Saturday, 09 November 2013 11:41

ትዳርዎ ጣፋጭ ነው? ወይስ ነፋስ ገብቶታል?

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(5 votes)

ድስትና ጉልቻ እንኳ ይጋጫል፤ አልፎ አልፎ ከትዳር አጋር ጋር መጋጨት ምንም አይደለም፤ እንዲያውም ፍቅር ይጨምራል፤ በትዳር ደስተኛ ሳይሆኑ “ደስተኛ ነኝ” ብሎ ማሰብ፣ እንዲሁም ሚስቴን ብዋሻት…ምንም አይደለም፤ ብለው ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ 25ኛ የጋብቻ በዓላችሁን እያከበራችሁ ያላችሁ ጥንዶች፣ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎችን ሳታነሱ አትቀሩም ትላለች “The Normal Bar” የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ ክሪሳና ኖርዝራፕ፡፡ ደራሲዋ፤ ይህን ሐሳብ ማሰላሰል የጀመረችው፤ በትዳር ዓለም ለ15 ዓመታት ቆይታ የራሷ ትዳር መንገጫገጭ ከጀመረ በኋላ ነው፡፡ “ትዳራችን እንዲህ መሆኑ ጥሩ ነው ብዬ አስብ ነበር፡፡

ነገር ግን እኔና ባለቤቴ “ትክክል ነው” ወይም “ኖርማል ነው” በማለት የፈጠርነው ነገር፤ ሁለታችንም ከምናምነው በላይ ግንኙነታችንን አሻክሮ እየጐዳው ነበር” ብላለች ኖርዝራፕ፡፡ ኖርዝራፕ በትዳሯ ያጣችውንና የተዳፈነውን የደስተኝነት ስሜት እንደገና ለመጫር፣ በትዳር ዓለም ለረዥም ጊዜ በቆዩ ጥንዶች ዘንድ “ትክክለኛ” ወይም “ኖርማል” የሚባለው የትዳር ግንኙነት ምን እንደሚመስል ለማወቅ አንድ ፕሮጄክት ቀርፃ መንቀሳቀስ ጀመረች፡፡ ኖርዝራፕ የሐሳቡ አመንጪ ትሁን እንጂ ፕሮጀክቱን የሠራችው ብቻዋን አልነበረም - ከምሁራን ጋር ነው፡፡ የማኅበራዊ ሳይንስ ጥናት ባለሙያ (ሶሾሎጂስት) የሆኑት ዶ/ር ፔፐር ሸዋትዝ፣ ዶ/ር ጀምስ ዋትና እንደሪደርስ ዳይጀስት ያሉ ተባባሪ የሚዲያ አካላት አብረዋት በጥናቱ ተሳትፈዋል፡፡ በመላው ዓለም ከ80ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ስለፍቅር፣ ጋብቻ፣ ወሲብ፣ እምነት፣ ደስታና ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ርዕሰ ጉዳዮች አንስታ ጠይቃቸዋለች፡፡ ለእነዚያ በጣም አጠቃላይና እጅግ ተጨባጭ ለሆኑ ጥያቄዎች የተሰጡ ምላሾች፣ በአሁኑ ወቅት ደስተኛ የሆነ ትዳር ለመፍጠር ዋነኛ መሠረት እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

“የጥናቱን ውጤት ካየሁ በኋላ ባለቤቴን “ፍቅሬ” እያልኩ መጥራት ጀምሬአለሁ” ትላለች ኖርዝራፕ፡፡ “አስቀያሚና አስጠሊታ በሆነ የሞቀ ክርክር ውስጥ እንኳ፣ ፍቅሬ፣ ማሬ፣ የእኔ ቆንጆ፣ ሆዴ እያሉ መጥራት፣ ፍቅር በተሞላበት መንገድ ውይይቱን ማካሄድ ያስችላል” ትላለች ኖርዝራፕ፡፡ እነዚያ አስገራሚና አንዳንዴም አስደንጋጭ የሆኑት የጥናት ውጤቶች ምን ይሆኑ? ቀጥለን እናያለን፡፡ ጥያቄው ከቀረበላቸው እጅግ ደስተኛ የጋብቻ ተጓዳኞች ውስጥ 76 በመቶ ያህሉ የሚጠራሩት፣ ሆዴ፣ ፍቅሬ፣ ነፍሴና… በመሳሰሉ የፍቅር ቃላት ነው። በዓለም ላይ እጅግ የፍቅር አገር ማን እንደሆነች ያውቃሉ? ስፔይን ናት፡፡ ከመቶ ስፔናውያን መካከል 77 የትዳር ተጓዳኞች፣ በሳምንት ውስጥ ባሉ አብዛኞቹ ቀናት ብዙ ጊዜ በመተቃቀፍ ፍቅራቸውን ይገላለፃሉ፡፡

72 በመቶዎቹ ደግሞ በሳምንት ውስጥ ብዙ ጊዜ በጋለ ጥልቅ የፍቅር ስሜት (Passionately) ይሳሳማሉ፡፡ 62 በመቶ ስፔናውያንም እንዲሁ በሳምንት ውስጥ ብዙ ጊዜ ፍቅራቸውን በአደባባይ ይገላለጻሉ፡፡ ይህን አኅዝ ከአሜሪካ ጋር እያነፃፀርን ብናየው፣ ከመቶ አሜሪካውያን የትዳር ተጓዳኞች መካከል በሳምንት ብዙ ጊዜ በመተቃቀፍ ፍቅራቸውን የሚገልጹት 17ቱ ብቻ ናቸው፡፡ በየሳምንቱ በጋለ ጥልቅ የፍቅር ስሜት የሚሳሳሙት ከመቶ 20 እንዲሁም፤ በየሳምንቱ ብዙ ጊዜ በአደባባይ በመሳሳም ፍቅራቸውን የሚገላለጹት፣ ከመቶ አሜሪካውያን ባልና ሚስቶች 18ቱ ብቻ ናቸው፡፡ በዓለም ላይ ካሉ እጅግ ደስተኛ የትዳር ተጓዳኞች የምንማራቸው ስምንት ነገሮች አሉ፡፡ ከመቶ 74 ደስተኛ ጥንዶች ጀርባቸውን ይተሻሻሉ። ከመቶ ደስተኛ ጥንዶች 20ዎቹ እንደቀድሞው የትዳር አጋራቸውን መማረክ አቅቷቸዋል፡፡ 45 ከመቶ ጥንዶች ከትዳር አጋራችን ጋር ብዙ በጋራ የምንጋራቸው ነገሮች አሉን ይላሉ፡፡ ከመቶ ሰዎች 95ቱ በግንኙነታቸው እጅግ ደስተኛ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

እጅግ ደስተኛ እንደሆኑ ከገለጹት ባለትዳሮች መካከል 40 በመቶዎቹ፤ መግባባትና አንዱ ሌላውን መረዳት፣ ከጓደኝነት፣ ከፍቅር ወይም ከወሲብ በላይ፣ የግንኙታቸው እጅግ አስደሳች ክፍል መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ሌሊት ተለያይቶ መተኛት ጥሩ አይደለም። ጥያቄው ከቀረበላቸው እጅግ በጣም ደስተኛ ጥንዶች መካከል፣ ተለያይተን ሶፋ ላይ አድረናል ያሉት ከመቶ አንድ ብቻ ናቸው፡፡ የሚዋደዱ ደስተኛ ጥንዶች ምስጢር ቢደባበቁ አይገርምም። እጅግ ደስተኛ ከሆኑ የትዳር ተጓዳኞች መካከል ከመቶ 27ቱ ምስጢር ይደባበቃሉ፡፡ በትዳር አብሮ ለመዝለቅ ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ ወሲባዊ ግንኙነት ነው፡፡ እጅግ ደስተኛ ከሆኑትና ከ20 ዓመት በላይ አብረው ከኖሩ ጥንዶች መካከል፣ ከመቶ 60ዎቹ በሳምንት ውስጥ ሦስት ወይም አራት ጊዜ ወሲብ ይፈጽማሉ፡፡ በትዳር ዓለም ያለመግባባት ያለ ነው። እጅግ ከሚዋደዱ ደስተኛ ጥንዶች መካከል ከመቶ 78ቱ አልፎ አልፎ ይጋጫሉ። በጭራሽ የማይጋጩ ጥንዶች፣ ለጠበቀ ቁርኝት አስፈላጊ የሆነውን ውይይት አቁመዋል ማለት ነው፡፡ ጥናቱ፤ አስደናቂ ነገሮችንም ይፋ አድርጓል። ከወንዶችና ከሴቶች ቀድሞ በፍቅር የሚወድቀው ማን ይመስልዎታል? ወንዶች ናቸው፡፡ ከመቶ ወንዶች 48ቱ ገና በመጀመሪያው እይታ በፍቅር ሲነደፉ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ለፍቅር የሚሸነፉት ከመቶ ሴቶች 28 ብቻ ናቸው፡፡ ሌላ የሚገርመው ነገር የማይዋደዱ ጥንዶች ናቸው፡፡

ደስተኛ ግንኙነት ከሌላቸው ሰዎች መካከል ከመቶ 57ቱ አሁንም ፍቅረኛቸው ከመጠን በላይ ማራኪ መሆኑን ወይም መሆኗን ይናገራሉ፡፡ ጥሩ “የቡድን አባል” የግድ ጥሩ የትዳር ተጓዳኝ አይሆንም፡፡ ፍቅረኛቸውን በዚህ ምድብ የሚያስቀምጡ ሰዎች፣ ምናልባትም ግንኙነታቸው መጠነኛ ደስታ እንደጐደለው ጠቋሚ ናቸው። ሌላው አስገራሚ ነገር ወንዶች ለፍቅር ያላቸውን ስሜት ሌሎች ያለመረዳታቸው በጣም የሚያሳስባቸው መሆኑ ነው፡፡ በጣም ሀብታም ጥንዶች ብዙ ጊዜ እንደሚጋጩም ጥናቱ ያሳያል፡፡ በጥናቱ የተካተቱ ሀብታም ጥንዶች፣ አነስ ያለ ሀብት ካላቸው ጋር ሲነፃፀሩ በተደጋጋሚ የሚጋጩ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በትዳር ዓለም እንቅልፍ እያጡ ተጓዳኝን መጠበቅ ለፍቺ ይዳርጋል፡፡ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ወይም ፊልም ከሚከታተሉ መቶ ሰዎች፤ 33 ያህሉ፣ ትዳራቸው በመናጋቱ ከድርጊታቸው ለመታቀብ አቅደዋል፡፡ ሌላው አስገራሚ ነጥብ ደግሞ የትዳር አጋሮች በመካከላቸው ያለው ትዳራቸው በሐሴት የተሞላ ባይሆንም እስከ ሕይወት ፍጻሜ አብሮ የመቆየት አዝማሚያ ማሳየታቸው ነው።

በግንኙነታቸው ደስተኛ ያልሆኑ 60 በመቶ ያህል ወንዶችና ሴቶች ቀሪ ጊዜያቸውን አብሮ የማሳለፍ ፍላጐትና ፈቃደኝነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ያለመግባባትን ወይም አንዱ የሚለውን ሌላው ያለመረዳትን ትክክል ነው ወይም ኖርማል ነው ብሎ መቀበልም አለ፡፡ ከመቶ ሴቶች 92ቱ፣ ከመቶ ወንዶች ደግሞ 90ዎቹ ራሳቸውን ጥሩ ተግባቢና ራሳቸውን በቅጡ የሚገልፁ አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ ነገር ግን ተጓዳኛቸው ጥሩ ተግባቢ እንደሆነች ሲጠየቁ፤ ከመቶ ሴቶች 33ቱ፣ ከመቶ ወንዶች ደግሞ 25ቱ ምላሻቸው “ጥሩ ተግባቢ አይደለም/አይደለችም” የሚል ነው፡፡ መተማመን ሌላው ጥያቄ ነበር፡፡ ጥናቱ ከተካሄደባቸው ሰዎች መካከል፤ ከመቶ ሴቶች 39 ብቻ “ባሌን አምናለሁ” ሲሉ፤ “ሚስቴን አምናለሁ” ያሉት ወንዶች ግን ከመቶ 53 ናቸው፡፡ ሌላው አሳዛኝ ነገር ከመቶ ወንዶች 75ቱ፣ ከመቶ ሴቶች 71ዱ የትዳር ተጓዳኛቸውን እንደሚዋሹ ተናግረዋል፡፡ ከመቶ ሴቶች 54ቱ፣ ከመቶ ወንዶች ደግሞ 49ኙ የትዳር አጋራቸውን ኢ - ሜይል ከፍተው እንደሚያነቡ አልደበቁም፡፡ ከአሜሪካውያን የትዳር ተጓዳኞች መካከል 75 በመቶ ያህል ጥንዶች ጨርሶ አንድ ላይ ሽርሽር ወይም እረፍት ወጥተው አያውቁም፡፡ ከመቶ ጥንዶች 44ቱ ደግሞ በፍፁም ለፍቅር ወጥተው አያውቁም ወይም ጥቂት ጊዜ ብቻ ወጥተዋል፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ ከ10 ዓመት ወይም ከዚያ ዓመት በላይ በጋብቻ ከቆዩ ሰዎች መካከል ከመቶ ሰዎች 15ቱ ከትዳር አጋራቸው ጋር በፍፁም ስቀው አያውቁም፡፡ ከመቶ ወንዶች መካከል 24ቱ ወሲብ ሲፈጽሙ ካልሆነ በቀር ሚስቶቻቸውን በፍፁም ስመዋቸው እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡ 56 በመቶ የትዳር ተጓዳኞች ደግሞ በጣም ጥቂት ጊዜ ካልሆነ በስተቀር፣ በጋለ የፍቅር ስሜት ተሳስመው አያውቁም፡፡ እነዚህን አምስት ነገሮች ፈጽማችሁ ከሆነ በእርግጥም በትዳር ጅሎች ናችሁ ይላል፤ መጽሐፉ፡፡

Read 3415 times