Print this page
Saturday, 09 November 2013 12:06

ውሸታም

Written by  ፀጋዬ ገ/መድህን
Rate this item
(4 votes)

እሷ የደም እሳት የላት!
እኮ! ትዝታኮ ለካ ከቶውኑ ቅድስት ናት
ምንም ህመም አይሰማት
እሷን፤ የእግዜር ፍቅር እንጂ፣ የሰው እሳቱም
ብቁ ናት ለካ ፍፁም ናት፡፡
እነሱራፌል ኪሩቤል፤ በእሳት ሰረገላ ወርደው
በመለኮት ብርሃን አቅፈው
በአክናፋት አኮቴት ቀዝፈው
በህብር አዝለው አንከባክበው
ሰባቱን ሰማያት መጥቀው
ሽቅብ ይዘው፣ ሽቅብ ይዘው
አዎ ትዝታኮ ለካ
በሥጋዌ ልቡሰ ሕመም፣ ሳትወሰን ሳትለካ
በምድር ስሜት ሳትነካ
በሰው መውደድ ሳትረካ
ቅዱስ መንፈስ ያላበሳት
ብቁ ናት፣ ለካስ ፍፁም ናት
የሰው እሳት የማይሞቃት!
ከመላዕክት ጋር አብራ፣ ክንፍ አውጥታ ተፈትልካ
ምንም ምንም ሳትነካ
በቃች! ትዝታኮ ለካ
ሰው አይደለችም ቅዱስ ናት
የሰው ንዳድ የማይሞቃት፡፡
ብዙ ነች አዎ፣ ፍፁም ነች፡፡
ምን ያረጋል….ሰው አይደለች፡፡
እሷ የደም እሳት የላት
እውነት የእውነት…ውሸታም ናት፡፡

1962 -ስድስት ኪሎ
(“እሳት ወይ አበባ”)

Read 3417 times