Saturday, 09 November 2013 10:18

በሣኡዲ ሁለት ኢትዮጵያውያን ተገድለው፤ በርካቶች ታስረዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(13 votes)

           ፖሊስ ከተለያዩ አገራት የገቡ ህገወጥ ስደተኞችን እያሳደደ ነውስደተኞች የ2 ዓመት እስርና የ100ሺ ሪያል መቀጮ ይጠብቃቸዋል መንግሥት ዜጐችን ከጥቃት እንዲከላከል ኢትዮጵያውያን ጠየቁ

የሣኡዲ አረቢያ መንግስት በሀገሩ የሚኖሩ የውጭ አገር ዜጐች ህጋዊ የሚያደርጋቸውን የመኖሪያ ፍቃድ እንዲያወጡ ያስቀመጠው ቀነ ገደብ ባለፈው እሁድ መጠናቀቁን ተከትሎ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ህገወጥ ያላቸውን የተለያዩ አገራት ዜጐችን እያደነ ሲሆን በዚሁ ሂደት ሁለት ኢትዮጵያውያን መገደላቸውንና በርካቶች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን አለማቀፍ ሚዲያዎች ዘገቡ፡፡ በአገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለዜና ምንጮች እንደተናገሩት፤ በሰዶ ማሳደዱ ሂደት በፖሊስ ከተገደሉትና ታፍሰው ከታሰሩት ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ፣ በ10ሺህ የሚገመቱ ስደተኞች ተመሳሳይ እጣ ይደርስብናል በሚል ስጋት የእለት ስራቸውን አቁመዋል፡፡

ረቡዕ ዕለት የሪያድ ፖሊስ አዛዥ ናስር ኤል አታኒ በሰጡት መግለጫ፤ አንደኛው ኢትዮጵያዊ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሊውል ሲል ባደረገው የማምለጥ ሙከራ፣ ኤል ማኑፍ በተባለ ቦታ መገደሉን ገልፀዋል፡፡ ስለ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ግድያ ከአገሪቱ መንግስት የተሰጠ ማብራሪያ ባይኖርም በርካታ አለማቀፍ ሚዲያዎች ዘግበውታል፡፡ የሣኡዲ መንግስት እስከ ጥቅምት 24 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ቀነ ገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ ፖሊስ፤ ህገወጥ ዜጐች ይበዙባቸዋል የተባሉ የሸቀጣሸቀጥ ሱቆች፣ የግንባታ ሳይቶች፣ ምግብ ቤቶች እና የንግድ ማዕከሎችን በመክበብ በ48 ሠአት ውስጥ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከ16ሺ በላይ የተለያዩ ሀገር ዜጐችን ማፈሱን የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አረጋግጠዋል፡፡ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሣኡዲ ከየመን ጋር በምትዋሰንበት የድንበር አካባቢ የተያዙ ሲሆን 5ሺህ ያህሉ በመካ፣ አንድ ሺህ የሚሆኑት በሪያድ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል፡፡

የአገሪቱ መንግስት ህገወጥ ስደተኞችን ለማደን 1200 አባላት ያሉት ልዩ የፖሊስ ሃይል ያሠማራ ሲሆን አሁንም ድረስ ህገወጥ ያላቸውን የውጭ ሃገር ዜጐች አድኖ የመያዙን ስራ በተጠናከረ መልኩ እንደቀጠለ ታውቋል፡፡ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ ህገወጥ ስደተኞች እጣ ፈንታን በተመለከተ የሃገሪቱ መንግስት በሰጠው መግለጫ፤ በርካቶቹ የሁለት አመት እስርና የ100ሺ ሪያል የገንዘብ መቀጮ የሚጠብቃቸው ሲሆን ይህን ቅጣት ከጨረሱ በኋላም ከሃገሪቱ ይባረራሉ፡፡ የሣኡዲ መንግስት ቀደም ሲል ለ7 ወራት የቆየ የምህረት አዋጅ አውጆ የነበረ ሲሆን በርካታ ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተሟላ ቅልጥፍና ሊያስተናግዳቸው ባለመቻሉ ህጋዊ ፍቃድ ሳያገኙ እንደቀሩ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የአገሪቱ መንግስት እየወሰደ ባለው እርምጃ ቀዳሚ ተጐጂዎቹ ኢትዮጵያውያንና የፊሊፒንስ ዜጐች እንደሆኑ እየተነገረ ሲሆን በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፤ መንግስት ዜጐቹን ከስቃይና ከጥቃት እንዲከላከል በማህበራዊ ድረገፆች እየጠየቁ ነው፡፡ ስለጉዳዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሣደር ዲና ሙፍቲን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ ስብሰባ ላይ በመሆናቸው ሊሳካልን አልቻለም። መንግስት ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚደረጉ ማናቸውንም የስራ ጉዞዎች መከልከሉንና በአገራቱ የሚገኙ ዜጐችን መብት ለማስከበር እንደሚሰራ መግለፁ ይታወሳል፡፡

Read 6101 times