Saturday, 09 November 2013 10:23

ታይቶ የማይታወቅ መግቢያ መውጪያ የሚያሳጣ ስለላ

Written by 
Rate this item
(14 votes)

            ኒውዮርክ ታይምስ ባለፈው መስከረም መግቢያ ላይ እንደዘገበው፣ የአሜሪካ ብሄራዊ የፀጥታ ኤጀንሲ (NSA) በየቀኑ 4 ቢሊዮን የስልክ እና የኢሜይል መረጃዎችን እየመዘገበ ያከማቻል። ዎልስትሪት ጆርናል በበኩሉ፣ NSA በአሜሪካ በየእለቱ በቢሊዮን ከሚቆጠሩ የኢሜይል ልውውጦች መካከል 75 በመቶ ያህሉን የመከታተል አቅም እንዳለው ገልጿል። ስለላው የስልክ እና የኢሜይል ብቻ ሳይሆን፣ የጉዞና የሆቴል አዳርን፣ የመኪናና የአፓርትመንት ኪራይን ጨምሮ የማያካልለው የህይወት ገጽታ የለም፡፡ የሱፐርማርኬት ሸቀጦች ግዥና ሽያጭን፣ የባንክ ብድርና የገንዘብ ልውውጥን፣ የትምህርት ቤት ምዝገባና የስራ ቅጥርን የሚገልፁ መረጃዎች ሁሉ ስለላ ይካሄድባቸዋል፡፡ የሚያመልጥ ነገር የለም የሞባይል እና የኢንተርኔት ስለላ በእርግጥ፣ “የስልክና የኢንተርኔት ግንኙነቶችን እየተከታተለ መረጃዎችን ይሰበስባል” ማለት፣ “ጆሮውን ደቅኖ ይሰማል፤ አይኑን ተክሎ ይቃኛል፤ በየሴኮንዱም ድምፅና ፅሁፍ፣ ፎቶና ቪዲዮ እየቀረፀ ያከማቻል” ማለት ላይሆን ይችላል።

ስልክ ደውለን ስናነጋግር፣ ሞባይላችን መረጃዎችን ይመዘግብ የለ? የንግግራችንን ድምፅ ባንቀርፀውም እንኳ፣ ወደ የትኛው የስልክ ቁጥር መቼ እንደደወልን ወይም እንደተደወለልን፣ ለምን ያህል ደቂቃ እንዳነጋገርን ማወቅ እንችላለን። እንዲህ አይነቱ መረጃ “ሜታዳታ” ይሉታል። የተቀረፀ ንግግር ደግሞ “ዳታ” ብለው ይጠሩታል። ኮምፒዩተር ላይ ፋይሎችን ስንከፍት የምናገኘውን ድምፅ ወይም ቪዲዮ፣ ፎቶ ወይም ፅሁፍ፣ “ዳታ” ይሉታል። የፋይሎች ስምና አይነታቸውን፣ መጠንና ቦታቸውን፣ መቼ እንደተቀመጡና መቼ እንደተከፈቱ የሚገልፅ የመረጃ ዝርዝር ደግሞ ሜታዳታ ይባላል። የአሜሪካ ብሄራዊ የፀጥታ ኤጀንሲ፣ ዜጎች በስልክ የሚያወሩትን በድምፅ እየቀረፀ፣ በኢሜይል የሚለዋወጡትን ፅሁፍ እየገለበጠ እንደማያከማች ይገልፃል።

“ማን ለማን መቼ ደወለ?፣ ለምን ያህል ደቂቃ አነጋገረ? ማን ለማን መቼ ኢሜይል ላከ?” እንዲህ የመሳሰሉ “ሜታዳታዎችን” ነው የምሰልለው ይላል NSA። ይቅርታ፣ “ሜታዳታዎችንም አከማቻለሁ እንጂ አልሰልልም” ባይ ነው NSA። “መረጃዎችን አከማቻለሁ፤ መረጃዎች ላይ አንዳች ምርመራ ወይም ስለላ የማካሂደው፣ አጠራጣሪ ፍንጭ ሲኖር ብቻ ነው” ይላል - ኤንኤስኤ። ፖፕላር ሳይንስ መጽሔት ሰሞኑን ባወጣው ዘገባው፣ የNSA አሰራር ተራራ በሚያክል የሳር ክምር ውስጥ፣ መርፌ ፈልጎ እንደማግኘት መሆኑን ያስረዳል። በአንድ ሰው ተነስቶ ሺዎችን የሚያዳርስ የስለላ ድር NSA በየእለቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ መረጃዎችን የሚያከማች ቢሆንም፣ ከመረጃው ብዛት የተነሳ እያንዳንዱን እየመዘዘ መመርመር አይችልም። ነገር ግን አቋራጭ ዘዴዎች አሉ። ፍንጮችን በማነፍነፍ ላይ የተመሰረተ ምርመራና ስለላ! የተቋሙ ስለላ እንዴት እንደሚካሄድ ፒኤም መፅሄት ሲያስረዳ፣ አንድ በሽብር ተግባር የሚጠረጠር ተፈላጊ የመን ውስጥ ይኖራል በማለት ይጀምራል።

ተጠርጣሪው ሞኝ ካልሆነ በቀር፣ በቀጥታ አሜሪካ ውስጥ ወደሚገኝ ምልምል አባል ስልክ አይደውልም፣ ኢሜይል አይልክም። ነገር ግን፣ እዚያው የመን ውስጥ፣ የስልክ ወይም የኢሜይል ግንኙነት ማድረጉ አይቀርም። እዚህ ላይ ነው ስለላው የሚጀምረው፡፡ ተጠርጣሪው ለማንና መቼ ደወለ? ለምን ያህል ደቂቃ አነጋገረ? ለእነማን መቼ ኢሜይል ላከ? ከእነማን መቼ ተደወለለት? …. በእነዚህ ሜታዳታዎች አማካኝነት፣ የተጠርጣሪው የግንኙነት መረብ በኮምፒዩተር ይቀናበራል። በዚህ መረብ ውስጥ መቶ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ብዙዎቹ ከተጠርጣሪው የሽብር ተግባር ጋር ግንኙነት የሌላቸው የቤተሰብና የዘመድ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፤ በሰፈርና በቢዝነስ የሚተዋወቁም ይኖራሉ። ነገር ግን ከመካከላቸው ውስጥ አንዱ የተጠርጣሪው የሽብር ሴራ ተባባሪ፣ አለቃው ወይም ተላላኪው ሊሆን ይችላል። ግን የትኛው እንደሆነ ለይቶ ለማወቅ ያስቸግራል። እናም በደፈናው፣ መቶዎቹ ሰዎች በስልክና በኢሜል የሚያደርጉት ግንኙነት እየተመዘገበ በኮምፒዩተር ይቀናበራል - በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያካልል ሌላ ሰፊ መረብ ተፈጠረ ማለት ነው። እነዚህ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችስ ከማን ጋር ይደዋወላሉ? ሌላ የተንቦረቀቀ ሦስተኛ መረብ መሆኑ ነው፡፡

በሌላ አነጋገር፣ “የተጠርጣሪው የጓደኛ፣ ጓደኛ፣ ጓደኛ…” እየተባለ የስለላ መረብ ይዘረጋባቸዋል፡፡ እንዲህ በአንድ የመናዊ ተጠርጣሪ ዙሪያ ያጠነጠኑ በርካታ የግንኙነት መረቦች እየተለዩ ክትትል ይደረግባቸዋል። በግንኙነት መረብ ውስጥ ከተካተቱት በአስር ሺ የሚቆጠሩ የስልክ ቁጥሮች መካከል አንዱ ወይም ሁለቱ፣ በሆነ አጋጣሚ ለአንድ የአሜሪካ ነዋሪ ሲደውሉ ነው፣ በNSA ኮምፒዩተሮች ውስጥ “ቀይ መብራት” ብልጭ የሚለው። ግን ምን ዋጋ አለው? ከመካከለኛው ምስራቅ በየጊዜው የሚደወልላቸው የአሜሪካ ነዋሪዎች በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ናቸው። ሁሉንም በተጠርጣሪነት መመርመር አይቻልም። ምን ተሻለ? NSA በየእለቱ መረጃ የሚሰበስበው የስልክና የኢሜይል ግንኙነት ላይ ብቻ አይደለም። የገንዘብ ልውውጦችንም ይመዘግባል፤ “ማን ለማን መቼ ምን ያህል ገንዘብ፣ ጌጣጌጥና ስጦታ አበረከተ?” በየደቂቃውና በየሴኮንዱ መረጃዎች እየተሰበሰቡ ይከማቻሉ። ይህም ብቻ አይደለም። “ማን፣ መቼ፣ ምን፣ ከየት ገዛ?” … በክሬዲትካርድ ከየሱፐርማርኬቱና ከየመደብሩ የተፈፀሙ የግዢ መረጃዎች ይከማቻሉ። የሆቴል እና የአፓርትመንት ክፍያዎችን፣ የትምህርት እና የስልጠና ምዝገባዎችን፣ የአውሮፕላንና የባቡር ትኬቶችን፣ የመኪና ግዢና ኪራይን በተመለከተም መረጃዎች ይሰበሰባሉ።

እነዚህ ሁሉ ይጠናቀራሉ። ግዙፍ ኮምፒዩተሮችና ተዓምረኛ ሶፍትዌሮች በአንድ የመናዊ የሽብር ተጠርጣሪ ዙሪያ የስልክና የኢሜይል ግንኘነቶቹን በመቃኘት የተጀመረው ‘ፍንጭ ፍለጋ’፣ ብቻውን ያን ያህል ጥቅም አይኖረውም፡፡ ከሌሎች መረጃዎች ጋር ሲቀናበር ግን ውጤቱ ለማመን የሚያስቸግር ይሆናል። “አንድ የአሜሪካ ነዋሪ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ ስልክ ይደወልለታል” ከሚለው ፍንጭ በተጨማሪ፤ “መኪና መከራየትን የሚያዘወትር ነው ወይ?” ተብሎ ይፈተሻል። ከውጭ አገርስ ገንዘብ ይላክለታል? ተቀጣጣይ ነገሮችን ለመስራት የሚያገለግሉ ሸቀጦችን ከሱፐር ማርኬት ገዝቶ ያውቃል? የአክራሪዎችን ፕሮፓጋንዳ በኢንተርኔት የሚከታተል ወይም የፈንጂ አሰራርን የሚያሳዩ ድረገፆችን መመልከት የሚያበዛ ከሆነም ተጨማሪ ፍንጭ ነው። የጥቃት ኢላማ ናቸው ተብለው ወደሚገመቱ ስፍራዎች በተደጋጋሚ የተጓዘ ወይም በአቅራቢያ አፓርታማ የተከራየ ከሆነም ያስጠረጥራል።

በየጊዜው የትምህርትና የስልጠና ቦታዎችን እየለዋወጠ ከተመዘገበም እንዲሁ! እነዚህ ሁሉ፣ “የአሸባሪዎች ልዩ ባህርይ ናቸው” ተብለው የሚጠቀሱ መለያዎች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹን ነገሮች የሚያሟላ የአሜሪካ ነዋሪ አለ ወይ? እንዲህ አይነት ሰው፣ ያለጥርጥር ለሽብር ጥቃት የተዘጋጀ ሰው ነው። ግን አለ ወይ? ይሄ ነው የ NSA ጥያቄ። NSA አሰስ ገሰሱን ሁሉ እያሰሰ የመረጃ መአት የሚያሰባስበው፣ እንዲህ አይነት ጥያቄዎችን ለመመለስ ነው። በእርግጥ፣ እንደተራራ የገዘፈ የመረጃ ክምር ላይ መቀመጥ ብቻውን በቂ አይደለም። ያን ሁሉ መረጃ በአጭር ጊዜ መፈተሽና ለጥያቄው ምላሽ መስጠት የሚችል የኮምፒዩተር አቅምና ጥበብ ያስፈልጋል። NSA፣ ከመረጃ ክምችት በተጨማሪ፣ መረጃዎችን በፍጥነት ፈትሾና አመሳክሮ፣ አንጥሮና አቀናብሮ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ግዙፍ የኮምፒዩተር አቅም አለው። ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ የተራቀቁ የኮምፒዩተር ፕሮግራሞች (ሶፍትዌሮች) ባለቤት ነው። ከተራቀቁት ሶፍትዌሮቹ መካከል በአዲስነቱና በውስብስብነቱ የሚጠቀሰው ኤክስኪስኮር (Xkeyscore) የተሰኘው ሶፍትዌር እንደሆነ ዘጋርድያን ጋዜጣ ዘግቧል። ኤክስኪስኮር፣ መረጃዎችን አስሶና ፈልፍሎ፣ ለቅሞና አንጥሮ የማውጣት አቅሙ እጅግ ሃያል ከመሆኑ የተነሳ፣ “ብዙ ያዩና የሚያውቁ የNSA ባለሙያዎች” ሳይቀሩ አስደናቂ ትንግርት እንደሆነባቸው ዘጋርድያን ገልጿል።

ልብወለድ ይመስላል። ነገር ግን፣ በእንግሊዝ የስለላ ድርጅት ስራ ላይ የዋለው ዲሰንት (DScent) የተሰኘ ሶፍትዌር ምን ያህል ስኬታማ እንደሆነ በማየት ማነፃፀር ይቻላል። የእንግሊዙ ሶፍትዌር (ዲሰንት) “ማን፣ ምን አይነት ሸቀጦችን መቼ ሸመተ? ማን፣ መቼ፣ የት የት ቦታ ሄደ?” የሚሉ ጥያቄዎች ላይ በማተኮር ምርመራ የሚያከናውን መሆኑን ፒ ኤም መፅሔት ዘግቧል። ሶፍትዌሩ የሰዎችን የሸቀጥ ግዢና የጉዞ መዳረሻ በመፈተሽ፣ አሸባሪዎችን ለይቶ ማወቅ ይችላል ብሏል መጽሔቱ። ሶፍትዌሩ ሁሉንም አሸባሪዎች ለይቶ ያውቃል ማለት ነው? አይደለም። ነገር ግን፣ አንድ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ዝግጅት ከሚያካሂዱ አስር አሸባሪዎች መካከል 6ቱን ለይቶ ለማወቅ እንደሚችል በሙከራ ተረጋግጧል ሲል ፒኤም መፅሄት ዘግቧል። የእንግሊዙ የስለላ ድርጅት የሚጠቀምበት ሶፍትዌር (ዲሰንት) ጉደኛ ነው ቢባል የሚበዛበት አይመስልም። የአሜሪካው ኤክስኪስኮር የተሰኘው ሴፍትዌር ደግሞ፤ ከዲሰንት በእጅጉ የላቀ እንደሆነ ተነግሮለታል። ለምሳሌ፣ “ተጠርጣሪው ሰውዬ የጀርመንኛ ቋንቋ የሚናገር የፓኪስታን ነዋሪ እንደሆነ መረጃ ደርሶናል። ሰውዬውን እንዴት ማግኘት እንችላለን?” የሚል ጥያቄ ይነሳል። ኤክስኪስኮር ለዚህ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ መስጠት ይችላል። “አንድ የማይታወቅ ሰው የሆነ አገር ውስጥ፣ ለሽብር ጥቃት የተመረጡ ቦታዎችን በኢንተርኔት ሲቃኝ ነበር። የኢሜይል አድራሻውን ማወቅ እችላለሁ?” … ኤክስኪስኮር አሁንም ፈጣን ምላሽ ያቀርባል። ተአምረኛ ሶፍትዌር ነው። አለምን የሚሸፍን የዘመናችን የስለላ መረብ በኢንተርኔትና በስልክ የሚተላለፉ ድምፆችን፣ ፅሁፎችን፣ ፎቶዎችንንና ቪዲዮዎችን በሙሉ በደፈናው መሰለልና ቀርፆ ማከማቸት አይቻልም።

በመላው አለም የሚመነጨውና የሚሰራጨው የኤሌክትሮኒክስ መረጃ እጅግ ብዙ ነው። በየቀኑ 7.8 ቢሊዮን ጊጋባይት መረጃ ይመነጫል። በየእለቱ የሚመነጨውን ዲጂታል መረጃ ለመቅረፅና ለማከማቸት፣ ምን ያህል ባለ አራት ጊጋባይት ፍላሾች ወይም ዲቪዲዎች እንደሚያስፈልጉ አስቡት። ሁለት ቢሊዮን ፍላሽ! ወይም ሁለት ቢሊዮን የዲቪዲ ዲስኮች! በየቀኑ! 35 ሚሊዮን መፃህፍት ከያዘው ግዙፉ የኮንግረስ ቤተመፃህፍት ጋር ማነፃፀርም ይቻላል። ዲጂታል መረጃዎችን በሙሉ ማከማቸት፣ በየእለቱ ስምንት መቶ ሺ ተጨማሪ ግዙፍ ቤተመፃህፍት እንደመገንባት ነው። ይሄን ሁሉ ጥሬ መረጃ (ዳታ) በየእለቱ መከታተልና ቀርፆ ማከማቸት አይቻልም። የመፃህፍቱን ርዕስ፣ ደራሲ፣ አሳታሚ፣ ወዘተ መዝግቦ ማስቀመጥ ይቀላል - ሜታዳታ መሰብሰብና ማከማቸት እንደሚባለው። NSA ይህንን ያደርጋል - ከአለም ዙሪያ “ሜታዳታ” ይሰበስባል። ወገኖቹ አውሮፓውያን፣ ቀልደኞቹ ራሺያና ቻይና በእርግጥ NSA ሁሉንም አገራት አይሰልልም። በተለይ አፍሪካን ዞር ብሎ የሚያያት አይመስልም። እንኳን የአፍሪካ አገራትን ሊሰልል ይቅርና፣ የምስራቅ አውሮፓ አገራት ላይም እንኳ ብዙ ትኩረት አያደርግም። ዋነኛ ትኩረቶቹ፣ ቻይና፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ኢራን፣ ሶሪያ፣ ፓኪስታንና አፍጋኒስታን የመሳሰሉ አገራት ናቸው - “ለአሜሪካ ደህንነት ስጋት ናቸው” በሚል።

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ የምዕራብ አውሮፓ አገራት ላይ ያተኩራል - “የአውሮፓ ደህንነት ያሳስበኛል” በሚል። NSA በአውሮፓ አገራት ላይ ስለላ የሚያካሂደው ለወዳጅ አገራት ደህንነት በማሰብ እንደሆነ ቢገልፅም፣ በርካታ የአውሮፓ መንግስታት ቁጣቸውንና ቅሬታቸውን ሲገልፁ ሰንብተዋል። በእርግጥም፣ የጀርመኗ መራሄ መንግስት አንጌላ ሜርከልን ጨምሮ፣ በርካታ የአውሮፓ መሪዎችና ሚኒስትሮች ስልካቸው በNSA መጠለፉ አስገራሚ ነው። የራሺያ እና የቻይና መንግሰታትም በፊናቸው፣ አሜሪካን ለማጥላላት ጥሩ አጋጣሚ አገኘን ብለው ሲተቹ ከርመዋል። እንዲያም ሆኖ፣ የአውሮፓ ባለስልጣናት ቁጣና ቅሬታ፣ ከአስመሳይነት ተለይቶ እንደማይታይ የዘገበው ዎልስትሪት ጆርናል፣ ከቻይናና ከራሺያ የሚሰነዘረው ትችትም አስቂኝ እንደሆነ ይገልፃል። እንዴት በሉ። በኒው ዮርኩ የተባበሩት መንግስታት ተቋም የአውሮፓ ህብረት ተወካይ መስሪያ ቤትን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። NSA በአውሮፓ ህብረት መስሪያ ቤት ውስጥ የስለላ መሳሪያዎችን እንደተከለ የዘገበው ዎልስትሪት ጆርናል፣ “ይሁን እንጂ ቀድሞም ቢሆን ቦታው ከስለላ ነፃ አልነበረም” ብሏል። የNSA የስለላ ባለሙያዎች የአውሮፓ ህብረት ቢሮዎችን በስለላ መረብ ውስጥ ለማስገባት ሲሰማሩ ነው፣ ከነሱ ቀድሞ የቻይና መንግስት የስለላ መረብ መዘርጋቱን በአካል ያዩት። የራሺያ መንግስትም እንዲሁ፣ ለጂ20 ስብሰባ የመጡ የተለያዩ ፕሬዚዳንቶችንና ባለስልጣናትን ለመሰለልና ስልኮቻቸውን ለመጥለፍ የሚያስችል መሳሪያ ተጠቅሟል።

ታዲያ፣ ራሺያና ቻይና፣ ከዳር ሆነው ትችት መሰንዘራቸው የምን አስመሳይነት ነው? የአውሮፓ መንግስታት ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። የአሜሪካ መንግስት፣ በአንድ ወር ውስጥ ከአራት ቢሊዮን በላይ የስልክ መረጃዎችን ከጀርመን እንደወሰደ የገለፁ ዘገባዎች፣ ከፈረንሳይና ከስፔንም በአንድ ወር ውስጥ ከመቶ ሚሊዮን በላይ የስልክ መረጃዎችን እንደሰበሰበ ገልፀዋል። ነገሩ እውነት መሆኑ በተለያዩ ምንጮች ቢረጋገጥም፤ የጀርመን፣ የፈረንሳይና የስፔን ባለስልጣናት በቁጣ ቅሬታቸውን ሲገልፁ መታየታቸው አስቂኝ ድራማነት ያለፈ ትርጉም የለውም። ለምን ቢባል፣ መረጃዎቹን ሰብስበው ለNSA የሰጡት የየአገሮቹ የስለላ ተቋማት ናቸው - NSA በፈንታው የራሱን መረጃ ያካፍላቸዋላ። እንዲህም ሆኖ፣ NSA ከዳር እስከ ዳር መረጃዎችን አፋፍሶ መሰብሰቡ ትክክል ነው ማለት አይደለም። የሰዎችን የግል ሕይወት ይዳፈራል። መግቢያ መውጪያ የሚያሳጣ የመንግስት ስለላ እርግጥ ነው፤ የአሜሪካ ብሄራዊ የፀጥታ ኤጀንሲ (NSA)፣ የዜጎችን የግል ሕይወት ይጥሳል በሚል የሚቀርብበትን ተደጋጋሚ ወቀሳ ከማስተባበል ተቆጥቦ አያውቅም። “የዜጎችን የስልክ ንግግርና የኢሜይል መልእክት እየጠለፍኩ አይደለም” የሚለው NSA፣ ሰዎችን በስም የማይጠቅስ የስልክ፣ የኢሜይል፣ የግዢ፣ የባንክ፣ የሐዋላ፣ የክፍያ ጥቅል መረጃዎችን (ሜታዳታዎችን) ማከማቸት የዜጎችን የግል ሕይወት አይጥስም ይላል።

ከየትኛው ቁጥር ለየትኛው ቁጥር እንደተደወለ፣ መቼ ተደውሎ ለምን ያህል ደቂቃ የስልክ ግንኙነቱ እንደቀጠለ የሚያሳዩ ጥቅል መረጃዎችን እንሰበስባለን እንጂ፣ የዜጎችን የስልክ ንግግር አንቀርፅም ብለዋል የNSA ዳሬክተር። በዚያ ላይ፣ “የተሰበሰቡትን መረጃዎች አከማቻለሁ እንጂ በዘፈቀደ መረጃዎቹን አልመረምርም፣ አልሰልልም” የሚለው NSA፤ መረጃዎቹን የምመረምረውና የምሰልለው የጥርጣሬ ፍንጮች ላይ በመመስረት ብቻ ነው ይላል። ካለፈው ሰኔ ወር ወዲህ በአውሮፓ እና በአሜሪካ ጋዜጦች የተሰራጩ ዘገባዎች ግን፣ ይህንን የNSA ማስተባበያ የሚቃረኑ ናቸው። NSA፣ “ፕሪዝም” እና “አፕስትሪም” በሚሉ የስለላ ፕሮጀክቶች፣ የስልክ ንግግሮችንና የኢንተርኔት ግንኙነቶችን በቀጥታ እየጠለፈ እንደሚሰልልና እየቀረፀ እንደሚያስቀምጥ ዘጋርድያን ዘግቧል። የየእለቱን መረጃ ሁሉ ሰብስቦ ለማስቀመጥ፣ በየእለቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አዳዲስ ኮምፒዩተሮችን መግዛት እንደማይቻል ግልፅ ቢሆንም፣ ሌሎች ዘዴዎች አሉ።

ለምሳሌ፣ ከአሜሪካ ጋር በቅርበት ከሚሰሩ አራት አገራት መካከል አንዷ የሆነችው እንግሊዝ፣ የስለላ መረጃዎችን ለመጥለፍና ለማከማቸው ዘመናዊ ተቋም እየገነባች ነው። ተቋሙ ግዙፍ ከመሆኑ የተነሳ፣ በአውሮፓና በኤስያ አገራት ዙሪያ፣ በስልክና በኢንተርኔት የሚሰራጩ መልእክቶችን በሙሉ ለሶስት ቀናት ቀርፆ ማቆየት እንደሚችል የዘገበው ዘጋርዲያን፣ የ30 ቀናት ጥቅል መረጃዎችንም (ሜታዳታዎችንም) ሰብስቦ ማቆየት ይችላል ብሏል። እንግሊዝ እንዲህ ማድረግ ከቻለች፣ እጅግ ግዙፍ የሆነው የአሜሪካው NSA በብዙ እጥፍ የሚበልጥ የመረጃ ሰብስብ አከማችቶ ማቆየት እንደሚችል ለመገመት አይከብድም። (በነገራችን ላይ፣ ለአመታት ተደብቆ የቆየ ይሄ ሁሉ ሚስጥር፣ ድንገት በግላጭ የተዘረገፈው ለNSA በኮንትራት ይሰራ የነበረው ሮበርት ስኖደን ሰርቆ ባወጣቸው 50 ሺ ገደማ ሚስጥራዊ ደብዳቤዎች ሳቢያ ነው።) የስልክ፣ የኢሜይል፣ የግዢ እና የሽያጭ፣ የኪራይና የስጦታ፣ የጉዞ እና የጉብኝት መረጃዎች ላይ፣ የጐዳና ካሜራዎችና የጂፒኤስ፣ የሰው አልባ አውሮፕላንና የሳተላይት መረጃዎች ሲጨመሩበት፣ የዘመናችን ስለላ ምንኛ የሰዎችን የግል ሕይወት እንደሚያጠፉ ሲታሰብ ያስፈራል፡፡

Read 7865 times