Saturday, 09 November 2013 11:02

‘በሰው አጥር መንጠላጠል…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ስሙኝማ…‘ኳሱ’ ደረሰ አይደል! አንድዬ ‘በሰው አገር’ ከአጠገባችን አይለየንማ! ሀሳብ አለን… አሁንም ቢሆን ሚዲያ ላይ ያለን ሰዎች…አለ አይደል አስተያየት ስንሰጥ ሁለቴ ብናስብ አሪፍ ነው። አሁንም መታወቅ ያለበት ነገርዬው የእግር ኳስ ግጥሚያ ነው፣ የሰላም መድረክ ነው፡፡ ካሸነፍን ለዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ እናልፋለን፣ ከተሸነፍን አናልፍም… አለቀ፡፡ ከእግር ኳስ ጨዋታ ውጪ የሚያስመስሉ ስሜታዊ አነጋገሮች ላይ ጥንቃቄ ይደረግልንማ! “ማታ ነው ድሌ!” ለማለት ያብቃን! ስሙኝማ…የጃፓኖች ተረት ምን ይል መሰላችሁ…“በአንተ ላይ የተደረጉ መጥፎ ነገሮችን አሸዋ ላይ ጻፋቸው፣ ግን ለአንተ የተደረጉ መልካም ነገሮችን በእብነበረድ ላይ ጻፋቸው፡፡” አሪፍ አባባል አይደል! ሳላውቀው ቀርቼ ይሆናል እንጂ በአማርኛም ይሄን የሚገልጹ ወርቅ አባባሎች ይኖራሉ፡፡ እናላችሁ…ዘንድሮ ችግር የሆነብን…አለ አይደል… መልካም ነገሮች የማድረግ ባህል የት እንደሄደ ‘‘የበላው ጅብ ለምን አልጮህ እንዳለ’ ነው፡፡ የምር እኮ… እንደውም ሰዎች መልካም ነገር ሲያደርጉ ስናይ የምንገረምበት ደረጃ እየደረስን ነው። ዛሬ በአጥር ተንጠላጠሎ “እስቲ ቡና መቁያሽን አውሺኝ…” ማለት ብርቅ እየሆነ ነው፡፡ “ገበያ ደርሼ እስክመጣ ቤቴን ጠብቂልኝ…” ማለት ብርቅ እየሆነ ነው፡፡ “መጽሐፉን አንብቤ እንድመልስልህ…” መባባል ብርቅ እየሆነ ነው፡፡ “ምን የማግዝህ ነገር አለ…” መባባል ብርቅ እየሆነ ነው፡፡ ታዲያላችሁ…አይደለም በእብነ በረድ የምንጽፈው… ጭርሱን በምንም ነገር ላይ የምንጽፈው መልካም ነገር እያጣን ነው፡፡ በቦታው ምን ተተካ መሰላችሁ…ምቁነት! ከ‘ቦተሊካ’ ጀምሮ (“በተለይ ቦተሊካ…” የሚለውን ሀረግ ለመጠቀም ጥናት እያካሄድኩ ነው፡፡ ልክ ነዋ…‘የደላውም’ ‘ያልደላውም’… ‘ቦተሊከኛ’ አብሮ “አሼሼ ገዳሜ፣ መቼ ነው ቅዳሜ…” ሲባባል ከርሞ ድንገት “ዓይንህ ለአፈር…” የሚባባለው የተደበቀ ምቁነት ቢኖረው አይደል!) …አለ አይደል… በ‘ቢዙ’ በሉት፣ በወዳጅነት በሉት፣ በእሷና በእሱ ግንኙነት በሉት…መሪያችንን የሚዘውረው ‘ምቁነት’ እየሆነ ነው፡፡ እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ድሮ ‘መንፈሳዊ ቅናት’ የሚባል ነገር ነበር አይደል! (የቅናት ጨዋታ ከመጣ ይቺን ስሙኝማ…ባል አገር ሰላም ብሎ ተቀምጦ ጋዜጣ ያነባል፡፡ ሚስትየው ትንደረደርና በመጥበሻ አናቱን ታቀምሰዋለች፡፡ ባልየውም ደንግጦ “ምን ሆነሻል! ጭራሽ በመጥበሻ ትመችኛለሽ!” እሷም ምን ትለዋለች “ኪስህ ውስጥ ወረቀት አገኘሁ፡፡ ላዩ ላይ ጄኒ የሚል ስም ተጽፎበታል፡፡ ጄኒ ማነች?” ባል ሆዬም ምን ብሎ ይመልሳል… “ያለፈው ሳምንት የፈረስ ውድድር ተካፍዬ ነበር፣ ጄኒ የፈረሴ ስም ነው፡፡” ነገርዬው በዚህ አልቆ ከአንድ ሁለት ቀን በኋላ ሚስት እንደገና ተንደርድራ ባሏን በመጥበሻ ትነርተዋለች፡፡ “አንቺ ሴትዮ አሁን ደግሞ ምን ሆንሽ?” ይላል። ሚስት ምን ብትለው ጥሩ ነው… “ስልክ ላይ ጄኒ ትፈልግሀለች፡፡” አንዳንዱ ሰው እንዴት ጨካኝ ነው…‘እነሆ በረከት’ ካለ በኋላ ፈረስ ያደርጋታል! (ነው…ወይስ ነገርዬው ቅኔ አለበት!) እናላችሁ…በቃ “እንትና የደረስበትማ መድረስ አያቅተኝም…” ምናምን ብሎ እንትና ደረጃ ለመድረስ ጥርስ ነክሶ መሥራት አይነት መንፈሳዊ ቅናት አለ፡፡ ይሄ ምንም ክፋት የለውም፡፡ ‘እንትና’ ላይ የሚደርስበት የለም፣ ምኑም፣ ምናምኑም አይነካም…የእኛ እሱ ደረጃ መድረስ ከእሱ ላይ አንዲትም ሳንቲሜትር የሚነካበት ነገር የለም፡፡ የዘንድሮ ቅናት ግን…አለ አይደል…መንፈሳዊ የለ፣ ምናምናዊ የለ፣ ምን አለፋችሁ…ዋናው ነገር “እንትና ከደረሰበት ቦታ ላይ እንዴት ነው ፈንግዬ አፈር የማስቅመው?” አይነት ነገር ነው፡፡ የምር…አገር በመመቀኛኘት እየተተረማመሰላችሁ ነው! ሀሳብ አለን… ግን የማህብረሰብ ጥናት ባለሙያዎች አንድ በሉንማ! …ለምንድነው፣ አይደለም አብረን ያደግን ወይም የተጎራበትን… በምንም በምናምንም የማንገናኘውና ትውውቅ እንኳን የሌለን ሰዎች አንዳችን ሌላችንን ‘አፈር ድሜ ማስጋጥ’ የምንሞክረው! የቅናት ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ሴትዮዋ አዲስ ልብስ ትገዛላችሁና መስታወት ፊት ቆማ ራሷን ታያለች፡፡ ባየችውም አልተደሰተችም። እናላችሁ…ለባሏም “በዚህ አዲስ ቀሚስ በጣም አስቀያሚ የሆንኩ ይመስለኛል፡፡ ምን ይመስልሀል?” ትለዋለች፡፡ ባል ምን ቢል ጥሩ ነው… “ዓይንሽ በደንብ አጥርቶ ያያል ማለት ነው፡፡” አሪፍ አይደል። አሀ…እሷ የጠበቀችው “ኧረ ምን በወጣሽ፣ አንቺን የመሰለች ቆንጆ! አስቀያሚው ቀሚሱ እንጂ አንቺ አይደለሽም፣” ለመባል ነበር፡፡ ዘንድሮ ብዙ ነገር የተበላሸው “ዓይንሽ በደንብ አጥርቶ ያያል ማለት ነው፡፡” የሚል ሰው እየጠፋ ነው። እውነቱን የሚናገር ባል፣ እውነቱን የምትናገር ሚስት፣ እውነቱን የሚናገሩ ሰዎችን ሙሉ ለሙሉ አያጥፋብን፡፡ የባልና የሚስት ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ባልና ሚስት ‘ኩሼ’ ብለዋል፡፡ (‘አራድነት እንዳይጠፋ’ ብዬ ነው፡፡) ሚስትየዋ የሆነ ህልም ታይና ደንግጣ ትነሳና ታማትባለች፡፡ ትንሽ ቆይቶ ማልቀስ ጀመረች፡፡ ባልም እያጽናናት “ምን ያስለቅስሻል?” ይላታል፡፡ እሷም ምን ትላለች… “በህልሜ አንድ ቅልጥ ያለ ሀብታምና መልከ መልካም ወንድ ከአንተ ላይ ነጥቆ አግቶኝ ሲወስደኝ አየሁ፡፡” ባልም “አይዞሽ፣ አታልቅሺ፡፡ ህልም ነው እኮ!” ይላታል፡፡ ሚስት ምን ብትል ጥሩ ነው…“እኔን ያስለቀሰኝ ታዲያ ህልም መሆኑ አይደለም!” ብላው እርፍ አለች፡፡ የኑሮ መጠንሽን ከእኔ ጋር አትለኪ በዘመዶችሽ ሀብት ይቅር አትመኪ የሚለው አይነት ግጥም በአዲስ መልክ ያስፈልገናል! የኑሮ መጠንሽን ከእኔ ጋር ለኪ በህልሙ ውሽማሽ ይቅር አትመኪ ይባልልንማ! ቂ…ቂ…ቂ… እናላችሁ… ብዙዎቹ የዘንድሮ ወሬዎች…አለ አይደል…“እሱ እኮ…” “እሷ እኮ…” የሚል ነገር ነው፡፡ የበርካታ ሰዎች ስምና ሰብእና በማያውቁትና ቤሌሉበት ነገር መሬት ለመሬት የሚጎተተው መመቀኛኘት ‘ኮምልሰሪ’ ባህላችን እየሆነ ስለመጣ አይመስላችሁም? ታዲያላችሁ…“እከሌ ከእነ እከሌ ጋር ታየ…” “ከእነ እከሌ ጋር ዕቁብ ትጠጣለች…” “የሼራተንን የሚያስንቅ ፎቴ አስገብቷል…” ምናምን የሚባሉ ነገሮችን ተከትሏቸው የሚመጣው “እንዲህ የሚያደርገው እንዲህ ስለሆነ ነው…” አይነት ‘የማስወጋት’ ነገር ነው፡፡ ኮሚክ እኮ ነው…አዲስ የጠረዼዛ ልብስ ስትለውጡ የቤት ኪራይ የሚጨምር አከራይ የሞላበት ዘመን ነው እኮ! ዕቃ መግዛት ችለው ገና ለገና የቤት ኪራይ ይጨመርብናል ብለው ፈርተው ‘ጭጭ ምጭጭ’ ብለው የተቀመጡ ሰዎች እናውቃለን፡፡ ደግሞላችሁ…ከፊሉም በሩን እንደ ናሳ ምርምር ጣቢያ ግጥም አድርጎ ዘግቶ የሚቀመጠው የፎቴ ልብስ ተለውጦ ሲታይ በሺህ አምስት መቶዋ ላይ ሌላ ሺህ እንዳይጨምሩበት ነው፡፡ እናላችሁ…የፎቴ ልብስ ስለተለወጠና አዲስ ትሪ ስለተገዛ ኪራይ የሚጨምሩ ‘ምቁነት’ ነው፡፡ (ከጫንጮ ገበያ ተቀርጦባት! እንደተባለው ነው፡፡) እናላችሁ…“ምቀኛ አታሳጣኝ”… ማለቱ ጥርስን ነክሶ ለመሥራትና ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ለመድረስ ጥሩ ቢሆንም የዘንድሮ ምቁነት ግን ‘በአይነቱ ልዩ የሆነና እኛ ዘንድ ብቻ የሚገኝ’ ብርቅዬ ነገር እየመሰለ ነው፡፡ በሆነ ባልሆነው ‘በሰው አጥር እየተንጠላጠልን’… “ከአቧራ ባልደባልቀው እሱን አያድርገኝ አይነት ‘ምቁነትን’ የሆነ ሱናሚ ይዞልን ጥርግ ይበል፡፡ ‘ምቁነትን’ ታሪክ የሚያደርግ ነገር ያምጣልንማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!!

Read 5829 times