Saturday, 09 November 2013 11:35

አባባ ተስፋዬ - በሐዋሳው ተረት ቤት

Written by  መልካሙ ተክሌ
Rate this item
(6 votes)

“ወጣቶች፤ ሀገራችሁን ውደዱ፤ አንብቡ!”

           በሐዋሳ ከተማ ሐይቁ ዳርቻ በሚገኘው “ሌዊ ሪዞርት” የተሰራው “የተረት ቤት” ጥቅምት 23 ቀን 2006 ዓ.ም ተመርቋል፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመርያው እንደሆነ የተነገረለት “የተረት ቤት”፤ ለበርካታ አስርት ዓመታት በሬዲዮና በቴሌቪዥን ተረት በመንገር በሚታወቁት የ90 አመቱ አርቲስት ተስፋዬ ሳህሉ (አባባ ተስፋዬ) ስም የተሰየመ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት የተረት ቤቱ ሲመረቅ በክብር እንግድነት የተገኙት አባባ ተስፋዬ፤ “የጥንቸልና የዔሊ ውድድር” የተሰኘ ታሪክ በመናገር ተረት ቤቱ በይፋ ሥራ መጀመሩን ይፋ አድርገዋል፡፡ በምረቃው ዕለት ንግግር ያደረጉት የሌዊ ሪዞርት ባለቤት አቶ ወንድይፍራው እንደሻው፤ የተረት ቤቱን መሰራት አስመልክተው ሲናገሩ፤ “የልጆችን የንባብ ልምድ ለማዳበርና በየሳምንቱ ለልጆች ቁምነገር በተረት መልክ የምናስተላልፍበት ነው” ብለዋል፡፡

ተረት ቤቱ ከቢዝነስ ጋር የተገናኘ አይደለም ያሉት አቶ ወንድይፍራው፤ “በውጭ ፊልሞችና ታሪኮች እየተመሰጡ ላሉ ልጆቻችን ታሪካችንን እና ባህላችንን ለማስተላለፍ አስበን ነው” በማለት የተረት ቤቱን ዓላማ ተናግረዋል፡፡ በአዋሳው የተረት ቤት ምረቃ ወቅት የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መልካሙ ተክሌ ከአባባ ተስፋዬ ጋር አጭር ቆይታ በማድረግ የልጅነት ሕይወታቸውን ያስታወሳቸው ሲሆን ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የለቀቁበትን ሁኔታና ዳግም የመመለስ ሃሳብ እንዳላቸው እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን አንስቶ ተጨዋውተዋል፡፡ እነሆ፡- በልጅነትዎ ተረት እየሰሙ ነው ያደጉት እንዴ? ተረት አይደለም በልጅነቴ የተነገረኝ፡፡ ቤተሰቦቼ እርግጡን እየነገሩ ነው ያሳደጉኝ፡፡ ቤተሰባችን ለንጉሣውያን ቤተሰብ ቀረብ ያለ ነው፡፡ የተወለድኩት ባሌ አካባቢ ነው፡፡

ጥሩ ነገር ስለመስራት፣ ትእግስተኛ ስለመሆን እየሰማሁና በሥነምግባር ተኮትኩቼ ነው ያደግሁት፡፡ ሥነስርዓት አክብሮና ከሰው ጋር ተግባብቶ የመኖር ፋይዳ ከቤተሰቦቼ ተምሬአለሁ። ብዙ ሥነስርዓቶችን የተማርነው ቤተመንግሥት ውስጥ ነው፡፡ ዳዊት ከደገምን በኋላ ፈረንሳይ ትምህርት ቤት ገብተናል፡፡ እዚያም መልካም የሚባሉ ሥነምግባሮችን አስተምረውናል፡፡ በጣልያን ወረራ ወቅት ታዳጊነትዎን እንዴት አሳለፉ? ጓደኞቼ ለጦርነት ዘመቱ፡፡ እኔ ግን እግሬን ታምሜ ቀረሁ፡፡ ጣሊያን ሲገባ፤ ሐኪሞች እግሬን አዩልኝና፡፡ ቀዶ ሕክምና ተደረገልኝ፡፡ ያከመኝ ሐኪም የግራዚያኒ አማች ነበር፡፡ ያኔ መብራት አልነበረም፤ ሲያክመኝ እጅ እጁን ነበር የማየው። ይኼ ጣልያን በጣም ይወደኝ ነበር፡፡ በጣም የማይወደኝ ሌላ ጣሊያናዊ ደግሞ ነበር፡፡ እኔን ነገር ለመፈለግ “ምኒሊክ ኔግሮ (ጥቁር) ነው” እያለ ያበሽቀኛል፡፡ እኔ ግን “ምኒሊክ በአድዋ ጊዜ ጦርነት አሸንፏል” እያልኩ እሟገተው ነበር፡፡ ለልጆች ተረት መንገር የጀመሩት መቼ ነው? የጀመርኩት በሬዲዮ ነበር፡፡ በኋላ ብሔራዊ ትያትር ተከፈተ፤ በ1948፡፡

እኔ ከኮሪያ እንደመጣሁ ማለት ነው፡፡ (ሁለቴ ነው የዘመትኩት፡፡) የማዘጋጃ ቤት ተዋንያን የነበርነው ብሔራዊ ትያትር ገባን። በ1937 ዓ.ም ከሐረር እንደመጣሁ ሴት ተዋናይ አልነበረም፡፡ የብላታ ግርማቸው ተክለሐዋርያት ድርሰት ነበር፡፡ እዚያ ላይ የሴት ገፀ ባህርይን ወክዬ ተጫውቻለሁ፡፡ የመጀመርያው የኢትዮጵያ “ሴት” ተዋናይ ሆንኩኝ፡፡ ብላታ “ዘመዶችህ ቢያዩህ በጥይት ነው የሚገድሉህ” አሉኝ፡፡ ዞሮ ዞሮ ሰራሁት። ከቃጫ የተሰራ ሹሩባ አጥልቄ ነው የተወንኩት፡፡ ምን ያህል የተረት መፃህፍት አሳትመዋል? አምስት መፃህፍት አሳትሜአለሁ፡፡ መፃህፍትና ሲዲ እያዞሩ ሲሸጡ ያዩዎት ሰዎች “አርቲስት የማይከበርበት ሀገር” እያሉ ሲያማርሩ ሰምቻለሁ… እኔ እየዞርኩ የምሸጠው ሰዎች ከፀሐፊው ገዛን የሚል ስሜት እንዲያድርባቸው ነው እንጂ ለገንዘቡ ብዬ አይደለም፤ ብዙ አከፋፋዮች “እናከፋፍልልህ” እያሉ ሲለምኑኝ እምቢ ብዬ ነው ሳዞር የነበረው፡፡ የዘፈን አልበምም አለዎት አይደል? አዎ፡፡ እንደገና ማሳተም አልፈለግሁም፡፡ “ዓለም እንዴት ሰነበተች” የሚለውን ያካተተ አንድ አልበም ነው ያለኝ፡፡ አብዛኞቹ የምክር ናቸው፡፡ ኮርያ ሆኜ ነው የዘፈንኳቸው፡፡ በኮርያ ዘመቻ ወታደራዊ ሹመት አግኝተዋል? እንዴታ! ፶ ዓለቃ ተስፋዬ ሣሕሉ፣ የሃምሳ ካሊበር አዛዥ ተብያለሁ፡፡ የዘመትኩት ከሁለተኛ ቃኘው ሻለቃ ጋር ነው፡፡ አዛዡ ኮሎኔል አንዳርጌ ይባላሉ፡፡

ጓደኞችዎ እነማን ነበሩ? ጓደኞቼ ግጥሞቼ ናቸው፡፡ የብሔራዊ ትያትሩ መርአዊ ስጦት በጣም ጐበዝ ነው፡፡ ጌታቸው ደባልቄም እንደዚያው፡፡ መርዓዊ ሃሳብ ስነግረው አሳምሮ ይጽፈዋል፡፡ ጌታቸውም እንደዚሁ ነው የሚጽፈው፡፡ እኔ ጓደኛ የለኝም፡፡ አብሮ አደጌ አበራ በዳኔ፣ ብዙ ዘመን አብረን ኖረን ሕይወቱ አልፏል፡፡ ሌላው ፶ ዓለቃ እሸቱ ደስታ ነበር፤ እሱም አለፈ። የጄነራል ጓደኞቼን ስም አልጠራልህም። “ኒ ታዓ ጄኔ ሃሬ ቀሌ፣ ሂንተኡ ጄናን ባስኔ ገኔ” ይባላል በኦሮምኛ። (ይሆናል ቢሉን አህያ አረድን፤ አይቻልም ሲሉን አውጥተን ጣልን፤ ማለት ነው) የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በድጋሚ “አብረን እንሥራ” የሚል ጥያቄ ቢያቀርብልዎ ምን ይላሉ? እኔ ፈቃደኛ ነኝ፡፡ ግን ከዚህ ቀደም ተናግሮታል ብለው ያወሩትን “እኛ ነን” ብለው ካስተባበሉ ብቻ ነው የምስማማው፡፡ ምክንያቱም ያላልኩትን ብለዋል፡፡ አሁንም እየጠየቁኝ ነው፡፡

“አን አከነ ጄዴ ሂንኦዴ ሲኔ” (እኔ እንደዚያ አላወራሁም እንደማለት ነው) በጃንሆይ ጊዜ አንዱ ለብላታ ግርማቸው “ንጉሥ ሲያራ” እያለ ያወራል ብሎ ቢከሰኝ፣ ከት ብለው ሳቁና “ሥለ ንግሥት ሳራ ነው የሚያወራው ባክህ፤ አትሳሳት” ብለው መለሱት፡፡ አሁን 90 ዓመትዎ ነው፡፡ ምን እየሰሩ ነው? ምንስ ያስባሉ? ዘጠና ዓመት ከስድስት ወር ሊሆነኝ ነው። ሰኔ 20 ቀን 1915 ዓ.ም ነው የተወለድኩት፡፡ ደግሞ ሽማግሌ ምን ያስባል? (እየሳቁ) እንግዲህ እግዚአብሔር ያውቃል፡፡ ምንም ቢሆን የአባትህን የእናትህን ሃይማኖት ይዘህ ሂድ፤ የሌላውንም አትዝለፍ፡፡ የዘመኑን ወጣት ምን ይመክራሉ? ሀገራችሁን ውደዱ፡፡ ሽንኩርት ትከሉ፡፡ ሀገር አልሙ፡፡ እኔ ተዋናይ በነበርኩበት ጊዜ የትወና ሥራ በሌለበት ወቅት፣ ሻሸመኔ ወርጄ አጄ የሚባል ቦታ አንድ ጋሻ መሬት ስለነበረኝ ያንን አለማ ነበር። በአብዮቱ ጊዜ ባይወሰድብኝ ኖሮ ቦሎቄ ወደ እስራኤል መላክ ጀምሬ ነበር፡፡ ወጣቶች ያንብቡ፣ ከተቀደደ ወረቀትም ላይ ቢሆን ያገኙትን ማንበብ አለባቸው፡፡

Read 5707 times