Print this page
Saturday, 09 November 2013 10:41

ኢትዮጵያውያን የመንግስትን ስለላ አይፈሩም፤ ሁለመናቸው በመንግስት እጅ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአሜሪካ የስለላ ተቋም፣ አለምን ከዳር ዳር በሚያዳርስ የመረጃ መረብ፣ የውጭ ዜጎችን (የጠቅላይ ሚኒስትሮችና የፕሬዚዳንቶች ጭምር) የስልክና የኢሜይል ልውውጦችን የቱን ያህል በስፋት እንደሚሰልል ሲታይ ጉድ ያሰኛል። በእርግጥ የስለላ ተቋሙ የአሜሪካ ዜጐችን በዘፈቀደ አልሰልልም ብሏል፡፡ የዜጐች የግል ሕይወትና የመልእክት ልውውጥ በመንግስት መነካት እንደሌለበት በአገሪቱ ሕገመንግስት ታውጇላ። የዜጐችን የስልክ እና የኢሜይል መልእክት የምበረብረው፣ በተጠርጣሪዎች ላይ በማተኮርና ፍርድ ቤትን በማስፈቀድ ብቻ ነው ይላል - የአሜሪካ የስለላ ተቋም። ታዲያ “ፍርድ ቤት” ሲባል፣ የወትሮው አይነት አይደለም። በሚስጥር የሚሰራ ልዩ ፍርድ ቤት ነው። ማዘዣ ወረቀቱም በሚስጥር የሚጠበቅ ስለሆነ፣ ከጊዜ በኋላ የፍርድ ቤቱን ውሳኔዎችና ትዕዛዞች መመርመር ያስቸግራል። ፍርድ ቤትን ማስፈቀድ በኢትዮጵያ አይሰራም በእውነቱ፣ እንዲህ አይነቱ ድብቅ የፍርድ ቤት አሰራር፣ ከታላቋ የነፃነት አገር (ከአሜሪካ) የሚጠበቅ አይደለም።

ለማንኛውም፣ የስለላ ተቋሙ “የፍርድ ቤት” ማዘዣ በማቅረብ ባለፉት አምስት አመታት የተለያዩ መረጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል፡፡ ጉግል፣ ያሁ፣ ሆትሜይል፣ ፌስቡክ እንዲሁም ኤቲኤንድ ቲ የመሳሰሉ የኢንተርኔት እና የስልክ ኩባንያዎችም፣ የመቶ ሺ ገደማ ደንበኞች መረጃ ለስለላ ተቋሙ ለማስረከብ መገደዳቸውን ገልፀዋል። ኩባንያዎቹ የሕግ ግዴታ ሆኖባቸው እንጂ፣ የአንድም ሰው መረጃ አሳልፈው መስጠት አይፈልጉም - እንጀራቸው ነዋ። በደንታ ቢስነት የደንበኞችን መረጃ እያወጣ ለመንግስት የሚዘረግፍ ኩባንያ፣ የቱንም ያህል ግዙፍ ቢሆን መንኮታኮቱና በአጭር መቀጨቱ አይቀርም። ደንበኞቹ ይሸሹታል፤ ፊታቸውን ወደ ሌላ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ በማዞር ጀርባቸውን ሲሰጡት፣ በኪሳራ ይፈራርሳል። ኩባንያዎቹ እንጀራቸውን ማጣት አይፈልጉም፤ እናም በተቻላቸው መጠን የደንበኞቻቸውን መረጃ ለመጠበቅ በሚያደርጉት ጥረት ለመንግስት ትልቅ ፈተና መሆናቸው አይገርምም።

በእኛ አገር ግን፣ መንግስት ይሄ ሁሉ ጣጣ አይኖርበትም። የኢንተርኔትና የስልክ አግልግሎት ሁሉ በመንግስት እጅ ነዋ። በፈለገ ጊዜ ባሰኘው መጠን፣ የስልክ ንግግሮችን ሲያዳምጥ ቢያድር፣ የፅሁፍ መልእክቶችን ሲበረብር ቢውል ማንም አያውቅም። ኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ይሸሹኛል ብሎ አይሰጋም። ከቴሌ ሸሽተን የት ልንደርስ! ሌላ አማራጭ የለንም። እናም፣ ኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞችን መረጃ አሳልፎ ላለመስጠትና ጠብቆ ለመያዝ የሚገፋፋ ጫና የለበትም። በአጭሩ፤ የስልክ እና የኢንተርኔት ግንኙነታችን በሙሉ በመንግስት እጅ ነው። የሰዎችን የስልክ እና የኢሜይል ግንኙነትን ለመጥለፍ ፖሊስ ፍ/ቤትን ማስፈቀድ እንደማያስፈልገው፣ የፀረ ሽብር ህጉ ይደነግጋል “ሁሉም በእጄ ሁሉም በደጄ” ነው ነገሩ፡፡ በፍ/ቤት ያልተፈቀደ ድብቅ ስለላስ? የአሜሪካ የስለላ ተቋም በ“ፍርድ ቤት” ማዘዣ አማካኝነት የሚሰበስባቸው መረጃዎች አያረኩትም። ተጨማሪ ብዙ መረጃ ለመሰብሰብ፣ በተለያዩ የኢንተርኔትና የስልክ ኩባንያዎች ላይ በድብቅ ስለላ እንደሚያካሂድ ባለፈው ሳምንት የተሰራጩ ዘገባዎች ገልጸዋል።

እንዴት በሉ። የአሜሪካ የስለላ ተቋም፣ ያለ “ፍርድ ቤት” ማዘዣ የጐግል ወይም የማይክሮሶፍት የመረጃ ማዕከላትን መበርበር አይችልም። በድብቅ መሰለልም ቀላል አይሆንለትም። በቴክኖሎጂ የተራቀቁት ኩባንያዎች፣ የየራሳቸው የመረጃ ማዕከላት ላይ ከፍተኛ ጥበቃ ያካሂዳሉ። የመረጃ ማዕከላትን የሚያገናኙ የስልክና የኢንተርኔት ማስተላለፊያ (የፋይበር ኦፕቲክስ) መስመሮችስ? አገር አቋራጭ መስመሮች ላይ፣ ከጫፍ እስከ ጫፍ ጥበቃ ማካሄድ ከባድ ነው። የስለላ ተቋሙም፣ የኢንተርኔት ኩባንያዎች ዋና ዋና የግንኙነት መስመሮችን በድብቅ በመጥለፍ ነው መረጃዎችን እንደሚሰበስብ የተዘገበው። በእርግጥ፣ በዘገባዎቹ ምክንያት ከፍተኛ ጫና እንደሚደርስበት የተገነዘበው የስለላ ተቋሙ፣ ሳይውል ሳያድር ዘገባዎቹን አስተባብሏል - “የኩባንያዎቹ የመረጃ ማዕከላት ላይ ስለላ አላካሄድኩም” በማለት። “የግንኙነት መስመሮች ላይስ ስለላ አካሂደሃል ወይ?” ተብሎ ሲጠየቅም የተቋሙ ምላሽ ተመሳሳይ ነው። “የመረጃ ማዕከላት ላይ ስለላ አላካሄድኩም” የሚል ሆኗል የተቋሙ ምላሽ፡፡ አጣብቂኝ ውስጥ የገባ ይመስላል፡፡

በአገራችን ግን፣ መንግስት በድብቅ መሰለል አያስፈልገውም፤ ውዝግብና ጭቅጭቅ ውስጥ የሚገባበት ምክንያትም የለም። የስልክ እና የኢንተርኔት ግንኝነቶቻችንን የሚያከማቹ የመረጃ ማዕከሎች በሙሉ በመንግስት እጅ ናቸው። የስልክ ንግግሮችን ጨምሮ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ የምናካሂዳቸው ግንኝነቶችን የሚያመላልሱ ዋና ዋና የመረጃ ማስተላለፊያ (የፋይበር ኦፕቲክስ) መስመሮችም የመንግስት ናቸው። ያሻውን ቢያደርግ ማን ይጠይቀዋል? “1ለ5” ማደራጀት ያልቻሉ፣ ለስለላ ይደክማሉ መቼም፣ የአሜሪካ የስለላ ተቋም፣ የስልክና የኢሜይል ልውውጦችን እየጠለፈ የሚሰበስበው፣ ማን መቼ ከማን ጋር እንደተገናኘና ምን እንዳወራ ለመሰለል ነው። የኛ አገር መንግስት ግን፣ መረጃ ለመሰብሰብ መባተል አያስፈልገውም። ማን መቼ ከማን ጋር እንደሚገናኝ ለማወቅ አይደክምም። ይልቁንስ፣ በ“1ለ5” አደረጃጀት ማን ከማን ጋር መገናኘት እንዳለበት ትዕዛዝ ያስተላልፋል። በትምህርት ቤትም ሆነ በስራ ቦታ፣ በገጠርም ሆነ በከተማ፣ “1ለ5” እንዲደራጁ የታዘዙ ዜጎች፣ በሳምንት ሁለት ቀን በየትኛው ሰዓት መገናኘት እንዳለባቸው መመሪያ የሚመጣባቸው ከመንግስት አካላት ነው። ተገናኝተው ምን ምን ማውራት እንዳለባቸውም ጭምር ትዕዛዝ ይደርሳቸዋል።

ታዲያ፣ የዜጎችን ህይወት በእጁ አስገብቶ ኑሯቸውን በትዕዛዝ የሚመራ መንግስት፣ ለምን ብሎ ይሰልላቸዋል? የአሜሪካ መንግስት የሰዎችን የመኪናና የአፓርትመንት ኪራይ በድብቅ ለመሰለል ይጣጣራል፡፡ ሰዎች የት እንዳደሩ ወዴት እንደተጓዙ ለማወቅም በስውር ይጣጣራል፡፡ የአገራችን መንግስት ግን ለድብብቆሽ ጊዜ አያጠፋም፡፡ እያንዳንዱ የቤት እና የመኪና አከራይ፣ የየእለቱን መረጃ መዝግቦ፣ በራሱ ወጪ መጥቶ ያስረከበኝ በማለት በኢቲቪ መመሪያ ያስተላልፋል፡፡ አዋጅ ማርቀቅና ማጽደቅ፣ ወይም ደንብ ማዘጋጀት እንኳ አያስፈልገውም፡፡ የዜጐች የመንቀሳቀስ ነፃነት በህገመንግስት በግልጽ እውቅና ቢሰጠውም፤ ሰዎች ከከተማ ከተማ በማታ እንዳይንቀሱ በመግለጫ ተከልክለው የለ! በትራንስፖርት ሚኒስቴር ተግባራዊ የተደረገ “የሰዓት እላፊ” ልንለው እንችላለን፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ ወደ አረብ አገራት መሄድ ተከልክሏል የሚል መግለጫ አውጥቷል፡፡ ህጋዊውን ስርዓት ተከትለው ምዝገባ በማካሄድ በየአመቱ በአማካይ 130ሺ ኢትዮጵያውያን ለስራ ወደ አረብ አገራት ሲሄዱ ቆይተዋል፡፡

በዚህ መሃል ነው፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድንገት ተነስቶ፣ “ጉዳት እንዳይደርስባችሁ ስለምጨነቅላችሁ እንዳትጓዙ አዝዣለሁ” የሚል መግለጫ ያወጣው፡፡ የመንቀሳቀስ ነፃነት የሚባለው የህገመንግስት አንቀጽ የት ደረሰ? የገንዘብ ሚኒስቴርስ፣ “ደሞዛችሁን እንዳታባክኑ ስለምጨነቅላችሁ፣ ግማሽ ደሞዛችሁን እንድትቆጥቡ አዝዣለሁ” ብሎ መግለጫ ማውጣት አይችልም? “በራሴ ደሞዝና ገቢ መንግስት ምን አገባው” ብላችሁ ታስቡ ይሆናል፡፡ በእርግጥም የንብረት ባለቤትነትና ነፃነት የሚሉ የህገመንግስት አንቀፆች አሉ፡፡ ግን በርካታ አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት፣ ለቁጠባ ገንዘብ ለማስቀመጥ እንደሚገደዱ አታውቁም? የግል ባንኮችም፣ በየአመቱ ከሚሰጡት የብድር መጠን ከሩብ በላይ የሚሆነውን የመንግስት ቦንድ በመግዛት እንዲቆጥቡ ግዴታ ከተጣለባቸው ሁለት አመት አልፏቸዋል፡፡ በአጭሩ፣ መንግስት የዜጐችን እንቅስቃሴና የገንዘብ ልውውጥን ለመሰለል የሚደክምበት ምክንያት የለም፡፡

በየትኛው ሰዓት እና ወዴት አገር መጓዝ እንደምችል፣ ከደሞዛችን ምን ያህል መቆጠብና ለአስቤዛ እንደሚፈቀድልን ወይም እንደማይፈቀድልን በመግለጫ ማዘዝ እየቻለ፣ መንግስት የስለላ ጣጣ ውስጥ መግባት አይኖርበትም፡፡ የትምህርት ቤት ምዝገባና የስራ ስምሪትን፣ የሸቀጦች ግዢና ሽያጭን በተመለከተ መረጃ ለመሰብሰብ እነ አሜሪካ መከራቸውን ሊያዩ ይችላሉ፡፡ የአገራችን መንግስት ግን፣ ተማሪዎች የትኛው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መማር፣ በየትኛው የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ መለማመድ እንደሚችሉ ምደባ ማካሄድና መወሰን ይችላል፡፡ የሸቀጦችን ግዢ እና ሽያጭን ከነዋጋ ተመናቸው በመግለጫ ትዕዛዝ እንደሚያስተላልፍም እናውቃለን፡፡ ስኳርና ዘይት በጅምላ የሚከፋፈለው ለሸማቾች ማህበር ብቻ ነው ተባለ፡፡ ደግሞም በስኳርና በዘይት ብቻ አይደለም የዋጋ ተመን የወጣብን፡፡ የበግ እና የፍየል ቆዳ ከ40 ብር በላይ ማንም መሸጥ የለበትም የሚል መግለጫም ሰምተናል፡፡

አሁን ደግሞ የእንስሳትና የቆዳ ገበያ ውስጥ እነማን ሻጭ እና ገዢ ለመሆን እንደሚፈቀድላቸው የሚደነግግ ህግ ተዘጋጅቷል፡፡ ታዲያ መንግስት ለምን ሲባል፣ የስለላ ጣጣ ውስጥ ይገባል፤ ሁሉም በእጁ ሁሉም በደጁ፡፡ ዜጎች የሕይወታቸው ብቸኛ ባለቤት ሆነው እንደየፍላጎታቸው ካሰኛቸው ሰው ጋር መገናኘትና መደራጀት፣ መስራትና መገበያየት ሲችሉ፣ ኑሯቸውን በየራሳቸው የግል ፈቃድ በነፃነት እየመሩ፣ እንደየሃሳባቸው ያመኑበትን ነገር መናገርና መፃፍ ሲችሉ… ያኔ፣ “ማን ከማን ጋር እየተገናኘ ይሆን? ማን ምን እያወራ ይሆን?” ብሎ መሰለል ወግ ነው። ዜጎችን መሰለል፣ ተገቢና ጥሩ ስራ ባይሆንም፣ “ትርጉም” ይኖረዋል። የእያንዳንዱን ሰው ገመና ለማወቅ የሚደረግ ስለላ ነዋ። የዜጎች ግንኙነት ከመንግስት በሚመጣ የ“1ለ5” አደረጃጀት የሚታዘዝ፣ የዜጎች ወሬ ከመንግስት በሚመጣ “አጀንዳ” የሚመራ፣ የዜጐች ስራ እና ግብይት በመንግስት የስምሪትና የተመን መግለጫ የሚቦካ የሚከካ ሲሆን ግን፣ ስለላ የሚባል ነገር ጨርሶ “ትርጉም” ያጣል። የዜጎች ሕይወትና ኑሮ በመንግስት እጅ ከሆነ፣ ለስለላ የሚያነሳሳ “ገመና” ከየት ይመጣል?

Read 2714 times
Administrator

Latest from Administrator