Saturday, 09 November 2013 10:56

የአዳማ ጉዞ ማስታወሻ!

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(2 votes)

የደብረ ብርሃን ጉዞዬ ማስታወሻ የደብረ ብርሃን ሰው የደብረ ብርሃንን ብርድ እንዴት እንደሚቋቋመው ያቃል - የአገሩን ሠርዶ ባገሩ በሬ በተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር የእየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ድርጅት በተለይ ማህበረሰብ አቅፍ ማህበራትን በማደራጀት ልዩ ልዩ የልማት እንቅስቃሴዎችን እንዴት እያገዘ መሆኑን፣ በህዝቡ ያለውን ተቀባይነትና ድርጅቱ ምዕራፉን ጨርሶ ሲወጣ (Phase out ሲያደርግ) አገሬው እንዴት ተረክቦ ሥራውን እንደሚቀጥለው እየተረክሁላችሁ ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ደብረዘይት፣ ናዝሬት፣ አዋሳን ያካተትኩ ሲሆን ዛሬ ደብረብርሃን ላይ ነኝ፡፡ ከጠቀስኳቸው ህፃናትና ማህበረሰብ - ተኮር የልማት እንቅስቃሴዎች ባሻገር የየከተማዎቹን አየርም ያሸተትኩትን ያህል እያዳሰስኩ ነው የማልፈው፡፡ የዛሬ ትኩረቴ የከተማ ግብርና ነው፡፡ ደብረብርሃንን፤ ጥንት አድሬባትም፣ ደጋግሜ አልፌባትም አውቃለሁ፡፡ በዱሮው አጠራር ተጉለትና ቡልጋ ውስጥ ነው ምድቧ፡፡ በኃይለስላሴ ዘመነ - መንግሥት የአውራጃ አካባቢዎች በጥምረት (duality) ሁለት ሁለት ቦታዎች በማቀፍና በማቀናጀት እንደሚጠሩ ይታወቃል፡፡ መንዝና ግሼ፣ ይፋትና ጥሙጋ፣ ሐይቆችና ቡታጅራ፣ የረርና ከረዩ ወዘተ፡፡

ተጉለትና ቡልጋ ይኸው የጥምረት መንፈስ ውጤት መሆኑ ነው፡፡ ደብረብርሃን የጥንት መንገዶቿንና ሆቴሎቿን እንደያዘች ያለች ከተማ ናት። በተለይ በዋናነነት የምትታወቅባቸው የቲቲአይ (የመምህራን ኢንስቲቲዩት) እና የብርድ ልብስ ፋብሪካዋ እንዲሁም ዛሬም የአዲሳባን የበግ ተራ በየበዓሉ የሚያጣብበው የደብረ ብርሃን በግ፤ የሚታወሱ ናቸው፡፡ ከደብረ ሲና ቀጥሎ በማታ ቅዝቃዜ ደብረብርሃን የምትቻል አይደለችም፡፡ ታንቀጠቅጣለች፡፡ በደብረብርሃን ከተማ የቀበሌ 08 ማህበረሰብ አቀፍ ልማት ማህበርን፣ የቀበሌ 01፣ 03፣ 04፣ 05 እና 06 የማህበረሰብ ልማት ማህበርንና የአዲስ ህይወት የወጣቶች ማህበርን አይቻለሁ፡፡ ባለፈው ሳምንት በከፊል ተርኬላችኋለሁ፡፡ ዛሬ ቀጣዩን እናያለን፡፡ ባለፈው እንዳነሳሁላችሁ፤ ህዝቡን በማሳተፍ፣ ዕድሮችን በማቀፍ፣ ያላቸውን ያካባቢ ሀብት በማንቀሳቀስ፣ ከመንግሥት አካላት ጋር በመልካም ግንኙነት በመሥራት፣ አገሬውን በማደራጀትና፤ በቁርጠኝነትና በታማኝነት ልማቱን በማጐልበት የሚሠሩ መሆናቸውን፤ መሬት በጨበጠ ገቢር አስረግጠውልኛል፡፡

የእየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት የደብረ ብርሃን ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ፣ የጥንቱ የት/ቤቴ ዩኒት ሊደር፣ ወደማህበሩ ጽ/ቤት አድርሶኝ ሄደ፡፡ እኔ ካመራሮቹ ጋር ውይይት ቀጠልኩ፡፡ “ይሄ ማህበር ደሞ የተመሠረተው የከተማ ግብርናን መሠረት አድርጐ ነው፡፡ ከተማ ግብርና የጀመርነው በቀበሌ 4 ነው፡፡ ከዛ ቀበሌ 1፣3፣4፣5፣ ውስጥ ነው የገባነው፡፡ ፌዝ አውት ስናደርግ ይሄንን ማህበር አደራጅተን ነው፡፡ ይሄ ማህበረሰቡ ቤዙ “urban agriculture” ነው፡፡ የከተማ ግብርና የማይነካው ወንድም ሴትም ህፃንም የለም፡፡ እዚህ ውስጥ አንድ የዕድሮች ህብረት አለ፡፡ የሴቶቹ ስብስብ አለ፤ ይሄ ማህበር አለ ተሰባስቧል፡፡ ይሄንን ቢሮ ቦታውን የሰጣቸው ቀበሌው ነው፡፡ የገንዘብ እገዛው የእየሩሣሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ነው፡፡ ፎረሙና ማህበሩ በመተባበር ይሠራሉ፡፡” ነበር ያለኝ መንገድ ላይ፡፡ ፀጋው ገ/መድህን የተባለው የማህበሩ ሥራ አስፈፃሚ ሰብሳቢ “ልምድ መዓት አለኝ!” አለኝ፡፡ ቀጥሎም “የ5 ቀበሌዎች ህብረት ነው፡፡ 01፣ 03፣ 04፣ 05፣ 06 ቀበሌ ነዋሪዎች ቀበሌ አቀፍ ልማት ማህበር፡፡ የተመሠረተው መጋቢት 2003 ነው፣ የዛሬ ሁለት ዓመት። 1992 ጠባሴ 09 ጀመረ፡፡ 04 እያለ ቀጠለ፡፡

አንዳንድ ቀበሌዎች ዕውቅና እያገኙ ወደ ማህበራት ሲለወጡ ማህበራት ውስጥ የነበርነው ሰዎች ግን በልማት ኮሚቴ በየቀበሌው ነበር የምንሠራው፡፡ ተወያየንና “ዕውቅና ለማግኘት ማህበር መሥርተን እንሞክር” አልን፡፡ ተስማማን፡፡ መጋቢት ላይ ፈጠርን፡፡ ዓላማችን በመደራጀትና በራስ መተማመን ልማት ተስፋፍቶ ማየት ነው፡፡ አባይንም እንገድባለን) የከተማ ግብርናም በዋነኛነት አለ፡፡ በ5ቱም ቀበሌዎች ኑሮ ዝቅተኛ የሆኑ ሰዎች እየተመለመሉ የእርሻ መሣሪያ ድጋፍ እየተደረገላቸው፣ ዘር ይሰጣል፡፡ በዓይነቱ እንዴት እንደሚዘሩ ሥልጠና ተሰጥቷቸው ነው፡፡ ቀይ ሥር፣ ሠላጣ፣ ቆስጣ፣ ይዘራሉ፡፡ ኮሚቴውና ቀበሌ ይመለምላቸዋል። ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ አሁን ማህበረሰብን ከፈጠርን በኋላ ግን በገቢ ይተዳደራሉ፡፡ ምን ዓይነት ገቢ ብትል፣ እህል መጋዘን አለን፡፡ ለገቢያችን ዱቄት እያስገባን ነው፡፡ ጄክዶ Phase out ሲያደርግ ገቢ እንፈጥርና በራሳችን እንንቀሳቀሳለን፡፡ እስካሁን በጋራ እየሠራን ነው፡፡ በሂደት የወፍጮም ጥቅም እናስባለን፡፡ ለ2006 ከባለሃብቶች ፣ ከNGOዎች፣ ከእኛም አባላት አድርገን በትርፉ እንጠቀማለን፡፡ የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት የምንለው፤ ቀደም ሲል ጄክዶ ከመምጣቱ በፊት የከተማ ግብርና አይታወቅም ነበር፡፡ አሁን ግን እያንዳንዱ ሰው ጓሮው አትክልት አለ፡፡ የምድብ ፍጆታውን እገዛ አደረገ ማለት ነው፡፡ ፅዳቱንም ይጠብቃል፡፡

በጣም በርካታ ሰዎች እየሸጡም እየተጠቀሙ ነው፡፡ በከተማ ግብርና የተመለመሉ የዝቅተኛ ህብረተሰብ ክፍሎች ፓም ሁሉ የተከሉ አሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ህዝቡ ጓሮዎን የሚያዳፍን አይሆንም፤ ዘላቂ ነው፡፡ ሳይገነዘብ በፊት ለከብት መኖ እንኳን የሚሆን አልነበረውም፡፡ ሣማና አራሙቻ ነበር ያለው፡፡ አሁን ከነቃ በኋላ ከውጪ አያገባም፤ እንዲያውም ለሌላ ይሰጣል፡፡ ምግብም ሽያጭም አለው፡፡ ያ ብቻ አይደለም፡፡ የበግ ማድለቢያ ያላቸውም አሉ፡፡ አድልቦ ገንዘብ ያገኛል፡፡ “በጉን ወደ ሽሮ እለውጠዋለሁ ልጆቼን እመግባለሁ” ያሉኝ እናት አጋጥመውኛል፡፡ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ሁሉ ገዝተን እናድላለን፡፡ በነፃም ባይሆን በረጅም ጊዜ ክፍያ በሚመልሱበት መልኩ እናድላቸዋለን፡፡ እንደ ብድር እናግዛቸውም፡፡ “የእኔ አስተያየት ደሞ” ያለችኝ ወጣት፤ ስሜ መስከረም ታደሰ ይባላል፡፡ የማኅበሩ ፀሐፊ አመቻች ሠራተኛ ነኝ፡፡ volunteer ነን የቅጥርም ሠራተኛ አለ፡፡ አትክልት ብቻ ሳይሆን ከብት እርባታ፣ ዶሮ እርባታና በግ እርባታ አለ፡፡ መጀመሪያ በየቀበሌው ያሉ ኮሚቴዎች አሉ በነሱና በአመቻቾች አማካኝነት ይመለመላሉ፡፡

ሠፈሬዎቹ ዝቅተኛ የድሀ ድሀዎች ናቸው፡፡ በትንሽ ቦታ የማምረት የግንዛቤ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ እቺን ጠረጴዛ በምታህልም ቦታ ቢሆን እንዴት እንደሚዘራ ይማራል፡፡ “ችግር የፈጠራ እናት ናት!” ውሃ የሌለው ደሀ እንኳ ከእጅ መታጠቢያው፣ ከዕቃ፣ ከልብስ የሚፈሰውን ውሃ ቆጥቦ አትክልቱን ያጠጣል፡፡ አትክልት ህይወትን ሙሉ በሙሉ ባይለውጥም በተወሰነ ደረጃ ለውጥ አለው፡፡ አብዛኛው ሹሮ ነው እሚባለው፡፡ አትክልት ይጨመርበታል፡፡ ቢያንስ ቆስጣ፣ ካሮት፣ ጐመን ይኖረዋል፡፡ ጥሩ ምግብ በልቶ ት/ቤት የሚሄድ ልጅ ይኖራል፡፡ ጽዳት መጠበቅንም ያውቃሉ፡፡ ዓይናለም የሺጥላ የ03 አመቻች ናት፡፡ “መሸጥና ገንዘብ ማግኘት ሲችሉ ያንን ሙሉውን አይጠቀሙበትም፡፡ 2ትም ትሁን 3 ብር ቆጥበው ያስቀምጣሉ፡፡ ቤት ለቤት ሄደን እንቆጣጠራለን። አሁን ገበያ ሊወጡ የተዘጋጁ አሉ፡፡ በግ አርብታ ቤት የሠራችም አለች -ሥልጠና ወስዳ፡፡” አለች፡፡ ሰብሳቢው ማህል ገባ - “የዚህ ማህበረሰብ ጉባዔተኛ 50 ሰው ነው፡፡ ማን ማነው? የቀበሌ አንድ 10 ሰው፣ ሥራ አስፈፃሚ የቀ 4-5-6 ንዑስ ብለነዋል ንዑሱ ከአመቻቾች ጋር ያን የከተማ ግብርና ይከታተላል፡፡ ሪፖርት ያደርጋል፡፡ ሲያስፈልግ ማህበረሰብን ጠርቶ እንዲያይ ያደርጋል፡፡ መጀመሪያ ከእየሩሳሌም ጋር ስንመለምል ዝቅተኛውን ነው የምንመለምለው፡፡ ልጅ የሌለው ሰው ከሆነ ዶሮ ነው እምንሰጠው፡፡ ልጆቹም የከተማ ግብርና ውስጥ ይገባሉ፡፡ እየሩሳሌም ከየትም ብሎ ባለሙያ ያመጣል - በግብርና፡፡

ይሄ ቢሮ የእኛ ነው - መንግሥት ነው ቦታውን የሰጠን። ተቀራርበን እንሠራለን፡፡ እንጠይቃለን ይተባበረናል፡፡ ያም ሆኖ፤ እንደሌላው አገር አደለም - ገና ይቀደናል፡፡ መጋዘኑን ተከራይተን ነው፡፡ ቦታ እንዲሰጠን እየጣርን ነው፡፡ ኪራይ ለሌላ የህብረተሰብ አገልግሎት ይውላል፡፡ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ፣ የሠራተኞች ማህበር ጉዳይ አብሮን ነው፡፡ እሚሰጡን ይመስለናል፡፡ ይሄ ካልሆነማ እዚያው ፈላ እዚያው ደላ ይሆናል!...የልምድ ልውውጥ ጉዞም እናደርጋለን፡፡ ጋይንት፣ ጐጃም፣ ደብረዘይት፣ ድሬዳዋ…ሄደናል፡፡ ከዚያ ከፍተኛ ቅናት ነው ያደረብን፡፡ ለምሳሌ ኮልፌ የዕድር ህብረት አለ፡፡ ከራሱ አልፎ ካገር አገር እየዞረ እያደራጀ NGO ሆኗል፡፡ ጄክዶም ሁሌ ከጐናችን አለልን፡፡ የሩጫ ጊዜ ላይ ነን፡፡ ሥራውን ማስፋፋት አለብን፡፡ እየሩሳሌምን ለመተካት ነው አሳባችን፡፡ እሱ ያደራጃቸውን ዝቅ ዝቅ ያሉትን መርዳት ማጐልበት አለብን፡፡ ማህበሩ ነው በሥራ የሚያግዝ፡፡ እየሩሳሌም በገንዘብ ነው፡፡ እርግጥ አንዳንዶች ከስረው ይመጣሉ፡፡ የጋራ ስብሰባም አድርገን ሄደንም የልምድ ልውውጥ አድርገን እንገናኛለን፡፡ እነሱም መጥተው ያዩናል ሥራችንን እንፈትሻለን፡፡ ከዕድር ህብረትም፤ ከልማት ማህበርም፣ አምቻችተው ሳይሸፋፍኑ ይነጋገራሉ፡፡

መተራረምና መተጋገዝ አለ፡፡ ከሰው ይልቅ መሬቱ ይናገራል፡፡ 36 ማኅበራት ጥምረት ፈጥሯል፡፡ ከጐናችን አለ፡፡ በ6 በ6 ወር ማህበራቱን ምዘና ያረጋል፡፡ የፎረሙ መሪ እኔ ነኝ፡፡ እንደ ጉባዔ እርስበርሱ እንዲወያይና እንዲፋጭ ያደርጋል፡፡ ይህ ብቻ አደለም\11 አገር አቀፍ ፎረም ለማቋቋም Network ተጀምሯል፡፡ አቅም ለማግኘት ጥረት አለ፡፡ አቅም ያለው ከመንግሥት ጋር ሆኖ ችግር ይፈታል፡፡ አሁን 31 ጠንካራ ማኅበራት አሉት፡፡ ልምድ መዐት ነው፡፡ ከቤት ቤት አትክልት ጉብኝት ላድርግ አልኳቸውና ቀበሌው ውስጥ መዟዟር ጀመርንና ባለ አትክልቷን እናት አገኘኋቸው፡፡ ደጃቸው ላይ መሸጫ ሱቅ ሊጀምሩ ነው፡፡ “ካሮት ነበረ። ተሸጧል፡፡ ነጭ ሽንኩርት አረኩት፤ ልቀይር ብዬ ነው። ተሸጧል ቆስጣው አሉ፡፡ (አነጋገራቸው ግጥም ይመስላል እንዴት እንደነገሩኝ ቀጥሎ እዩ:- “ፖም አለኝ፡፡ በሶቢላም አለኝ፡፡ ልጄም ደሞ ታግዛለች፡፡ ቁጭ ሲሉ እንቅልፍ ነው፡፡ ሲሰሩ እግዜርም ያግዛል፡፡ አስሙ ነው አላሰራኝ ያለው፡፡ ላስተማረን፤ ይሄን ሥሩ ላለን መልካም እንጀራ ይስጠው በርቱ እሚሉን ይባረኩ ከሠራሁ ምን ችግር አለው፤ አትክልቱን ወደ ሽሮ ፣ ይሄው እየለወጥኩት ነው!” በፍቅር ነው እማማን ያዳመጥኳቸው! ኃይለኛ ጥበባዊ ልበ - ሙሉነት ነው ያላቸው!! (ጉዞዬ ይቀጥላል)

Read 2961 times