይቅ እንደተደረገላቸው አወጓት፡፡ አባቷ እውነታቸውን ነው፡፡ ሰዓታትን የፈጀው በቀዶ ህክምና የታገዘ ወሊድ፣ ብዙዎችን አስደንቋል። አስደምሟል፡፡ በአገሪቱ የቀዶ ህክምና ታሪክ ጉልህ ሥፍራ እንደሚኖረውና የሀኪሞቻችንን ብቃት እንደሚያሳይ ተመስክሮለታል፡፡ እሴተ ራሷን ጠላች፡፡ ሌሎች ወደሞት በተሸኙበት መንገድ ወደ ህይወት የመጣች ጨካኝ፣ ስለእናቷ የማትራራ የእፉኝት ልጅ፣ ከእህቷ በቀማችው ትንፋሽ ነፍስ ዘርታ፣ የቆመች እርጉም ፍጡር አድርጋ ራሷን ቆጠረች፡፡ ከተፈጸሙ መንታ ነፍሶች የተወጠነች የግፍ ፍጡር እንደሆነች ተሰማት፡፡ አባቷ እውነቱን ከነገሯት እለት አንስቶ፣ የእናቷና የእህቷ የሙት መንፈስ እረፍት ይነሳት ጀመር፡፡ በህይወት ለመቀጠል የሚያበቃ አቅምና ወኔ አልነበራትም፡፡ ዶክተሩ አቅም ይሆኑኛል ብላ ነበር ተስፋ የጣለችው፡፡

ተጭኖ ካጎበጣት የበደል ሸክም እፍኝ ቆንጥረው ቀለል ሊያደርጉላት፣ ትንሽም ቢሆን የመጽናናት ምክንያት እንደሚፈጥሩላት አስባ ነበር፡፡ አሁን ግን የመጽናኛ ምክንያቷን ተነጠቀች። ዶክተር ፊሊጶስ መሞታቸውን የቴሌቪዥኑ ዜና አንባቢ አረዳት፡፡ ራሷን ትራሷ ስር ቀብራ ተንሰቀሰቀች፡፡ ዶክተር ፊሊጶስ ጭላጭ ተስፋዋን ይዘውባት ላይመለሱ ሄደዋል፡፡ “ዛሬ እንኳን ፔሸንት ይበዛል፣ ለምን አርብ ብቅ አትይም?” ብለው አዘናጓትና እስከወዲያኛው አሸለቡ፡፡ የሆስፒታሉን ኮሪደር ካጣበበው ታካሚ የማይተናነስ የውስጥ ህመም እንደሚያሰቃያት አያውቁም፡፡ ኮሪደሩ ላይ ቆማ ሲያዩዋት፣ ከባለጉዳይ እንጂ ከታካሚ አልቆጠሯትም፡፡ እንደምትፈልጋቸው ስትነግራቸው ሌላ ቀጠሮ ሰጥተው ያሰናበቷት፣ ጉዳይዋ አስቸኳይ ስላልመሰላቸው ነበር፡፡ ወደሳቸው የወሰዳት፣ ፋታ እማይሰጥ አስቸኳይ ጉዳይ መሆኑን የምታውቀው እሷ ብቻ ናት፡፡ ራሷን ለማጥፋት ስትሞክር እጅ ከፍንጅ የያዟት አባቷ፣ የሆነውን ሁሉ ከነገሯት ዕለት አንስቶ እንደቸኮለች ናት፡፡ መወለዷ ድራማ የሚመስል፣ ለማመን የከበደ፣ ገድል መሳይ ዜና እንደነበር አባቷ ነግረዋታል፡፡

ድራማ በሚመስለው ዜና ውስጥ፣ ብዙ ተዋንያን ነበሩበት፡፡ ከሁሉም ጎልተው የወጡት ግን፣ ቀዶ ህክምናውን ያከናወነው የሃኪሞች ቡድን መሪ ናቸው፡፡ ብዙዎች ዜናውን ሰምተው አጀብ ያሉት ስለ እሳቸው ነው፡፡ ሌሎቹን የድራማው ተሳታፊዎች ነገሬ ያላቸው አልነበረም፡፡ መሪ ተዋናዩ ስለሰሩት የህክምና ገድል ብዙ ተብሏል፡፡ በወሊዱ ስለሞቱት ምስኪን ነፍሶች ግን ያሰበም የጠየቀም አልነበረም፡፡ እሴተ ወደሞት ይወስደኛል ብላ ተስፋ ያደረገችውን የመርዝ ብልቃጥ ከጣለች ከወራት ጊዜ በኋላ፣ በህይወት ለመኖር መጽናኛ ይሆነኛል ያለችውን ይህን ጥያቄ አነሳች፡፡ “ቆይ ሃኪሙ ግን ስማቸው ማን ይባላል?” በጉጉት ስሜት አባቷን ጠየቀች፡፡ አባትየው በረንዳ ላይ ቁጭ ብለው ወደ ሰማይ እንዳንጋጠጡ ማሰብ ጀመሩ፡፡ “ማን ነበር ያሏቸው?...የኔ ነገር!... በየራዲዮናው ሲጠሩ ነበርኮ…” ለማስታወስ ሞከሩ፡፡ እሴተ ቸኩላለች፡፡ “እ… እሺ… የትኛው ሆስፒታል ነበር የሚሰሩት?” በጉጉት ተውጣ ጠየቀች፡፡ ለጊዜው ሆስፒታሉን ማወቋ በቂ ነበር፡፡ እሴተ ወደ ሆስፒታሉ ሄዳ ዶክተሩን መፈለግ ጀመረች፡፡ ከብዙ ልፋትና ድካም… ከአስቸጋሪ ውጣውረድ… ከእልህ አስጨራሽ እንግልት በኋላ… ዶክተሩ የግላቸውን ሆስፒታል ከፍተው እየሰሩ እንደሆነ ደረሰችበት፡፡ ጋውናቸውን እንደለበሱ ወደ ታካሚዎች መኝታ ክፍል ሲጓዙ ኮሪደር ላይ ተገጣጠሙ፡፡ ለጉዳይ እንደምትፈልጋቸው ስትነግራቸው፣ እርምጃቸውን ሳይገቱ ነበር መልስ የሰጧት፡፡ “ኧርጀንት ኬዝ ስላለብኝ ላነጋግርሽ አልችልም” አሏት፡፡

አርብ ከሰዓት በኋላ ተመልሳ እንድትመጣ ቀጠሮ ሰጥተዋት ተለያዩ፡፡ ዶክተሩ በመኪና አደጋ መሞታቸውን ቴሌቪዥኑ ሲነግራት፣ ትራስ አቅፋ ተንሰቀሰቀች፡፡ “አገኘሁት!... እሴቴ… የዶክተሩን ስም አገኘሁት!” የአባቷ የደስታ ድምጽ ከሳሎን ተሰማ፡፡ ለቅሶዋን አቁማ ቀና ብላ ልታያቸውም ሆነ ልትሰማቸውም አልፈቀደችም፡፡ ሲያምባርቅ በቆየው የቴሌቪዥኑ ድምጽ ፋንታ፣ የልጃቸው ለቅሶ ተሰማቸው፡፡ በእጃቸው የያዙት አሮጌ ጋዜጣ እስከሚርገበገብ በድንጋጤ እየተርበተበቱ የመኝታ ቤቷን በር በርግደው ገቡ፡፡ እሴተ በእንባ እየታጠበች አልጋዋ ላይ ተዘርራለች፡፡ አጽናንተው ቀና ማድረግ ይቅርና የሆነችውን ለማወቅ አልቻሉም፡፡ አቅፈዋት ተንሰቀሰቁ፡፡ ቀና ብላ ልታያቸውም፣ የሚሉትን ልትሰማቸውም አልፈቀደችም፡፡ ቀና ብላ ብታይ ኖሮ፣ የተወለደች ሰሞን ለንባብ የበቃውን አሮጌ ጋዜጣ ትመለከተው ነበር፡፡ “አስደናቂው የወሊድ ቀዶ ህክምና በስኬት ተጠናቀቀ” የሚል ርዕስ ካለው ዜና ስር፣ የአንድ ራሰ በራ ጎልማሳና አይኗን ያልገለጠች ጨቅላ ፎቶግራፍ ጎን ለጎን ሆኖ ትመለከት ነበር፡፡ ራሰ በራው ጎልማሳ፣ ዶክተር ፊሊጶስ… አይኗን ያልገለጠችዋ ጨቅላ፣ ራሷ መሆኗን ታውቅ ነበር፡፡ ዶክተሩን ትፈልግ የነበረው አንድ ነገር እንዲነግሯት ነው፡፡ የሆነ… ጸጸቷን የሚያቀልላት ነገር እንዲያቀብሏት፡፡ ቢያንስ እሷን ለመውለድ ሲሉ በሞቱ እናቷ እንጂ፣ ተጣብቃት ወደ ምድር በመጣች እህቷ ሞት ተጠያቂ እንዳልሆነች እንዲያረጋግጡላ። ዶክተሩ የፈለገችውን ሳይነግሯት ወደማይቀርበት እብስ አሉ፡፡

እርግጥ ለእሷም ባይሆን፣ ለህዝቡ ተናግረው ነበር፡፡ ከአመታት በፊት የተናገሩትን እውነት ነው፣ ይህ አሮጌ ጋዜጣ የያዘው፡፡ ቀና ብላ ጋዜጣውን ብታየው፣ ከዶክተሩ አንደበት የወጣውን እውነት ትመለከት ነበር፡፡ “የምትጋሩትን ልብ ለመንታ እህትሽ ብንሰጣት፣ የመኖር ዕድል እንደማይኖራት እናውቅ ነበር፡፡ ሁለታችሁም ከመሞታችሁ በፊት ልቡን ለአንቺ በመስጠት፣ ቢያንስ አንቺን ማትረፍ እንዳለብን የህክምና ቡድኑ አባላት የጋራ ውሳኔ ላይ ደረስን፡፡ እሷ መሞቷ እንደማይቀር የሚያረጋግጡ ምልክቶች ስላየን እንጂ፣ አንቺን በህይወት ለማቆየት በሚል አይደለም በእህትሽ ላይ የፈረድነው…” ሲሏት ታደምጣቸው ነበር፡፡ ቀና ብትል ኖሮ የጓጓችለትን እውነት ተንፍሰው፣ ከጭንቀቷ ይገላግሏት ነበር፡፡ እሴተ ግን አባቷ ክንድ ላይ ሆና ትንሰቀሰቃለች፡፡

Read 3603 times