Saturday, 09 November 2013 11:35

በብስክሌት የመሞረድ አገልግሎት የሚሰጠው ወጣት!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ከሥምህ እንጀምር…

አብርሃም አስመላሽ እባላለሁ፡፡ የ18 ዓመት ወጣት ነኝ፤ ትውልድና ዕድገቴ በትግራይ ክልል መቀሌ ገጠራማ አካባቢ ሲሆን ወላጆቼ ገበሬዎች ናቸው፡፡ ከቤተሰባችን አራት ልጆች አንዱ ነኝ፡፡ የትምህርት ታሪክህ ምን ይመስላል? መቀሌ እያለሁ እስከ 4ኛ ክፍል ተምሬያለሁ፡፡ አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ 5ኛ ክፍል ቀጥዬ የነበረ ቢሆንም ከዚያ በላይ መማር አልቻልኩም፡፡ እንዴትና መቼ ወደ አዲስ አበባ መጣህ? ታላቅ ወንድሜ ቀደም ብሎ መጥቶ ነበር፡፡ እሱን ተከትዬ ነው የመጣሁት፡፡ አዲስ አበባ ከመጣሁ ሁለት ዓመት ያስቆጠርኩ ሲሆን ወንድሜ አራት ዓመት ሆኖታል፡፡ መቀሌ እያለህ ምን ትሰራ ነበር? ቤተሰቦቼን በሥራ ከማገዝ ውጭ ምንም አልሰራሁም፡፡ አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ ከወንድሜ ጋር ሸቀጣ ሸቀጥ እያዞርኩ እሸጥ ነበር፡፡ የወንድሜ ስም ሞገስ ነው፤ የግለሰብ ቤት ተከራይተን ኳስ ሜዳ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አካባቢ ነው የምንኖረው፡፡

በብስክሌት ላይ የመሞረድ አገልግሎት መስጠት የጀመርከው መቼ ነው? ከወንድሜ ከሞገስ ጋር ማስቲካና ሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦችን እያዞርን በመሸጥ ላይ እያለን ሥራችንን ወዴት እናሳድግ ብለን ስናስብ፣ ይህ ሃሳብ መጣልን። ባለ ክቡን ሞረድ በእጅ በመዘወር ስለታማ ነገሮች ሲሞረዱ ያየነው በመቀሌ ከተማ ነበር፡፡ በእጅ የሚዘወረውን ለምን በብስክሌት ፔዳል አናደርገውም ብለን አዲስ ሥራ በመፍጠር ወደ ሥራው ገባን፡፡ አሁን እኔም ወንድሜም በሁለት የተለያዩ ብስክሌቶች ላይ ሞረድ አስገጥመን ከቦታ ወደ ቦታ በመንቀሳቀስ ለሕብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጠን ነው፡፡ አሰራሩ እንዴት ነው? ሞረዱን በብስክሌቱ ላይ ለማስገጠምስ ምን ያህል ገንዘብ አወጣችሁበት? ዝርዝር ወጪውን የሚያውቀው ወንድሜ ቢሆንም ለስራው የገዛነው አሮጌ ብስክሌቶችን ነው፡፡

ሞረዱ ብስክሌቱ እጀታ አካባቢ የተገጠመ ሲሆን በብስክሌቱ የኋላ ጐማ ላይ ተጨማሪ ቸርኬ በማስገጠም፤ የኋላው ጐማ መሬት ለቆ እንዲቆም ካደረግነው በኋላ የብስክሌቱን ፔዳል በመምታት ከቸርኬውና ከሞረዱ ጋር በተያያዘው ቺንጋ ሞረዱ ሲሽከረከር ነው መሞረድ የምንጀምረው፡፡ ለዚህ ሥራ መነሻ የሆነንን ገንዘብ ያገኘነው ሸቀጣ ሸቀጥ ሸጠን ካጠራቀምነው ትርፍ ነው፡፡ ቸርኬውን፣ ቺንጋውና ሞረዱን በብስክሌቱ ላይ የገጠሙልን የጋራዥ ባለሙያዎች ነው፡፡ ሞረዱ ለስንት ጊዜ ያገለግላል? የአንዱ ክብ ሞረድ ዋጋ 160 ብር ሲሆን ሁለት ወር ያህል ከቆየ ብዙ ቆየ እንላለን፡፡ ለነገሩ እኛ በእግር (ጉልበት) የብስክሌት ፔዳል እየመታን ስለምንሰራ ነው እንጂ በዲናሞ ቢሆን ኖሮ ከሁለት ወር በላይም ሊያገለግል ይችል ነበር፡፡ ይህንን ሥራ ከጀመርክ ስንት ጊዜህ ሆነህ? እኔ ሁለተኛ አመቴን ልይዝ ነው፡፡

ወንድሜ ሦስት አመት ይሆነዋል፡፡ ምን ምን ትሞርዳለህ? ቢላዎችና መቀስ የመሳሰሉ እንሞርዳለን፡፡ ለዳግመኛ አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶችን በሙሉ እሞርዳለሁ፡፡ የመሞረጃ ዋጋ ምን ያህል ነው? ቢላዋ 3 ብር፣ መቀስ 2 ብር፣ የመፋቂያ ነጋዴዎች ቢላዋ በ1 ብር እንሞርዳለን፡፡ ዋጋው እንደሚሞረደው ዕቃ ትልቅነትና ትንሽነት ሊለያይ ይችላል፡፡ የት አካባቢ ነው አገልግሎት የምትሰጠው? ተንቀሳቃሽ ነኝ፡፡ ሁሉም ቦታ እሄዳለሁ፡፡ ካዛንችስ፣ ሾላ፣ ቦሌ፣ መገናኛ፣ መርካቶ፣ ፒያሳ፣ አስኮ… ተንቀሳቅሼ ነው ስራውን የማገኘው፡፡ የሚፈልግህ ሰው የት ያገኝሃል? ለምሳሌ ዛሬ አንተ እኔን ያኘኸኝ በድንገት ነው፡፡ እኔም ወደ መርካቶ የመጣሁት በአጋጣሚ ነው፡፡ በድንገት ያገኙኝ አራት መፋቂያ አዟሪዎች ቢላቸውን አስሞርደውኛል፡፡ በአብዛኛው በዚህ መልኩ ነው እየተንቀሳቀስኩ የምሰራው፡፡ በስልክ ጠርተው የሚያሰሩኝ በተለይ ባለ ሆቴል ቤት ደንበኞችም አሉኝ፡፡ በቀን ምን ያህል ብር ትሰራለህ? እስከ 200 ብር የምሰራበት ጊዜ አለ። እንዳልኩህ ሞረዱም ቺንጋውም ቶሎ ቶሎ ስለሚቀየር ወጪ አለው፡፡ ቀጣይ የህይወት አላማህ ምንድነው? አሁን ወንድሜም እኔም ተመሳሳይ ሥራ በተለያዩ ቦታዎች እየሰራን ውለን ማታ እንገናኛለን፡፡ የመሞረዱን አገልግሎት በዲናሞ ለመሥራት እያሰብን ነው፡፡ ይህንን ሥራ እየሰራን ገጠር ያሉ ቤተሰቦቻችንን እንረዳለን፡፡ ከዚህ የተሻለ በመሥራት ህይወታችንን የመለወጥ አላማ አለን፡፡ የእረፍት ጊዜህ መቼ ነው? ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ቀኑን ሙሉ እሰራለሁ፡፡ እሁድ የእረፍት ቀኔ ነው፡፡

Read 1642 times